የነሐሴ 17 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ነሐሴ 17 2013ኬንያ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ በተከናወነው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ፍጻሜ ውድድር ላይ ውጤት ያስመገበው የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ከዓለም አራተኛ ከአፍሪቃ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ስላጠናቀቀው ወጣት ቡድን የሚቃኝ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል። የእንግሊዙ የቀድሞ አጥቂ ዴቪድ ቤክሃም የቀድሞው የባርሴሎና ኮከብን ወደ አሜሪካው ቡድን ለማስመጣት ንግግር መጀመሩ ተሰምቷል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሮሜሉ ሉካኩ ቸልሲን ከፍ ከፍ አድርጓል። ሊቨርፑል አንፊልድ ውስጥ በጆታ እና ማኔ ግቦች ደጋፊዎቹን አስፈንድቋል። በፈረንሳይ ሊግ የኒስ እና ማርሴ ግጥሚያ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ተመው በመግባታቸው ተቋርጧል።
አትሌቲክስ
ኬንያ ናይሮቢ ከተማ ውስጥ ትናንት በተጠናቀቀው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ፍጻሜ ውድድር ላይ የተካፈለው የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። የአትኬቲክስ ቡድኑ 115 የዓለማችን ሃገራት በተካፈሉበት ፉክክር 12 ሜዳሊያዎችን በማስገኘት ከዓለም የአራተኛ ደረጃን ይዞ ነው ያጠናቀቀው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርስም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራር እና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጉንጉን አበባ እንደተበረተከተለት እና ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ፌዴሬሽኑ ገልጧል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በዓለም አቀፍ መድረክ ውጤቱ ምን ይመስላል? በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የስፖርት አዘጋጅ ጋዜጠኛ ምሥጋናው ታደሰ ዉጤቱ ድንቅ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ውድድሩን በሦሶስት ወርቅ፣ ሰባት የብር እና ሁለት የነሃስ ሜዳልያዎች በድምሩ 12 ሜዳልያዎች በማግኘት ነው ኬንያ፣ ፊንላንድ እና ናይጄሪያን ተከትላ አራተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው።
የፓሪ ሳንጃርሞ ደጋፊዎች የዓለማችን ድንቅ የኳስ ጠቢብ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ማሊያቸውን ለብሶ ሲጫወት ለመመልከት ገና መጠበቃቸው ግድ ኾኗል። ባለፈው ዐርብ ፓሪ ሳንጃርሞ ስታዴ ብሬስትን 4 ለ2 ባሸነፉበት ግጥሚያ በልምምድ ጉዳዮች የተነሳ ሊዮኔል ሜሲ አልተሰለፈም። ከሁለት ዐሥርተ ዓመታት በላይ ከቆየበት ባርሴሎና ቡድን በዓመት የተጣራ 40 ሚሊዮን ዩሩ ገቢ እየተደረገለት በፓሪ ሳንጃርሞ ለመቆየት የሁለት ዓመት ውል የፈረመው የ34 ዓመቱ አጥቂ ጉዳይ ገና ሙሉ ለሙሉ ሳይጠናቀቅ ከወደ አሜሪካ ጥሪ ቀርቦለታል። ልክ የሁለት ዓመቱን ውል እንዳገባደደም ወደ ኢንተር ሚያሚ በማቅናት በአሜሪካ ዋናው የሶከር ሊግ (MLS) ለመጋጠም የቀድሞው የብሪታንያ ኮከብ ዴቪድ ቤክሃም ከወዲሁ ጥሪ እንዳቀረበለት እና ሁለቱ የእግር ኳስ ከዋክብት በዚሁ ጉዳይ ላይ እንደተነጋገሩ ተዘግቧል።
