1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 28 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 28 2013

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ፋሲል ከነማ ከዩኤስ ሞናስቲር ጋር ተጫውቶ ቢያሸንፍም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን ግን ባለቀ ሰአት አምክኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቶትንሃም እና ሊቨርፑል አንገት ላንገት ተናንቀዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ከላይፕትሲሽ ጋር አቻ በመውጣቱ የመሪነት ስፍራውን በገዛ እጁ አጥብቧል።

https://p.dw.com/p/3mLsf
Äthiopien Addis Abeba |  Ethiopia Fasil Kenema vs Monastir CAFCC
ምስል Omna Taddele/DW

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ለድል ስትበቃ ሌላኛዋ የሀገሯ ልጅ እና የቀድሞ የውድድሩ የአምስት ሺህ ሜትር አሸናፊ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ሳትሳተፍ ቀርታለች። ትግራይ ውስጥ ባለው ውጊያ መንቀሳቀስ እንዳልቻለች ተገልጧል። በካፍ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ፋሲል ከነማ ከዩኤስ ሞናስቲር ጋር ተጫውቶ ቢያሸንፍም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሉን ግን ባለቀ ሰአት አምክኗል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቶትንሃም እና ሊቨርፑል አንገት ላንገት ተናንቀዋል፤ በደረጃ ሰንጠረዡ የሚበላለጡት በግብ ክፍያ ብቻ ነው። በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባየር ሙይንሽን ከላይፕትሲሽ ጋር አቻ በመውጣቱ የመሪነት ስፍራውን በገዛ እጁ አጥብቧል። ባየር ሌቨርኩሰን በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ይከተለዋል። በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ከታች ባደገ ቡድን መሸነፉ ደጋፊዎቹን እጅግ አበሳጭቷል። ያደገው ቡድን በገዛ መረቡ ላይ በስህተት ባያስቆጥርም ባርሴሎና በዜሮው ሊወጣ ይችል ነበር። 

በቅድሚያም አትሌቲክስ

China Beijing 2015 IAAF Weltmeisterschaft Genzebe Dibaba
ምስል picture-alliance/dpa/S. Suki

ትናንት በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በተደረገው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ያሸነፈችበት ጊዜ በርቀቱ ፈጣኑ ሰአት ኾኖ መመዝገቡን የዓለም አትሌቲክ ዐስታወቀ። አትሌት ገንዘቤ ዲባባ የግማሽ ማራቶን ሩጫውን ለማሸነፍ የፈጀባት ጊዜ 1:05:18 ነው። ኬንያዊቷ አትሌት ሼይላ ቼፕኪሩይ በ1 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ ሮጣ ኹለተኛ ወጥታለች። ኢትዮጵያዊቷ ሰንበሬ ተፈሪ ደግሞ በ1 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ የሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ከዚህ ቀደም በቫሌንሺያ ከተማ የ5 ሺ ሜትር ውድድር አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገቧ ዓለምን አስደምማ የነበረችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት ግደይ ትግራይ ውስጥ ባለው ውጊያ ምክንያት በውድድሩ ሳትሳተፍ መቅረቷ ተዘግቧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌት ለተሰንበት ግደይ በአሁኑ ወቅት መቀሌ እንደምትገኝ በመግለጥ የመጓጓዣ መንገድ ባለመኖሩ ወደ አዲስ አበባ መምጣት አለመቻሏን ለዶይቸ ቬለ ገልጧል።

በተመሳሳይ የቫሌንሺያ ወንዶች ፉክክር ኬኒያዊው አትሌት ኪቢዎት ካንዲ የርቀቱን ክብረ ወሰን ሰብሮ ማሸነፍ ችሏል። የ24 ዓመቱ ኬኒያዊ የ21 ኪሎ ሜትሩን የሩጫ ውድድር ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 57 ደቂቃ ከ32 ሰከንዶች ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ርቀቱ በጄዎፍሬይ ካምዎሮር ክብረ ወሰን ተይዞ ነበር። አኹን ኪቢዎት በ29 ሰከንዶች ማሻሻል ተሳክቶለታል።  

ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ

Äthiopien Addis Abeba |  Ethiopia Fasil Kenema vs Monastir CAFCC
ምስል Omna Taddele/DW

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ኹለተኛ ዙር ግጥሚያ ፋሲል ከነማ ትናንት የቱኒዝያው ዩኒየን ስፖርቲቭ ሞናስቲርን 2 ለ1 ቢያሸንፍም ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ግን አልቻለም። በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ምክንያት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ በተዛወረው የካፍ ኮንፌድሬሽን የእግር ኳስ ግጥሚያ በሀገሩ ሜዳ የተጋጠመው ፋሲል ከነማ የማለፍ ዕድሉን አለምልሞ ነበር። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠረበት ብቸኛ ግብ ግን ፋሲል ከነማ የአፍሪቃ መድረክ ጉዞው በቱኒዚያው ዩኒየን ስፖርቲቭ ሞናስቲር ተገቷል።

ለፋሲል ከነማ ትናንት ሱራፌል ዳኛቸው በ28 ደቂቃ ላይ የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር፤ ሙጂብ ቃሲም በሁለተኛው አጋማሽ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ኾኖም መደበኛ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ፌዲ አርፋዊ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ለሞናስትሪ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል።  በአጠቃላይ የ3 ለ2 ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።  በደርሶ መልሱ ጨዋታ ውጤት መሰረት በ3 ለ 2 ድል ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የቻለው ሞናስትሪ  ቡድን ነው።

የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በ80ኛው ደቂቃ በግብ ጠባቂያቸው እና በሞናስቲሩ ተከላካይ ቤን ራህማን ላይ የተከሰትው ጉዳት የጨዋታውን መልክ መቀየሩን ለዶይቼ ቬሌ ገልፀዋል። «አንደኛ በተጫዋቾቹን መካከል የነበረው ጨዋታውን ባያቀዘቅዘው፤ ለተጨማሪ ጎል የምንሄድ ይመስለኛል። ምክንያቱም እነሱ የእኛን ፍጥነት እና እንቅስቃሴ ብዙም መቋቋምም አልቻሉም። ጥሩ እየሄድንባቸው ነበር። ከዛ ጉዳት በኃላ ነው እነሱ መምጣት የቻሉት። የእኛም ደግሞ ትኩረት ወረድ ማለት የጀመረው። ትልቁ በሽታ የምለው የጎሉን ማስተናገድ ሁኔታችን ነው።»

Äthiopien Addis Abeba |  Ethiopia Fasil Kenema vs Monastir CAFCC
ምስል Omna Taddele/DW

በትናንቱ ግጥሚያ በኹለተኛው አጋማሽ የሞናስቲር ተጨዋቾች በ76ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት ለማግባት ባደረጉት ጥረት ፋሂም ቤን ረመዳን እና ሚኬል ሳማኬ ተጋጭተው ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ነበር። በተለይ የዩኒየን ሞናስተሩ ተጫዋች ፋሂም ቤን ረመዳን ምላሱ የመተንፈሻ አካሉን ዘግቶበት እንደነበረም በስፍራው ውድድሩን የተከታተለው ኦምና ታደለ ዘግቦልናል። የፋሲል ከነማ ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኪ ደግሞ ጭንቅላቱ ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ፋሲል ከነማ የተሻለ በነበረበት ጨዋታ 2-1 ቢያሸንፍም ከሜዳው ውጪ የተሸነፈበት ውጤት በጊዜ በቅደም ማጣሪያው ዙር እንዲሰናበት አድርጎታል። አሰልጣኝ ሥዩም ቡድናቸው ቅዳሜ በሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፊቱን  በማዞር ለዋንጫ እንደሚፎካከሩ ተናግረዋል።

