የሞዛምቢክ ተቃዋሚ መሪ ማፑቶ መግባት በአገሪቱ ውጥረቱን አባብሷል
ቅዳሜ፣ ጥር 3 2017ሐሙስ ጥር 1 ቀን፤ 2017 ዓ.ም ማፑቶ፤ የሞዛምቢክ ዋና ከተማ በተኩስ ሩምታ ስትናጥ ውላለች ። ምክንያት? የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ ድንገት ወደ ሞዛምቢክ መመለስ ። በጥቅምቱ የሞዛምቢክ ምርጫ ዋዜማ ብጥብጥ ከአራት መቶ በላይ ሰዎች የተገደሉባት፤ 1,500 የቆሰሉባት ሞዛምቢክ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወደ ማፑቶ መመለሳቸው ከፍተኛ ውጥረት አንግሷል ። የሞዛምቢክ ፖሊስ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ ቬናንሲዮ ሞንድላኔን ለመቀበል ሐሙስ ዕለት አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ጥይት ማዝነቡ ተዘግቧል ። በጥይት ውርጅብኙ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ወዲያው ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውም ተዘግቧል ።
የተቃዋሚው መሪ ቬናንሲዮ ሞንድላኔ በአገሪቱ ምርጫ አሸናፊ መሆናቸውን በመግለጥ የምርጫ ውጤቱን እንደማይቀበሉት ሐሙስ ዕለትም ሞዛምቢክ ውስጥ ከአውሮፕላን ሲወርዱ ተናግረዋል ። በአንድ እጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው የማፑቶ አየር ማረፊያ መሬትን በመሳም ንግግር ያሰሙት ቬናንሲዮ ለሞዛምቢክ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደሚታገሉ ዐሳውቀዋል ።
ቬናንሲዮ ከሁለት ወራት በፊት ከአገር የሸሹት የቅርብ ሰዎቻቸው ላይ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ለራሳቸው በመሥጋት እንደነበር ተናግረዋል ። በጥቅምቱ ምርጫ ገዥው የፍሬሊሞ ፓርቲ ማሸነፉን የሀገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ሸንጎ ካረጋገጠ በኋላ በአገሪቱ ብጥብጥ ተነስቶ ነበር ። በወቅቱ የተጭበረበረ ሲሉ ታቃዋሚዎች ያወገዙትን የምርጫ ውጤት ከፍተኛ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ቢያጸድቅም ንብረት ማውደም እና ዝርፊያ የተቀላቀሉበት ብጥብጥ ሞዛምቢክን ለወራት ንጧታል ።
የተቃዋሚው መሪ አገር ቤት መግባት ያነገሠው ውጥረት
ተቃዋሚዎች እና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ውድቅ ያደረጉትን ምርጫ አሸንፌያለሁ ያሉት የፍሬሊሞ ፓርቲ መሪ ዳንኤል ቻፖ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ጥር 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በሞዛምቢክ ፕሬዝዳንትነት ቃለ መሀላ ይፈጽማሉ ተብሏል ። ከዚያ በፊት ግን ከተቃዋሚዎች ጋር ንግግር እንደሚያደርጉ ዐሳውቀዋል ። ለንግግሩ ይኸው እዚሁ ሞዛምቢክ አለሁ ሲሉ የተቃዋሚ መሪው ቬናንሲዮ ሞንድላኔ ማፑቶ ተገኝተዋል ። ቃል የተገባው ንግግር ላይም ለመሳተፍ ፍቃደኛ መሆናቸውን ዐሳውቀዋል ። የሞዛምቢክ ሕገ መንግሥታዊ ሸንጎ ያለውን ግን ዛሬም ፈጽሞ አይቀበሉትም ።
የጥቅምቱን ምርጫ የገዢው ፍሬሊሞ ፓርቲ ዳንኤል ቻፖ 65 በመቶ ድምፅ በማግኘት ማሸነፋቸውን የተቃዋሚው እጩ ተወዳዳሪ ቬናንስዮ ሞንድላኔ ደግሞ 24 በመቶ ድምፅ ማግኘታቸውን ነበር ሸንጎው ያሳወቀው ። 33 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ሞዛምቢክ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1975 ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን የሚያስተዳድረው ይኸው የፍሬሊሞ ፓርቲ ነው ። በቀጣይ ሁለትሳምንታት ጭንቅ ውስጥ በምትገኘው ሞዛምቢክ ምን እንደሚከሰት ዐይታወቅም ። ፍጥጫው ግን እንዳየለ ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