1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማንደሪን ተናጋሪዎች ተፈላጊነት አሻቅቧል

ዓርብ፣ ጥር 19 2009

በኢትዮጵያ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ቻይናውያን የሀገራቸውን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ኢትዮጵያዊያን ሲያገኙ ይደማማሉ፡፡ ብዙዎቹ አፍ የፈቱበትን ቋንቋ ብቻ ይዘው ባህር የተሻገሩ ናቸውና እንዲህ አይነት ኢትዮጵያውያንን ማግኘት እፎይታ ይሰጣቸዋል፡፡ የ26 ዓመቷ ማርታ ታከለ ቁጥራቸው እምብዛም ከሆነው የቻይና ቋንቋ ተናጋሪዎች አንዷ ናት፡፡ 

https://p.dw.com/p/2WWcZ
China Einfluss in Afrika Baustelle in Addis Abeba Äthiopien
ምስል Getty Images

የቻይና ቋንቋ ቱርጁማኖች

ማርታን ያሻትን በቋንቋው እንድትናገር ጋበዝኳት፡፡ ንግግሯን ለዶይቸ ቨለ የቻይና ክፍል ባልደረቦች አሰማኋቸው፡፡ የተናረገችውን በትክክል ተረድተው ትርጉሙን ነገሩኝ፡፡ ማንነቷን ማስተዋወቋን፤ የቻይና ስም እንዳላት መግለጿን፤ ቻይናንና ቻይናዎችን እንደምትወድ መናገሯን ተረጉሙልኝ፡፡  ቅላጼዋ የውጭ ሀገር ሰው መሆኗን ከማሳበቁ በቀር የምትናገረው የማንደሪን ቋንቋ መሆኑን እና “ጥሩ ተናጋሪ”ም እንደሆነችም ጭምር መሰክሩልኝ፡፡

ማንደሪን የቻይና ይፋዊ ቋንቋ ነው፡፡ ቴሌቪዥኑ፣ ሬድዮው እና ሌላውም ዜና ማሰራጫ የሚጠቀመው ይህንኑ ቋንቋ በመሆኑ “ሁሉም ቻይናዊ ሊያውቀው ግድ የሚለው ቋንቋ ነው” ይባላል፡፡ በበርካታ ሀገራት ባሉ ህዝቦች በመነገር እንግሊዘኛ ቋንቋ የመሪነት ቦታው ላይ ቢቀመጥም በአፍ መፍቻ ቋንቋነት ብዙ ሰው የሚናገረው ግን የቻይናው ማንደሪን ነው፡፡ መቀመጫውን በጀርመን ሀመቡርግ ያደረገው የምርምር ተቋም ስታቲስታ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ወደ አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በማንደሪን ቋንቋ አፋቸውን ፈትተዋል፡፡ በአንጻሩ እንግሊዘኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሆኑ ሰዎች 375 ሚሊዮን ብቻ ናቸው፡፡ 

የማንደሪን ሀ..

ኢትዮጵያዊቷ ማርታ አዲስ አበባ ላይ ተቀምጣ ከሩቅ ምስራቁ ቋንቋ ጋር የተዋወቀችው ገና የ18 ዓመት ወጣት እያለች ነበር፡፡ ያኔ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ በጎን የቻይና ምግብ ቤት ውስጥ የመስራት ዕድል ታገኛለች፡፡ ቻይናዎች የሚናገሩትን ቋንቋ መማር ለስራዋ ጠቃሚ እንደሆነ ለመገንዘብ ብዙ መቆየት አላስፈለጋትም፡፡

China Investment Afrika Äthiopien - Adama toll road Arbeiter
ምስል AFP/Getty Images

“በእኛ 2000 ዓ.ም ነበረ፡፡ ቦሌ መድኃኒያለም አካባቢ የቻይና ምግብ ቤት ከቻይናውያን ጋር ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ ስድስት ወር ከሰራሁ በኋላ ደግሞ ደምበል ላይ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ነበር እዚያ ገባሁ፡፡ የሶስት ወር ኮርስ ነበር፡፡ ጄሪ የምትባል ቻይናዊት ኮርሱን ትሰጥ ነበር፡፡ እርሱን ኮርስ ወሰድሁ፡፡ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ዓመት እዚያው ቻይና ምግብ ቤት እሰራ ነበር፡፡ ከዚያ ቋንቋዬን አዚያው እያዳበርኩ መጣሁ ማለት ነው” ትላለች ከማንደሪን ቋንቋ ጋር ያላት ተግባቦት መቼ እንደጀመረ ስታስረዳ፡፡

