1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሣሥ 12 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2013

በፕሬሚየር ሊጉ ሊቨርፑል ግስጋሴውን ቀጥሏል። አርሰናል ቊልቊለቱን ተያይዞታል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተደረጉ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ዩናይትድ በስድስት ሊቨርፑል በ7 ግቦች ተንበሽብሸዋል። በቡንደስሊጋው የ16 ዓመቱ ዩሱፍ ሙኮኮ ድንቅ ብቃት ቢያሳይም ወደ ቤርሊን ያቀናው ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ግን ከመሸነፍ አልታደገውም።

https://p.dw.com/p/3n1Px
Deutschland Fussball Bayern München gegen  VfL Wolfsburg
ምስል Lukas Barth-Tuttas/POOL/AFP via Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በፕሬሚየር ሊጉ ሊቨርፑል ግስጋሴውን ቀጥሏል። አርሰናል ቊልቊለቱን ተያይዞታል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተደረጉ ግጥሚያዎች ማንቸስተር ዩናይትድ በስድስት ሊቨርፑል በ7 ግቦች ተንበሽብሸዋል። በቡንደስሊጋው የ16 ዓመቱ ዩሱፍ ሙኮኮ ድንቅ ብቃት ቢያሳይም ወደ ቤርሊን ያቀናው ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ግን ከመሸነፍ አልታደገውም። ኤዲን ቴርዚች ብሬመንን በማሸነፍ የጀመሩት የአሰልጣኝነት ዘመናቸው ዋና ከተማዪቱ ላይ ሊደገም አልቻለም።  በቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ማሸነፉን ቀጥሏል። ሻልከ ዘንድሮ ተሰናባች መኾኑን ያረጋገጠ ይመስላል፤ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ስር ተዘርግቶ እንቅልፉን ይለጥጣል። እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች በሴካፋ ግጥሚያ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ለጥቂት ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፉ ቀርተዋል። 

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች ለዋንጫ ለማለፍ ከታንዛኒያ አቻቸው ጋር ትናንት ተጋጥመው በፍጹም ቅጣት ምት መለያ ተሸንፈዋል። የምስራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ዋንጫ (CECAFA) ግጥሚያ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ነው የሚካሄደው። በትናንቱ ግጥሚያ፦ መደበኛ ጨዋታው አንድ እኩል ከመጠናቀቊ በፊት ታንዛኒያ በ70ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተጨዋች በቀይ ተሰናብቶባታል። በፍጹም ቅጣት ምት መለያውም ታንዛኒያ 5 ለ 4 በሆነ  ድምር ውጤት ኢትዮጵያን አሸንፋ ለዋንጫ አልፋለች። ኡጋንዳን ትገጥማለች። ማክሰኞ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ለደረጃ ትጫወታለች። የኢትዮጵያ ቡድን ለዋንጫ ቢደርስ ኖሮ ሞሮኮ በጎርጎሪዮሱ ቀጣይ ዓመት በምታስተናግደው እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪቃ ዋንጫ በቀጥታ ያልፍ ነበር።

ፕሬሚየር ሊግ

Fussball I Chelsea v Liverpool
ምስል Laurence Griffiths/Getty Images

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ የመሪው ሊቨርፑል አሰልጣኛ እና ተጨዋቾች የዓመቱ ምርጥ ተብለው ተሰየሙ። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ እና ቡድናቸው የዓመቱ ምርጥ የተባሉት በቢቢሲ የስፖርት ሰብእና የዓመቱ ዝግጅት ላይ ነው። ዬርገን ክሎፕ ሊቨርፑል ለሠላሳ ዓመታት ሲጠብቀው የከረመውን ዋንጫ እንዲያነሳ ያስቻሉ ድንቅ አሰልጣኝ ናቸው።

ሊቨርፑል በዬርገን ክሎፕ ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫም አንስቷል። ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊጉን በ31 ነጥብ እየመራ ይገኛል። በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የደርሶ መልስ ግጥሚያውን ከወራት በኋላ ያከናውናል። በተለይ ቅዳሜ እለት ክሪስታል ፓላስን 7 ለ0 ያሸነፈበት ድሉ የሊቨርፑል ስኬት መገለጫ ነው።

