1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የሚያዝያ 12 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2012

መላ ዓለም ከኮሮና ተሐዋሲ ስጋት ባልተላቀቀበት በአኹኑ ወቅት ጀርመን ውስጥ የቡንደስሊጋው የእግር ኳስ ግጥሚያ ስለሚጀምርበት ኹኔታ ውይይት እየተካሄደ ነው። ምናልባትም ውድድሮች ከግንቦት 1 ጀምሮ በዝግ ስታዲየሞች ሊካሄዱ ይችላል ተብሏል።

https://p.dw.com/p/3bBWe
Symbolbild Absage Bundesliga wegen Coronavirus
ምስል picture-alliance/Geisler

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

መላ ዓለም ከኮሮና ተሐዋሲ ስጋት ባልተላቀቀበት በአኹኑ ወቅት ጀርመን ውስጥ የቡንደስሊጋው የእግር ኳስ ግጥሚያ ስለሚጀምርበት ኹኔታ ውይይት እየተካሄደ ነው። ምናልባትም በዝግ ስታዲየሞች ስለሚከናወንበት መንገድ ማጠያየቅ ተይዟል። በርካታ ሃገራት በተሐዋሲው ሥርጭት የተነሳ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባስነገሩበት እና እንቅስቃሴን በገደቡበት በአኹኑ ወቅት እቤት ውስጥ ስፖርታዊ ውድድሮችን መከወን እና በኢንተርኔት መፎካከር በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ መኾን ጀምሯል። 

የጀርመን  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ፍሪትስ ኬለር የቡንደስሊጋው የእግር ኳስ ውድድሮች በዝግ መካሄድ እንዲጀምሩ ለማድረግ ስፖርት አፍቃሪያን ድጋፋቸውን እንዲሰጧቸው ጠየቊ። ውድድሮቹ የማይጀመሩ ከኾነ የእግር ኳስ ቡድኖች በብርቱ የገንዘብ ችግር እንደሚጎዱ አስጠንቅቀዋል። ፕሬዚደንቱ ኪከር ከተሰኘው በጀርመንኛ ቋንቋ ከሚታተመው የስፖርት መጽሄት ጋር ዛሬ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ውድድሮቹ በጊዜ የማይጀምሩ ከኾነ «አንዳንድ ቡድኖች ቡድኖቻቸውን ዳግም ወደ ውድድር ማምጣት ይሳናቸዋል» ብለዋል። «የትኛውንም ቡድን ማጣት አንሻም» ሲሉም ውድድሮቹ ባለመካሄዳቸው ቡድኖች የተጋረጠባቸውን ስጋት ለማጉላት ሞክረዋል። 

ኪከር በቅርቡ እንደዘገበው ከኾነ ከ36 የቡንደስሊጋ ቡድኖች መካከል 13ቱ እና በኹለተኛ ዲቪዚዮን የሚገኙ የእግር ኳስ ቡድኖች በሰኔ ወር መገባደጃ ላይ ኪሳራ ሊገጥማቸው እንደሚችል ዐስጠንቅቀዋል። የእግር ኳስ ጨዋታ አፍቃሪያን በበኩላቸው በዝግ ስታዲየሞች የሚደረጉ ግጥሚያዎችን እንደማይደግፉ በተደጋጋሚ ገልጠዋል። ለተቃውሞዋቸው እንደምክንያት ካቀረቧቸው ነጥቦች መካከልም እግር ኳስ ተጨዋቾች በኮሮና ቀውስ ወቅት ከሌላው ማኅበረሰብ ተለይተው ሊታዩ አይገባም የሚል ነው። የጀርመን  እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ፍሪትስ ኬለር ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ውድድሮች መጀመር ይገባቸዋል ባይ ናቸው። «ጨዋታዎች የጤና ስርዓታችንን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ እንደማይጀምሩ ቃል እንገባለን » ሲሉም ተደምጠዋል።

