1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ 100ኛ ዓመት

ሰኞ፣ ሰኔ 28 2013

ከቼን ሌላ ማን ሊሆን ይችላል።በሌሉበት ጠቅላይ ፀኃፊ ሆነዉ ተመረጡ።የተለያዩ ትናንሽ ፓርቲዎችን አሰባስቦ «ኮርማ» ወይም ግንባር ቀደም የሆነዉ ፓርቲ ሲመሰረት 900 አባላት ነበሩት።በ1925 ለአራተኛዉ ጉባኤ ሲቀመጥ ግን የአባላቱ ቁጥር ወደ 2428 ተንቻርሮ ነበር።የፓርቲዉ የሐሳብ አፍላቂ፣መስራችና የመጀመሪያ መሪ ቼን ግን አብረዉ አልዘለቁም

https://p.dw.com/p/3w4FK
China 100. Jahrestag Kommunistische Partei | Peking
ምስል Tingshu Wang/REUTERS

ቻይና፣ ከዕርሻና ጨርቃጨርቅ አምራችነት ወደ ዓለም 2ኛ ሐብታምነት

ከሐብታም፣ ባለስልጣናት ቤተሰብ ተወለዱ። በልጅነታቸዉ ከሐብታምነት ይበልጥ የድሆች ተቆርቋሪነት፣ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት ፣ከምሁራዊነት ይብስ አመፀኝነት የሚጫጫናቸዉ ነበሩ።ሲያድጉ እዉቅ ፕሮፌሰር፣ፈላስፋና ፖለቲከኛ ወጣታቸዉ።ቼን ቱህስዩ።በ1915 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ማሳተም የጀመሩት «ወጣት» ያሉት ጋዜጣ የሌኒኑ ኢስካራ አቻ፣ እሳቸዉን የቻይና ሌኒን ያሰኛል ብሎ ያሰበ አልነበረም።ግን ሰዉዬዉ የሚመስሉትን አያደርጉም፣ የሚያደርጉትን አይመስሉም።በ1921 ከጥቂት ጓደኞቻቸዉ ጋር የመሰረቱት የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ ብዙ ጦርነቶችን ድል ያደረገ፣ 1,4 ቢሊዮን ሕዝብን የሚያንደላቅቅ፣ ድሕነትን የሚደፈልቅ፣ ዓለምን የሚያንቀጠቅጥ፣ የዘንድሮ መሪዉ እንዳሉት «የብረት አጥር» የሚሸመጥጥ ይሆናል ብሎ የገመተ ከነበረ በርግጥ እሱ እሳቸዉን ሆነ።የፓርቲዉ መቶኛ ዓመት መነሻ፣ የመስራቾቹ ማንነት ማጣቀሻ፣ ገድል-ድሉ መድረሻችን ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
                                                                        
