1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ

ሐሙስ፣ ሰኔ 8 2015

በትግራይ ክልል ለተጎጅዎች የተላከ የሰብዓዊ እርዳታ እህል መዝብረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው አካላት ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂ እንዲሆኑ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የተራድዖ ድርጅት ስምምነት ላይ መደረሳቸው ተገልጿል።አምባሳደር መለስ አለም እንዳሉት ይህ የሆነው ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ከተደረገ ፀረ አይ ኤስ አይ ኤስ ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረገ ውይይት ነው።

https://p.dw.com/p/4SbVE
The Ministry of foreign affairs
ምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ

በትግራይ ክልል ለተጎጅዎች የተላከ የሰብዓዊ እርዳታ እህል ወስደዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት ለማስፈን ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ስቴትስ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) እና የአሜሪካው የተራድዖ ድርጅት ( USAID ) በኢትዮጵያ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የሚውል የእርዳታ እህል መሰረቁ እጅግ እንዳሳዘናቸው በመግለጽ እርዳታ ማቋረጣቸውን አስታውቀው ነበር።በሌላ በኩል የሱዳንን ግጭት ለማስቆምና መፍትሔ ለማፈላለግ ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን  ኢጋድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአራት አባል ሀገራት መሪዎች በቀጣይ አሥር ቀናት ውስጥ የሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ተወካዮች አዲስ አበባ ላይ እንዲያገናኙ ውክልና መስጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በትግራይ ክልል ለተጎጅዎች የተጓጓዘን የሰብዓዊ እርዳታ እህል መዝብረዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው አካላት ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂ እንዲሆኑ በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና በአሜሪካ የተራድዖ ድርጅት እንዲሁም ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ከተደረገ ፀረ አይ ኤስ አይ ኤስ ጉባኤ ጎን ለጎን በምክትል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ውይይት ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል። ክስ ከቀረበባቸው አካላት መካከል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚገኙበት ሲሆን መከላከያ ሠራዊት “ሠራዊታችንም ኩሩና የችግረኞችን ስንዴ የማይሻማ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ነው" በሚል ክሱን ማጣጣሉ ይታወሳል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በጉዳዩ ላይ "ተገቢው ምርመራ ይደረጋል" ብለዋል።ሱዳን የምትታመስበት የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን መፈናቀል እና የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ሽሽትን በተመለከተም በስደተኝነት የገቡትን ሳይጨምር በመደበኛነት የጉዞ ሰነድ አግኝተው በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የሸሹት 33 ሺህ 269 ናቸው ብለዋል ቃል ዐቀባዩ።

The Ministry of foreign affairs
ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለምምስል Solomon Muchie/DW

ከሰሞኑ ኤርትራን ከ 16 ዓመታት በኋላ ወደ አባልነት የመለሰው ፣ የመሪነቱን ኃላፊነት ከሱዳን ለጅቡቲ ያስረከበው፣ ዋና ፀሐፊውን ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ዳግም የመረጠው እና የአባል ሀገራቱን መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማትን የሥራ ኃላፊዎች ያሳተፈው የኢጋድ ጉባኤ የአራት አባል ሀገራቱ መሪዎች የሱዳን ተፋላሚ ኃይላትን ተወካዮች በቀጣዮቹ አሥር ቀናት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ እንዲያገናኙ ውክልና እንደሰጣቸውም ተገልጿል።

የምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ደህንነት ዋነኛ ሥጋት ነው የሚባልለት ከአልቃይዳው ግር ግንኙነት አለው የሚባለው አልሸባብ ሥጋት መሆኑ ሙሉ በሙሉ እንዳልጠፋ የገለፁት አምባሳደር መለስ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ በምትዋሰንበት የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያዋ ዶሎ ከተማ ላይ የፈፀመውን ጥቃት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ የደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር ባይገልፁም ቡድኑ ላይ ጠንካራ የአፀፋ እርምጃ እንደተወሰደበት አመልክተዋል።

የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ባለፈው ሳምንት አንድ የእንግሊዝ የመንግሥት ተቋም የፀጥታ ሥጋት መኖሩን በመግለጽ ዜጎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች እንዳይጓዙ ጉዞ  ያለማድረግ የጥቆማ መልእክት ማስተላለፉን በተመለከተ ተጠይቀው መሰል ማስጠንቀቂያዎች አዲስ ነገሮች እንዳልሆኑ እና ዋጋ እንደሌላቸው ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ሰላም መኖሩን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ታምራት ዲንሳ