ከፈረንሳይ ሊግ ኧ ሳንወጣ ማርሴ እና ኒስ ዐርብ እለት ያደረጉት ጨዋታ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው በመትመማቸው 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል። የሁለቱ ግጥሚያ ለረቡዕ የተላለፈ ሲሆን፤ ኒስ በሜዳው ማርሴይን 1 ለ0 እየመራ ነበር ጨዋታው የተቋረጠው። ለጨዋታው መቋረጥ ምክንያቱ፦ የማርሴዩ ዲሚትሪ ፓዬት ከደጋፊዎች በተወረወረ የውኃ መያዣ መመታቱ ነበር። ዲሚትሪ የተመታበት ውኃ መያዣ እቃ ወደደጋፊዎች መልሶ ሲወረውር በርካታ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው ተመዋል። ከዚያም ከተጨዋቾች ጋር ግብግብ ለመፍጠርም ሞክረዋል። ሁለቱም ቡድኖች በፈረንሳይ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሊግ የጠባይ ገምጋሚ ኮሚቴ ተጠርተዋል። በአሊያንስ ሪቪዬራ ውስጥ ስለተከሰተው ያልተለመደ ድርጊት የፊታችን ረቡዕ እንዲያብራሩም ተጠይቀዋል።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቤልጂየማዊው አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ በቸልሲ ቆይታው ለሁለተኛ ጊዜ ተሰልፎ ቡድኑ አርሰናልን 2 ለ0 ድል እንዲያደርግ አስችሏል። እሁድ እለት ቸልሲ ከሌላኛው የለንደን ባላንጣው አርሰናል ጋር ባደረገው ግጥሚያ ለቸልሲ በቅርቡ የቡድኑ ከፍተኛ ክፍያ በሚባል የፈረመው ሮሜሉ ሉካኩ ኳሷን ከመረብ ለማሳረፍ የፈጀበት 15 ደቂቃ ብቻ ነበር። 135 ሚሊዮን ዶላር የተከሰከሰበት ቤልጂየማዊ አጥቂ በ9 ቁጥር መለያው ገና ብዙ ያስደምመናል ሲሉ የቸልሲ ደጋፊዎች ተስፋ ሰንቀዋል። ሁለተኛውን ግብ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሪቼ ጄምስ ነው። የቸልሲው አሰልጣን ጀርመናዊው ቶማስ ቱኁል፦ «ያለቅጥ ለመፈንጠዝ ጊዜው አሁን አይደለም» ሲሉ ቡድናቸውን በማድነቅ እንዲረጋጋ ግን አጽንኦት ሰጥተዋል። አርሰናል ዘንድሮ እጅግ ደካማ በሚባል አጀማመር በተደጋጋሚ መሸነፋን በተመለከተ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ሲናገሩ፦ ቡድናቸው «አስቸጋሪ እና ግራ የሚያጋባ ኹኔታ ውስጥ ነው» ብለዋል።
እስካሁን ቸልሲ እና ሊቨርፑል ሁለት ጨዋታቸውን በተመሳሳይ የግብ ክፍያ ማሸነፍ ችለዋል። ሊቨርፑል በርንሌይን 2 ለ0 ድል ባደረገበት ግጥሚያ ዲዬጎ ጆታ እና ሳዲዮ ማኔ በ18ኛው እና 69ኛው ደቂቃ ላይ ደጋፊዎቻቸውን አንፊልድ ውስጥ አስቦርቀዋል። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ በበኩላቸው በአንፊልድ ሜዳችን ሕልማችን እውን ኾኗል ሲሉ ደስታቸውን ገልጠዋል።
በተያያዘ ዜና፦ የሊቨርፑል አማካይ አጥቂ ዤርዳን ሻቂሪ ወደፈረንሳዩ ሊዮን ቡድን ሊያቀና እንደሆነ ተገልጧል። ስዊዘርላንዳዊው አጥቂ በአንፊልድ የሦስት ዓመት ቆይታው ለቡድኑ ለ63 ጊዜያት ቢሰለፍም፤ የመጀመሪያ የቡድኑ ተመራጭ ለመሆን ከብዶት ግን ቆይቷል። እሱም ቢሆን ያለፈው የጨዋታ ጊዜ ሲገባደድ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ መቆየት እንደማይፈልግ ገልጦ ነበር። አሁን ሊቨርፑል እና ሊዮን በዤርዳን ሻቂሪ ጉዳይ መስማማታቸው ተዘግቧል። ዤርዳን ሻቂሪ ዛሬ የህክምና ምርመራ እንደሚደረግለት ትናንት ማታ ነበር የተነገረው፤ ዝርዝሩም ይገለጣል ተብሏል።