«ከጅምሩ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማግኘት የክለቡ ራዕይ ሆኖ እየተንቀሳቀስ 2011 ላይ ጫፍ ደርሶ መጨረሻ ላይ ያጣበት ጊዜ አለ። ዓምናም እስከ17 ጨዋታ ስንሄድ ጥሩ ሄደናል። አሁን ደግሞ ሙሉ በሙሉ የሊጉን ዋንጫ ለመጎናፅፍ በምንፈልጋቸው ክፍተቶች ላይ ተጨማሪ ሃይል ጨምረናል። ይህንንም የጨምርነው አንድ አምስት ልጆች ካለፈው ዓመት ቡድናች ላይ ያሳድጉልናል ብለን ነው። አንድ እና አንድ ሁለት ነው ምንም ጥያቄ የለውም የሊጉን ዋንጫ ለማግኘት ነው ራዕያችን።»

የዘንድሮ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ግጥሚያ ከኅዳር 18 ቀን፣ 2013 ዓ.ም እስከ የካቲት 12 ቀን፣ 2013 ዓም እንደሚከናወን የተያዘው የጊዜ ሠሌዳ ያመለክታል። 16 ቡድኖች የሚሳተፉበት የውድድር ምድብ ውስጥ ለመግባት 67 የአፍሪቃ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን ያከናውናሉ።

Äthiopien Addis Abeba |  Ethiopia Fasil Kenema vs Monastir CAFCC
ምስል Omna Taddele/DW

የቀድሞ የአርሰናል እና የባርሴሎና ኮከብ ተጨዋች የነበረው አሌክስ ሶንግ የሚጫወትበት ጅቡቲ የሚገኘው አዲሱ ቡድኑ 9 ለ1 ከመንኮታኮት መታደግ አልቻለም።   የጅቡቲው አርታ ሶላር 7 ቡድን ላይ 9 ግብ በተከታታይ በማስቆጠር የግብ ጎተራ ያደረገው የግብጹ አል ሞካውሉን አል አራብ የተሰኘው ቡድን ነው። በሜዳው ከባድ ሽንፈት ለደረሰበት የጅቡቲው አርታ ሶላር 7 ብቸኛዋን ግብ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ዳዲዜ ነው።

የ33 ዓመቱ ካሜሩናዊ አሌክስ ሶንግ ቡድኑ እንዲያ መጫወቺያ ሲኾን አንዳችም ማድረግ አልቻለም። የካፍ ኮንፌዴሬሽን ግጥሚያ በአፍሪቃ የእግር ኳስ ደረጃው ሌላ ቢኾንም የጨዋታው አይነት ከአውሮጳ ሊግ ጋር ተመሳሳይ ተደርጎ ይወሰዳል።

በሌላ ግጥሚያ፦ የዛምቢያው ናስፓ ስታር የኮሞሮሱን ናጋዚ በደርሶ መልስ ውጤት 9 ለ2 ድል አድርጓል። የትናንት ውጤቱ 4 ለ1 ነበር። የሊቢያው አል ኢቲሃድ የትናንቱን 3 ለ0 ጨምሮ በደርሶ መልስ የሶማሊያው ሆርሲድን ያሸነፈበት የ7 ለ1 ውጤትም ሌላው በግብ የተንበሸበሸ ግጥሚያ ነበር።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ቶትንሀም ትናንት ከአርሰናል ጋር ባደረገው ግጥሚያ 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። አርሰናል በ13 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ አሽቆልቁሏል። በደረጃ ሰንጠረዡ ከቶትንሃም ጋር በተመሳሳይ 24 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ግን ተበልጦ ኹለተኛ የኾነው ሊቨርፑል ዎልቨርሀምፕተንን ትናንት 4 ለ0 ድል አድርጓል። እንዲያም ኾኖ ግን ሊቨርፑል በቶትንሀም በአምስት የግብ  ክፍያ ይበለጣል። በ22 ነጥቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ሊድስን ቅዳሜ ዕለት 3 ለ1 አሸንፏል። ላይስተር ሲቲ በ21 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ1 ድል አድርጓል። በሌላ የቅዳሜ ግጥሚያ ዌስትሀምን 3 ለ1 ያደባየው ማንቸስተር ዩናይትድ 19 ነጥብ ይዞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  ዛሬ ማታ ብራይተን እና ሳውዝሀምፕተን ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

Großbritannien Leeds | Premier League | Nicolas Pepe
ምስል Molly Darlington/AFP/Getty Images

