የኤርትራ የመልዕክተኞች ጓድ በአዲስ አበባ
የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት
ለቅልቅሉ አስመራ ላይ ዝግጅት
አዲስ አበባ አንድ ነን እያለች የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ«ፊዮሪና -በፍቅርሽ ጨክኜ ብርቅሽም ግን እስካሁን ልረሳሽ አልቻልኩም።» እያዳመጠች የሁለቱን መንግሥታት ዉይይት ፍሬን ለመስማት ትጠብቃለች። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በበኩላቸዉ «አርቲስቶች መጭዉ እንቁጣጣሽን የምናከብረዉ አስመራ ላይ ስለሆነ ዝግጅት እንድታደርጉ። ምጽዋ ላይ ወክ ማድረግ የናፈቃችሁ ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ ስለሚጀምር እንድትዘጋጁ። ከኤርትራ ወንድምና እህቶች ሲመጡ እንኳን ደህና መጣችሁ ብላችሁ እንድትቀበሉ» ሲሉ ምክርና እቅዳቸዉን ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ የወጡ ሰልፈኞች ደግሞ«ነይ ነይ ኤርትራ ነይ ነይ» ዘፍነዋል።
ታሪካዊዉ የሰላም ድርድር ተጀመረ
ከአስመራ የመጡት የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህ ናቸዉ። ወደ ሃያ ዓመት ገደማ ዉዝግብ ላይ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም መቀራረብን በጀመሩበት እለት በርካታ የዓለም ሃገር ሚዲያዎች ትኩረታቸዉን ወደ ሁለቱ ሃገሮች አድርገዋል። አንድ የኤርትራ መንግሥት የመልዕክተኞች ቡድን ኢትዮጵያን በይፋ ሲጎበኝት ከ1990 ወዲሕ ይህ የመጀመሪያዉ ነዉ። ኤርትራ የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ ተቀብላ የልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደምትልክ በይፋ ከተሰማ በኋላ፣ የተመድ ሂደቱን በደስታ መቀበሉን አስታዉቋል።
የአበባ ጉንጉን ለኤርትራዉያኑ ወንድሞች
የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ እና የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህን ቦሌ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ጣብያ በመገኘት ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረጉላቸዉ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ናቸዉ። በዚሁ ሥነ ስርዓት ላይ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ወርቅነህ ገበየሁ እና ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት፤ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ተወካዮችም ተገኝተዋል። በአቀባበል ሥነስርዓቱ ላይ የማርሽ ሙዚቃ ባንድና የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ዘፈንና ጭፈራ ታይቶአል።
የተለያየ ስሜት አላደረብንም
በፎቶዉ የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ይታያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ አቶ የማነ ገብረአብ ባደረጉት ንግግር «ለተደረገልን ደማቅ አቀባበል ለማመስገን እፈልጋለሁ። ዛሬ ከ 20 ዓመት በኋላ ነዉ የተገናኘነዉ። ግን ዛሬ ስንገናኝ 20 ዓመት ያህል ተለያይተን እንደነበር የሚያሳይ ስሜት አልነበረም። በመካከላችን የአስተሳሰብም ልዩነት አይታይም። አንድ የሚያሳዝን የታሪክ ምዕራፍ ዘግተን ወደ አዲስ ምዕራፍ ገብተናል የሚል እምነት አለን።» ብለዋል።
አንድ ሕዝብ ነን
