1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዝያ 18 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 18 2013

ቡንደስሊጋው ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። ሻልከ መውረዱን ሲያረጋግጥ መሪው ባየርን ሙይንሽን ዳግም ዋንጫውን ለማንሳት ተቃርቧል። ላይፕትሲሽ ከባየርን ሙይንሽን 25 ሚሊዮን ዩሮ የአሰልጣኝ ዝውውር ካሳ ጠይቋል። ዋትፎርድ ዳግም ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተመልሷል። የሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ ነገ እና ከነገ በስተያ ይከናወናል።

https://p.dw.com/p/3sbV4
Bildkombo | Paris Saint-Germain und Manchester City

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ቡንደስሊጋው ሊጠናቀቅ ጫፍ ደርሷል። ሻልከ መውረዱን ሲያረጋግጥ መሪው ባየርን ሙይንሽን ዳግም ዋንጫውን ለማንሳት ተቃርቧል። ላይፕትሲሽ ከባየርን ሙይንሽን 25 ሚሊዮን ዩሮ የአሰልጣኝ ዝውውር ካሳ ጠይቋል። ዋትፎርድ ዳግም ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ተመልሷል። ሼፊልድ ዩናይትድ በ17 ነጥቡ ከወዲሁ ተሰናብቷል። ዌስት ብሮሚች እና ፉልሀም ጓዛቸውን እየሸከፉ ነው። ብራይቶን ነጥብ መጣሉ ወደ ወራጅ ቃጣናው አጣብቂኝ ጠርዝ ጎትቶ አስጠግቶታል። ኒውካስትል ከሊቨርፑል ጋር ነጥብ መጋራቱ በመጠኑም ቢሆን ከወራጅ ስጋት አትርፎታል። ለሊቨርፑል ግን ነጥብ መጣሉ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት የነበረውን ዕድል አጥብቦበታል። ጁቬንቱስ ቱሪን ነጥብ መጣሉ ወደ ሻምፒዮስ ሊግ የማለፍ ተስፋውን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል። ታች ከሚገኘው ፊዮሬንቲና ጋር አቻ መውጣቱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ለትችት ዳርጓል። አሰልጣኝ አንድሬ ፒርሎ ግን ለክርስቲያኖ እየተሟገቱ ነው። በሻምፒዮንስ ሊጉ ነገ እና ከነገ በስተያ የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ ሁለት የእንግሊዝ ቡድኖች የስፔን እና የፈረንሳይ ብርቱዎችን ይገጥማሉ።

ፕሬሚየር ሊግ

Britain Soccer Premier League Arsenal vs Chelsea
ምስል Andre Boyers/AP/picture alliance

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ማንቸስተር ሲቲ በአሸናፊነቱ እየገሰገሰ ነው። 77 ነጥብ ሰብስቦ ማንቸስተር ዩናይትድን በ10 ነጥብ ርቋል። 59 ነጥብ ያለው ላይስተር ሲቲ እና 58 ነጥብ የሰበሰበው ቸልሲ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታቸውን አስጠብቀዋል። ዌስት ሐም እና ሊቨርፑል በቅርብ ርቀት ይከተላሉ። አምስተኛ ደረጃ ላይ 55 ነጥብ ይዞ የአውሮጳ ሊግ ቦታውን የተቆናጠጠው ዌስት ሀም ሊቨርፑልን የሚበልጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው። ቶትንሀም በ53 ነጥብ ሊቨርፑልን ተከትሎ 7ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ኤቨርተን በበኩሉ 52 ነጥብ ይዞ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እነዚህ በሙሉ ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ውስጥ ገብተው በቀጣይ የውድድር ዘመን ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ ዕድል አላቸው። ከምንም በላይ ግን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚመጡ ቡድኖች ዕድላቸውን ከወዲሁ ተጠቅመዋል።

የዋትፎርድ ደጋፊዎች በሳምንቱ መጨረሻ ፈንድቀዋል። ዋትፎርድ ኖርዊች ሲቲን ተከትሎ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ማለፉን ያረጋገጠ ሁለተኛ ቡድን ኾኗል። ዋትፎርድ ከፕሬሚየር ሊጉ ሮቆ የቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። በስፔናዊው አሰልጣኝ ሲስኮ ማኽቴ የሚመራው ዋትፎርድ ቅዳሜ ዕለት ሚልዋል ቡድንን 1 ለ0 ማሸነፉ ወደ ፕሬሚየር ሊግ መግቢያ በር ከፍቶለታል። አሰልጣኝ ሲስኮ ማኽቴ ከአራት ወራት በፊት የኤልቶን ጆን ቡድንን የተረከቡት አምስተኛ ደረጃ ላይ እያለ ነበር። ባለፈው የጨዋታ ዘመን የፕሬሚየር ሊጉ ሦስተኛ ወራጅ የነበረው ቦርመስ እነ ዋትፎርድ እና ኖርዊች ሲቲን ተከትሎ ዳግም የመመለስ ዕድል አለው።

