1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና መዋዕለ-ንዋይ እና ኩባንያዎች ፈተናዎች በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 3 2013

በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካና አውሮፓ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ሲበረታ ቻይና በምታራምደው ጣልቃ ያለ መግባት አቋም እንደ ጸናች ይታያል። ለኢትዮጵያ ብድር ስትሰጥ የቆየችው ቤጂንግ ቆጠብ ማለቷን የሚጠቁሙ ምልክቶች ታይተዋል። ኢትዮጵያን ያጎበጣት ዕዳና የሰሜኑ ውጊያ በቻይና መዋዕለ-ንዋይ ላይ ምን አይነት ጫና አሳደረ?

https://p.dw.com/p/405Zi
Äthiopien Awassa
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

ከኤኮኖሚው ዓለም፦የቻይና መዋዕለ-ንዋይ እና ኩባንያዎች ፈተናዎች በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ካለባት ዕዳ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማውን አከፋፈል ለማስተካከል ከምዕራባውያኑ ድርድር ስትጀምር ከወደ ቻይና ሌላ እንቅፋት ገጥሟታል። የቻይናው ኤክዚም ባንክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል የገባውን ብድር ለመልቀቅ አሻፈረኝ ማለቱን በገንዘብ ሚኒስቴር የቻይና ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለሬውተርስ ተናግረዋል። ኃላፊው አቶ ደምሱ ለማ ለሬውተርስ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ "የዕዳ ክምችት ላይ የበለጠ ጫና ይፈጥራል በሚል ባንኩ ወደ 339 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።" የኤክዚም ባንክ በአቋሙ ጸንቶ ብድሩ ካልተለቀቀ በመጓጓዣ እና ኃይል ማመንጫ ዘርፎች የተጀመሩ አስራ ሁለት ፕሮጀክቶች ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አቶ ደምሱ መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

ቻይና እና ኢትዮጵያን ያጎበጣት የዕዳ ጫና

አቶ ደምሱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከፓሪስ የአበዳሪዎች ክለብ የጀመረችው የዕዳ አከፋፈል ድርድር እስኪጠናቀቅ የቻይናው ኤክዚም ባንክ ብድሩን እንደማይለቅ አስታውቋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ድርድሩ ባለፈው ሰኔ መጀመሩን ይፋ ያደረገ ሲሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ በአፋጣኝ እንዲቋቋም ጠይቋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ገደማ ከቻይና በምትበደረው ጠቀም ያለ ገንዘብ መንገዶች፣ የባቡር መጓጓዣዎችን እና ፋብሪካዎችን ጨምሮ ግዙፍ መሠረተ-ልማቶች ስትገነባ ቆይታለች። በአሜሪካው ጆን ሖፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የቻይና አፍሪካ ጥናት ማዕከል መረጃ እንሚጠቁመው በጎርጎሮሳዊው ከ2010 እስከ 2018 ባሉት ስምንት አመታት ኢትዮጵያ ከአንጎላ በመለጠቅ ትልቋ ተበዳሪ ነበረች። በተጠቀሰው ጊዜ አንጎላ 37 ቢሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ፣ 11 ቢሊዮን ዶላር፣ ዛምቢያ 9 ቢሊዮን ዶላር፣ ኬንያ 8.3 ቢሊዮን ዶላር ናይጄሪያ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ከቻይና በመበደር ቀዳሚ የነበሩ አምስት አገሮች ናቸው። የዕዳ አከፋፈላቸውን ከቻይና የተደራደሩ አራት አገሮች በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. ከቤጂንግ አዲስ ብድር ሳያገኙ ቀርተዋል። እነዚህም ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞዛምቢክ፣ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ናቸው።

Äthiopien Industriegebiet in Hawassa
ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ገደማ ከቻይና በምትበደረው ጠቀም ያለ ገንዘብ መንገዶች፣ የባቡር መጓጓዣዎችን እና ፋብሪካዎችን ጨምሮ ግዙፍ መሠረተ-ልማቶች ስትገነባ ቆይታለች።ምስል Imago/Xinhua Afrika

የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ

ቤጂንግ ለኢትዮጵያ በቀጥታ ከምትሰጣቸው ብድሮች ባሻገር የቻይና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ኩባንያዎች በኤኮኖሚው ውስጥ ላቅ ያለ ሚና እየተጫወቱ ለአመታት ዘልቀዋል። በቻይና ፉጂያን ግዛት በሚገኘው ፉጆ ዩኒቨርሲቲ በኤኮኖሚክስ እና ማኔጅመንት ትምህርታቸውን የተከታተሉት ዶክተር አምሳሉ ክንዱ ለሰራተኞች የሚከፈለው ዝቅተኛ ደሞዝ እና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን የመሳሰሉ ዕድሎች ኢትዮጵያ የቻይናን የኢንቨስትመንት ቀልብ ከሳበችባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚገኙበት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ዶክተር አምሳሉ ኢትዮጵያ "በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ስለሆነች ግዙፍ የገበያ ፍላጎትም አለ። በተጨማሪ የኢንቨስትመንት መብት ይከበራል። አስተማማኝ የመንግሥት ዋስትና መኖሩ ይኸም ሌላኛው ምክንያት ነው" ሲሉ ኢትዮጵያ ለቻይና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ሆነ ለግል ኩባንያዎች መዋዕለ-ንዋይ ሳቢ የሆነችባቸውን ምክንያቶች ያስረዳሉ። 

አብዛኞቹ የቻይና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከአገራቸው የፖሊሲ ባንኮች ገንዘብ ማግኘት የሚችሉ እና በኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ የሚሳተፉ መሆናቸውን የብሪታኒያው ኦቨርሲስ ደቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት በነሐሴ ወር ይፋ ያደረገው ጥናት ይጠቁማል።  ይኸ ጥናት የቻይና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ኩባንያዎችን የኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋይ ሥጋት እና ዕድል የሚተነትን ነው። 

በጥናቱ መሠረት የቻይና የግል ኩባንያዎች ከጎርጎሮሳዊው 1997 እስከ 2017 ባሉት አመታት ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል በ604 ፕሮጀክቶች ተሰማርተዋል። የማምረቻው ዘርፍ የቻይና የግል ኩባንያዎችን ቀልብ በመሳብ ቀዳሚው ሲሆን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የማሽን እና የመሳሪያዎች ኪራይ እንዲሁም የማማከር አገልግሎት ይከተላል።

የተመናመነ የውጭ ምንዛሪ ቋት እና የቻይና ተቋማት ፈተናዎች

የብሪታኒያው ኦቨርሲስ ደቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት (ODI) ባለሙያዎች ባከናወኑት ጥናት የቻይና ተቋማት በኢትዮጵያ የገጠሟቸውን አምስት ፈተናዎች ዘርዝሮ አቅርቧል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው። ጥናቱን ካከናወኑ ባለሙያዎች አንዷ የሆኑት ሊንዳ ካላብሬሴ ለዶይቼ ቬለ "የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ካልቻልክ ጥሬ ዕቃ ከውጭ አስገብቶ ለማምረት ፈታኝ ነው። በችግሩ ምክንያት መንግሥት እያንዳንዱ ኢንቨስትር ምን ያክል ማግኘት እንዳለበት የሚወስን ገደብ አስቀምጧል። ይኸ ማለት ኢንቨስተሮች ሸቀጥ ለማስገባት ፈተና አለባቸው ማለት ነው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ፋብሪካዎች እና ማምረቻዎችን በጎበኘንበት ወቅት አንዳንዶቹ ጥሬ ዕቃ ለማስገባት በቂ የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታቸው ምርታቸውን መቀነሳቸውን ተመልክተናል። ኩባንያዎቹ ዶላር ካላገኙ ለሥራ ፈጠራ እና ለወጪ ንግድ ጭምር ፈተና ነው" ሲሉ አስረድተዋል። 

ሊንዳ ካላብሬሴ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ከውጭ ምንዛሪ እጥረት በተጨማሪ የዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት እና የምርት ሒደትን ያወከው የኮቪድ ወረርሽኝ ተጽዕኖ አሳድሯል። የኢትዮጵያ መንግሥት የማስፈጸም አቅም እና የጸጥታ ሥጋት በሰነዱ የተዘረዘሩ እና የቻይና ባለወረቶች የገጠሟቸው ፈተናዎች ናቸው።

