የነሐሴ 11 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ነሐሴ 11 2012የሻምፒዮንስ ሊግ
በሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ቸልሲን 4 ለ 1፤ በደርሶ መልስ ደግሞ 7 ለ1 የረመረመው ባየር ሙይንሽን በሩብ ፍጻሜው ባርሴሎናን 8 ለ2 ድባቅ መትቶ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፏል። የፈረንሳይ ሊግ አንድ ዋንጫን በተደጋጋሚ ያነሳው ቡድን ኦሎምፒክ ሊዮንን ረቡዕ ምሽት ይገጥማል። ሌላኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ የጀርመን ቡድን ኤር ቤ ላይፕሲሽ የዓለማችን ምርጥ ተጨዋቾች የኾኑት እንደነ ኔይማር እና ኬሊያን ምባፔን የሚያሰልፈው ፓሪስ ሴንጀርሜንን ይጋጠማል። ፖርቹጋል መዲና ሊዛቦን ውስጥ በሚካኼደው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ኹለቱ የጀርመን ቡድኖች ሊገናኙ የመቻል ዕድል እንዳላቸውም ብዙዎች ገምተዋል።
ሦስት ጀርመናዊ አሰልጣኞች ለግማሽ ፍጻሜው
በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ጀርመናዊ አሰልጣኞች ለግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል። የ55 ዓመቱ የባየር ሙይንሽኑ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ ዋንጫውን የመውሰድ የተሻለ ዕድል አላቸው ተብሏል። ከባየርን ሙይንሽን ምክትል አሰልጣኝነት፤ ወደ ጊዜያዊነት ከዚያም ዋና አሰልጣኝነት ያደጉት ዲተር ሐንሲ ፍሊክ በስድስት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ስድስት ድል አስመዝግበዋል። እንደ ሐንሲ ፍሊክ ተመሳሳይ ድል ያስመዘገቡት የኤስ ሚላኑ አሰልጣኝ ፋቢዮ ካፔሎ ከ28 ዓመት በፊት እንዲኹም የፓሪስ ሰንጄርሜን አሰልጣኝ የነበሩት ሉዊ ፈርናንዴዝ ከ36 ዓመት በፊት ነበሩ።
የፓሪስ ሴንጄርሜኑ አሰልጣኝ የ46 ዓመቱ ቶማስ ቱኸል ደግሞ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018/2019 ወደ ፓሪስ ሴንጄርሜን ከመጡ ወዲህ በ400 ሚሊዮን ዩሮ ኔይማርን እና ምባፔን ለቡድኑ በማስፈረም ፈረንሳይ ውስጥ በስድስት የተለያዩ የፍጻሜ ግጥሚያዎች አሸናፊ መኾን ችለዋል። አራቱ ድሎች ዘንድሮ የተመዘገቡ ናቸው።
የ33 ዓመቱ ዩሊያን ናግልስማን በበኩላቸው ኤር ቤ ላይፕሲሽን ይዘው ለግማሽ ፍጻሜ ብቅ ያሉ ወጣቱ አሰልጣኝ ናቸው። በዘመናቸው ቡድናቸውን በቡንደስሊጋው ሦስተኛ ኾኖ እንዲጨርስ በማስቻል ለቀጣይ ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር እንዲያልፍ አስችለዋል። ዘንድሮ ለፍጻሜው ደርሰው ተጨማሪ ታሪክ ያስመዘግቡም ይኾናል። በተለያዩ ግጥሚያዎች የተለያዩ አይነት የአሰላለፍ ስልት የሚከተሉት ያገራቸው ልጅ ቶማስ ቱኸል ግን በቀላሉ የሚበገሩላቸው አይነት አይመስሉም።
በእርግጥ የፓሪስ ሴንጄርሜኑ ዋና ግብ ጠባቂ ኪይሎር ናቫስ አታላንታ ቤርጋሞን 2 ለ1 ባሸነፉበት የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ታፋው ላይ ጉዳት ደርሶበት ተቀይሯል። ለነገው ጨዋታ የሚደርስ አይመስልም። በአታላንታው ግጥሚያ ዋና ግብ ጠባቂውን ተክቶ የገባው ሠርጂዮ ሪኮ በነገው ፍልሚያ ተሰላፊ ይኾናል ማለት ነው። ተቀናቃኝ ቡድን ላይ ጫና በማሳደር ተጨዋቾች በግብ ክልል ውስጥ ስህተት እንዲፈጽሙ የማስቻል የአጨዋወት ስልት ይዘው ወደ ሜዳ ለሚገቡት አሰልጣኝ ዩሊያን ናግስልማን ሌላ አጋጣሚ ይመስላል።
