1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤትና ኤርትራ፣

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 9 2002

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት አባላት፣ በቅርቡ በኤርትራ ላይ የጦር መሣሪያና በባለሥልጣናት ላይ የጉዞ እገዳ፣ ለማስተዋወቅ ፣ በውጭ የሚገኝ ንብረታቸውም እንዳይንቀሳቀ ሳይወስኑ አይቀሩም ተባለ።

https://p.dw.com/p/L8Pt
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤት ስብሰባ፣ምስል AP

በታሰበው እገዳ ዙሪያ ፣ ተክሌ የኋላ፣ የዓለም አቀፍ ውዝግቦች ተማራማሪ ድርጅት፣ (ICG) የአፍሪቃው ቀንድ ክፍል፣ ተመልካቾች ከሆኑት አንዱን በማነጋገር የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

በኤርትራ ላይ አንዳንድ የእገዳ እርምጃዎችን ለማንቀሳቀስ ግፊት በመደረግ ላይ ያለው ፣ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፣ ኤርትራ የሶማልያን አማጽያን በጦር መሳሪያጭምር በመርዳት የሽግግርሩ መንግሥት እንዳይደላደል ሰበብ ሆናለችም በሚል ነው ። ሊወሰድ የታሰበውም ሆነ ስምምነት ሳይደረግበት አልቀረም የተባለው የእገዳ ደንብ ተግባራዊ ቢሆን ፣ የኤርትራን አቋም የሚያስለውጥ ይሆናል ወይ? Mr. Earnst Jong Hogendoorn

«እኔ እንደምለው፣ ፣ እገዳ የተወሰነም ቢሆን ፣ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። ጥያቄው፣ ታዲያ፣ ኤርትራ የፀጥታ ጥበቃውን ም/ቤት ውሳኔ ችላ የማለት አቋሟ እንዲቀጥል ማድረጓ፣ ያን ያህል ጠቃሚ ይሆናል ወይ ? የሚለው ነው። እንደእውነቱ ከሆነ፣ ዓለም-አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ኤርትራ ሶማልያ ውስጥ ማንኛውንም ነገር እንዳታደርግ መከልከል አይቻለውም። ግን፣ በእርግጥ ሁኔታውን ይበልጥ ያከብደዋል። »

አማጽያንን ትደግፋለች የምትባለው ኤርትራ፣ ከተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ከዩናይትድ እስቴትስና ከሌሎችም አገሮች ፣ በሶማልያ ጉዳይ ይቀርብላት የነበረውን የመታቀብ ጥያቄ ችላ ብላ የቆየችበት ምክንያት ምን ይመስሎታል?

«ጉዳዮችን በግልጽ ለማስቀመጥ፣ ኤርትራ ኧል ሸባብን ለመርዳቷ ምንም ዓይነት ማረጋገ ጫ የለም። የምናውቀው ፣ ከሞላ ጎደል፣ ዘርዘር ብሎ በቀረበ ዘገባ መሠረት ሂዝቡል እስላም የተባለውን ስትረዳ መቆየቷን ነው። እንዲሁም፣ በደቡብ ሶማልያ ፣አንዳንድ ቡድኖችን መርዳቷን ነው።

አሁን የማስተባበል ነገር ከተነሣ፣ ጉዳዩ የተለመደና የጦር መሣሪያ እገዳን የሚጥሱ አገሮች የሚያደርጉት ነው። ህግ መጣሳቸው ቢረጋገጥም እንኳ፣ ማስተባበሉን እንደሚገፉበት የታወቀ ነው። የአፍሪቃውን ቀንድ አካባቢ ውዝግብ በተመለከተ፣ ልንገነዘበው የሚገባ አንድ ጉዳይ ፣ ኤርትራ፤ ሶማልያ ውስጥ ለአንዳንድ ቡድኖች ጦር መሣሪኢ ማቅረብ መቀጠሏ፣ በአመዛኙ ከኢትዮጵያ ጋር ባለባለባት የድንበር ውዝግብ ፣ በኢትዮጵያ ላይ ግፊት ለማድረግ ነው።»

እገዳ ከተደረገ ፣ ኤርትራን ምን ያህል ይጎዳታል ይላሉ ?

"ምንም ቢሆን ለኤርትራ ይበልጥ ከባድ ይሆናል ። በይፋ የጦር መሣሪያ ማቅረብ አትችልም ፣ አንዳንድ ባለሥልጣኖቿም ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወይም ወደ ምዕራቡ ዓለም ለመጓዝ አይቻላቸውም ። በጣም ከባድ ይሆንባቸዋል ። ሁኔታው አይመቻቸውም ። ነገር ግን ፣ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብለው እስካመኑበት ድረስ ፣ የጦር መሣሪያ ደንብን ከመሻር የሚገታቸው አይኖርም ።፡»

ከታሰበው የፀጥታ ጥበቃው ምክርቤት እገዳ አንፃር የኤርትራ መንግስት አቋም ምን እንደሆነ ለመስማት ያደረግነው ሙከራ፣ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ፣ በስብሰባ በመጠመዳቸው ለጊዜው አልተሳካልንም ። በሌላ ጊዜ እንመለስበት ይሆናል ።

ተክሌ የኋላ/ሒሩት መለሰ