1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተመድ የኤርትራ ዘገባና የጀርመን ሚኒስትር አስተያየት

ሰኞ፣ ሰኔ 15 2007

ተፅዕኖ ማድረግ ይገባናል ይላሉ የጀርመን የምክር ቤት አባል እና በፓርላማው የእህማማቾቹ የክርስትያን ዲሞክራት ህብረት እና የክርስትያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተጠሪ ፤ ፍራንክ ሀይንሪሽ ።ፖለቲከኛው ከዶይቸ ቬለ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/1FlD8
UN-Untersuchungskommission zur Menschenrechtssituation in Eritrea
ምስል OHCHR

[No title]

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን መንግሥት በሀገሪቱ ለሚፈፀሙ በርካታ የመብት ጥሰቶች ሰሞኑን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል። ኤርትራ በበኩሏ የኮሚቴው ዘገባ «እጅግ የተጋነነ» እንዲሁም«መሠረተ ቢስና ብቃት የሌለዉ» ነው ስትል አጣጥላለች።

የኤርትራን የሰብአዊ መብት አያያዝን የመረመረው ኮሚሽን ይፋ ያደረጋቸው የመብት ጥሰቶች ብዙም አላስገረሙኝም ይላሉ፤ ፍራንክ ሀይንሪሽ ። ሀይንሪሽ የጀርመን የምክር ቤት አባል እና በፓርላማው የእህማማቾቹ የክርስትያን ዲሞክራት ህብረት እና የክርስትያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተጠሪ ናቸው። ፖለቲከኛው ለዶይቸ ቬለ እንዳስረዱት፤ ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ ጉዳዩን በጥብቅ በሚከታተሉበት ወቅት ለመረዳት የቻሉት የሰብዓዊ መብቱ ይዞታ የተገደበ መሆኑን ነው። የተመድ ዘገባ ይፋ የሆነው ልዑኮቹ ወደ ኤርትራ ሳይጓዙ በመሆኑ ተዓማኒነቱን አስመልክቶ ሀይንሪሽ ለዶይቸ ቬለ የሰጡት መልስ፤« ሶስቱ የተመድ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን አባላት ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም። በምስክርነት የቀረቡትም 550 ሰዎች ማንነታቸውን በግልዕ ለመናገር ስጋት ነበራቸው። ይህ አያስተማምንም ለማለት ይቻላል፤ ነገር ግን ይህ ሁሉ ቁጥር የሚያመላክተው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ነው ።»

Menschenrechtsaktivistin Meron Estefanos
ምስል DW/Meron Estefanos

ኤርትራ ከበርካታ ሀገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጠንካራ የሚባል አይደለም። ሆኖም ይህን ግንኙነት በተቻለ መጠን ጠብቆ መያዙ አስፈላጊ ነው ይላሉ ሀይንሪሽ። እሳቸው እንደሚሉት ከሀገሪቷ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ከሌለ ስለሀገሪቷ በግልፅ ለመናገር አዳጋች ያደርገዋል ይላሉ። ስለሆነም እንደሳቸው ግንኙነቱን በሀገር ደረጃ ማቋረጥ አያስፈልግም ፤ ፋይናንስን በሚመለከት ጉዳይ ላይም መጠንቀቅ ያሻል። ሀይንሪሽ ያብራሩታል።

« ኤርትራ በአንድ በኩል ውጭ ሀገር ከሚኖሩ ዜጎቿ ጀርመንን ጨምሮ በግዳጅ ቀረጥ እንዲከፍሉ የምትጠይቅ ከሆነ፤ የኛ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴትር ፤ ጀርመን ይህንን አትፈቅድም ማለት አለበት። ሌሎች ሀገራትም የሚያሳስቡት ይህንን ነው። የጀርመን የልማት ሚኒስትር ጌርድ ሙለር፤ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ኤርትራ ይጓዛሉ፤ ያኔ ይህንን ርዕስ ማንሳታቸው አይቀርም። ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሲኖራቸው ብቻ ነው። ነገር ግን በዚህ ገንዘብ ህገወጥ ተግባራት ማለትም የሰዎች ንግድ ሙስና ና ብዝበዛ የሚፈፀሙ ከሆነ፤ የግንኙነቱ አካሄድ ሊታሰብበት ይገባል ። ግንኙነቱ መቀጠል ያለበትም አስፈላጊዎቹ ርምጃዎች ከተወሰዱ በኋላ መሆን አለበት ።»

ስለሆነም የሀይንሪሽ የግል አስተያየት ወቀሳዎቹ ተሰሚነት ካገኙ ፤ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት መፍጠሩ ጥሩ ነው።እስካሁን ግን ይህንን የሚጠቁም ምልክት አላየሁም ይላሉ ሀይንሪሽ። የተመድ፣ ወደ360,000 የሚጠጉኤርትራውያን ወደ አውሮፓ እንዲሰደዱ በሃገሪቱ ይፈጸማል የተባለው የመብት ጥሰት ትልቅ ሚና ሳይጫወት እንዳልቀረ ኮሚሽኑ አስታውቋል። ይህም በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ችግር ሆኗል። በርካታ የኤርትራ ስደተኞች በሜዲቴራንያን ባህር አድርገው አውሮፓ ገብተዋል። ስለሆነም ሀይንሪሽ አውሮፓ ጠንካራ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባት ጠቁመዋል።

Symbolbild Flüchtlinge Mittelmeer Ankunft Italien Gebet
ምስል Reuters/A. Parrinello

« ጀርመን ፣ የኤርትራ ስደተኞችን ያህል ፣ የሌሎች ሀገራት ስደተኞችን በከፍተኛ መጠን አልተቀበለችም። የሶርያን ጉዳይ ማንም ይረዳዋል። ከኤርትራ ደግሞ ሰዎች በራሳቸው መንግሥት በሚደርስባቸው ችግር እና ስቃይ ምክንያት እንደሚሰደዱ በጣም ግልፅ እየሆነ መጥቷል ። በዚህ ጉዳይ ላይ ደግሞ እኛ የበኩላችንን ጫና ማድረግ አለብን።»

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን በኤርትራ ስለሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያዘጋጀውን ዘገባ ነገ (ማክሰኞ) ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ለሚገኘው የተመ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቀርባል።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