አሠልጣኝ ቶማስ ቱሁል በበኩላቸው ዘመናዊ የጀርመን እግር ኳስ የሚባለውን የአጨዋወት ስልት ተከታይ ናቸው። ግን ደግሞ በኮከብ ተጨዋቾቻቸው ላይም የተመሠረተ ጨዋታ ነው የሚያከናውኑት። የፓሪስ ሠንጀርሜኑ ከዋክብት ኬሊያን ምባፔ እና ኔይማር የቡድናቸው ሞተር ተደርገው ይወሰዳሉ። ዩሊያን ናግልስማን እንዲኽ አይነቱን ነገር በቀላሉ አንብበው ወደ ለሜዳ ለመግባት የተካኑበት ነው።
የቶማስ ሙይለር ብቃት መመለስ
ባሳለፍነው ሳምንት የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ በርካቶች ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪን ሲጠብቁ ቶማስ ሙይለር በ31 ደቂቃዎች ውስጥ ኹለት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ባርሴሎናዎችን መብረቅ የወረደባቸው አስመስሏል። ሊዮኔል ሜሲ ከ2015 ወዲህ የሻንፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት ሕልሙ ነበር።
ሊዮኔል ሜሲ የዛሬ አምስት ዓመት ባርሴሎና በፍጻሜው ጁቬንቱስን 3 ለ 1 አሸንፎ በወሰደው ዋንጫ የተፈጠረውን ፌሽታ ታቅፎ ቀርቷል። እናም የሌዮኔል ሜሲ ሕልምን ቶማስ ሙይለር ነጥቆታል። ቶማስ ሙይለር በወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ግብ የማስቆጠር ልዩ ብቃት አለው። የተወሰኑትን ወሳኝ ግጥሚያዎች እና ግቦችን መለስ ብለን እንመልከት።
ጀርመን እንግሊዝን በዓለም ዋንጫ ኹለተኛ ዙር ግጥሚያ ወቅት በ2010 ዓም 4 ለ1 ስታሸንፍ በአራት ደቂቃዎች ነበር ኹለት ግቦች አስቆጥሮ ኩም ያደረጋቸው። በ2013 ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ባርሴሎናን በደርሶ መልስ 7 ለ 0 ባሸነፈበት ግጥሚያ ሦስት ግቦች የቶማስ ሙይለር ናቸው።
ጀርመን ብራዚልን በዓለም ዋንጫ 7 ለ1 ባዋረደችበት ግጥሚያ አዘጋጅ ሀገሯ ላይ በ11ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠረም ችሎ ነበር። ብራዚል ከ1 ዓመት ቀደም ብሎ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ስፔንን 3 ለ0 አሸንፋ ለድል በቅታም ነበር።
በ2012 የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ወቅትም ይኸው ቶማስ ሙይለር የቸልሲን ሕልም ለጥቂት ቀምቶ ነበር። መደበኛ ጨዋታው ሊፈጸም 7 ደቂቃ ሲቀረው ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ በማድረግ የቸልሲ ባለቤት ሮማን አብራሞቪች ለበርካታ ዓመታት በርካታ ሚሊዮኖችን አፍስሶ ያለመውን ለጥቂት አምክኖበት ነበር። በእርግጥ በዚያ ጨዋታ ቸልሲ በፍጹም ቅጣት ምት አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል።
የቶማስ ሙይለር ብቃቱ በተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል የተከላካዮችን ክፍተት በፍጥነት በማንበብ በቦታው ተገኝቶ ግብ ማስቆጠሩ ነው። በጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮአኺም ሎይቭ፤ በፔፕ ጓርዲዮላ፤ በሉዊስ ቫን ጋል፣ ዩፕ ሃይንከስ እና አኹን ደግሞ በሐንሲ ፍሊክ ዘመን ቶማስ ሙይለር ዘመኑ አብቧል። በኒኮ ኮቫች እና ካርሎ አንቼሎቲ ዘመን ግን ቶማስ ሙይለር ማበቡ ወደ መክሰም እየተቀየረ ነበር።