ያቺን ሰፊ፣ታሪካዊ፣ ሥልጡን፣ ኃያል ሐገር ከ1644 ጀምሮ የገዛዉ የቂንግ ሥርወ-መንግስት በ19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ከዉጪም ከዉስጥም የገጠመዉ ጦርነትና ግጭት ወደ ፍፃሜዉ እየገፋዉ ነበር።በተለይ በ1894 የተጀመረዉ የመጀመሪያዉ የሶኖ-ጃፓን ጦርነት፣ በማከታተል ራስዋ ጃፓን፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጀርመን፣ ኢጣሊያ፣ ሩሲያና ኦስትሮ-ሐናጋሪና ለስምት ሆነዉ በቻይና ላይ የከፈቱት ጦርነት ወትሮም ለሞቱ የሚያጣጥረዉን የቂንግ ሥርወ-መንግስት በ1912 ወደቀብሩ ነዱት።ተደጋጋሚዉ ሽንፈት በኩሩዉ ቻይናዊ ላይ ያደረሰዉ ሐፍረት፣ ድሕነት፣የኑሮ መቃወስና ቁጭት የዘመኑን ወጣት፣ የተማረ ቻይናዊ አዲስ ሥርዓት እንዲያማትር ሳያስገድደዉ አልቀረም።እንደ ሐብታም፣ የባለስልጣን ልጅ ኮንፉሺንዝም በተሰኘዉ የቻይና ባሕላዊ ትምሕርት ተኮትኩቶ ያደገዉ ወጣት ቼን ቱህስዩ ዘመናዊዉን ትምሕርት ጃፓን ዩኒቨርሲዎች ቀስሞ ሲመለስ እንደ እድሜ-ዕዉቀት አቻዎቹ ፖለቲካን ማነፍነፍ፣ ሐገሩ ከዉርደት፣ ሐፍረት የምትወጣ የምትለወጥበትን ሥልት ማማተር የጀመረዉም ያኔ ነበር።ቼን የሱና የብጤዎቹን አስተሳሰብ ለሕዝብ ለማድረስ በ1915 ወጣት፣ (በዓመቱ ሻንጋሐይ ላይ  አዲሱ ወጣት) ያለዉን ጋዜጣም ማሳተም ጀመረ።
የቼንና የጓደኞቹ አስተሳሰብ ሐገር-ሕዝባቸዉን ለዉድቀትና መከራ ዳርጓል ያሉትን ነባሩን የቻይናን ፖለቲካዊ ሥርዓት፣ የአኗኗር ይትባሐልና ባሕልን ከመለወጥ ባለፍ የማርክሲስት አስተምሕሮ አራማጆች መሆናቸዉ በግልፅ አይታወቅም ነበር።በጊዜ ሒደት ግን የሩሲያዉ አብዮት መሪ ቭላድሚር ኤሊየች ሌኒን በ1900 ለመጀመሪያ ጊዜ ላይፕሲሽ-ጀርመን ላይ ያሳተማት ኢስካር (ብልጭታ) ለሩሲያዎች እንደነበረች ሁሉ፣ የቼኗ አዲሱ ወጣት የቻይኖች ሆነች።በ1917 ሞስኮ ላይ የተቀጣጠለዉ የቦልሸቪኮች አብዮት ያኔ፣ የፔኪንግ ዩኒቨርስቲ መምሕርና ዲን (ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ) የነበሩትን የቼን እና የሊ ታዦአን ቀልብ ሳይስብ አልቀረም።ቼን በዚያዉ ዓመት በፃፉት መጣጥፍ «ከዘመናችን ጋር የሚጣጣም አዲስ ሐገረ-መንግስት መመስረትና አዲስ ማሕበረሰብ መገንባት ከፈለግን» አሉ «የምዕራባዉያንን የአኗኗር ስልትን የሚከተል ማሕበረሰብና ሐገር የሚገነባበትን መሰረት ከዉጪ ማስገባት አለብን።» 
ተንታኞች እንደሚሉት ቼን «ምዕራብ ያሉት ሥርዓት» ዛሬ የምናቀዉን በፖለቲካ ዉድድርና በነፃ ገበያ ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሳይሆን ሁሉም ዜጋ እኩል  የሚወከል፣ የሚኖር፣ የሚጠቀምበት ሥርዓት ማለተቻዉ ነበር።ሶሻሊዝም መሰል።«ሶሻሊዝም፣ የፖለቲካ አብዮትን የሚከተል ማሕበራዊ አብዮት ነዉ፣ ዓላማዉም የበላይና የበታችነትና ጭቆናን በሙሉ ማጥፋት ነዉ።» ፃፉ- ቼን። «የቻይናዉ ሌኒን የተባሉትም» ያኔ ነበር።ቼን እና ሊ እንደነሱዉ ሁሉ ማርክሲዝንም ሲያጠኑ ከነበሩ ሌሎች የአስተሳሰብ ተጋሪዎቻቸዉ ጋር ሆነዉ፣ በሩሲያ ቦልሼቪኮች ድጋፍ የዛሬዉን ግዙፍ ፓርቲ መሰረቱ።የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ።CCP
                                                                                               
