የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የትይዩ ገበያውን ሁለተኛ ፈርጅ መቆጣጠር ይችላል?
ረቡዕ፣ ጥቅምት 2 2015በኢትዮጵያ በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ተመን እና በተለምዶ "ጥቁር" እየተባለ በሚጠራው ትይዩ ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሲመጣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "በሕገ-ወጥ የሐዋላ ሥራ" የተጠረጠሩ ከ390 በላይ ግለሰቦች የባንክ አካውንት ከነ ገንዘባቸው ማገዱን አስታውቋል። ባለፈው አርብ መስከረም 27 ቀን 2015 የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ ተደርጎ "ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው" ባንኩ የሥም ዝርዝራቸውን ለፍትኅ ሚኒስቴር አስተላልፏል።
"እነዚህ ሰዎች ከአንድ አካውንት በሣምንት ከ50 እከከ 80 ለሚደርሱ ሰዎች ገንዘብ ያዛወሩ ናቸው። እዚህ ያሉ ሰዎች ለእነዚህ 50 እና 60 ሰዎች የሚልኩት ገንዘብ ምንም አይነት የንግድ ልውውጥ የሌለበት፤ ምንም አይነት የቢዝነስ ግንኙነት የሌለበት ነው" ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዢ "ይኸ ሙሉ በሙሉ በውጭ አገር የሚካሔደውን የሐዋላ ሥራ የሚደግፉ ናቸው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ዶክተር ይናገር ደሴ ከአንድ አካውንት ወደ በርካታ ሰዎች ከሚደረግ የገንዘብ ዝውውር ባሻገር ተጠርጣሪዎቹ "በሕገ-ወጥ የሐዋላ ሥራ" መሰማራታቸውን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ስለመኖሩ ያሉት ነገር የለም። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ግን "እግዱን ያመጣው የሰሞኑ ድንጋጤ ነው" የሚል እምነት አላቸው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው የጠቀሱት "ድንጋጤ" በትይዩው ገበያ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ተመን ወደ 100 ብር ገደማ በመድረሱ የተፈጠረ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥር 2013 ከአንድ የባንክ አካውንት ወደ ሌሎች አካውንቶች በአንድ ሣምንት የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር ከአምስት መብለጥ እንደሌለበት ያወጣውን ገደብ አንስቷል። በሞባይል ባንኪንግ፣ በኤቲኤም እና በሽያጭ መፈጸሚያ ማሽኖች (PoS) የሚፈጸሙ የገንዘብ ዝውውሮችን ዘግየት ብሎ የጨመረው ገደብ ሥራ ላይ የቆየው ግን ለአንድ ዓመት ገደማ እስካለፈው ጥር 2014 ድረስ ብቻ ነበር።
የትይዩው ገበያ ሁለተኛ ፈርጅ ወይስ ሶስተኛ የውጭ ምንዛሪ ገበያ?
ይኸ የብሔራዊ ባንክ እርምጃ በተለይ በቅርብ ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት እና መወሳሰብ ባሳየው የውጭ ምንዛሪ ትይዩ ገበያ ሁለተኛ ፈርጅ ላይ ያነጣጠረ ነው። የገበያው ዋንኛ ተሳታፊዎች ከአገሪቱ ርቀው የሚኖሩ የገንዘብ አዘዋዋሪዎች እና ነጋዴዎች ናቸው። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን እንዲያውም የኢትዮጵያ ሶስተኛ የውጭ ምንዛሪ ገበያ አድርገው ይቆጥሩታል። የመጀመሪያው ገበያ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚተመነው መደበኛ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ነው። በዚህ ገበያ ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2015 አንድ ዶላር በ53 ብር ከ75 ሳንቲም ገደማ ይመነዘራል። በመደበኛው ግብይት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ባለፉት 52 ሣምንታት 14 በመቶ ገደማ ቢዳከምም በተለምዶ ጥቁር ከሚባለው የትይዩ ገበያ የመቀራረብ ምልክት ግን አላሳየም።
ሁለተኛው አዲስ አበባ ብሔራዊ ቴዓትር ፊት ለፊት፤ መርካቶ እና ፍልውኃን በመሳሰሉ አካባቢዎች ይታይ የነበረው የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢትዮጵያ ብር ወይም ብር ወደ የውጭ ምንዛሪ የሚቀየርበት ነው። ይኸ የኢትዮጵያ መንግሥት ለረዥም ዓመታት አንድ ጊዜ ጠበቅ ሌላ ጊዜ ላላ የሚል ቁጥጥር ሲያደርግበት ታይቷል። "ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ ከባንክ እንደፈለጉ ስለማያገኙ፤ ውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ እየሰበሰቡ ለነጋዴዎች ውጭ አገር ክፍያ የሚያካሒዱ አሉ" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን "ይኸ ሶስተኛው ገበያ ማለት ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "መንግሥት እዚህኛው ገበያ ላይ ምንም ቁጥጥር የለውም" የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "ልዩነቱ ሰፊ ስለሆነ ሰዎች መደበኛውን የባንኮች መንገድ ተከትለው ወደ አገር ቤት ሐዋላ አይልኩም" ሲሉ አስረድተዋል።
