የአድዋ ድል በዓልና የምንሊክ አደባባይ
ማክሰኞ፣ የካቲት 22 2014መንግስት የአድዋ ድል በሕግ ተደንግጎ የኖረውን ብሎም ድሉ በብሔራዊ ደረጃ መከበር ከጀመረበት ላለፉት 100 አመታት ገደማ የተከበረበትን የምኒልክ አደባባይ ከመከበሪያ ስፍራነት ለመቀየር እሞከረ ነው በማለት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አማረሩ። ነዋሪዎቹና አንዳንድ የመንግስት ሹማምንት ጭምር በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንደገለጹትና ለDW በሰጡት አስተያየት እንዳሉት መንግስት የአድዋን በአል ከአጼ ሚኒሊክ ለመነጠል እየሰራ ነው ብሏል። የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ባወጣው መግለጫም ይህንኑ ተቃውሟል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የመገናኛ ብዙሃን የዜና ሽፋን ስለመስጠት በጻፈው ደብዳቤ 126ኛው የአድዋ በአል በአድዋ ድልድይ እንደሚከበር አስታውቋል። በተጭማሪም በአዲሱ አብርሆት ቤተ መጻህፍትም በሚደረገው ዝግጅትም ታዳሚዎች እንዲገኙ የጥሪ ወረቀት ተበትኗል። በአሉ በአጼ ሚኒሊክ አደባባይ እንደወትሮው አለመከበሩ ያሳሰበው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ባወጣው መግለጫ ``በዚህ አመት የማክበሪያ ቦታው ወደ ሌላ ቦታ መዛወሩ የድሉን መታሰቢያነት ከማግነን ይልቅ ዝቅ ያደርገዋል የሚል ስጋት አለን``ሲል ተቃውሞታል።
ይህን ተከትሎ በአዲስ አበባ ነዋሪዎችና በመንግስት ሹማምንት ጭምር ቁጣን ቀስቅሷል። ካነጋገረናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎቸ አንዱ የሆኑት አቶ ወንድም ካባው ለDW በሰጡት አስተያየት `` የአድዋ ድል በአል በሚኒሊክ አደባባይ እንዲክበርና ቢሮ ዝግ እንዲሆን የተወሰነው በአዋጅ ነው። መንግስት ለምን እንዲህ እንደሚያደርግ ሊገባን አልቻለም። አምናም መስቀል አደባባይ ሲክብር የባልቻ አባሳፎና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ ተለጥፎ ነበር። የሚኒሊክ ፎቶ እንኳን አልነበረም። እና ድርጊቱ ብዙዎቻችንን አስደንግጦናል።``
ሌላው የአዲስ አበባ ነዋሪና በፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ወጣት ሚኪኤልም ``በአሉ ይከበራል ተበሎ የተገለጸበት መንገድ ኢትዮጵያዊነትን በፍጹም የማይቀበልና ከአድዋ ድል ጋ ተጻራሪነት ያለው ነው ሲል አክሏል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል ጆቴን አነጋግረናቸው ከመናበብ የተፈጠረ ስህተት ነው ብለዋል። በመግለጫ የተቃወማችሁት እንዴት በመናበብ ችግር ሊባል ይችላል ስንል ጥያቄ አነሳንላቸው ``ክፍተቱ ከሁላችንም ነው። መንግስት በአሉ እዛ መከበሩ እንደማይለወጥ ያውቀዋል። ግን መግለጫ በሚሰጥበት ጊዜ የአድዋ ድልድይ በሚለው ላይ ስላተኮሩ ቦታው ተለወጠወይ ብለን ባነሳነው ጥያቄ ያ የነበረውን የመናበብ ክፍተት እንዲጣበብ አድርገንዋል`` ብሏል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ምላሽ እንደሚሰጡን ቀጠሮ ከሰጡን በኋላ ደጋግመን ብንደውልላቸውም ስልካቸው ባለማንሳታቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልቻልንም። ሆኖም ግን ፋና የተባለው ለመንግስት ቅርበት ያለው ራድዮ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዲኤታን ጠቅሶ ``በዓሉ በሚኒሊክ አደባባይ አይከበርም`` በሚል የሚናፈሰው ወሬ ሃሰት ነው ብሏል።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