1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሣሥ 3 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 3 2015

የቃጠር የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ የበርካቶችን ቀልብ እንደገዛና ልብ እንዳንጠለጠለ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው። የፍጻሜው ተጋጣሚዎች ነገና ከነገ ወዲያ በሚደረጉ ሁለት ግጥሚያዎች ይለያሉ። አፍሪቃዊቷ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፏ የበርካታ አፍሪቃውያን ኩራት ምንጭ ሆኗል። ሞሮኮን ብሎም አፍሪቃን ያኮሩት በዋናነት የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4KqDm
WM Katar 2022 I Portugal vs Marokko
ምስል Martin Meissner/AP/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የቃጠር የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ ውድድር የበርካቶችን ቀልብ እንደገዛ እና ልብ እንዳንጠለጠለ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው። የፍጻሜው ተጋጣሚዎች ነገ እና ከነገ ወዲያ በሚደረጉ ሁለት ግጥሚያዎች ይለያሉ። አፍሪቃዊቷ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፏ የበርካታ አፍሪቃውያን ኩራት ምንጭ ሆኗል። ሞሮኮ ብሎም አፍሪቃን ለዚህ ኩራት ያበቁት በዋናነት የ47 ዓመቱ አሰልጣኝ ናቸው። እኚህ ሞሮኮዋዊ አሰልጣኝ በእርግጥ ማን ናቸው? ምን አይነት የኳስ ጥበብስ ተጠቅመው ለዚህ ድል መብቃት ቻሉ? የዛሬው የስፖርት ዘገባችን ዋነና ትኩረት ነው። የባየር ሙይንሽኑ ግብ ጠባቂ በበረዶ መንሸራተት ግጥሚያ እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበት ቀዶ ጥገና ተደርጎለታል። በዘንድሮ ቀሪ የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች መሰለፍ አለመቻሉ ቡድኑን አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶታል።

በዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የደረሱ ሃገራት

በዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፉክክር «የአትላስ አናብስት»ን የሚያስቆማቸው አልተገኘም። ለዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ከደረሱት አራት ሃገራት መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት አፍሪቃዊት ሀገርም መገኘት ለበርካታ አፍሪቃውያን የኩራት ምንጭ ሆኗል። «የአትላስ አናብስት» የሚል ቅጽል ስያሜ ያለው የሞሮኮ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፊፋ (FIFA) 34ኛ ደረጃ ይዘዋል። በፊፋ የወንዶች እግር ኳስ መስፈርት በዓለም የ1ኛነት ደረጃን የያዘችው ቤልጂየም፤ 3ኛዋ ብራዚል 4ኛ ደረጃ እና 6ኛ ደረጃ የተሰጣቸው የእንግሊዝ እና የስፔን ቡድኖች ተሰናብተው ነው ሞሮኮ ለዚህ ክብር የበቃችው። 7ኛ ደረጃ ያላት ጣሊያን ጭራሱኑም ዘንድሮ ለዓለም ዋንጫ አላለፈችም። 12ኛ ደረጃ ያለው የጀርመን ቡድን ካለፈው የዓለም ዋንጫ ትምህርት ወስዶ እግር ኳስ ላይ ብቻ አለማተኮሩ ሽንፈት ተከናንቦ ዘንድሮም ከዓለም ዋንጫ በጊዜ ተሰናብቷል። የአትላስ አናብስት ግን በኩራት በቃጠር ምድር ማግሳታቸውን ቀጥለውበታል።  

FIFA Fußball WM 2022 in Katar | Marokko - Portugal
የሞሮኮው ሠሊም አማላህ እና የፖርቹጋሉ ብሩኖ ፈርናንዴሽ በቃጠር ዓለም ዋንጫ ኳሷን ለመቆጣጠር ሲጣጣሩምስል Ariel Schalit/AP Photo/picture alliance

ለመሆኑ እንዲያ በዓለም ዙሪያ አሉ የሚባሉ ስመ-ገናና የእግር ኳስ ቡድኖች በጊዜ ተሰናብተው «የአትላስ አናብስት» በቃጠር የዓለም ዋንጫ አስጨናቂ እንዲሆኑ ያስቻሏቸው አሠልጣኙ ማን ናቸው? ፈረንሳይ ተወልደው ያደጉት ትውልደ-ሞሮኮው አሠልጣኝ ዋሊድ ሪግራግዊ በእርግጥ ማን ናቸው? ወደዚያ ከማለፋችን አስቀድሞ ሞሮኮ ለግማሽ ፍጻሜ መብቃቷ ቃጠር ውስጥ ስለፈጠረው ስሜት እንዲነግረን የሐትሪክ ጋዜጣ መስራች እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ይስሐቅ በላይ ጋር ደውለንለታል። ይስሐቅ የዓለም ዋንጫ እግር ኳስ ጨዋታዎችን ለመዘገብ ቃጠር ነው የሚገኘው። ወደ ቃለ መጠይቁ እንለፍ።