በጥናቱ መሠረት የቻይና ባለወረቶች የሰው ኃይላቸውን እና የኩባንያዎቻቸውን ጥሪቶች ወደ ኢትዮጵያ ለማዛወር የማጓጓዣ ወጪ መጨመር፣ በተሰማሩበት ገበያ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እና የሚያስከትለው ዝቅተኛ ምርታማነት እንዲሁም የሰራተኛ በከፍተኛ ሁኔታ መልቀቅ ሌላው ተጨማሪ  ፈተና ነው። ሰነዱ ይኸ ጫና በተለይ በማምረቻው ዘርፍ ላይ መበርታቱን ይጠቁማል።

በኢትዮጵያ እየበረታ የመጣው ማህበራዊ እና ፖለቲካ አለመረጋጋት ለቻይና ኩባንያዎች ሌላው ፈተና ነው። የፈረሰው ኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ በየካቲት 2010 ዓ.ም ከሥልጣን መልቀቅ በቻይና ባለወረቶች ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሮ እንደነበር ሰነዱ ያትታል። ጥናቱ እንደሚለው የኃይለማርያም ስንብት በቻይና ኢንቨስተሮች ዘንድ የኢሕአዴግ ውድቀት ምልክት ሆኖ ታይቷል።

Li Keqiang Präsident China Besuch in Äthiopien mit Hailemariam Desalegn
የፈረሰው ኢሕአዴግ ሊቀ-መንበር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ በየካቲት 2010 ዓ.ም ከሥልጣን መልቀቅ በቻይና ባለወረቶች ዘንድ ድንጋጤ ፈጥሮ እንደነበር የብሪታኒያው ኦቨርሲስ ደቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ጥናት ይፋ አድርጓል። ምስል Reuters

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚያቀነቅኗቸው ተራማጅ ፖሊሲዎች አዎንታዊ ተጽዕኖ ቢኖራቸውም የመዋዕለ-ንዋይ ከባቢው ግን እንደ ቀድሞ አበረታች አይደለም የሚል ስሜት በቻይና ባለወረቶች ዘንድ እንዳረበበ ይኸው ሰነድ ያትታል። ሰነዱ እንደሚለው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ጨምሮ በመንግሥት ተቋማት የተደረገው የአወቃቀር እና የአመራር ለውጥ የቻይና ኩባንያዎች ጥሪት ያፈሰሱባቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የመሠረተ-ልማት ግንባታ ዘርፎችን መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ማበረታታት ያቆማል የሚል ሥጋት ፈጥሯል።

ሊንዳ ካላብሬሴ "የቻይና ኢንቨስተሮች ለመረጋጋት ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣሉ። መረጋጋት ሲባል የግድ አንዳች የፖለቲካ ሥርዓት ማለት ላይሆን ይችላል። እነሱ ዋጋ የሚሰጡት ማረጋገጫ የሚሰጥ እና ቃሉን የሚያከብር መንግሥት መኖሩ ላይ ነው። መንግሥት በሚሰጣቸው ማረጋገጫ መሠረት በዚያ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችሉ ያውቃሉ። በዚያ መሠረት በአገሪቱ ደህንነታቸው የተጠበቀ ለመሆኑ ማረጋገጫ ይፈልጋሉ። በቀደመው ሥርዓት ዋጋ የነበረው እንዲህ አይነቱ መረጋጋት ነበር። የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ እርግጠኝነት ማጣት እንዲፈጠር አድርጓል። በዚያ ላይ አሁን በትግራይ የተፈጠረው ግጭት በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የቻይና ኢንቨስተሮች ሥጋት ሊገጥማቸው እንደሚችል አሳይቷል። ይኸ ቀድሞም በነበሩ አለመረጋጋቶች ላይ የሚታከል ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው እና ብርቱ ሰብዓዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ ቀውስ የፈጠረው ግጭት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ቻይና በኢትዮጵያ ባላት መዋዕለ-ንዋይ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ግጭቱ በጥቅምት በይፋ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአዲስ አበባ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በትግራይ የነበሩ ከ600 በላይ የቻይና ባለወረቶች እና ቻይናውያን ሰራተኞችን አስወጥቷል። ባለፈው የካቲት መጨረሻ ሁለቱ አገሮች መንገድ እና መቀነት (Belt and Road Initiative) በተሰኘው መርሐ-ግብር ሥር ለተገነቡ ፕሮጀክቶች ጥበቃ ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።"ይኸ በቻይና ኩባንያዎች ዘንድ ጥሪታቸው ሥጋት እንደተጋረጠበት እና ሊጠብቁት እንደሚገባ አንዳች መረዳት መኖሩን ያሳያል። በሌላ ወገን ደግሞ መንግሥት በዚህ ረገድ ከኩባንያዎቹ ጋር ለመተባበር ያለውን ፈቃደኝነት ይጠቁማል። ስለዚህ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መሥራታቸውን እንዲቀጥሉ ለማረጋገጥ ሁለቱም ወገኖች ጥንቃቄ እያደረጉ ነው" ሲሉ ሊንዳ ካላብሬሴ ትርጉሙን ይናገራሉ። 

