የኅዳር 14 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ኅዳር 14 2013እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚፎካከሩበት የእግር ኳስ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኬንያ ቡድን ተሸንፏል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ዳግም የመሪነቱን መንበር ለመረከብ ጫፍ ደርሷል። በትናንትናው ግጥሚያ በጨዋታ በልጦ ተጨማሪ ነጥብ አስመዝግቧል። አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት አርሰናል በበኩሉ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ነጥብ ተጋርቶ መውጣት ችሏል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙይንሽን በመሪነት እየገሰገሰ ነው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ እግር በእግር እየተከታተለው ነው።
ትናንት በተጀመረው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ተጨዋቾች በሚፎካከሩበት የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (CECAFA)የእግር ኳስ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኬንያ አቻው 3 ለ0 ተሸንፏል። ውድድሩ ትናንት የተጀመረው በታንዛኒያ አስተናጋጅነት አሩሻ ከተማ ውስጥ ነበር። ኢትዮጵያ በመቀጠል ከነገ ወዲያ የምትጫወተው ከሱዳን ጋር ይኾናል። በምድብ ሐ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ኬንያ ይገኛሉ።አዘጋጇ ሀገር ታንዛኒያ በምትገንበት ምድብ ሀ ሶማሊያ እና ጅቡቲ ይፎካከራሉ። ምድቡ ለ ላይ ደግሞ፦ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ተሳታፊ ናቸው። በሦስት ምድቦች በአጠቃላይ 39 ውድድሮች ይከናወናሉ።ትናንት የተጀመረው ውድድር የሚጠናቀቀው ኅዳር 27 ቀን ነው።
የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ፕሬዚደንት አኅመድ አኅመድ ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ጉዳይ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን (FIFA) የአምስት ዓመት እገዳ ተጣለባቸው። የፊፋ የሥነ ምግባር ኮሚቴ ውሳኔውን ያሳለፈው የእግር ኳስ ባለሥልጣናት ምርጫ ለማድረግ በተቃረበበት ወቅት ነው። ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን፦ ዓርብ መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ከሚያከናውነው አጠቃላይ ምርጫ ቀደም ብሎም እጩ ተፎካካሪዎች ላይ ማጣራት እንዲደረግ ተጠይቋል።
ቀድሞ የማዳጋስካር መንግሥት ውስጥ በሚንስተርነት ያገለገሉት የካፍ ፕሬዚደንት ከሦስት ዓመት በፊት የአፍሪቃ እግር ኳስን እንዲመሩ በፕሬዚደንትነት ከመመረጣቸው ቀደም ሲል ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ስማቸው ይነሳል። ከዛሬ 10 ዓመት በፊት አኅመድ አኅመድ ከኳታር አንድ ባለሥልጣን የገንዘብ ሥጦታ ከተሰጣቸው ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ይነገራል። አኅመድ ካይሮ በሚገኘው የካፍ መቀመጫ የበላይ በኾኑበት ወቅት ቀደም ሲል ተሠራ ለተባለው ስኅተት ተጠያቂ ኾነው ፓሪስ ውስጥ በፈረንሳይ ፖሊስ ታስረው ምርመራ ተደርጎባቸዋል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበራት ፌዴሬሽን፦ «አኅመድ ስጦታቸውን እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን በማቅረብ፤ ብሎም የተመሰበ ገንዘብን በቅጡ ባለማስተዳደር እንዲሁም እንደ ካፍ ፕሬዚደንትነታቸው ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ለሞያቸው ያላቸውን ታማኝነት ጥሰዋል» ሲል ከሷል። አኅመድ 200,000 የስዊስ ፍራንክ ማለትም ($220,000) ዶላር እንዲቀጡም ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። ላለፉት 3 ዓመታት ካፍን በበላይነት ሲመሩ የቆዩት የ60 ዓመቱ አኅመድ አኅመድ ፓሪስ ውስጥ ከሚገኝ ቅምጥል ሆቴል በቊጥጥር ስር ውለው የነበሩት ባለፈው ዓመት በዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ዋዜማ ላይ ነበር።