ሻምፒዮንስ ሊግ

ፕሬሚየር ሊጉን በ77 ነጥብ የሚመራው ማንቸስተር ሲቲ ከነገ በስተያ የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን በሻምፒዮንስ ሊግ ለግማሽ ፍጻሜው ይፋለማል።  ነገ ሪያል ማድሪድ በሜዳው አልፍሬዶ ዲ ሽቴፋኖ ስታዲየም ከቸልሲ ጋር ይጋጠማል። ረቡዕ ደግሞ ፓሪስ ከተማ በሚገኘው ፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም ማንቸስተር ሲቲ ፓሪ ሳንጃርሞን ይፋለማል። ሁለቱም የመልስ ግጥሚያዎቻቸውን በቀጣዩ ሳምንቱ ይከናወናሉ።

UEFA Logo
ምስል Fabrice Coffrini/Getty Images/AFP

ሴሪኣ

የዓለማችን እጅግ ዝነኛው ኳስ ተጨዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ በትናንቱ ወሳኝ ግጥሚያ ግብ ባለማስቆጠሩ ከደጋፊዎች ብርቱ ትችት ገጥሞታል። በጣሊያን ሴሪአው 66 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጁቬንቱስ ቱሪን ትናንት ከፊዮሬንቲና ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ለፊዮሬንቲና ቀዳሚዋን ግብ ዱሻን ቭላሆቪች ሲያስቆጥር ጁቬንትስን ከሽንፈት የታደገችውን ኳስ ከመረብ ያሳረፈው ክርስቲያኖ ሮናልዶ አልነበረም። 46ኛ ደቂቃ ላይ ጁቬንቱስን ከጉድ የታደገው አልቫሮ ሞራታ ነበር። ከጁቬንቱስ ቱሪን ጋር ነጥብ የተጋራው ፊዮሬንቲና 34 ነጥብ ይዞ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከጁቬንቱስ በ3 ነጥብ ተበልጦ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ናፖሊ ዛሬ ማታ ከቶሪኖ ጋር ወሳኝ ግጥሚያውን ያከናውናል። 31 ነጥብ የሰበሰበው ቶሪኖ 16ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ናፖሊ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሻምፒዮንስ ሊግ የመጨረሻውን ቦታ ከጁቬንቱስ ቱሪን ይረከባል። የጁቬንቱስ ደጋፊዎችን እጅግ ያበሳጫቸው ይኸው አጣብቂኝ ነው። ሦስተኛ ደረጃ የያዘው ሚላን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው እንደ ጁቬንቱስ 66 ነጥብ አለው።  በእርግጥ ሴሪአው ሊጠናቀቅ አምስት ዙር ግጥሚያዎች ይቀሩታል። ግን ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በትናንቱ ወሳኝ ግጥሚያ ከግብ ርቀት አቅራቢያ ያገነውን የግብ ዕድል ባለመጠቀሙ በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ከደጋፊዎች ብርቱ ነቀፌታ ተሰንዝሮበታል። አሰልጣኝ አንድሬ ፒርሎ ከጎኑ የቆሙ ይመስላል። «ሮናልዶ መጥፎ ጨዋታ ያሳየ አይመስለኝም» አሉ አሰልጣኙ። «የተወሰኑ ዕድሎች አግኝቶ ነበር፤ በአጠቃላይ መጥፎ አልነበረም» ሲሉም አክለዋል።  

UEFA Champions League | Juventus v FC Porto
ምስል Jonathan Moscrop/empics/picture alliance

ቡንደስ ሊጋ

(መከረኛው ሻልከ)

በጀርመን የእግር ኳስ ታሪክ 160,000 ደጋፊዎችን ይዞ በደጋፊ ብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በዓለም ዙሪያ ካሉ ቡድኖች በደጋፊ ብዛቱ የአራተኛ ደረጃን ይዟል። ሻልከ። ከባየርን ሙይንሽን፣ ስፖርቲንግ ሊስቦን እና ቤኔፊካ ቀጥሎ በዓለም ዙሪያ የሻልከን ደጋፊዎች በብዛት የሚስተካከል የለውም። በቡንደስሊጋው ሻልከ የሚበለጠው በባየርን ሙይንሽን ብቻ ነው። ባየር ሙይንሽን በዓለም ዙሪያ 362,303 የተመዘገቡ ደጋፊዎች አሉት። ድንቅ ተጨዋቾችን በማፍራትም ይታወቃል። የዓለማችን ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር፤ ሌሮይ ሳኔ፣ ጁሊያን ድራክስለር፣ ሜትሱት ኦዚል እና ሌዎን ጎሬትስካን የመሳሰሉ ተጨዋቾችንም ያፈራ አንጋፋ ቡድን ነው፤ ሻልከ። ከ33 ዓመት የቡንደስ ሊጋ ቆይታ በኋላ ግን ዘንድሮ ተሰናባችነቱን ማረጋገጡ በርካቶችን ግራ አጋብቷል።  ንጉሣዊ ሠማያዊዎቹ በመባል የሚታወቁት ሻልከዎች አንገታቸውን ደፍተው ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወርደዋል። ከእንግዲህ በቡንደስሊጋው የሚያደርጓቸው ቀሪ ጨዋታዎች ለንጉሣዊ ሠማያዊዎቹ ያን ያህል ፋይዳም የለው።