ከ2018 የሩስያ የዓለም ዋንጫ የጀርመን ቡድን ደካማ ተሳትፎ በኋላም በብሔራዊ ቡድኑ እንደማያስፈልግ ወዲያው ነበር የተነገረው። በእርግጥ በ100 ግጥሚያዎች 38 ግቦችን ማስቆጠር ቢችልም ማለት ነው። ከባርሴሎናው ከፍተኛ ድል በኋላ ግን ወደ ብሔራዊ ቡድኑ መመለስ አለበት እየተባለ ነው። ፍራንትስ ቤከን ባወር ከቢልድ ጋዜጣ ጋር ትናንት ባደረገው ቃለ መጠይቅ፦ ቶማስ ሙይለር ወደ ብሔራዊ ቡድኑ መመለስ እንዳለበት ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በቀጥታ መልእክት አስተላልፏል። አሰልጣኝ ዮአሒም ሎይቭ ሐሳባቸውን ቀይረው ቶማስ ሙይለርን ወደ ቡድናቸው ይመልሱትም ይኾናል።
የሊዮኔል ሜሲና የባርሴሎና ፍጻሜ
ሊዮኔል ሜሲ በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ከባርሴሎና መንኮታኮት በኋላ ለዘመናት አብሮት የዘለቀው የልጅነት ቡድኑን ሊለቅ እንደኾነ ኤስፖርቴ ኢንተራቲቮ የተባለ የብራዚል ማሰራጪያ ትናንት የውስጥ ምንጮቼ እንደነገሩኝ ሲል ዘግቧል።
የ33 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂ ለ20 ዓመት አብሮት ከቆየው የልጅነቱ ቡድን ባርሴሎና የሚለየው በባየር ሙይንሽን የሩብ ፍጻሜ በደረሰባቸው ብርቱ ሽንፈት ነው። ምናልባትም ሜሲ ወደ ማንቸስተር ሲቲ አቅንቶ ለረዥም ጊዜ በሚያውቃቸው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ስር ሊታይ ይችላል ተብሏል። ባለፉት ሳምንታት ወደ ኢንተር ሚላንም ሊያቀና እንደሚችል ሲነገር ነበር። ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ጋር የገባው ውል እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2021 የሚያበቃ ነው። ምናልባትም ባርሴሎና ባለችው ጥቂት ጊዜ ተጠቅሞ ከሜሲ ዝውውር ከፍተኛ ገቢ ሊያገኝ ይችልም ይኾናል ተብሏል።
የአውሮጳ ሊግ
በአውሮጳ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ዛሬ ማታ የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን ከዩክሬኑ ሻካታር ዶንዬትስክ ጋር ይጋጠማል። ከኹለቱ አሸናፊ ቡድን ትናንት በግማሽ ፍጻሜው የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድን ያሰናበተው የስፔኑ ሴቪያን ዐርብ ማታ ለፍጻሜው ይገጥማል።
ፎርሙላ አንድ
በስፔን ግራንድ ፕሪ የመኪና ሽቅድምድ ሌዊስ ሐሚልተን አሸናፊ ኾኗል። የአጠቃላይ ውድድሩ መሪ ሌዊስ ሀሚልተን ባለፈው ሳምንት በማክስ ፈርሽታፓን ተቀድሞ ነበር፤ በትናንቱ 88ኛ ግራንድ ፕሪ ውድድር ኹለቱ አሽከርካሪዎች የአሸናፊነት ደረጃቸውን ተቀያይረው ፈርሽታፓን ኹለተኛ ወጥቷል። በባርሴሎናው ውድድር በተረጋጋ መንፈስ አሽከርክሮ ለድል የበቃው ብሪታንያዊ የመርሴዲስ አሽከርካሪ በትናንቱ ድል ከአጠቃላይ ውድድር በ37 ነጥብ ልዩነት ይመራል። የሬድ ቡሉ አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፓን በ95 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ 89 ነጥብ ሰብስቦ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። የፌራሪ አሽከርካሪ ጀርመናዊው ሠባስቲያን ፌትል በ16 ነጥብ ብቻ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