የኢትዮጵያ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበርነት
ሰኞ፣ ጥር 13 2005ኢትዮጵያ በዙር የሚደርሰውን የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበርነት በቅርቡ ትረከባለች ተብሎ ይጠበቃል ። የፊታችን ኡህድ የሚጀመረው የአፍሪቃ ህብረት 20ኛው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያን እጎአ የ2013 የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበር አድርጎ እንደሚመርጥ ይጠበቃል ። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ሃላፊነቱን ስትረከብ ከምታተኩርባቸው ጉዳዮች አንዱ የአፍሪቃ ሠላምና ፀጥታ ነው ።
በሳምንቱ መጨረሻ ለሚካሄደው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሚያቀርቡት የአባል ሃገራት አምባሰደሮች ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ጉባኤያቸውን ጀምረዋል ። ከአምባሰደሮቹ ቀጥሎም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመጪው ሐሙስና አርብ ከተሰበሰቡ በኋላ የፊታችን እሁድና ሰኞ የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ይካሄዳል ። በዚህ በ20ኛው የአፍሪቃ ህብረት ጉባኤ መክፈቻ ላይም
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአባል ሃገራት መሪዎች በይፋ እጎአ የ 2013 የህብረቱ ሊቀመንበር ሆነው ይመረጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዳስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የወቅቱ ሊቀመንበር የሚሆኑት ለምሥራቅ አፍሪቃ በዙር በደረሰው ተራ መሰረት ነው ።
በከዚህ ቀደሙ የዙር አሰራር መሠረት እስካሁን ተራው ለሰሜን ለደቡብ ለማዕከላዊ አፍሪቃ ና ለምዕራብ አፍሪቃ ደርሷል ። አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሊቀመንበርነት ሃላፊነቱን የሚረከቡት ከቤኒኑ ፕሬዝዳንት ከቦኒ ያያ ነው ። የአፍሪቃ ህብረት ከተመሰረተበት እጎአ ከ2003 ወዲህ ኢትዮጵያ የህብረቱ ሊቀ መንበር ስትሆን የአሁኑ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው ። ከምሥራቅ አፍሪቃ የመጨረሻዋ የህብረቱ ሊቀመንበር ታንዛኒያ ነበረች ። እጎአ በ 2009 የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪክዌቴ የህብረቱ ሊቀመንበር ነበሩ ።
ኢትዮጵያ ይህን ሃላፊነት አሁን ማግኘቷ ድርጅቱን ለማጎልበት ጠንክራ እንድትሰራ እድል እንደሚሰጣት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል ። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በሊቀ መንበርነቷ ዘመን ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችም ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።የቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተ የፊታችን ግንቦት ግምሽ ምዕተ አመት ይደፍናል ። ድርጅቱ ወደ አፍሪቃ ህብረትነት ከተቀየረ ወዲህ ደግሞ ዘንድሮ የሚያካሂደው 20ኛውን የመሪዎች ጉባኤ ነው ። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መሥራች ኢትዮጵያ ፣ የድርጅቱን የወርቅ ኢዮቤልዮ በአልና ና 20 ኛውን የመሪዎች ጉባኤም ድርጅቱ በተቋቋመባት በአዲስ አበባ ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኗን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል ።
ሂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