ሻንግሐይ-ኃምሌ 1 1921።የፓርቲዉ መሪ ከቼን ሌላ ማን ሊሆን ይችላል።በሌሉበት ጠቅላይ ፀኃፊ ሆነዉ ተመረጡ።የተለያዩ ትናንሽ ፓርቲዎችን አሰባስቦ «ኮርማ» ወይም ግንባር ቀደም የሆነዉ ፓርቲ ሲመሰረት 900 አባላት ነበሩት።በ1925 ለአራተኛዉ ጉባኤ ሲቀመጥ ግን የአባላቱ ቁጥር ወደ 2428 ተንቻርሮ ነበር።የፓርቲዉ የሐሳብ አፍላቂ፣መስራችና የመጀመሪያ መሪ ቼን ግን አብረዉ አልዘለቁም።በ1929 ተባረሩ።ፓርቲዉ ግን በእነ ሊ፣ በነ ማኦ ዜዱንግ መሪነት የትልቂቱን ሐገር ፖለቲካ፣ ማሕበረ-ምጣኔ ሐብታዊ ሒደት ባዲስ ጎዳና ማሾሩን ቀጠለ።ከ1927 ጀምሮ ኮሙንታግ ከተሰኘዉ ከቻይና ብሔረተኖች፣ አድሐሪ ከሚላቸዉ የጦር አበጋዞች፣ ቀልባሽ ካላቸዉ አባላቱም ጋር አቅሙ ሲጠረቃ ተዋግቷል።አቅሙ ሲዳከም አብሯል።የጃፓኖችን ወረራ፣ የአሜሪካኖች ሴራ፣ የብሪታንያዎችን ሻጥር ተራ በተራ እየበጣጠሰ፣ ሁለተኛዉን የዓለም ጦርነት ተቋቁሟል።በየጦርነቱ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አባላቱን ሰዉቷል። በ1945 በጦር አዋጊነታቸዉ፣ በፖለቲካ መሪነታቸዉም ስም ዝና ያተረፉት ማኦ ዜዱንጉ የፓርቲዉን የሊቀመንበርነት ስልጣን ጠቅልለዉ ያዙ።ጥቅምት 1 1949።የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ መመሥረቷን በይፋ አወጁ።
                                                                                              