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የባንክ ባለሙያ በሐዋላ ወደ ኢትዮጵያ መላክ የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ወደ ዱባይ እና ሻንጋይ የሚያሻግረውን ይኸን ትይዩ ገበያ ከነቀርሳ ያመሳስሉታል። የባንክ ባለሙያው እንደሚሉት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ከተቆጣጣሪዎቹ ርቆ መፋፋት የያዘው ትይዩ ገበያ በውጭ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የሚልኩት የሐዋላ መጠን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ከጀመረ ውሎ አድሯል።
አጥቋሪዎቹ
ይኸን ሥራ የሚከውኑ ግለሰቦች አጥቋሪ እየተባሉ ሲጠሩ ይደመጣል። በተለምዶ ትይዩው ገበያ "ጥቁር" እየተባለ ከመጠራቱ የመነጨ ስያሜ ይመስላል። ዶይቼ ቬለ ያነጋራቸው እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚገኙ እንደሚሉት ይኸኛው ትይዩ ገበያ "ጥንቃቄ የሚጠይቅ ግን ደግሞ ከፍ ያለ ትርፍ ያለው ንግድ" ሆኗል።
በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ግለሰቦች፣ የአነስተኛ መደብሮች እና የምግብ ቤት ባለቤቶች የብሔራዊ ባንክ ገዢ "ሕገ-ወጥ ሐዋላ" ያሉትን ሥራ እንደሚያከናውኑ ዶይቼ ቬለ ካነጋገራቸው ስድስት ግለሰቦች ለመገንዘብ ችሏል። በሥራው የተሰማሩ ግለሰቦች ለቤተሰቦቻቸው አሊያም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብ መላክ ከሚሹ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዶላር፣ ዩሮ፣ ድርሐም እና ሪያል ይሰበስባሉ። በኢትዮጵያ በሚገኝ ወኪል፣ ቤተሰብ ወይም የሥራ አጋር አማካኝነት የውጭ ምንዛሪው በትይዩ ገበያ ተመን ተመንዝሮ በኢትዮጵያ ብር በኢትዮጵያ በሚገኝ ባንክ አማካኝነት ለተላከለት ሰው ያስተላልፋሉ።
በዚህ መንገድ እንደ ሊቢያ በመሳሰሉ አገራት ለሚገኙ ስደተኞች የዕለት ወጪ ወይም በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚጠየቁትን ክፍያ እንደሚፈጸም ዶይቼ ቬለ ማረጋገጥ ችሏል። የውጭ ምንዛሪው በአንጻሩ ሰብሳቢዎቹ በዚያው በሚኖሩበት አገር ለሚገኝ እና መኪና ወይም አንዳች ዕቃ ገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ መላክ ለሚሻ ግለሰብ ወይም ለሌላ አስተላላፊ ይሸጣል። በግብይቱ ዋንኛ ተዋናዮች ግን ከዓለም ገበያ ሸቀጥ ሸምተው ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት የሚፈልጉ ነጋዴዎች ናቸው። ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ "ኢትዮጵያ ያለ ነጋዴ ዕቃ ሊያስመጣ ቻይና ክፍያ እንዲፈጸምለት ይፈልጋል እንበል። በአንድ ደቂቃ ወደ ቻይና ክፍያው ይፈጸማል። አገር ቤት ያለው ነጋዴ ደግሞ ብሩን እዚያ ለሚፈልግ ሰው ይከፍልላቸዋል። ያ ብር ደግሞ ከዚህ ለተላከው ገንዘብ መክፈያ ይውላል" ሲሉ አስረድተዋል።
ትይዩ ገበያው ለረዥም ዓመታት በመንግሥት በሚወሰነው መደበኛ የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ እየታከከ ይከናወን የነበረ ቢሆንም በጊዜ ሒደት በፍላጎት እና አቅርቦት ላይ መንተራስ መጀመሩን የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እና በግብይቱ የሚሳተፉ ግለሰቦች ታዝበዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ አቢስ ጌታቸው "ጥቁር ገበያው ድሮ በመንግሥት የምንዛሪ ተመን ላይ ጥገኛ ነበር። አሁን የራሱ ፍላጎት እና አቅርቦት ያለው፤ የራሱ ድንጋጤዎች ያሉት ገበያ ሆኗል። አሁን ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
የዋጋ ንረት፦ ገፊ ምክንያቶች፣ የብሔራዊ ባንክ እርምጃ እና የወደፊት ሥጋቶች