በፕሬሚየር ሊጉ፦ ትናንት ቶትንሃምን 2 ለ0 ድል ያደረገው ላይስተር ሲቲ 27 ነጥብ ይዞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ማንቸስተር ዩናይትድም ትናንት ሊድስ ዩናይትድ ላይ የተቀዳጀው የ6 ለ2 ድል ተደምሮለት በ26 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ገና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል። ተመሳሳይ ነጥብ ያለው ግን በግብ ክፍያ አራተኛ ደረጃን የያዘው ኤቨርተን ቅዳሜ ዕለት አርሰናልን 2 ለ1 አሸንፎታል። በ14 ጨዋታዎች 14 ነጥብ ብቻ የያዘው አርሰናል ታች 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አልሆነላቸውም። ማንቸስተር ሲቲ 23 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ሳውዝሐምፕተንን 1 ለ0 አሸንፏል። ቸልሲ በ22 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል። ዛሬ ማታ ዌስትሀምን ካሸነፈ ወደ አምስተኛ ከፍ የማለት እድል አለው። በርንሌይ፣ ዌስትብሮሚች እና ሼፊልድ ዩናይትድ ከ18ኛ እስከ 20 ደረጃ ወራጅ ቃጣናው ላይ ይገኛሉ። በእርግጥ በርንሌይ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ይቀሩታል። አንዱን ዛሬ ማታ ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ያከናውናል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ውድድር የቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽንፈት መነጋገሪያ ኾኗል። አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬን በቅርቡ ያሰናበተው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በአዲሱ አሰልጣኝ ወደ ቤርሊን አቅንቶ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። 21 ነጥብ ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዑኒዮን ቤርሊን ዐርብ እለት ባሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አሁን የሚበለጠው በ1 ነጥብ ብቻ ነው። የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተስፋ የኾነው የ16 ዓመቱ ታዳጊ ሙኮኮ በዐርቡ ግጥሚያ በ60ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ በሆነ ኹናቴ ቡድኑን አቻ አድርጎ ነበር። በ78ኛው ደቂቃ ላይ በፍሬድሪሽ በተቆጠረባቸው ግብ ግን ከመሸነፍ አልተረፉም። 

Deutschland Frankfurt | Bundesliga | Eintracht Frankfurt v Borussia Dortmund
ምስል Alex Grimm/Getty Images

አዲሱ የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚች በመጀመሪያ የአሰልጣኝነት ዘመናቸው ቬርደር ብሬመን ላይ የ2 ለ1 ድል አስመዝግበው ነበር። ቀደሞ የዶርትሙንድ ረዳት አሰሰልጣኝ የነበሩት ኤዲን በእርግጥ ችግር ውስጥ የወደቀው ቡድናቸውን ወደ ቀደመ ስሙ ለመመለስ ጊዜ አላቸው። ጠንክረው ግን መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ቀጣይ ጨዋታቸው ቡድናቸውን በ2 ነጥብ በልጦ በ24 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቮልፍስቡርግ ጋር ነው።

ባየር ሙይንሽን ከትናንት በስትያ ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ1 አሸንፎ የደረጃ መሪነቱን ሥፍራ ተረክቦታል። 28 ነጥብ ያለው ባየር ሌቨርኩሰን በባየር ሙይንሽን በ2 ነጥብ ብቻ ነው የሚበለጠው። ላይፕትሲሽ  ቅዳሜ ዕለት ከኮሎኝ ጋር ያለምንም ግብ መለያየቱ 28 ነጥብ ይዞ 3ኛ ደረጃ ላይ እንዲወሰን አድርጎታል። ታች 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝን አሸንፎ ቢኾን ኖሮ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ከፍ ባለ ነበር።

ሻምፒዮንስ ሊግ

አሁን ደግሞ በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ውድድር ስላለፉት አራቱ የጀርመን ቡድኖች እና ተፎካካሪዎቻቸው ጥቂት እናስቃኛችሁ። 16 ቡድኖች በደርሶ መልስ በሚያደርጉት ግጥሚያ ተሳታፊ የኾኑት ቡድኖች፦ ላይፕትሲሽ ከሊቨርፑል፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሴቪያ፤ ባየር ሙይንሽን  ከላትሲዮ እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ ከማንቸስተር ሲቲ ናቸው።