ታይናንሜን አደባባይ።ፔኪንግ።በሕዝብ ባሕር ተጥለቀለቀች።ቀይ ጥብጣብ ባጠለቀ፣ ቀይ ባንዲራ ባነገበ፣ ቀይ አበባ በሚያዉለበልብ፣ በደስታ በሚቦርቅ ሕዝብ ተዋጠች።ዓለም ሁለተናኛዉን ታላቅ ኮሚስታዊት ሐገር ተረከበ።ቀጣዩ ጉዞ ግን ከፓርቲዉ ምሥራታ እስከ ሪፐብሊክ ምሥረታ ከነበረዉም ከባድ፣ዉስብስብ፣ምናልባት የመቶ ሺዎችን ሕይወትም ያስገበረ ነበር።ማኦና ተከታዮቻቸዉ «የወረቀት ላይ ነብር  ኢፕሪያሊስት» ከሚሏቸዉ ምዕራባዉያን በተለይም ከዩናይትድ ስቴትስና ከብሪታንያ  ጋር አዲሲቱ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ የገጠመችዉ ተዘዋዋሪ ጦርነት ከኮሪያ ልሳነ-ምድር እስከ ሕንድ ጠረፍ፣ ከቬትናም እስከ ሆንግ ኮንግ ድረስ የብዙ ሺዎችን ሕይወት ቀጭቷል።ቢሊዮነ ቢሊዮናት ዶላር አክስሯል።በ1972 የያኔዉ የዩናያትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት እስከዚያ ዘመን ድረስ የተካረረዉን የሁለቱን ሐገራት ግጭት፣ቁርቁስ፣ ሽኩቻ ለማርገብ የመጀመሪያዉ እርምጃ ነበር።
«ባለፉት 3 ዓመታት በተደጋጋሚ እንደጠቀስኩት፣ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና እና 750 ሚሊዮን ሕዝቧ ሳይሳተፍበት በዓለም ላይ የተረጋጋና ዘላቂ ሠላም ሊኖር አይቻልም።ለዚሕም ነዉ፣ በሁለቱ ሐገሮቻችን መካከል የበለጠ መደበኛ ግንኙነት የሚመሰረትበት በር ለመክፈት በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ ጥረቶችን ሳደርግ የቆየሁት።ከዚሕ ግብ ለመድረስ፣ከጠቅላይ ሚንስትር ቹንላይ ጋር ዉይይት የማደርግበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ  የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪዬን ኪሲንጀሪን ወደ ፔኪንግ መልሼ ልኬቸዋለሁ።»
የዩናይትድ ስቴትስና የኮሚንስት ቻይና መሪዎች አንዳቸዉ የሌላቸዉን ርዕሠ-ከተሞች መጎብኘትና መወያያታቸዉ የሁለቱን ኑክሌር የታጠቁ ሐገራትን ጠብና ቁርቁስ ለማርገብ በጅጉ ረድቷል።ሙሉ በሙሉ ግን አላስቀረዉም።ቻይና ከ1978 ጀምሮ ገቢር ያደረገችዉ የምጣኔ ሐበት መርሕ እስከዚያ ዘመን ድረስ  «ኃላቀር የገበሬዎች ምድር» የምትባለዉን ትልቅ ሐገር ምጣኔ ሐብት ሽቅብ ሲያጎነዉ ደግሞ የኮሚንስታዊቱ ቻይናና የአሜሪካ መራሹ የካፒታሊስት ዓለም ጠብ ወደ ምጣኔ ሐብታዊ ጦርነት ተሸጋግሯል።ዩናይትድ ስቴትስ ከነባሮቹ የአዉሮጳ ወዳጆችዋ በተጨማሪ ከእስያ ጃፓንን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ ሕንድን፣ ፊሊፒንስን፣ ከኦሺኒያ አዉስትራሊያን የመሳሰሉ ቻይናን የሚጎራበቱና ለቻይና የሚቀርቡ መንግሥታትን  አስተባብራ በቤጂንግ ላይ ጫና ለማሳረፍ የጀመረችዉ ዘመቻ ቻይናም እነ ሰሜን ኮሪያን አስጠግታ፣ ከነሩሲያ ጋር ተወዳጅታ ለአፀፋ ዘመቻ እንድትዘጋጅ አድርጓታል።ከዓለም የመጀመሪያዉንና ሁለተኛዉን ምጣኔ ሐብት የሚቆጣጠሩት ሁለቱ ሐብታም ኃያል መንግስታት ከግብር ማጭበርበር  እስከ ኮሮና ተሕዋሲ ስርጭት፣ ደሴቶችን ከመቆጣጠር እስከ ገበያ ስፍራ ሽሚያ የገጠሙት ጠብ፣ቁርቁስ መባባሱ ኒክሰን ከ49 ዓመት በፊት የዓለም «የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም» ያሉት ዛሬም ለዓለም ሕዝብ ገና ከሕልም አለማለፉን የሚያረጋግጥ አስጊም ነዉ።የቻይና ኮሚንስት ፓርቲ የተመሰረተበት 100ኛ ዓመት በዓል ባለፈዉ ሐሙስ ሲከበር የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ ያስተላለፉት መልዕክትም ከዕርቅ፣ድርድር መለሳለስ ይልቅ ፍጥጫ ሥጋቱ ለመቀጠሉ ዋቢ ነዉ።
                                                                                                     