የዛሬ ሰባት ዓመት የቋንቋ ትምህርቷን ስትማር አብረዋት የነበሩት ሃያ የማይሞሉ ተማሪዎች እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡ አብዛኞቹም እንደእርሷው ከቻይናውያን ጋር የሚሰሩና ቋንቋቸውን ለማዳበር የመጡ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ቻይናዊቷ ጄሪ ከኢትዮጵያዊ ባልደረባዋ ጋር የጀመረችው ይህ ትምህርት ቤት ግን ብዙም አልተራመደም፡፡ በአዳዲስ ተማሪዎች እጦት ተዘጋ፡፡

ፍላጎት እና አቅርቦት

ዓመታት አልፎ ግን ቋንቋውን በልምድ ያዳበሩት ሳይቀሩ በባትሪ የሚፈለጉበት ጊዜ መጣ፡፡ ማንደሪንን በመደበኛ ትምህርት ቤት ያጠኑት ደግሞ በቀን እስከ 700 ብር እየተከፈላቸው የማስተርጎም ስራ ይደራረብባቸው ገባ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቻይናውያን ቁጥር መጨመር ነው፡፡ የቻይናውያን መብዛት ተከትሎ የሚሳተፉበት የስራ መስክም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በኢትዮጵያ በብዝሃኑ ዘንድ በመንገድ ስራ ይታወቁ የነበሩት ቻይናዎች ከግድብ ግንባታ እስከ ከቴሌኮምዩኒኬሽን አውታር ተከላ፣ ከባቡር ሃዲድ ዝርጋታ እስከ ኢንዱስትሪ መንደር ምስረታ፣ ከፋብሪካ ማቆም እስከ ከብሔራዊ ስቴድየም እነጻ ድረስ በበርካታ ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቻይናውያን ቁጥር አስመልክቶ ጥርት ያለ መረጃ የለም፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ሰዎች የሰጧቸው ቃለ ምልልሶች የሚያመለክቱት የዛሬ ሦስት ዓመት 20 ሺህ ገደማ የነበሩት ቻይናውያን በጎርጎሮሳዊው 2016 በሦስት እጥፍ መጨመራቸውን ነው፡፡ ከቻይናውያን ጋር አብሮ የሚሰራው እና ቋንቋቸውን ድንቅፍ ሳይለው የሚያወርደው ዳዊት ንጉሴም የቻይናውያን ቁጥር ማደግን ታዝቧል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአስተርጓሚም ሆነ የማንደሪን ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን የማግኘት ፍላጎት ማሻቀቡንም ተመልክቷል፡፡

ሰሜን ምስራቅ ቻይና ቲያንጂን ግዛት ለአምስት ዓመት ትምህርቱን ተከታተሎ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ዳዊት ቀደም ሲል የነበረው ከአሁኑ ጋር ያነጻጽራል፡፡ አሁን ያለው ፍላጎት ከአቅርቦት ጋር አልተመጣጠነም ባይ ነው፡፡

Äthiopien Stadtbahn Probefahrt in Addis Abeba
ምስል DW/Yohannes G. Egiziabher

“ከፍላጎቱ ጋር ቁጥሩ አልደረሰም፡፡ ገና ነው፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ ቁጥር በጣም እየጨመረ ስለመጣ ብዙ እየተፈለገ ነው፡፡ ቁጥሩም በጣም ያንሳል፡፡ ከበፊቱ ጋር ስናወዳድረው አሁን የተማሪው ብዛት ጨምሯል፡፡ በፊት በእኛ ጊዜ የነበረው ቻይና ሄደው የመጡ ተማሪዎች ናቸው ወደዚህ ሲመጡ የሚበልጠው ደምወዝ እና ገቢ አስተርጓሚ ሆኖ መስራት ስለሆነ አብዛኛው ሰው ወደ አስተርጓሚነት አዘነበለ፡፡ አሁን ግን በከተማችን ላይ በዩኒቨርስቲ እየተሰጠ ነው፡፡ በቋንቋ ትምህርት ቤቶችም እየተሰጠ ነው፡፡ የተማሪዎቹ ቁጥር አሁን እየበዛ ነው” ይላል ቀደምት ዓመታትን ከዘንድሮ ጋር አወዳድሮ፡፡