የሞሮኮ የዓለም ዋንጫ ግስጋሴ

ሞሮኮ በፊፋ መስፈርት የ1ኛ ደረጃ ከተሰጣት ቤልጂየም እና እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 የፍጻሜ ተጋጣሚ ከሆነችው ክሮሺያ ጋር ተመድባ ስፔን እና ፖርቹጋልን ማሰናበቷ በርካቶችን አስደንቋል።  ሞሮኮን ለዚህ ድል ያበቁት አሠልጣኝ ዋሊድ ሪግራግዊ ተወልደው ያደጉት በግማሽ ፍጻሜ የሚጋጠሙት ፈረንሳይ ውስጥ ነው። አሰልጣኙ የሞሮኮ እና የፈረንሳይ ጥምር ዜግነት አላቸው። ለቤተሰባቸው ከስድስት ልጆች ሦስተኛው የሆኑት ዋሊድ ሪግራግዊ በልጅነታቸው በዓመት ቢያንስ ለሁለት ወራት ወደ ሞሮኮ ይጓዙ ነበር። ይህ ደግሞ የእናት እና አባታቸው ግዴታ እንደነበር ይናገራሉ። ያ በመሆኑም ከሞሮኮ ጋር ያላቸው ቁርኝት ጠንካር መሆኑን ይገልጣሉ።

FIFA Fußball WM 2022 in Katar | Marokko - Portugal
የሞሮኮ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች ዩሴፍ ኤን-ኔሲሪ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ሜዳ ውስጥ ተሰባስበውምስል Martin Meissner/AP Photo/picture alliance

አሰልጣኙ ቀደም ሲል ለፈረንሳይ ቱሉስ ጨምሮ ለኤ ሲ አያቺዮ እና ሬሲንግ ሳንታንደር ተከላካይ ሆነው ተጫውተው ያውቃሉ። በእግር ኳሱ ዓለም በገናናነት ስማቸው የሚጠቀሰው ስፔንን እና ፖርቹጋልን ከውድድር ያስወጡት አሰልጣኝ ዋሊድ ሪግራግዊ ይህን የመከላከል ጥበባቸውን በአሰልጣኝነትም ዐሳይተዋል።  ቡድናቸውን 4-1-4-1 በሚባለው አሰላለፍ ወደ ሜዳ አስገብተውም በዋናነት በመከላከል ላይ ተመስርተው ተጋጣሚያቸው ላይ ክፍተት ሲኖር በመልሶ ማጥቃት ብቃታቸውን ዐሳይተዋል። አንድ አጥቂ ኤን ኔሲሪን ከፊት አድርገውም ክፈት ሲገኝ በመልሶ ማጥቃት የክንፍ ተመላላሾቹ ሐኪሚ እና ማዝራዊን እንዲሁም የኳስ ጥበበኛው ሲይሽ እና ሌላኛው የክንፍ ተጨዋች ሶፊያን ቦውፋልን ወደፊት በማስፈንጠር ተጋጣሚያቸውን አስጨንቀዋል። ብረት የመከላከል አጥራቸውንም ሳያስደፍሩ አጽንተዋል።

አሰልጣኙ የሞሮኮ ቡድንን ከያዙም ገና አምስት ወርም አልሆናቸው። ቦስኒያዊው የሞሮኮ አሰልጣኝ ቫሂድ ሐሊሆዲች በምርጫ ወቅት ሐኪም ሲይሽን አላካትትም በማለታቸው በሞሮኮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ይባረራሉ። ክፍተቱንም የዋይድ ካዛብላንካ ቡድንን በማሰልጠን በአፍሪቃ ሻምፒዮንስ ሊግ ለድል ያበቁት አሠልጣኝ ዋሊድ ሪግራግዊ እንዲሸፍኑ ይጠየቃሉ። አሰልጣኙ አላመነቱም። የተነገረላቸውን የመከላከል እና የመልሶ ማጣቃት ጥበብ በመተግበርም ቡድናቸውን ለአስደናቂ ለውጤት አብቅተዋል። ከእንግዲህስ ስለ ዓለም ዋንጫው የማናልምበት ምን አንዳች ምክንያት ይኖራል?» ብለዋል። በእኚሁ አሠልጣኝ ዋሊድ ሪግራግዊ ብቃት በሩብ ፍጻሜው የተሰናበተው የፖርቹጋል ቡድን አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የእግር ኳስ ወርቃማ ዘመን በእንባ ተቋጭቷል።

