1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመጋቢት 7 ቀን፣ 2012 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 7 2012

የስፖርት ጥንቅራችን የሚያተኩረው በመላም ዓለም በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘው የኮሮና ተሐዋሲ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያሳረፈው ተጽእኖ እና እየተወሰዱ ስለሚገኙ የመከላከል ርምጃዎች ይኾናል።

https://p.dw.com/p/3ZXFl
Coronavirus in Japan
ምስል picture alliance/AP Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኮሮና ተሐዋሲ ስርጭትን ለመግታት በሚል በኢትዮጵያ፤ በአውሮጳ እና ብሎም በመላው ዓለም የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው። ተሐዋሲው በአውሮጳ የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ እና ለሌላ ጊዜያት እንዲተላለፉ አስገድዷል። ጀርመን ውስጥ ቡንደስሊጋን ጨምሮ ሌሎች የስፖርት ክንዋኔዎች እንዲቋረጡ ተወስኗል።

ጀርመን በምትዋሰንባቸው የአውሮጳ ሃገራት ድንበሮች ላይ ዛሬ ጥብቅ ቁጥጥር ጀምራለች። ላለፉት 35 ዓመታት የሽብር ድርጊቶች ሲፈጸሙ ካልኾነ በቀር ቁጥጥር ባልነበረባቸው ድንበሮች ላይ በተለይ ከፈረንሳይ በኩል ወደ ጀርመን ለማለፍ የሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ተበራክተዋል። ጀርመናውያን ወደ ሀገራቸው መግባት እንደሚችሉ ኾኖም ፈረንሳውያንም ኾነ የሌሎች ሃገራት ዜጎች በድንበር ጠባቂ ፖሊሶች፦ «ወደየት ነው የምትሄዱት» እና «የጉዟችሁ ምክንያት ምድንድ ነው?»  የሚሉ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ ተገልጧል። ድንበር ጠባቂ ፖሊሶቹ አጥጋቢ መልስ ካላገኙ ተጓዦቹን ከድንበር እንደሚመልሱም ለማወቅ ተችሏል።

Frankfurt Commerzbankarena
ምስል picture-alliance/bild pressehaus

በኮሮና ተሐዋሲ ድንበሮቿን ዛሬ መዝጋት የጀመረችው ጀርመን የቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችንም ቢያንስ እስከ መጋቢት 24 ድረስ እንዳይደረጉ በዛሬው እለት ወስናለች። በቡንደስሊጋው እና በኹለተኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ ውድድሮች ቀደም ሲል እንደተገመተው እንዳይካሄዱ የወሰነው የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ነው።

18 ቡድኖች የሚወዳደሩበት የጀርመን እጅ ኳስ በአንጻሩ አኹን እስከ ሚያዝያ 14 ድረስ ውድድሮቹ እንዲቀጥሉ ወስኗል። ቀደም ሲል ውድድሮቹ ሊሰረዙ እንደነበር የተነገረ ቢኾንም፤ የእጅ ኳስ ቡድኖች አመራር ዛሬ ባደረጉት የቴሌፎን ኮንፈረስ ግን ከወዲሁ ውድድሮቹ ለሚቀጥሉት አምስት ሳምንታት አይቋረጡም ብለዋል።

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ እና አውሮጳ ሊግ ውድድሮችን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች ነገ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።  በኹለቱም የአውሮጳ ውድድሮች የጀርመን ቡድኖች ተሳታፊ ነበሩ። የአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያን በተመለከተም በታቀደለት መሠረት ሰኔ እና ሐምሌ ወራት ላይ ይከናወናል ተብሎ የነበረው ተስፋ የተመናመነ ይመስላል። ምናልባትም ውድድሮቹ በሚቀጥለው ዓመት የበጋ ወራት  አለያም በልግ እና ክረምት ወራት ውስጥ ቢደረጉ ይሻላል የሚሉ ሐሳቦች እየተሰነዘሩ ነው።

Borussia Dortmund Signal-Iduna-Park
ምስል picture-alliance/Digitalfoto Matthias

እስከ ዛሬ ረፋዱ ድረስ ጀርመን ውስጥ በኮሮና ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4.195 ደርሷል፤ 8 ሰው ሞቷል። ከሟቾቹ መካከል አምስቱ የቦን ከተማ በሚገኝበት የኖርዝ ራይን ቬስትፋሊያ ግዛት ሐይንስበርግ በተባለው አካባቢ ኗሪ የነበሩ ናቸው። በመላው ዓለም ደግሞ በ146 ሃገራት 164.837 ሰዎች በተሐዋሲው ሲያዙ 6.470 ሰዎች ሞተዋል።

አድማጮች በኮሮና ተሐዋሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ዐርብ በአንድ ጃፓናዊ ላይ መገኘቱ ከተነገረ በኋላ የኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ እና የስፖርት ክንዋኔዎች ምን ይመስላሉ? የስፖርት ጋዜጠኛው ዖምና ታደለን በስልክ ጠይቀነዋል። ኮሮና ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ እየታወቀም በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በርካታ ሰዎች የታደሙባቸው ውድድሮች ተከናውነዋል። ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች የሳተፉበት በርካታ ውድድሮች በተለያዩ ሃገራት ተሰርዘዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ዖምና ታደለ

እሸቴ በቀለ