China Einfluss in Afrika Baustelle in Addis Abeba Äthiopien
ቤጂንግ ለኢትዮጵያ በቀጥታ ከምትሰጣቸው ብድሮች ባሻገር የቻይና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ኩባንያዎች በኤኮኖሚው ውስጥ ላቅ ያለ ሚና እየተጫወቱ ለአመታት ዘልቀዋል። ምስል Getty Images

ቻይና ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገሮች የምትከለተውን የኢንቨስትመንት ስልት አዋጪነት ቆም ብላ ማጤን ለመጀመሯ ጥቆማ ከሰጠች ከራርማለች። ኢትዮጵያ ያጎበጣት የዕዳ ጫና፣ መረጋጋት የራቀው ምጣኔ ሐብት እና ፖለቲካ ቻይናን እንደማያርቅ የቻይና አፍሪካ አማካሪ ተቋም መሥራች እና ዳይሬክተር አቶ አሌክሳንደር ደምሴ ያምናሉ።

"ለቻይና ኢትዮጵያ በጣም ወሳኝ አገር ነች። አገሪቱ ውስጥ ብዙ ኢንቨስትመንቶች ስላሉ ቻይና በማንኛውም ጊዜ ከኢትዮጵያ ለቃ እንደምትወጣ አይገመትም። እነሱን ለመጠበቅ እና ለማሳደግ አሁንም ትልቅ ፍላጎት አለ" የሚሉት አቶ አሌክሳንደር ባለፉት ሶስት አመታት የቻይና ኩባንያዎች በሚሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች ለውጦች መታየታቸውንም ተናግረዋል። 

"በመጪዎቹ አመታት ግንኙነቱ ከዚህ በላይ ላያድግ ይችል ይሆናል፤ ምን አልባት የቻይና ኢንቨስተሮች እና አበዳሪዎች በአሁኑ ወቅት ጥንቁቅ ሊሆኑ ይችላሉ" የሚሉት ሊንዳ ካላብሬሴ "ችግሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት አገር ሆና ትቀጥላለች " የሚል አቋም አላቸው። ባለሙያዋ የቻይና ኩባንያዎች "በመጪዎቹ ጥቂት አመታት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ጥለው አይወጡም። ሁለቱ አገሮች በጥምረት እስካሁን በጋራ የሰሩት ትንሽ የሚቀጥል ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል። 

የብሪታኒያው ኦቨርሲስ ደቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት አጥኚዎች ይፋ ባደረጉት ሰነድ የኢትዮጵያ መንግሥት አምራቾች በተለይ ከውጪ ንግድ ጋር በተሳሰረው ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች የተጋረጡባቸውን ኤኮኖሚያዊ እና የፋይናንስ ችግሮች ማቃለል ላይ እንዲያተኩር ጥቆማ ሰጥተዋል። የአዳዲስ ብድሮችን ፍተሻ ማጠናከር፣ ለመሠረተ-ልማት ግንባታ አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ማፈላለግ እንዲሁም የመንግሥትን መሠረተ-ልማት የማቀድ፣ የመንደፍ እና የመገንባት አቅም ማጠናከር በጥናት ባለሙያዎቹ የቀረቡ ተጨማሪ ጥቆማዎች ናቸው። የቻይና የፋይናንስ ተቋማት በወገናቸው የሚሰጡት ገንዘብ ከተበዳሪ አገሮች የዕድገት መርኅ እና ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች ጋር ማጣጣም ይገባቸዋል።

እሸቴ በቀለ 

ነጋሽ መሐመድ