ለመሆኑ በቡንደስሊጋው ለአራት ጊዜያት ለፍጻሜ የደረሱት፣ የጀርመን ዋንጫን አምስት ጊዜ ያነሱት፣ በሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ እና በአውሮጳ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻሉት ሻልከዎች ምን አንኮታኮታቸው? የብዙዎች ጥያቄ ነው።  በዋነት ታዲያ ለዚያ ብርቱ ቡድን እንዲህ በፍጥነት ማሽቆልቆል የተጨዋቾች በብዛት መሸጥ አለያም መሰናበት፣ የአሰልጣኞች በአጭር ጊዜያት በተደጋጋሚ መቀያየር እንደምክንያት ይጠቀሳሉ። በዋናነት ግን ቡድኑን ላለፉት 20 ዓመታት ግድም ከጀርባ ደጋፊ መስለው ግን ደግሞ የቡድኑ ዋና ፈላጭ ቆራጭ ኾነው እንደ አምባገነን አለቃ ሲያሾሩ የከረሙት ክሌሞን ቶይኒስ ተጠያቂ ናቸው። እኚህ የሻልከ ባለሀብት 1,4 ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ሐብት ያካበቱ፤ ማንም የማይናገራቸው የሻልከ ገዢ ነበሩ ማለት ይቻላል። የ64 ዓመቱ ቢሊዬነር ክሌሞን ቶኒዬስ የፈለጉትን ሲያባርሩ፣ ያሻቸውን ሲያስመጡ እና የፈለጉትን ሲናገሩ ቆይተው ከሻልከ በስተመጨረሻ ግን ራሳቸውን አሰናብተዋል።

Arminia Bielefeld - FC Schalke 04
ምስል Fabian Strauch/dpa/picture alliance

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2019 ነሐሴ ወር ውስጥ አፍሪቃውያንን በተመለከተ የሰጡት የዘረኝነት ንግግር ከቡድኑ ኃላፊነት መጀመሪያ በጊዜያዊነት እንዲሰናበቱ አድርጓል። ከዚያ ደግሞ በቅርቡ የሥጋ ማቀናበሪያ ቄራቸው ውስጥ ከጥንቃቄ አልባ እንቅስቃሴ የተነሳ ከፍተኛ የኮሮና መስፋፋት በመታየቱ በብዙዎች ተተችተዋል። ደጋፊዎች ሳይቀሩ የባለሐብቱን ቄራ ከሻልከ ጋር አነጻጽረው ነቅፈዋቸዋል። «ሻልከ ቄራ አይደለም» ሲሉ መፈክር አሰምተዋል። የ1,4 ቢሊዮን ባለጸጋው ላለፉት 27 ዓመታት ግድም የሻልከ ተቆጣጣሪ ቦርድ አባልም ነበሩ።

ሻልከ መውረዱ የተረጋገጠው ባለፈው ማክሰኞ በአርሜኒያ ቢለፌልድ 1 ለ0 የተሸነፈ ጊዜ ነው። የመውረዳቸው ነገር ግን ቀድሞም ሳይታለም የተፈታ ነበር። ያሸነፈው 2 ጊዜ ብቻ ሲሆን፤ ለ7 ጊዜ አቻ ወጥቷል። 21 ጊዜ ተሸንፏል። በዚህም ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ወርዷል። የመውረድ እጣ ፈንታቸውን የወሰነውም ከታችኛው ዲቪዚዮን ዘንድሮ ያደገው አርሜኒያ ቢሌፌልድ መሆኑ ስላቁን አጉልቶታል።  የሻልከ ተጨዋቾች ባለፈው ረቡዕ ለልምምድ ወደ ስታዲየም ሲያመሩ የቡድኑ መውረድ እጅግ ያበሳጫቸው ወደ 600 የሚጠጉ ደጋፊዎች የቡድኑ አውቶብስ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። 

