1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ

ረቡዕ፣ ግንቦት 29 2010

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ አፋጥጧት የቆየውን የድንበር ውዝግብ ጉዳይ እልባት ልታደርግለት መዘጋጀቷን የሚያመለክት ውሳኔዋን አሰምታለች። ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑ የወሰነውን ተቀብላ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኗን አሳውቃለች። የፖለቲካ ተንታኞች ውሳኔው የአቋም ለውጥ ያመላከተ ነው ብለውታል።

https://p.dw.com/p/2z3Hu
Karte Äthiopien Eritrea Grenze Englisch

የኢትዮጵያ ውሳኔ አቋም ለውጥ ሊባል ይችላል፤

በ1989ዓ,ም ሁለቱ ሃገራት በድንበር ውዝግብ ሰበብ የገቡበት ይፋዊ ጦርነት ለአራት ዓመታት ቆይቶ ከ80 ሺህ ሕዝብ በላይ ፈጅቷል። ዉጊያው እንዲያበቃ ያሸማገለውን የአልጀርስ ስምምነት ኢትዮጵያ በ1993 ተቀብላ ፈርማለች። ስምምነቱ ሁለቱ ሃገራት በመካከላቸው ግጭት እንዲያቆሙ፤ የጦር ምርኮኞች እና ሌሎች እስረኞችን እንዲለቁ፤ አንዳቸው የሌላቸውን በየሀገራቸው የሚገኙ ዜጎች የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ የሚሉትን ያካተተ ነበር። ያኔም ኢትዮጵያ በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲውም መስክ ድል እንዳገኘች በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተገልጾ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ደስታውን መግለፁ አይዘነጋም። ይህ ስምምነት በተፈረመ በሦስት ዓመቱ ድንበር ለማካለል የተሰየመው ኮሚሽን በኃይል የተያዙ ያላቸውን ባድመን ጨምሮ አወዛጋቢዎቹን አካባቢዎች በተመለከተ ውሳኔውን አቀረበ። ኢትዮጵያ በመርህ ደረጃ ጉዳዩን ተቀብያለሁ ነገር ግን ለተግባራዊነቱ መነጋገር ያስፈልጋል ብላ ውድቅ አደረገች። ኤርትራ ደግሞ የገለልተኛው አካል ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን መነጋገር የለም በሚል አቋሟ ጸናች። በሁለቱ ሃገራት መካከል በድንበር ሰበብ የተለኮሰው እሳትም አመድ ለብሶ ተቀመጠ። የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት ግንኙነትም ከባሩድ ተኩስ ወደ ቃላት ተሸጋግሮ በተገኘው መነሻ አጋጣሚ ሁሉ በመካሰስ በመወነጃጀል ተጠመደ። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በመካከላቸው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ መቆይታቸውን የሚናገሩ ቢኖሩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ግን በዚህ መልኩ ገልጸውታል። 

«አሁን ያለውን በርካታ የዓለም ሰዎች ኖ ዋር ኖ ፒስ ይሉታል። እኔ በዚህ ትርጓሜ አልስማማም። ኖ ዋር ኖ ፒስ የሚባል ነገር የለም። የአሁኑን ሁኔታ ሞት አልባ ጦርነት ብዬዋለሁ።»

Äthiopien Soldat an der Grenze zu Eritrea
ምስል Getty Images/AFP/M. Longari

በአዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መመራት ከጀመረች ሁለት ወራት ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ ትናንት ይህን ሁኔታ ሊለውጥ ይችል ይሆናል የተባለ አዲስ አቋሟን ይፋ አድርጋለች። የሁለት ቀናት የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባውን ትናንት የጀመረው የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት እንዲሁም የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ መቀበሉን እና ለተግባራዊነቱም እንደሚሰራ አሳውቋል። ከዜጎች አልፎ የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረትን የሳበው ይህ የኢህአዴግ ውሳኔ ምን ማለት ይሆን? በአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ ትንታኔ የሚታወቁት ረዳት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ሰላም ያመጣል ተብሎ ባይባልም የአቋም ለውጥ ነው ይላሉ።

«ሰላም ያመጣል ማለትም ባይሆን ያው የአቋም ለውጥ አለ። የአቋም ለውጥ እንግዲህ ብዙ ነገሮችን መሠረት ያደረገ ነው።»

በወቅቱ ይላሉ የምሥራቅ አፍሪቃው የፖለቲካ ተንታኝ ኢትዮጵያ ሦስት አማራጭ ነበራት።

«ወይም ጦርነቱን ማስቀጠል እና መደምደም ነበረ የኢትዮጵያ አማራጭ፤ ወይም አልጀርስ አለመሄድ ነው፤ ወይም ከዚያ በኋላ የአልጀርሱን ስምምነት አለመቀበል ነው የነበረው። እነሱ ጊዜ ሲያልፍባቸው ችግሮች ሥር እየሰደዱ እዚህ ደርሰዋል ማለት ነው።»

እናም እንደእሳቸው ትንታኔ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰማው ነገር የኤርትራ መንግሥት የሚጠቀምባቸውን ካርዶች ለማቃጠል የአቋም ለውጥ ማሳየት ነው። በእርግጥ ይህ ለውጥ ምን ያስከትላል ብሎ መጠበቅ ይቻላል።  ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ውድቅ ያደረገችውን የድንበር ኮሚሽን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እቀበላለሁ ማለቷ ድንበር ለማካለል ጥርጊያ ቢከፍትም በቀላሉ ይከናወናል ማለት እንዳልሆነ የሚያስረዱት ረዳት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ የኤርትራ መንግሥት ማንገራገር መቀጠሉ አይቀርም ነው የሚሉት።

Grenzgebiet zwischen Eritrea und Äthiopien
ምስል AP

እንዲያም ሆኖ በኤርትራ በኩል የድንበሩ ውዝግብ ከእንግዲህ የመቀስቀሻም ሆነ የመነዛነዣ ምክንያትነቱ ያበቃል ባይ ናቸው የፖለቲካ ተንታኙ። ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ስምምነት ተደረገ ማለትም ኤርትራ ውስጥ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ ይገባልም ነው የሚሉት። ይህም በሁለቱ ሕዝቦች መካከል መልካም ግንኙነቶች እንዲሻሻሉ የሚደረጉ ጥረቶችንም በአዎንታዊ መልኩ ይረዳል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል። ይህንን ሃሳብ ጋዜጠኛ እና የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ማርቲን ፕላውት ሰላም የሚፈልገው የሁለቱም ሃገራት ሕዝብ ለረዥም ጊዜ ሲጠብቀው እንደኖረ ነው የሚያመለክተው።

«ይህ ምናልባት ይፋዊም ሆነ ይፋ ባልሆነ መልኩ ሰላም እንፍጠር በማለት ለኤርትራ የመንደርደሪያ ነጥብ ሊሆናት ይችላል። ምክንያቱም የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምን ሲናፍቅ ነው የኖረው። ይህም እጅግ ረዥም ጊዜ ሆኖታል።»

በጉዳዩ ላይ የኤርትራ መንግሥትን አስተያየት ለማግኘት ወደ ኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ሆነ በተለያዩ ሀገራት ወደሚገኙ የኤርትራ ኤምባሲዎች  ስልክ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም። 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