ዶክተር አብዱልመናን በበኩላቸው "ከኦፊሴላዊው ግንኙነት በሌለው መልኩ አቅርቦት በሚኖርበት ሰዓት ወረድ ይላል። አቅርቦት በሚያንስበት እና ፍላጎት በጣም በሚጨምርበት ሰዓት ተመኑ ወደ ላይ ይወጣል" ሲሉ ከአቶ አቢስ የተስማማ ትንታኔ ሰጥተዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ግለሰቦች እንደሚሉት ይኸ በትይዩ ገበያው የታየው ለውጥ በተለይ በዱባይ ለሚገኙ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን ተመን የመወሰን ጉልበት ሰጥቷቸዋል። ዶክተር አብዱልመናን እንደሚሉት በዚህ በትይዩ ገበያ የሚንቀሳቀሰው የውጭ ምንዛሪ "ዋንኛ መዳረሻ" ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ሸቀጥ ከምትሸምትባቸው አገራት አንዷ በሆነችው ቻይና ነው። "ክፍያ የሚፈጸመው በቀጥታ በፓውንድም ወይም ዶላር አይደለም። በቻይና ዩዋን ነው የሚከፈለው። ስለዚህ ተመኑ ብር ወደ ዩዋን፤ ፓውንድ ወደ ዩዋን ሶስት ጊዜ ተገልብጦ ነው የሚተመነው" ሲሉ ምንዛሪው በውስብስብ ሒደት ውስጥ እንደሚያልፍ ዶክተር አብዱልመናን ያስረዳሉ።
ዶይቼ ቬለ ካነጋገራቸው ስድስት የትይዩ ገበያው ተሳታፊዎች አራቱ በሥራቸው ሳቢያ በኢትዮጵያ ባንኮች የሚገኙ አካውንቶቻቸው ታግደው እንደነበር ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ይኸ እርምጃ እና ባለሥልጣናቱ የሚያደርጓቸው ክትትሎች ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉትን ግለሰቦች ከግብይቱ ገሸሽ አላደረጋቸውም። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን የኢትዮጵያ መንግሥት ግብይቱን ለመቆጣጠር ከዚህ ቀደም የወሰዳቸው እርምጃዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
"ከዚህ በፊት በነሐሴ 2021 የዶላር የምንዛሪ ተመን በትይዩ ገበያ ከ60 ብር ወደ 65 ብር ሲገባ እንዲህ አይነት እርምጃ ተወስዶ ነበር። ብድር ሁሉ ወደ መከልከል ተሒዶ ነበር" የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን በትይዩ ገበያ ጭማሪ አሳይቶ የነበረው የዶላር የምንዛሪ ተመን የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ይኸ ግን የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው እንደሚሉት አልዘለቀም። የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃውን ሲወስድ "ወዲያው ምንዛሪው ወደቀ። ከዚያ ደግሞ ቀስ እያለ በሒደት መውጣት ጀመረ። ሰሞኑን በኃይለኛው ወጣና መንግሥት እርምጃ ሲወስድ ትንሽ ቀነሰ። አሁን ዶላር 105 ብር አካባቢ ነው ያለው። አሁንም የተፈጥሮ ጉዞውን ይዞ ወደ ላይ መውጣቱ አይቀርም" ሲሉ ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የዉጪ ምንዛሪ እጥረትና የብሔራዊ ባንክ መመሪያ
ግብይቱ እየተወሳሰበ፣ የተሳታፊዎቹ ቁጥር እና ጥቅም ላይ የሚውሉት የመገበያያ ገንዘቦች አይነት እየጨመረ የሔደውን ይኸን ትይዩ ገበያ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው "የኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎች ሊረዱትም፤ ሊቆጣጠሩትም አይችሉም" የሚል ሥጋት አላቸው። "ተሳታፊዎቹ ቁጥራቸው ሰፊ ስለሆነ፤ ቢዝነሱ ትርፍ ስላለው አትራፊ ነገር ደግሞ ሕገ ወጥ ብንለውም ባንለውም ማንንም ሰው ይስባል። በዚያ ላይ ነጋዴው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለበት በየትም ቀዳዳ ማግኘት ነው የሚፈልገው። እንደዚህ ሰፊ እና የተወሳሰበ የሆነን ገበያ መንግሥት በእንደዚህ አይነት እርምጃ ያረጋጋዋል የሚል እምነት የለኝም" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግብይቱን ለመቆጣጠር ካሉት መንገዶች አንዱ ባለፈው አርብ ይፋ እንዳደረገው የገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ የሚጠቀሙባቸው የባንክ አካውንቶች ላይ ክትትል ማድረግ ነው። ይኸ ግን የመጨረሻው መፍትሔ ላይሆን ይችላል። ዶክተር አብዱልመናን "አንድ ነጋዴ በአስር ዘመዱ በ20 ዘመዱ ሊያሰራው ይችላል። አንድ ሰው አምስት እና አስር አካውንት ሊኖረው ይችላል። ሁሉም ባንኮች ላይ አካውንት ሊኖረው ይችላል። አንዱን ክፍያ በዚህኛው፤ ሌላውን ክፍያ በዚያኛው አካውንት በመፈጸም ሊሰራ ይችላል" ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቁጥጥር ሥራ ፈተኝ እንደሚሆን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ የትይዩ ገበያ የሚፈጸም የገንዘብ ዝውውርን ለጠቆሙ ወሮታ ለመክፈል ተዘጋጅቷል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