1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተስፋ ዜማ የሚያፈልቁ ጊዜያት

ዓርብ፣ ሐምሌ 13 2010

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች ስልክ መደዋወል በተፈቀደላቸው ማግስት አንድ ወዳጄ መጥቶ "ከኤርትራ የመጀመሪያ የስልክ ጥሪዬን ተቀበልኩ"አለኝ። ቀጣይ የስልክ ጥሪ እንደሚኖረው በመተማመኑ ተገርሜ "ከማን?"አልኩት።

https://p.dw.com/p/31pnD
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

"ከልጅነት ጓደኛዬ"ነበር ያለኝ። ሌላኛው ወዳጄ ደግሞ የኤርትራን መግቢያ ኮድ ተጠቅሞ በአቦ ሰጡኝ የደወለውን ቁጥር፥ አማርኛ አቀላጥፋ የምትናገር የአስመራ ነዋሪ አንስታለት በደስታ ብዛት ለሰው ሁሉ ሲያወራ ነበር። "ወደ አዲስ አበባ መጀመሪያ ከሚመጡት ሰዎች ውስጥ እኔም አለሁበት"ብላዋለች።

የፖለቲካ ውሳኔዎች በግለሰቦች ሕይወት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በብዛት አይስተዋልም። የሰሞኑ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሠላም ማውረድ፥ ያስመሰከረው ትልቅ ቁም ነገር ቢኖር ይህንኛው ዋና ነው። ተነጣጥለው የከረሙ ቤተሰቦች በስልክ ሲደዋወሉ እና በአካል ሲገናኙ የነበረው የለቅሶና የደስታ ስሜት &ስንቶች ናቸው በየጓዳቸው ብሶታቸውን አፍነው የኖሩት?&የሚያስብል ነበር። በሁለቱ አገራት የእርቅ ዜና ማግስት እያንዳንዱ ሰው በጦርነቱ ግዜ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ስለተደረጉ ጎረቤቶቹ እና የልጅነት ጓደኞቹ ማውራት ጀመረ። ጠቅላላ ሁኔታው መላው ሕዝብ የተዳፈነ ናፍቆቱ ያገረሸበት ነበር የሚመስለው።

በሺሕ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ እና ከስደት የሚመለሱትም አገራቸው ሲገቡ በዙሪያቸው ያሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እፎይታ አግኝተዋል። በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ከ16 ዓመታት ስደት በኋላ የተመለሰው ጋዜጠኛ ሞሐመድ አዴሞ፥  አገር ቤት በገባ በጥቂት ቀናት ውስጥ አሳዳጊ አያቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ጋዜጠኛ ሞሐመድ አዴሞ ለአያቱ ቀብር መድረስ የቻለው በፖለቲካዊ ለውጥ ነው። እስከዛሬ ድረስ ስንቶች ይህንን ዕድል አጥተውታል? የፖለቲካ ውሳኔዎች የቤተሰብ አባላትን ለደስታ እና ለሐዘን እንዳይሰባሰቡ ከማድረግ ጀምሮ፥ እስከወዲያኛው ተበትነው እንዲቀሩ የሚያደርግ ቢሆንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዲስኮርስ ግን እምብዛም የተዳሰሰ አልነበረም። ለዚህም ነው የኢትዮ-ኤርትራ ወዳጅነት ሲታደስ፥ ብዙኃኑ ዘንግቶት የነበረው የተበታተኑ ቤተሰቦች ጉዳይ አዲስ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ያለው። ይህም ስሜትን ኮርኩሮ ከጀማሪ እስከ ነባር ዘፋኞችን ስሜት አነሳስቷል።

ዘመኑን በዜማ…

ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሐዘኖችም ይሁኑ ፌሽታዎች በሕዝባዊ ዜማዎች የሚገለጹባት አገር ነች። በቅርብ ግዜ ክስተቶች እንኳን የሕዳሴው ግድብ ሲጀመር የደስታ ዘፈኖች ተዥጎድጉደው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሞቱ ሰሞን ደግሞ የሐዘን ዜማዎች ተደምጠዋል። ባለፉት አራት ዓመታት ሕዝባዊ አመፆች በተነሱ ግዜ፥ በተለይ በአማርኛ እና በኦሮምኛ በርካታ የብሶት ዜማዎች እየተደመጡ ነበር። አሁን ደግሞ የአመፁ ግዜ ታግሶ፥ ትንሽ ዴሞክራሲያዊ ብርሃን ሲፈነጥቅ የተስፋ ዜማዎች እንደገና እየተዜሙ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በርከት ያሉ የሳተላይት ቴሌቪዥኖች በኢትዮጵያውያን ስርጭት ጀምረዋል። አብዛኛዎቹ ቴሌቪዥኖች እኒህን የተስፋ ዘመን ዜማዎች አከታትለው እያዘፈኗቸው ነው። ጣቢያ ቢቀያይሩ እንኳን ከነዚህ ዜማዎች ማምለጫ ያለ አይመስልም። ሌላው ቀርቶ፣ ለሕዳሴው ግድብ ተዜሞ የነበረው እና "We are the world"("እኛ ነን ዓለም") የሚለው ዜማ ቅጂ ሆኖ "እኛ ነን ኢትዮጵያ"በሚል የተዜመው የተስፋ ዝማሬ በአዲስ የቪዲዮ ምስል ተቀናብሮ፥ ለዘመኑ ተመቻችቶ እንዳዲስ እየተደመጠ ነው።  ዜማው ኢትዮጵያውያን በተራቡ ወቅት የዓለም ዕውቅ ድምፃውያን የተጫወቱት ቢሆንም፥ ቅጂው የኢትዮጵያውያንን ስምንት ዕውቅ ድምፃውያን አሳትፎ ለኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያውያን የተዜመ ነው፤ ግጥሙ ደግሞ ተስፈኛ። አሁን ኢትዮጵያውያን ያሉበትን ተስፈኛ ሁኔታ የሚገልጸው የዜማዎቹ ግጥም ነው።

መጪው ግዜ አሁን የበቀለውን ተስፋ የሚያፋፋ ወይም የሚያጠፋ ስለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሆኖም ፖለቲካ የነቀለውን ተስፋ፣ ፖለቲካ መልሶ ዘርቶታል። የመጪው ግዜ ታሪክ ቢቀላም ቢጠቁር፥ ተስፋ የደረሰው ዜማ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እየታተመ ነው።

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