1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 2 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 2 2014

የኦሬገኑ ድል በኮሎምቢያም ተደግሟል። እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደማሚ በሆነ መልኩ ከአፍሪቃ 1ኛ ከዓለም 3ኛ በመሆን ድል ተቀዳጅተዋል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ ፉክክርም ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ብቃቱን ዐሳይቷል።

https://p.dw.com/p/4FHFo
Fussball - 2. Bundesliga - Hansa Rostock - Hamburger SV
ምስል Danny Gohlke/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኦሬገኑ ድል በኮሎምቢያም ተደግሟል። እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደማሚ በሆነ መልኩ ከአፍሪቃ 1ኛ ከዓለም 3ኛ በመሆን ድል ተቀዳጅተዋል።  በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ ፉክክርም ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ብቃቱን ዐሳይቷል። ሊቨርፑል አሰልጣኙን እና ደጋፊዎቹን ያበገነ ውጤት ይዞ ወጥቷል። አርሰናል በፕሬሚየር ሊጉ መክፈቻ ተጋጣሚውን አንበርክኳል። ቶትንሀም ሳውዝሐምፕተን ላይ በግብ ተንበሽብሾ ሲፈነጭማንቸስተር ዩናይትድ በብራይተን ሽንፈት ገጥሞታል። በቡንደስሊጋው መክፈቻ ባየርን ሙይንሽን ዘንድሮም ማን ደፍሮ ሊጠጋኝ ብሏል። ፍራንክፉርትን ዐርብ እለት 6 ለ1 ጉድ አድርጎታል። አንድ የገባበት በግብ ጠባቂ ስኅተት ነበር።

Fussball Bundesliga Eintracht Frankfurt vs. FC Bayern München
ምስል Christian Kaspar-Bartke/Getty Images

አትሌቲክስ

ኮሎምቢያ ካሊ ውስጥ በተከናወነው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ፉክክር ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ 1ኛ ከዓለም ደግሞ 3ኛ በመሆን አጠናቃለች። በውድድሩ ኢትዮጵያ በሁለተኛ ደረጃ እንዳጠናቀቀችው ጃማይካ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። ቀዳሚዋ ዩናይትድ ስቴትስ ወርቅ በማግኘት በአንድ ሜዳሊያ ብቻ ነው የምትበልጠው። ኢትዮጵያ 5 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያ ስታገኝ፤ ጃማይካ በ7 የብር እና በ3 የነሐስ ሜዳሊያ የሁለተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች። ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ 4 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ያገኘቻቸው የሜዳሊያ ብዛቶች በበርካታ የውድድር ዘርፎች ተካፋይ ከነበሩት ዩናይትድ ስቴትስ እና ጃማይካ ተቀራራቢ ነው።  ይህ ምን ያመለክታል?  በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሻምፒዮን ስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ዘርዓይ እያሱ ውጤቱ አመርቂ ነው ወደፊት ግን ለማስጠበቅ የልምምድ ቦታዎች እጥረት ትኩረት ሊsx,ው ይገባል ብሏል።

ኮሎምቢያ ፖላንድ ቾርዞው ከተማ ውስጥ ባሳለፍነው ቅዳሜ በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ የሩጫ ፉክክርም ኢትዮጵያውያት አትሌቶች አመርቂ ድል ተቀዳጅተዋል። በ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር አትሌት ድርቤ ወለተጂ 3:56.91 በመሮጥ የአንደኛ ደረጃን አግንታለች። አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ እና ኂሩት መሸሻም የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በማግኘት ተከታትለው ገብተዋል። ጉዳፍ የገባችበት ሰአት 3:58.18ሲሆን፤ ኂሩት ከሁለት ሰከንዶች በኋላ በመግባት ነበር የሦስተኛውን ደረጃ ያገኘችው። በዚሁ ውድድር አክሱማይት እምባዬ 6ኛ፤ ገብሬ ደስታ 7ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ሐብታም ዓለሙ እና ለምለም ኃይሉ11ኛ እና 14ኛ ደረጃን አግኝተዋል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
ምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በ3000 ሜትር ፍጻሜ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በትውልደ ኢትዮጵያ ሆላንዳዊቷ ሯጭ ሲፋን ሐሰን ለጥቂት ተቀድማ የሁለተኛ ደረጃን አግንታለች። ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ ሽቅድምድም ሐዊ ፈይሳ 8ኛ፣ ዘርፌ ወንድማገኝ 9ኛ፣ ፋንቱ ወርቁ 11ኛ እንዲሁም አያል ዳኛቸው 12ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ቀጣይ የዳያመንድ ሊግ ውድድሮች፦ የሞናኮ ፉክክር ከነጌ በስትያ ከዚያም ከሁለት ሳምንት በኋላ የሉዛኔ ውድድር ይቀጥላል። የብራስልስ እና ዙሪክ ዳያመንድ ሊግ ውድድሮችም ጳጉሜ እና መስከረም መጀመሪያ ላይ ይከናወናሉ።