ሻልከ አሰልጣኝ ዳቪድ ቫግነርን ከአንድ ዓመት በኋላ ቢያሰናብት፣ አሰልጣኝ ማኑዌል ባውምን ለሦስት ወራት ቢያስመጣ፤ አሰልጣኝ ሁብ ስቴፋን ለአራት ቀናት አቆይቶ በአሰልጣኝ ክርስቲያን ግሮስ ቢተካ፤ እሳቸውንም በሁለት ወሩ አሰናብቶ ወጣቱ አሰልጣኝ ዲሚጥሪዮስ ግራሞዚስ ቢያስመጣ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከመሰናበት ግን ማንም አልታደገውም።

Fußball Bundesliga | SC Freiburg vs TSG Hoffenheim | Tor (0:1)
ምስል Loerz/Fotostand/imago images

ሻልከ እስካሁን 30 ጊዜ ተጋጥሞ 13 ነጥብ ብቻ ነው የሰበሰበው። 58 የግብ እዳ አለበት።ቀሪ አራት ጨዋታዎቹን በተአምር ቢያሸንፍ እንኳን ሊኖረው የሚችለው 25 ነጥብ ብቻ ነው። ከእሱ በላይ ያለው ኼርታ ቤርሊን 28 ጨዋታ አከናውኖ የሰበሰበው ነጥብ 26 ነጥብ ነው። አጠቃላይ ቀሪ ስድስት ጨዋታዎቹን ቢሸነፍ እንኳን ሻልከ በአንድ ነጥብ ይበለጣል። 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ 31 ጨዋታዎችን አከናውኖ 29 ነጥብ ሰብስቧል።

ቢሌፌልድ 15ኛ ደረጃ ላይ እንዲሁም ብሬመን 14ኛ ላይ ይገኛሉ። እያንዳንዳቸው 30 ነጥብ አላቸው። አውግስቡርግ በ33 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል። ሁሉም ታዲያ 31 ግጥሚያዎችን አከናውነዋል። 30 ግጥሚያ ያደረገው ማይንትስ በ34 ነጥብ ደረጃው 12ኛ ነው። 11ኛ ደረጃ ላይ ያለው ሆፈንሃይም 31 ግጥሚያ አከናውኖ 36 ነጥብ ሰብስቧል። ይህ የሚያሳየው እስከ 11ኛ ደረጃ ድረስ ያሉት ቡድኖች የመውረድ አደጋ ውስጥ የመግባት አለያም የመውረድ አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል ማለት ነው።

ሻልከ በመቀጠል የሚጋጠው የቅዳሜ ሳምንት ከሆፈንሃይም በሳምንቱ ከኼርታ ቤርሊን፤ ከዚያም ከፍራንክፉርት በቀጣይ ቅዳሜ የመጨረሻ ግጥሚያውን ከኮሎኝ ጋር አድርጎ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ይሰናበታል።

መሪው ባየር ሙይንሽን በ71 ነጥብ እና በ46 የግብ ክፍያ ከላይ ተኮፍሷል።  ቀጣዩን ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር የሚያደርገውን ግጥሚያ ካሸነፈ ሁለት ጨዋታ እየቀረው ዋንጫውን ይወስደዋል። ቀሪ ግጥሚያዎቹ ከፍራይቡርግ እና አውግስቡርግ ጋር ነው። 64 ነጥብ እና 30 የግብ ክፍያ ያለው ላይፕትሲሽ በመቀጠል ከቦሩስያ ዶርትሙንድ፣ ከቮልፍስቡርግ እና ከዑኒየን ቤርሊን ጋር ይጋጠማል።

Fußball Bundesliga Fußbälle der Marke Derbystar
ምስል Oliver Zimmermann/foto2press/picture alliance

ቮልፍስቡርግ 57 ነጥብ እና 22 የግብ ክፍያ አለው። ቀጣይ ግጥሚያዎቹ ከዑኒየን ቤርሊን፣ ከላይፕትሲሽ እና ከማይንትስ ጋር ነው። 56 ነጥብ ያለው አይንትራኅት ፍራንክፉርት በበኩሉ የግብ ክፍያው 15 ነው። ተጋጣሚዎቹ ደግሞ ማይንትስ፣ ሻልከ እና ፍራይቡርግ ናቸው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ 55 ነጥብ እና 24 የግብ ክፍያ ይዞ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይፕትሲሽ፣ ማይንትስ እና ባየር ሌቨርኩሰን ይጠብቁታል።

የባየር ሙይንሽን አሠልጣን ዲተር ሐንሲ ፍሊክ የላይፕትሲሹ አሠልጣን ጁሊየን ናገልስማን ሊተኳቸው እንደኾነ እየተነገረ ነው።  ጁሊያን ናገልስማን ከሁለት ዓመት ውላቸው በፊት ለማዘዋወር ግን ባየርን ሙይንሽን 25 ቢሊዮን ዩሮ ሊሰጠን ይገባል ብሏል።  ይህ ዋጋ በቡንደስሊጋው የአሠልጣኞች ዝውውር ታሪክ ከፍተኛው ዋጋ ይኾናል ማለት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