WM 2022 - Marokko - Portugal
የሞሮኮ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊን ተጨዋቾች ሜዳ ውስጥ ከፍ አድርገው ተሸክመዋቸው ምስል Tom Weller/dpa/picture alliance

ከነገ በስትያ በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይን ይገጥማሉ። ይሳካላቸው ይሆን? የብዙዎች ምኞት ነው። በነገው ምሽት በግማሽ ፍጻሜው አርጀንቲና ከክሮሺያ ጋር ይጋጠማሉ።

የአውሮፕላን አደጋ

የቀድሞው የኦሎምፒክ የ800 ሜትር ክብረወሰን ባለቤት ዴቪድ ሩዲሻ ኬንያ ውስጥ ከአውሮፕላን አደጋ ለጥቂት መትረፉ ተዘግቧል። የ33 ዓመቱ ኬንያዊ አትሌትን እና ሌሎች አምስት ሰዎችን አሳፍሮ ይበር የነበረው አውሮፕላን የተከሰከሰው ደቡብ ምሥራቅ ኬንያ ካጃዶ የምትባል አካባቢ ቅዳሜ ዕለት መሆኑን የዜና ምንጮች ዘግበዋል።  እንደ ጎርጎሮዮስ አቆጣጠር በ 2012 እና በ2016 ለንደን ውስጥ የወርቅ ሜዳይ ያገኘ አትሌት ነው። ተሳፋሪዎቹ ላይ የደረሰባቸው መጠነኛ ጉዳት እንደሆነ እና ታክመው ወደ ቤታቸው መግባታቸውም ተገልጧል። የአውሮፕላን አብራሪው ብርቱ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ሙከራ ማድረጉም ተገልጧል።

ማኑዌል ኖየር ተሰበረ

የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ዋና ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር በበረዶ መንሸራተት ሲዝናና እግሩ ላይ ጉዳት በመድረሱ በቀሪ የዘንድሮ የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች መሰለፍ አይችልም ተባለ። የ36 ዓመቱ ግብ ጠባቂ እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት የቀዶ ጥገና እንደተደረገለትም ተዘግቧል። እስከሚቀጥለው ሰኔ ወር ድረስ በውሰት ተወስዶ ለኤ ኤስ ሞናኮ የሚጫወተው የባየር ሙይሽንሽን የቀድሞ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ አሌክሳንደር ኑይብል ወደ ቡድኑ ሊመለስ ነው የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል። ተብሏል።  ሆኖም የአሌክሳንደር ወኪል ሽቴፋን ባክስ «እስካሁን ድረስ ከባየርን ሙይንሽን እኔም ሆንኩ አሌክስ የሰማነው ነገር የለም» ብለዋል። የዛሬ ሁለት ዓመት ከሻልከ ወደ ባየርን ሙይንሽን ከተዘዋወረበት ጊዜ አንስቶ አሌክሳንደር ኑይብል ተጠባባቂ ግብ በመሆን አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር። እናም ቀደም ሲል አሌክሳንደር ወደ ባየርን ሙይንሽን ይመለስ እንደሆን ተጠይቆ ሲመልስ፦ «ወንበር ለማሞቅ አልመለስም» ብሎ ነበር። አሁን ዋናው ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር በጉዳት ለረዥም ጊዜ መሰለፍ የማይችል በመሆኑ ተጠባባቂው ግብ ጠባቂ ሐሳቡን መቀየሩ አይቀርም ተብሎ ይጠበቃል።

Manuel Neuer liegt im Krankenhaus
የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኖየር እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበት ሐኪም ቤት አልጋ ላይ ይታያልምስል Manuel Neuer/Instagram/dpa/picture alliance

በቃጠር የዓለም ዋንጫ ያልተጠበቁ ወጤቶች ለታዋቂ ቡድኖች የእግር ኳስ አሰልጣኞች ስንብት ዳፋ ሆነዋል። ለዋንጫው ትደርሳለች ተብላ በብዙዎች ዘንድ ግምት ተሰጥቷት እነ ኔይማር እና ደጋፊዎቹን በእንባ ያራጨችው ብራዚል አንጋፋ አሰልጣኝ ተሰናብተዋል። ቲቴ በሚለው ስማቸው የሚታወቁት የ61 ዓመቱ የብራዚል አሰልጣኝ አዴኖር ሌዎናርዶ ባቺ በእርግጥ ከዚህ የዓለም ዋንጫ በኋላ ራሳቸውን እንደሚያሰናብቱ ቀድመው ተናግረው ነበር። የ5 ጊዜያት የዓለም ዋንጫ ባለድሉ ብራዚልን ክሮሺያ እንዲያ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ካርሎስ ዱንጋን የዛሬ ስድስት ዓመታት የተኩት አሰልጣኝ ቲቴ የስንብት ዘመናቸው በሽንፈት ተደምድሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