ፕሬሚየር ሊግ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር ዐርብ ዕለት ሲከፈት አርሰናል ተጋጣሚው ክሪስታል ፓላስን 2 ለ0 ድል በማድረግ ደፋፊዎቹን አስፈንድቋል። የጋብሪዬል ማርቲኔሊ ግብም የዘንድሮው የፕሬሚየር ሊግ የመጀመሪያዋ ግብ ተብላ ተመዝግባለች።   ከቅዳሜ ጨዋታዎች የፕሬሚዬር ሊጉ ምርጦች ከሚባሉት ዋነኛው ሊቨርፑል ከታችኛው ዲቪዚዮን በመጣ ቡድን ፈተና ገጥሞታል። ሊቨርፑል በሞሐመድ ሳላህ እና አዲሱ አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝ ሁለት ግቦች የማታ ማታ ተሸንፎ ነጥብ ከመጣል ተርፏል። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ከፉልሀም ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ መጋራታቸውን በተመለከተ ተጠይቀው በጨዋታው ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

UK | Fussball FC Liverpool Trainer Jürgen Klopp
ምስል Peter Byrne/PA Wire/dpa/picture alliance

«ሽንፈቱ አጨዋወታችን ነው እንጂ ውጤቱ አይደለም። ሽንፈቱ አጨዋወታችን ስለነበር ነገሮችን ማጤን ያስፈልጋል። ያ ዳግም ሊያጋጥመን ይችላል። ዛሬ አሸንፈን ከጨዋታው ምንም ባንማር እና ነጥብ ብቻ ይዘን ብንወጣ ኖሮ የከፋ ነበር።  ዋናው ነገር ትምህርት መውሰዳችን ነው።»

በመጀመሪያው ቀን ግጥሚያ ሊቨርፑል በርካታ ተጨዋቾቹን በጉዳት የተነሳ አለማሰለፉ ጎድቶታል። ኢብራሒም ኮናቴ፣ ናቢ ኪዬታ እና ዲዬጎ ጆታ በመጎዳታቸው መሰለፍ አልቻሉም። ቲያጎ አልካንታራም ቢሆን ጉዳቱ ወደፊት ምን ያህል ከጨዋታ እንደሚያገለው ዐልታወቀም። በእርግጥ በሁለቱም ግቦች ተሳታፊ የነበረው አዲሱ አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝ ለሊቨርፑል ታላቅ ተስፋ ሰንቋል።

ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ብቅ ካሉ አዳዲስ አጥቂዎች መካከል የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ በትናንቱ ጨዋታ ስኬታማ ኾኗል። ዌስትሀም ዩናይትድን 2 ለ0 ሲያሸንፉ ሁለቱም ግቦች የኖርዌያዊው አጥቂ ነበሩ። ፍጥነት፤ ጉልበት እና ከአንድ አንድ ንክኪ ግብ ማስቆጠር ኧርሊንግ ኦላንድ በቡንደስሊጋውም የተካነበት ነበር፤ በፕሬሚዬር ሊጉ ዐሳይቷል። በእርግጥ በሊቨርፑል በተሸነፉበት የኮሙኒቲ ሺልድ ዋንጫ ግጥሚያ ኧርሊንግ ኦላንድ ተደብቆ ነበር ማለት ይቻላል። ትናንት ግን ማንነቱን ዐሳይቷል። አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ አዲሱን አጥቂያቸውን አወድሰው ማሻሻል የሚገባውንም ጠቁመዋል።

 Manchester City Manager Pep Guardiola
ምስል Javier Garcia/Shutterstock/IMAGO

«በእርግጥም ኧርሊንግ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ግቦቹ ለእሱም ለእኛም ጠቃሚ ነበሩ። እናም ሌላ መሣሪያ እጃችን ገብቷል። በተመሳሳይ መልኩ ግን ችግሮቻችንን በሙሉ ለብቻው አይፈታውም። እንደ ቡድን ማድረግ የምንሻውን ወደፊት የሆነ ነገር ይጨምራል።»

በሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ አስቶን ቪላ በበርመስ የ2 ለ0 እንዲሁም ዎልቨርሀምፕተን በሊድስ ዩናይትድ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ኒውካስል አዲስ መጪው ኖቲንግሀም ፎረስትን 2 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ቶትንሀምሆትስፐር ሳውዝሀምፕተንን 4 ለ1 አንኮታኩቷል። በጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል የሚመራው ቸልሲ ኤቨርተንን 1 ለ0 በማሸነፍ ፕሬሚየር ሊጉን በድል ጀምሯል። ላይስተር ሲቲ እና ብሬንትፎርድ ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ሲጋሩ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲዬም በብራይተን 2 ለ1 ተሸንፏል። በእለቱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከቡድኑ ጋር በስልጠና የቆየው ለ10 ቀናት ብቻ ነበር ያ ደግሞ የመጀመሪያ ተሰላፊ ለማድረግ በቂ አልነበረም ብለዋል። የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዋይኔ ሩኒ፦ የዝውውር ጊዜው ከማብቃቱ በፊት ክርስቲያኖ ሮናልዶ ቢሰናበት ሲል መክሯል።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ዘንድሮም ብርታቱን ዐሳይቷል። በመክፈቻ ግጥሚያው ዐርብ እለት አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 6 ለ1 ጉድ አድርጎታል። አንደኛውም ግብ ብትሆን ግብ ጠባቂው ማኑዌል ኖዬር ዘና ብሎ የፍራንክፉርቱን አጥቂ አልፋለሁ ሲል ነው የተሳሳተው። በግብ ክልሉ አቅራቢያ አድብቶ የነበረው የፍራንክፉርቱ አጥቂ ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ ኳሷን ከማኑዌል ነጥቆ ከመረብ አሳርፏታል። በዚህም ፍራንክፉርት በሜዳው በዜሮ ከመሸነፍ ተርፏል። ባየርን ሙይንሽን ግን ዘንድሮም ዋንጫውን ለመውሰድ ማን ደፍሮ ይጠጋናል የሚል መልእክት በቡንደስሊጋው መክፈቻ አስተላልፏል።

Bayern München - VfB Stuttgart I Meisterschale
ምስል Matthias Balk/dpa/picture alliance

ቅዳሜ ዕለት ማይንትስ ቦሁምን 2 ለ1፤ ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ሆፈንሀይምን 3 ለ1, አሸንፈዋል። ቮልፍስቡርግ ከብሬመን ጋር ሁለት እኩል ወጥቷል። ሔርታ ቤርሊን በዑኒዮን ቤርሊን የ3 ለ1 ሽንፈት ሲገጥመው ፍራይቡርግ በግብ ተንበሽብሾ አውግስቡርግን 4 ለ0 ድል አድርጓል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሜዳው ሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም ውስጥ 10ኛው ደቂቃ ላይ በተገኘችው የማርኮ ሮይስ ብቸኛ ግብ ባዬር ሌቨርኩሰንን አሸንፏል።  

ትናንት ላይፕትሲሽ እና ሽቱትጋርት አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። ኮሎኝ ወደ ቡንደስሊጋው ዳግም የተመለሰው ሻልከን 3 ለ1 ድል አድርጓል። የሻልከ አሰልጣኝ የዳኛ አድልዎ ሲሉ አማረዋል። በእርግጠም ሻልከ ወደ 2ኛው ዲቪዚዮን ከወረደ ከ442ኛው ቀን በኋላ ባደረገው ግጥሚያ የሚያወራርደው ሒሳብ ነበረው። እናም በኮሎኝ ሜዳ ኮሎኝን አስጨንቆ የመጀመሪያዋን ግብ በ10ኛው ደቂቃ በሮድሪጎ ሳላዣር ቢያስቆጠርም ፌሽታው አፍታም አልቆየ። ግቧ ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሰርዛለች። 35ኛው ደቂቃ ላይ የሻልከው ዶሚኒክ ድሬክስለር ዮናስ ሔክቶርን ባቱ ላይ በመራገጡ የመሀል ዳኛው ድርጊቱን በተንቀሳቃሽ ምስል አጣርተው በቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል።

ላሊጋ፥ የፊታችን ዐርብ ኦሳሱና ከሴቪያ ጋር በሚያደርገወረ ግጥሚያ ይጀምራል። ቅዳሜ እለት ከራዮ ቫሌካኖ ጋር የላሊጋው ቀዳሚ ጨዋታውን የሚያደርገው ባርሴሎና ለወዳጅነት ገጥሞ ኡናም ፑማስን 6 ለ0 አሸንፏል። ከባየር ሙይንሽን የተዛወረው ፖላንዳዊ አጥቂ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ በባርሴሎና መለያ 9 ቁጥር ለብሶ ቀዳሚውን ግብ በ3ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። የጣሊያን ሴሪኣም በሳምፕዶሪያ እና አታላንታ የፊታችን ግጥሚያ ቅዳሜ ዕለት ይጀምራል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