DFB-Integrationspapier Türkiyemspor Berlin
ምስል DW/M. Vering

የጀርመን እግር ኳስ ሊግ በጉዳዩ ላይ ለመምከር የፊታችን ሐሙስ ቀጠሮ ይዟል። የጀርመን መንግሥት የጣላቸው አንዳንድ ገደቦች በአኹኑ ወቅት እስከ እሁድ ሚያዝያ 25 ድረስ ጸንተው የሚቆዩ ናቸው። መንግሥት ከዚያ በኋላ ስለሚኾነው ለመወሰን ከፍተኛ አመራሩን ለሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ቀጥሯል። የጀርመን እግር ኳስ ሊግ ከሚያዝያ 25 በኋላ ባሉት ጊዜያት የተቋረጠው የእግር ኳስ ግጥሚያ ጀምሮ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ይሻል። መንግሥት የእግር ኳስ ጨዋታዎቹን መጀመር ይቻላል የሚል ውሳኔ ላይ ቢደርስ እንኳን ያለ ደጋፊዎች ነው የሚኾነው። አኹን ባለው ኹኔታ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የእግር ኳስ ደጋፊ ታዳሚያን ስታዲየም መግባት አይፈቀድላቸውም። የሊጉ ፕሬዚደንት ፍሪትስ ኬለር «ባለስልጣናት አረንጓዴውን መብራት እንዳሳዩ» እግር ኳስ ግጥሚያውን ለመጀመር ዝግጁ መኾናቸውን ዐስታውቀዋል። ፕሮፌሽናልም ኾኑ አማተር የእግር ኳስ ተጨዋቾች «ለጋራ መልካም ውጤት ድንቅ ነገር ነው የሚከውኑት» ብለዋል።

በከኮሮና ቀውስ ምክንያት የተቋረጠው ቡንደስሊጋ ከሰሞኑ ይጀምር ወይንስ አይጀምር በሚለው ነጥብ ላይ  የጀርመን የስፖርት ሚንስትር ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር መክረዋል። ሚንስትሩ ከጀርመን ግዛቶች የስፖርት ሚንስትሮች ጋር የመከሩት በቴሌፎን ኮንፈረንስ መኾኑም ተዘግቧል። ያለተመልካች ግንቦት ወር ላይ እንደሚጀመር የተነገረለት የእግር ኳስ ጨዋታ ዋና ዋና ቡድኖችን በርካታ ሚሊዮን ዩሮ እንዳደሚያሳጣ ተገልጧል። እግር ኳሱ ያለተመልካች በሚካሄድበት ወቅት ለአብነት ያኽል አር ቤ ላይፕትሲሽ 50 ሚሊዮን ዩሮ ግድም ገቢ ያጣል ተብሏል። የጀርመን ቡንደስሊጋ በኮሮና ተሐዋሲ መዛመት ፍራቻ እንዲቋረጥ የተደረገው መጋቢት 4 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ነበር። ጀርመን ውስጥ በአኹኑ ወቅት 141,672 ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ተጠቅተዋል፤ 4,404 ደግሞ በተሐዋሲው የተነሳ ሞተዋል።

Corona-Schutzmaksen
ምስል picture-alliance/dpa/maxppp/Pierre Teyssot

ከአውሮጳ ሃገራት መካከል ኮሮና ተሐዋሲ በብርቱ የጎዳት ጣሊያን ውስም የሴሪአ የእግር ኳስ ውድድር ስለሚጀመርበት ኹኔታ ውይይት እየተካሄደ ነው።  የጣሊያን እግር ኳስ ማኅበራት ፕሬዚደንት ጋብሪዬሌ ግራቫኒ  ሴሪኣው በተቻለ መጠን በፍጥነት መጀመር አለበት ብለዋል። አንዳንዶች እግር ኳስ ብቻ አይደለም አጠቃላይ የስፖርት እንቅስቃሴ መቆም አለበት ሲሉ ተደምጠዋል። ፕሬዚደንቱ በጣሊያን እግር ኳስ በቶሎ የማይጀምር ከኾነ ስፖርቱ ላይ የሚያስከትለው ውድቀት በቀላሉ የሚመለስ እንደማይኾን አስጠንቅቀዋል። የጣሊያን እግር ኳስ ሲሞትም መቃብር ቆፋሪም መኾን እንደማይሹም ተናግረዋል። 

ስፖርታዊ ውድድሮች በዓለም ዙሪያ ለጊዜው በታገዱበት በአኹኑ ወቅት ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች እና ስፖርት አፍቃሪያን ከቤታቸው ኾነው በኢንተርኔት ውድድሮችን ማድረግ ጀምረዋል። ከእግር ኳስ አንስቶ እስከ ዋና እንዲሁም የጀልባ ቀዘፋ እና የማራቶን ሩጫ ሰዎች እቤታቸው ውስጥ ኾነው በኢንተርኔት ሲለማመዱ እና ሲፎካከሩ በመታየት ላይ ናቸው።

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የኢንተርኔት ፉክክር የፌራሪው አሽከርካሪ ቻርለስ ሌክሌርክ ትናንት የኢንተርኔት ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም አሸናፊ ኾኗል። አሽከርካሪው ውድድሩን ካሸነፋ በኋላ ኢንተርኔት ላይ ባሰፈረው መልእክት በውድድር መድረክ ላይ ወጥተህ የምታገኘው ደስታ እና ካሸነፍክ በኋላ ማዕድ ቤትህ ውስጥ የሚሰማህ የተለያየ ነው ብሏል። «በውድድሩ እና ውድድሩን በኢንተርኔት በማሰራጨቴ በደንብ ተዝናንቻለሁ። በተለይ ደግሞ ሳሸንፍ በጣም ነው ደስ ያለኝ» ሲል አክሏል።