ማንደሪን ዩኒቨርስቲ ገባ

በእርግጥም ማንደሪን የ67 ዓመት አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይቀር ሰተት ብሎ ገብቷል፡፡ ዩኒቨርስቲው ከአራት ዓመት በፊት ቋንቋውን በመጀመሪያ ዲግሪ ማስተማር ጀምሯል፡፡ ሊያውም በቻይናውያን በሚመራ እና በዕውቁ ቻይናዊ ፈላስፋ ኮንፊሽየስ ስም በተሰየመ ኢንስቲትዩት፡፡ ተቋሙ በዩኒቨርስቲው የሥነ-ስብዕ፣ የቋንቋ፣ ጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኔኬሽን ኮሌጅ ስር ያለ ነው፡፡

ማንደሪን በኮሌጁ የውጭ ቋንቋ እና ሥነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍል ለረጅም ዓመታት ሲሰጣቸው ከቆያቸው እንግሊዘኛ፣ አረብኛ እና ፈረንሳይኛ ጋር ተሰልፏል፡፡ ኮሌጁ እስካሁን ሁለቴ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዓመት ይህንኑ ቋንቋ የሚያጠኑ 80 ተማሪዎች በግቢው አሉ፡፡ የኮሌጁ ዲን የሆኑት ዶ/ር ዘላለም ልየው ማንደሪን የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ሌሎች የውጭ ቋንቋዎች ከሚማሩት ከፍ ያለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

ወደ ኮሌጁ ኃላፊነት ቦታ ከመጡ ገና አንድ ዓመታቸው ብቻ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ዘላለም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማንደሪን ቋንቋ ለማስተማር የወሰነበትን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ፡፡

“የቻይኒዝ ማንደሪን ቋንቋ በእኛ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የአውሮጳ እና የአሜሪካ የኒቨርስቲዎችም ይሰጣል፡፡ በተናጋሪው ቁጥር ብዛትም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ ዋና ዋና ቋንቋዎች ከሚባሉት ውስጥ እንደአንዱ ተወስዶ ይመስለኛል በዚያን ጊዜ እንዲሰጥ የተደረገው፡፡ እንግዲህ በሁለት ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ እኔ የማውቀው በቋንቋነት ደረጃ ያለውን ነው” ይላሉ ዶ/ር ዘላለም፡፡

China Afrika Engagement
ምስል AP

በቻይና መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ኮንፊሽየስ ኢንስቲትዩት ለተማሪዎች የውጭ የትምህርት ዕድል እስከመስጠት የዘለቀ አካሄድን ይከተላል፡፡ የሀገሯን ቋንቋ ለማስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት ያላት የምትምስለው ቻይና በአዲስ አበባ የተለያዩ የቋንቋ ትምህርት ቤቶች ማንደሪን ለሚያጠኑ ተማሪዎች ተመሳሳይ የትምህርት ዕድል እያመቻች ትገኛለች፡፡ በዩኒቨርስቲ እና ቋንቋ ትምህርት ቤቶች ሳትወሰን በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ቋንቋውን ለማሰጠት አቅዳ ነበር፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ለስራ የሚመጡ ቻይናውያንም ሀገራቸውን በግል ጥረታቸው ሲያግዟት ታይተዋል፡፡ አራት ቢሊዮን ብር ገደማ በጀት የተመደበለትን ከድሬዳዋ ደወሌ የሚዘረጋውን አስፋልት መንገድ ለመገንባት ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከመጡ ቻይናውያን መካከል ቼን ሼንግ የተሰኘው ግለሰብ ማንደሪንን በበጎ ፍቃደኝነት ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ “ታታሪው ሚስተር ቼን፡፡ ቻይንኛ መናገር አሁን ይጀምሩ” የሚል ማስታወቂያ አሰርቶ በአደባባይ ለጥፎ አስተዋውቋል፡፡ ድሬዳዋ እምብርት ላይ በሚገኘው ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ከሁለት ዓመት በፊት ይሰጥ የነበረው ትምህርት ወጣቶችን ቢስብም በመደበኛነት አልዘለቀም፡፡