ግላድባኅ የደረሰው ተጋጣሚ ማንቸስተር ሲቲ በሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ግጥሚያ ወቅት ነጥብ የጣለው ከፖርቶ ጋር ያለምንም ግብ የተለያያየ ጊዜ ብቻ ነው። ከምድቡ 16 ነጥብ ይዞ በአንደኝነት ነው ያለፈው። ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ 23 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። የፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን በላይስተር 5 ለ2፣ በሆዜ ሞሪኝሆ  ቶትንሃም ሆትስፐር ደግሞ የ2 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል። ቅዳሜ ዕለት በእርግጥ ሳውዝ ሀምፕተንን 1 ለ0 አሸንፏል።

Schweiz Nyon | Champions League | Auslosung Achtelfinale
ምስል UEFA/dpa/picture alliance

እስካሁን ድረስ ከቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ጋር በአውሮጳ ውድድር ለስድስት ጊዜያት ተገናኝተዋል።ለአውሮጳ ሊግ አራት ጊዜ (2014/15 እና 2015/16)እንዲሁም ለሻምፒዮንስ ሊግ 2 ጊዜ (1979) ተጋጥመዋል። የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ከሁለት ወራት በኋላ ሞይንሽንግላድባኅ ውስጥ፤ የመልሱን ጨዋታ ደግሞ ማንቸስተር ከተማ ውስጥ ያከናውናሉ። 

ባየርን ሙይንሽን የደረሰው ላትሲዮ ሮም በምድብ ግጥሚያው የምድቡ መሪ ኾኖ ወደ 16 ቡድኖች ያለፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድን 3 ለ1 ያሸነፈበት ድሉ ይጠቀስለታል። ከክሉብ ብሩጅ ጋር ያደረጉት የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ደግሞ ሁለት እኩል በማጠናቀቅ የምድቡ ሁለተኛ ኾነው አልፈዋል።

በጣሊያን ሴሪ ኣው ላትሲዮ ባለፈው ዓመት አራተኛ ኾኖ ቢጨርስም ዘንድሮ ከመሪው  ኤስ ሚላን በ10 ነጥብ ዝቅ ብሎ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት በሜዳው በሔላ ቬሮና የ2 ለ1 መሪር ሽንፈት ገጥሞታል። ትናንት ማታ ከናፖሊ ጋር ተጋጥሞ2 ለ0 ድል አድርጓል።

እስካሁን ከባየር ሙይንሽን ጋር ተጋጥሞ አያውቅም። ከአጠቃላዩ 32 የሻምፒዮንስ ሊግ ቡድኖች ግን ባየር ሙይንሽን የገጠመው እድል ድንቅ የሚባል ነው።

የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጋጣሚ ሴቪያ በምድቡ ከቸልሲ ጋር ወደያው ነበር የሁለተኛ ደረጃውን ያረጋገጠው። በምድቡ የነበሩት ክራስኖዳር እና ሬኔ ያን ያህል ጠንካራ ተፎካካሪ አልነበሩም። ለንደን ውስጥ ከቸልሲ ጋር ያለምንም ግብ ነበር የተለያየው። አናዳሉሲያን ውስጥ ግን ያደረጉት ግጥሚያ ለቸልሲ ነበር የኾነው። ሰማያዊዎቹ ሴቪያን 4 ለ0 ነበር ድል ያደረጉት። የቸልሲው አጥቂ ኦሊቨር ዢሩ አራቱንም ግቦች ከመረብ በማሳረፍ በርካቶችን አስደምሞ ነበር።

ሴቪያ በስፔን ላሊጋ ከመሪው አትሌቲኮ ማድሪድ በ9 ነጥብ ተበልጦ በ20 ነጥቡ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ከቫላዶሊድ ጋር ገጥሞ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ሴቪያ እጎአ ከ2009 ወዲህ ባለፈው ዓመት ለአራተኛ ጊዜ የአውሮጳ ሊግ ዋንጫን መውሰድ ችሏል። ከዶርትሙንድ ጋር ሁለት ጊዜ (በ2010/11)ለአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ ተገናኝተዋል።