በሌሎች የፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ብራይተን እና ቶትንሀምም ሁለት ጨዋታዎቻቸውን አሸንፈው ስድስት ነጥብ የያዙ ሲሆን፤ ብራይተን በግብ ክፍያ ይበልጣል። ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ኤቨርተን እና ከታች ያደገው ብሬንትፎርድ እያንዳንዳቸው አራት ነጥብ ይዘዋል። ማንቸስተር ሲቲ፤ ዌስትሀም፤ አስቶን ቪላ፤ ላይስተር ሲቲ እና ዋትፎርድ 3 ነጥብ አላቸው። ከታች ኖርዊችን ተከትሎ አርሰናል ያለምንም ግብ በአራት የግብ ክፍያ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ስር ይገኛል። ዛሬ ማታ ላይስተር ሲቲ ከዌስት ሀም ጋር ይጋጠማል።
ቡንደስ ሊጋ
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያም ያልተጠበቁ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በነበሩ 9 ግጥሚያዎች 27 ግቦች ተቆጥረዋል። አውግስቡርግ ከፍራንክፉርት ያለምንም ግብ ተለያይቷል። አርሚኒያ ቢሌፌልድ ዘንድሮ ከታች ያደገው ግሮይተር ፊዩርት ጋር የተለያየው አንድ እኩል በመውጣት ነው። ዑኒዬን ቤርሊን እና ሆፈንሃይምም ሁለት እኩል ነው ጨዋታቸውን ያጠናቀቁት። የተቀሩት ውድድሮች በመሉ አሸናፊ እና ተሸናፊ የታዩባቸው ነበሩ።
የቦን ከተማ አጎራባቹ ኮሎኝ ቡድን ትናንት ወደ ባየርን ሙይንሽን አቅንቶ የተሸነፈው በጠበበ የግብ ልዩነት 3 ለ2 ነው። ዩሊያን ናግልስማን በባየርን አሰልጣኝነታቸው በአሊያንስ አሬና ሜዳቸው ያደረጉት ግጥሚያ ደካማ ነበር ማለት ይቻላል። የባየርን ሙይንሽን ተጨዋቾች በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ዒላማቸውን የሳቱ ኳሶችን ለተጋጣሚ ቡድን በመላክ ድክመት ታይቶባቸዋል። የጃማል ሙሳይላ ሌሮይ ሳኔን ቀይሮ መግባት ግን ቡድኑን በደቂቃ ውስጥ እጅግ እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል። የመጀመሪያዋን ግብ ለሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ያመቻቸው ተቀይሮ በገባ በ2 ደቂቃ ውስጥ ነበር። ሁለተኛውን ግብ ሠርጌ ግናብሬ ከመረብ አሳርፏል።
ለ50 ደቂቃ ያኽል የግብ ክልላቸውን ሳያስደፍሩ ቆይተው 2 ለ0 የተመሩት ኮለኖች ወዲያው ነበር አጸፌታውን የመለሱት። ዮናስ ሔክቶር በግራ በኩል በፍጥነት ገፍቶ የላካትን ኳስ አንቶኒ ሞዴስቴ በድንቅ ኹኔታ በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ አሳርፏል። ከሠርጌ ግናብሬ ሁለተኛ ግብ ከ13 ሰከንድ በላይም አልተቆጠረ ኮሎን ሲያስቆጥር። ከሁለት ደቂቃ በኋላም ኮሎኝ ሁለት እኩል ኾኖ ነበር። ሠርጌ ግናብሬ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ክልሉ 15 ሜርት ርቀት ላይ በግሩም ኹኔታ በማስቆጠር ባየርን ሙይንሽንን ነጥብ ከመጣል ታድጎታል።
ዶርትሙንድ በፍራይቡርግ ሽንፈት ቀምሷል። ባዬርን ሌቨርኩሰን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 4 ለ0፤ ላይፕትሲሽ ሽቱትጋርትን በተመሳሳይ 4 ለምንም ድል አድርገዋል። ቮልፍስቡርግ ሔርታቤርሊንን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ቦኹም ማይንትስን 2 ለ0 ረትቷል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