«በዚያዉ ልክ የቻይና ሕዝብ ማንኛዉም የዉጪ ኃይል እንዲያስፈራራዉ፣ እንዲጨቁነዉ ወይም በባርነት እንዲረግጠዉ በፍፁም አይፈቅድም።ይሕን ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛዉም ኃይል በ1.4 ቢሊዮን የቻይና ሕዝብ ከተገነባዉ የብረት አጥር ጋር እየተላተመ ጭንቅላቱ ይቀነጠሳል ወይም በደም አበላ ይታጠባል።»
ፕሬዝደንት ኒክሰን ቻይናን ከጎበኙ ከጥቂት አመታት በኋላ የኮሚንስት ፓርቲዉን የመሪነት ሥልጣን የያዙን ዳን ዢዎፒንግ በ1978 የቀመሩት የቅይጥ ኤኮኖሚ መርሕ የቻይናን ምጣኔ ሐብት በጅጉ አሳድጎታል።ለዉጡ ሲጀመር የቻይናዊዉ የነብስ ወከፍ ገቢ 153 ዶላር ነበር።ዘንድሮ 10 ሺሕ 500 ዶላር ደርሷል።የእርሻ፣ እልፍ ካለ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ሐገር የነበረችዉ ቻይና ዛሬ የተወሳሰበዉ ኮምፒዉተር፣ ሕዋን ሰንጥቆ የሚከንፍ መንኮራኩር፣የግዙፍ አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ አምራች ሐገር ናት።አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቷ GDP 17 ትሪሊዮን ይጠጋል።የቻይና መንግስት የሚቆጣጠረዉ ኢንዱስትሪ ብቻ ከ78 ትሪሊዮን ይበልጣል።ከሁሉም በላይ እንደቻይና የረጅም ጊዜ የነፃነት ታሪክ አለን የሚሉት ሐገራት ገዢዎች ሕዝባቸዉን ቁል ቁል እየደፈቁ ሲጋልቡት ያ ኮሚኒስት ፓርቲ  የሚመራት ቻይና ከ1978 ወዲሕ 800 ሚሊዮን ሕዝቧን ከድሕነት አዉጥታ የመካከለኛ መደብ ድልቅቅ ሕይወት እንዲመራ አድርጋለች።
የአዉሮጳ ኮሚስቶች ሲፍረከረኩ፣ የሩሲያ ቦልሸቪኮች ተሽቀንጥረዉ ሲወድቁ፣ አፍሪቃ ላይ አቆጥቁጠዉ የነበሩት ኮሚንስቶች ሕዝብ ሲያተረማምሱ የቻይኖቹ በ1949 የያዘዉን ሥልጣን ዛሬም ፈጥርቆ እንደያዘ ነዉ።ሺ ጂንፒንግ ወደፊትም ይቀጥላል ባይ ናቸዉ።ሌላዉን ግን አልነካንም፣ ዛሬም ወደፊትም አንነካምም።
«እኛ ቻይኖች ፍትሕን የምንጠብቅ ሕዝቦች ነን፣ ለየትኛዉም ኃይልና ሥልጣን እንበገረም።የቻይና ሕዝብ ታላቅ ክብር፣ ኩራትና በራስመተማመን  የሚሰማዉ ሕዝብ ነዉ።ከዚሕ ቀደም፣ አሁንም ሆነ ወደፊት የሌሎች ሐገራት ሕዝብን ፈፅሞ አስፈራርተን፣ ጨቁነን ወይም በባርነት ገዝተን አናዉቅም።አሁንም ወደፊትም አናደርገዉምም።» 
የዛሬ መቶ አመት እነ ቼን ኢሚንት ነበሩ።900።ዛሬ እነ ሺ ጂንፒንግ የሚመሩት ፓርቲ 95 ሚሊዮን አባላት አሉት።በአባላት ብዛት ከዓለም ከሕንዱ ባሕራቲያ ጄናታን ፓርቲ ቀጥሎ ሁለተኛዉ ነዉ።1.4 ቢሊዮን ቻይናዊ ሌላ አማራጭ የለዉም።ወይዘሮዋ ግን ደስተኛ ናቸዉ።«እኛ ቻይናዉያን አሁን የምንመራዉ አስደሳች ኑሮ የተጀመረዉ እዚሕ ነዉ።» 
ታይናንሚን አደባባይ።ብዙ ደም ፈሶበታልም።ቻይናዊዉ ባደባባይ «ደስተኛ አይደለሁም» ሊል አይችልም።ከዚያ አንጋፋ ፓርቲ ሌላ፣ ሌላ አማራጭ ሊኖረዉ የሞከረ አይደለም ያሰበም እንዳሰበ ሊያንቀላፋ ይችላል።

China Peking | Feier zum 100. Geburstag der Gründung der Kommunistischen Partei Chinas
ምስል Thomas Peter/REUTERS
China Peking | Feier zum 100. Geburstag der Gründung der Kommunistischen Partei Chinas
ምስል Thomas Peter/REUTERS
100 Jahre Kommunistische Partei Chinas
ምስል Thomas Peter/Reuters
Der Tag in Bildern | Shanghai, China |  100 Jahre Kommunistische Partei
ምስል Hector Retamal/AFP

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