Champions League 8.12.-9.12. 2020
ምስል Jose Breton/picture-alliance/NurPhoto/Pics Action

ላይፕትሲሽ ከሊቨርፑል ፦ ሊቨርፑል ምድቡ እንደ እነ አያክስ አምስተርዳም፣ አታላንታ ቤርጋሞ እና ሚቺላንድን የመሰሉ ጠንካራ ቡድኖች ቢኖሩም ወዲያው ነበር መሪነቱን ያረጋገጠው። የጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ቡድን ሊቨርፑል በሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ግጥሚያው አራት ጊዜ አሸንፎ በሜዳው በቤርጋሞ ግን የ 2 ለ 0 ሽንፈት ደርሶበታል። ቢኾንም ምድቡን በ13 ነጥብ በአንደኝነት ነው ያጠናቀቀው። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ባለፈው የወሰደው ሊቨርፑል አሁንም ሊጉን ከላይስተር ሲቲ በ4 ነጥብ ልዩነት በ31 ነጥብ እየመራ ነው። በተለይ ቅዳሜ ዕለት ክሪስታል ፓላስን 7 ለ0 እየተመላለሰ ድባቅ የመታበት ብቃቱ ይጠቀስለታል። ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ፦ ቸልሲን 2 ለ0 እንዲሁም አርሰናልን 3 ለ1 ያሸነፈበት ተጠቃሽ ነው። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር አንድ እኩል መውጣቱም ጥንካሬውን ያሳያል።  ላይፕትሲሽ በቡንደስሊጋው ደረጃው 3ኛ ነው። ጀርመናዊው የላይፕትሲሽ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን ወይንስ ሌላኛው ጀርመናዊ የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ? ከሁለት ወራት በኋላ የሚከናወነ ውየሻምፒዮንስ ሊግ የደርሶ መልስ ግጥሚያ ዘንድሮ በጉጉት ይጠበቃል።

Champions League |  Liverpool FC v FC Midtjylland
ምስል Phil Noble/Getty Images

የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ፦በቡንደስሊጋው ከማይንትስ የጀመሩት ስኬታቸው በየጊዜው ከከፍታ ላይ ከፍታ እየጨመረ ነው። ሁለት ጊዜ ቦሩስያ ዶርትሙንድን በቡንደስሊጋው ዋናጫ እንዲያነሳ አስችለውታል። ከሊቨርፑል ጋር ኾነው ደግም በ2019 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በመጨበጥ ሊቨርፑሎችን አስፈንድቀዋል። ከበርካታ ዐሥርተዓመታት ጥበቃ በኋላም የ53 ዓመቱ አሰልጣኝ ሊቨርፑል የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ እንዲወስድ አስችለዋል። በሊቨርፑል የእስካሁን የአምስት ዓመት ቆይታቸው ከፍተኛ ስኬት አስመዝግበዋል። አሰልጣኙ ተጨዋቾቻቸው ባላጋራ ላይ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ተጋጣሚን ኳስ በማሳት እና ኳስን በመቆጣጠር ለድል እንዲበቊ በማድረግ ስልታቸው ይታወቃሉ። ሞ ሳላኅ፣ ሮቤርቶ ፊርሚኖ እና ሳዲዮ ማኔ የጫና ፈጠራ አንቀሳቃሾቹ ናቸው። የዲዬጎ ጆታ እና ታኩሚ ሚናሚኖም ወደ ቡድኑ መምጣት ተጨማሪ የማጥቃት ኃይል  ናቸው። አማካዩ ናቢ ኪዬታ በ2018 ከላይፕትሲሽ ነበር ወደ ሊቨርፑል የተዛወረው። የቀድሞ ቡድኑን ሊገጥም ነው ማለት ነው። መየሊቨርፑል ትልቊ ችግር በአሁኑ ወቅት በርካታ ተጨዋቾቹን በጉዳት ማጣቱ ነው። በተለይ ከተከላካይ ክፍሉ፤ የቪርጂል ቫን ጂክ ለረዥም ጊዜ በጉዳት መገለል ቡድኑ በተከላካይ በኩል ብርቱ ክፍተት ፈጥሮበታል።  ላይፕትሲሽ እስካሁን ከሊቨርፑል ጋር ገጥሞ ዐያውቅም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