ቅይጥ ቋንቋ 

በድሬዳዋ ከመንገድ ስራው ሌላ የባቡር እና የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ ላይ የተሰማሩ በርካታ ቻይናውያን ቢኖሩም የአስተርጓሚዎች እጥረት እንዳለ በስራው የተሰማሩ ይናገራሉ፡፡ በቻይና ሀገር ቋንቋውን አጥንተው ወደ ድሬዳዋ የመጡት ሁለት ብቻ እንደሆኑና ሌሎቹ በልምድ የሚሰሩ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ቻይና ተምረው የመጡቱ ለአጭር ጊዜ ስራ በሰዓት አንድ ሺህ ብር ሲጠይቁ ቻይናውያኑ ለመክፈል የማያቅማሙት፡፡

እንደ ድሬዳዋ ባለ ከአዲስ አበባ በወጣ ቦታ ለቻይናዎች በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ አስተርጓሚ ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እንደሚከፈለው ማርታም ሆነች ዳዊት ይናገራሉ፡፡ ማርታ ከዓመታት በፊት የቻይና ምግብ ቤት አስተናጋጅነቷን ቀይራ ከሌሎች ቻይናዎች ጋር ለመስራት ስትወስን ቋንቋውን ተመልክተው 4‚500 ብር ደመወዝ እንደቆረጡላት ትናገራለች፡፡ ቋንቋ መማሯ እንደጠቀማትትገልጻለች፡፡ ቋንቋውን ለሚማሩ ሰዎች ሰፊ የስራ ዕድል እንዳለ እና በአንጻራዊነት ጥሩ ክፍያ እንደሚያስገኝ ሁሉም ይስማማሉ፡፡ እስከዚያው ግን ክፍተቱን የሚሞሉት በልምድ ቋንቋውን የቻሉቱ ናቸው፡፡

China Einfluss in Afrika Baustelle in Addis Ababa Äthiopien
ምስል Getty Images

 ከቻይናውያን ጋር የሚሰሩ በርካታ ኢትዮያውያን ግን የራሳቸውን ቅይጥ ቋንቋ ፈጥረው መነጋገር ከጀመሩ ዓመታት ነጎዱ፡፡ ማርታ እና ዳዊት ስለዚህ ጉዳይ ሲነሳባቸው ሳቅ ይቀድማቸዋል፡፡ ዳዊት ይህ አይነቱ ቋንቋ ለቱርጁማኖች ሳይቀር ፈተና እንደሆነ ምሳሌ ጠቅሶ ይገልጻል፤፤ 

“አንዳንዴ በመደበኛነት ቻይንኛን ሲያስተርጎም የቆየ ሰው ሌላ ከተማ ላይ ተወስደውና እዚያ ያሉት የክፍለ ሀገር ሰዎች በዚያ አካባቢ በሚናገሩት ቋንቋ ቻይናዊው ሲግባባ እርሱ መሃል ላይ ገብቶ ላይረዳ ሁሉ ይችላል፡፡ እንግዳ ይሆናል፡፡ እኔ አንድ ጊዜ ቱርኮች ጋር እሰራ ነበር፡፡ ቱርኮች የቻይና ማሽን ገዝተው ቻይናውያን ነበሩ መጥተው የሚገጥሙት፡፡ እዚያ ድርጅቱ ውስጥ ስናወራ ብታይ በጣም የተቀላቀለ ነው፡፡ ቱርክኛ፣ እንግሊዘኛ፣ አማርኛ እና ቻይንኛ አለ፡፡ አራቱንም ቋንቋ ደበላልቀን ነበር የምንግባባው” ይላል ሳቅ ባጀበው ድምጽ ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ 

አዜብ ታደሰ