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ መሪው ባየር ሙይንሽን ትናንት ነጥብ በመጣሉ ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት በአንድ ነጥብ ብቻ ተወስኗል። ባየር ሙይንሽን ከትናንት በስትያ በሜዳው አሌያንትስ አሬና ላይፕትሲሽን ገጥሞ ሦስት እኩል ተለያይቷል። በ23 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን ይመራል። ተጋጣሚው ላይፕትሲሽ በ21 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

ሻልከን 3 ለ0 ትናንት ያሸነፈው ባየር ሌቨርኩሰን በበኩሉ 22 ነጥብ ሰብስቦ ኹለተኛ ደረጃውን አስጠብቋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከአይንትርኅት ፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ በመጣሉ በ19 ነጥብ የአራተኛ ደረጃው ላይ ለመወሰን ተገዷል። ከታችኛው ዲቪዚዮን ዘንድሮ ያደገው አርሜኒያ ቢሌፌልድ በመጣበት እግሩ ለመመለስ ቊልቊል ወደ 16ኛ ደረጃ ላይ ዝቅ ብሏል። 17ኛ እና 18ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ማይንትስ እና ሻልከ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተዘርግተዋል።

FC Schalke 04 - Bayer Leverkusen
ምስል Guido Kirchner/dpa/picture alliance

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና ከታችኛው ዲቪዚዮን ባደገ ቡድን ትናንት 2 ለ1 መሸነፉ በርካቶችን አስደምሟል።  ባርሴሎናን ጉድ ላደረገው ካዲሽ ቡድን የማሸነፊያዎቹን ኹለት ግቦች ያስቆጠሩት፦ አልቫሮ ኺሜኔዝ እና አልቫሮ ኔግሬዶ ናቸው። ቀዳሚዋ ግብ በ8ኛው ደቂቃ፤ እንዲሁም የማሸነፊያዋ ግብ በ63ኛው ደቂቃ ላይ ነበር የተቆጠሩት። ባርሴሎናን ከባዶ መሸነፍ ያዳነችውን ግብ ማግኘት የቻለው ደግሞ ፔድሮ አልካላ በ57ኛው ደቂቃ ላይ በገዛ ቡድኑ ላይ በማስቆጠሩ ነው።

ካዲሽ ባርሴሎናን ተናንቆ ያገኘው ነጥቡ ተደምሮለት በ18 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከስሩ በኹለት ነጥብ ዝቅ ያለው ሴቪያን አስከትሏል። ከበላዩ ደግሞ በ2 ነጥብ በልጦ ሪያል ማድሪድ አራተኛ ደረጃን ይዟል። ሪያል ማድሪድ እና ሴቪያ ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ወሳኝ  ግጥሚያ ደግሞ ሪያል ማድሪድ በቦኖ ብቸኛ ግብ 1 ለ0 ማሸነፍ ችሏል።  ባርሴሎና ከመሪው አትሌቲኮ ማድሪድ በ12 ነጥብ ርቀት 9ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

Champions League 2018 | Atletico Madrid v Borussia Dortmund
ምስል Reuters/J. Medina

የላሊጋውን የደረጃ ሰንጠረዥ በ26 ነጥብ የሚመራው አትሌቲኮ ማድሪድ ቫላዶሊድን 2 ለ0 ረትቷል። በ25 ነጥብ ኹለተኛ ደረጃ የያዘው ሪያል ሶሲዬዳድ ትናንት ከአላቬስ ጋር ባደረገው ግጥሚያ ያለምንም ግብ ነጥብ መጣሉ በደረጃ ሰንጠረዡ የመሪነት እድሉን አምክኗል። 21 ነጥብ ያለው ቪላሪያል ከኤልቼ ጋር ትናንት ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። ኤልቼ በ14 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኦሳሱና፣ ቫላዶይድ እና ኤስ ዲ ሆይስካ ከ18ኛ እስከ 20ኛ የወራጅ ቃጣናው ውስጥ ተደርድረዋል። ዛሬ ማታ አይባር ከቫሌንሺያ ይጋጠማሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