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ሊቨርፑል በጨዋታ ልቆ በታየበት ግጥሚያ ተፎካካሪው ሌስተር ሲቲን 3 ለ0 ድል አድርጓል። ለሊቨርፑል ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው የላይስተር ሲቲው ጆኒ ኤቫንስ በ21ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ጆኒ ወደ ግብ የተላከችውን ኳስ በጭንቅላት ወደ ውጪ ለማውጣት ቢሞክርም ኳሷ ያረፈችው ግን የገዛ ቡድኑ መረብ ላይ ነበር። በ41ኛው ደቂቃ ላይ ዲዬጎ ጆታ ኹለተኛውን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ዲዬጎ ጆታ በሊቨርፑል ቡድን ውስጥ ድንቅ ብቃት በማሳየት በከፍተኛ ኹኔታ ከሚጠበቊ ተጨዋቾች መካከል ይመደባል። የትናንቱን ድል በተመለከተ ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተጨዋቾቻቸውን አድንቀዋል። ተጨዋቾቹ ባሳዩት ድንቅ ብቃት «እጅግ» መደሰታቸውንም ገልጠዋል። የሊቨርፑሉ ወሳኝ ተከላካይ ቪርጂል ቫን ጂክ፣ ጆዜ ጎሜዝ፣ ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ፣ ጆርዳን ሔንደርሰን፣ ቲያጎ አልካንትራ፣ ዤርዳን ሻኪሪ እና አሌክስኦክሳሌድ ቻምቤርሊን በጉዳት ባልተሰለፉበት ጨዋታ ከዋነኛ ተፎካካሪዎቹ አንዱ የኾነው ላይስተር ሲቲን በሰፋ ልዩነት ማሸነፉ ቡድኑን ያለውን ጥንካሬ ያሳያል። አርሰናል ኒኮላስ ፔፔን በ51ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ባጣበት ግጥሚያ ትናንት ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል።
ሊድስ ዩናይትድ በትናንቱ ጨዋታ ብልጫ ዐሳይቶ ነበር። በዚህም መሠረት ቶትንሃም ሆትስፐር የደረጃ ሰንጠረዡን በ20 ነጥብ በአንደኛ ደረጃ ይመራል። ቅዳሜ ዕለት ኒውካስትል ዩናይትድን 2 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ በ18 ነጥብ ሦስተኛ ነው። ላይስተር ሲቲ በተመሳሳይ 18 ነጥብ ኾኖም በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ይዟል። ላይስተር ሲቲን ያሸነፈው ሊቨርፑል ከመሪው ቶትንሃም ጋር በተመሳሳይ ነጥብ ግን ደግሞ በግብ ክፍያ ተበልጦ የኾለተኛ ደረጃ መያዝ ችሏል።
ሊቨርፑል ለሻምፒዮስ ሊግ ግጥሚያ ከነገ በስትያ ምሽት ላይ የጣሊያኑ አታላንታ ቤርጋሞን ይገጥማል። በተመሳሳይ ሰአት የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም ከዴንማርኩ ሚድቲላንድ ጋር ይጫወታል። የፖርቹጋሉ ፖርቶ እና የፈረንሳዩ ማርሴ፣ የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከጣልያኑ ኢንተር ሚላን፤ የራሺያው ሎኮሞቲቭ ሞስኮ ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ የጀርመኑ ባየር ሙይንሽን ከኦስትሪያው ዛልስቡርግ፣ የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ከግሪኩ ፕሬውስ፣ ሌላናው የጀርመን ቡድን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከዩክሬኑ ሻካታር ዶኒዬትስክ ጋር የሚጫወቱት ረቡዕ ማታ በተመሳሳይ ሰአት ነው።
በነገው ዕለት ደግሞ፦ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከቤልጂየሙ ክሉብ ብሩዥ፣ የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቱርኩ ባሳክሽዬር፣ የፈረንሳዩ ፓሪ ሴንጄርሜን ከጀርመኑ ላይፕትሲሽ፣ የስፔኑ ባርሴሎና ከዩክሬኑ ዲናሞ ኪዬቭ፣ እንዲሁም የእንግሊዙ ቸልሲ ከፈረንሳዩ ሬ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ የሚጠበቅ ነው። የጣሊያኑ ላትሲዮ ከራሺያው ዜኒት፣ የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ከከሐንጋሪው ፌሬንክቫሮስ፣ የስፔኑ ሴቪያ ከራሺያው ክራስኖዳር ጋር ይጋጠማሉ።
ቡንደስ ሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት፦ ማይንትስ ፍራይቡርግን 3 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሔርታ ቤርሊንን ኦሎምፒያ ስታዲየም ውስጥ በሰፋ ልዩነት 5 ለ2 አሸንፏል። ከትናንት በስትያ በተደረጉ አምስት ግጥሚያዎች መሪው ባየር ሙይንሽን ከቬርደር ብሬመን፤ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከአውግስቡርግ ጋር አንድ እኩል እንዲሁም ሽቱትጋርት ከሆፈንሃይም ጋር ሦስት እኩል አቻ ወጥተዋል። ቮልፍስቡርግ ሻልከን 2 ለ0፤ ባየር ሌቨርኩሰን አርሜኒያ ቢሌፌልድን 2 ለ1 አሸንፈዋል።
በዚህም መሠረት፦ ባየር ሙይንሽን የደረጃ ሰንጠረዡን በ19 ነጥብ ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ18 ነጥብ ይከተላል። ባየር ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ 18 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይፕትሲሽ 17 ነጥብ ይዞ ደረጃው አራተና ነው። ዑኒዬን ቤርሊን በ15 ነጥብ አምስተኛ ደረጃውን ይዟል። ዘንድሮ ወደ ቡንደስሊጋው አድጎ ብቅ ያለው አርሜኒያ ቢሌፌልድ፣ ኮሎኝ እና ሻልከ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ተከታትለው ይገኛሉ። ሻልከ በዚህ አያያዙ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን ከቡንደስሊጋው በደካማ ነጥብ ወደ ታች የሚወርድ ይመስላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