Formel 1 Grand Prix in Abu Dhabi
ምስል Reuters/H. I. Mohammed

በትዊተር ይፋዊ ገጹ ላይ ደግሞ «ውድድሩን ካሸነፍክ በኋላ የሚሰሙህ ስሜቶች የተለያዩ ናቸው። ኮምፒተርህን አጥፍተህ ማእድ ቤት ፓስታ መቀቀል መድረክ ላይ በሻምፓኝ ከመረጫጨት ጋር ይለያያል» ሲል ጽፏል። በኢንተርኔት ውድድሩ ያሸነፈው በኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት የተነሳ ከቤት መውጣት በተከለከለበት ወቅት መኾኑን አጽንዖት በመስጠት። ውድድሩን በኢንተርኔት ባሸነፈበት ወቅትም በሺህዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎቹ ፉክክሩን በቀጥታ የኢንተርኔት ሥርጭት ተከታትለዋል። ዋናው የፎርሙላ አንድ ውድድር በኮሮና ምክንያት ለሌላ ጊዜ ከተላለፈ ወይንም ከተሰረዘ በኋላ የውድድሩ አዘጋጆች ተከታታይ የኢንተርኔት ፉክክሮችን አሰናድተዋል። የዘንድሮ የፎርሙላ አንድ የመስክ ውድድር መቼ እንደሚጀምር ግን ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።

በጃፓን የተላላፊ በሽታዎች ባለሞያ ለአንድ ዓመት ግድም የተራዘመው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ከዓመትም በኋላም ስለመካሄዱ ጥርጣሬ እንደገባቸው ዛሬ ተናገሩ። «እውነቱን ለመናገር የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄዱ አይመስለኝም» ሲሉ ባለሞያው ፕሮፌሰር ኬንታሮ ኢዋታ ጥርጣሬያቸውን ዐሳይተዋል። በኮቤ ዩኒቨርሲቲ የተዛማች በሽታዎች ጥናት መምህር የኾኑት ኬንታሮ «ኦሎምፒክን ለማስጀመር ኹለት ነገሮች ያስፈልጋሉ። አንደኛ ኮቪድ 19ኝን ጃፓን ውስጥ መቆጣጠር» ሲሉ በእንግሊዝኛ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል። ቀጠል አድርገውም፦ «ጃፓን በሚቀጥሉት የበጋ ወራት የተሐዋሲውን ሥርጭት ልትቆጣጠር ትችል ይኾናል። ኾኖም በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ያ የሚኾን አይመስለኝም» ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠዋል። በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ኮቪድ 19 ሳይገታ ውድድሩን ለማካሄድ ጃፓን አትሌቶችን ብትጠራ ለወረረሽኝ ልትጋለጥ እንደምትችልም አስጠንቅቀዋል። ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና ጃፓን የቶኪዮ ኦሎምፒክ በሌላ ጊዜ እንዲከናወን ከወሰኑበት ጊዜ አንስቶ ጃፓን ውስጥ በኮሮና ተሐዋሲ የሚጠቊ ሰዎች ቊጥር ጨምሯል። የጃፓን ጠቅላይ ሚንሥትር ሺንዞ አቤም በቶኪዮ እና ሌሎች ስድስት ከተሞች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስነግረዋል።

Fußball | VfB Stuttgart - Erzgebirge Aue
ምስል picture-alliance/dpa/T. Weller

ጀርመን ውስጥ ቀድሞ ነውጠኛ የእግር ኳስ ደጋፊ የነበሩ ሰዎች በኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት ወቅት ሰዎችን ቤት ለቤት በመርዳት ላይ ናቸው። ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ የሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በመሰባሰብ በከተማዪቱ እና ከከተማዪቱ ውጪ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት የቤት ለቤት ርዳታ እያደረጉ ነው። ርዳታ አድራጊዎቹ በቊጥር 80 ሲኾኑ በሳምንቱ ለስድስት ቀናት ርዳታ ይሰጣሉ። በለይ በመጠለያዎች እና ሐኪም ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ አዛውንቶች እና ደጋፊ አልባ ሰዎችም ነው ርዳታ የሚያደርጉት። ነውጠኛ ደጋፊዎችንም በኮሮና ቀውስ ወቅት የማኅበራዊ አገልግሎት ውስጥ ተሳታፊ እንዲኾኑ በማድረግ ላይ የሚገኙ ፕሮዠክቶች ተወድሰዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