የኤርትራ መንግሥት ህወሓትን ወነጀለ
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 21 2013"በአፍሪካ ቀንድ መታየት ከጀመረው ለውጥ ትግራይ ተቋዳሽ እንዳትሆን ህወሓት እንቅፋት ሆነ" ሲል የኤርትራ መንግሥት ከሰሰ።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሻባይት በተባለው ድረ-ገፅ ዛሬ ባወጣው መግለጫ "የወደቀ" ብሎ የገለፀው የትግራይ ገዢ ፓርቲ አስቀድሞ በቀጣናው ለነበሩ ችግሮች እንደ መነሻ፣ አሁን ላይ ተፈጠረ ላለው መልካም ዕድል ደግሞ እንደ እንቅፋት አድርጎ ወቅሶታል።
የአፍሪቃ ቀንድ ከነበረበት አስቸጋሪ ሁኔታ አሁን "ወደ አዲስ እና ልዩ ምዕራፍ" መሸጋገሩን የሚገልፀው የኤርትራ መንግሥት ለዚህም እንደማሳያ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ጎረቤታማቾቹ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የደረሱት የሰላም ስምምነት እና የትብብር ማዕቀፍ በቀዳሚነት አንስቷል።
አዲሱ ምዕራፍ ከሁለቱ አገራት አልፎ በአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች ተስፋ ይዞ የመጣ ተብሎ በኤርትራ መንግስት ተወድሷል። ይሁንና "የሩቅ" ያላቸው አውሮፓ ሕብረት እና ሌሎች የአህጉሩ ሀገራት (ሆላንድና ስዊድን) እንዲሁም "ጎሰኛ ቡድን" ብሎ የጠራው ህወሓት እንቅፋት ፈጥረዋል ሲል ወንጅሏል።
"ወያነ በሞት ጣር ላይ ሆኖ የሚያደርገው እንቅስቃሴ" ወደፊት መንደርደር የጀመረው ቀጠናዊው ሁኔታ ወደኋላ ሊመልሰው እንደማይችል የኤርትራ መንግስት በመግለጫው መጨረሻ አንስቷል።
የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሚመሩት የኤርትራ መንግሥት ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለው አስታውቆ ነበር።
የክልሉ መንግሥት ባለፈው ጥቅምት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ "የኢሳያስ ስርዓት ከትግራይ ህዝብ ጠላቶች ጋር ተሻርኮ ዳግም ወደ ደም መቃባት ሊያስገባን ላይ ታች በማለት ላይ ይገኛል" ብሎ ነበር።
ሚሊዮን ኃይለስላሴ
እሸቴ በቀለ