በፎቶዉ ላይ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ይታያሉ። በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በተደረገዉ የእራት ግብዣ አቶ ኦስማን ሳለህ «ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን የጋራ ቋንቋና ባህል ያላቸዉ ሕዝቦች ናቸዉ። ሁለቱ ሕዝቦች ለዘመናት ተለያይተዉ ቆይተዋል፤ ይሁንና አሁን የሠላም በር ተከፍቶአል። ዘላለማዊ ሠላም እንዲሆን፤ ሠላም እንዲነግስ አበክረን እንሰራለን። የጠ/ሚ ዐብይ አቀባበል በአድናቆት አይተነዋል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ሁለት የተለያዩ ሕዝቦች ሳይሆኑ አንድ ሕዝብ ነን። አዲስ አበባ ላይ ያለዉ የደስታ ስሜት አስመራ ዉስጥም ያለ ስሜት ነዉ።»ሲሉ ተናግረዋል።
እንኳን ደህና መጣችሁ
መዲና አዲስ አበባ ማልዳ ነበር ከኤርትራ የሚመጡትን የሠላም ልዑካን ለማስተናገድ ዝግጅትዋን ያጠናቀቀችዉ። በየጎዳናዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሠንደቅ ዓላማ ተሰቅሎአል« የእንኳን ደህና መጣችሁ» መልክት በትግርኛም በአማርኛም ይነበባል። የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገራት ጋዜጠኞች ታሪካዊዉን የኢትዮ- ኤርትራ አዲስ ግንኙነት በአራቱም የዓለም ማዕዘናት ለማብሰር ጉዞዋቸዉን ወደ ቦሌ ዓለም አቀፉ የአዉሮፕላን ማረፍያ ያቀኑት በጥዋት ነበር። ዓለም ፊቱን ወደ አፍሪቃዋ መዲና አዲስ አበባ አዙሮዋል። ታሪካዊዉ የኢትዮ-ኤርትራ አዲስ የፍቅር ጉዞ። ኢትዮጵያዉያን ከኤርትራዉያን የተደመሩበት የመጀመርያ ምዕራፍ! «እንኳዕ ደሐን መፃኹም»
የሁለቱ ሃገራት የሠላም ጉጉት
ኢትዮጵያ ከአስመራ የመጡትን እንግዶቿን ቀይ ምንጣፍ ዘርግታ ነዉ የተቀበለችዉ። በዚሁ ታሪካዊ እለት የተለያዩ የዓለም ሃገሮች ስለአዲሱ የኢትዮ - ኤርትራ የወዳጅነት ግንኙነት ብዙ ጽፈዋል። «በ 20 ዓመት ታሪክ ዉስጥ ለሠላም ድርድር ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የኤርትራ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ተቀብላለች።» « ጠቅላይ ሚንስትሩ አዉሮፕላን ጣብያ ድረስ ሄደዉ የሠላም ልዑኩን መቀበላቸዉ ኢትዮጵያ ከ 20 ዓመት ወዲህ ለሠላም ያላትን ጉጉት በግልፅ ያሳየችበት ነዉ።» «የኤርትራዉ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር በኩል የቀረበላቸዉን ግብዣ በአወንታዊ መልኩ መቀበላቸዉ እጅግ ዉብ ነዉ።» ሲሉ አስነብበዋል።
የሚያዋጣን ፍቅር ብቻ ነዉ
«በፍቅር ጌዜ በጣም እናምራለን። ከኤርትራዉያን ወንድሞቻችን ጋር የሚያዋጣን ፍቅር ብቻ ነዉ። ፀቡን ሞክረነዋል በሁለቱም ወገን አክሳሪ ነዉ። ፀብ ሰዉ ይበላል፤ሃብት ይበላል፤ ጊዜን ይበላል፤ጭንቅላትንም ይበላል። ሰዉ ለመግደል እንቅልፍ ከምናጣ እንዴት ነዉ ምዕራብ ትግራይንና በዝያ በኩል ያለዉን የኤርትራ ክፍል አገናኝተን የምናለማዉ፤ እንዴት ነዉ ድንበር አልባ ሆነን ለጋራ ሰላም በጋራ የምንጠብቀዉ፤ የቸገረንን እንዴት ነዉ ከኤርትራዉያን ጠይቀን፤ የተረፈንን አዉሰን አብረን የምንኖረዉ የሚለዉ ሃሳብ ለኛ ይጠቅመናል።» ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የእራት ግብዣ ላይ ያደረጉት ንግግር።
አዲስ አበባ በደስታ ላይ
የኤርትራ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጠ/ሚ ዐብይ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያና የኤርትራን የድንበር ላይ ጦርነት ለማስቆም የሁለቱ ሐገራት መሪዎች በ1993 አልጀርስ-አልጄሪያ ላይ የተፈራረሙትን ሥምምነት ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ መቀበሏን መወሰኑን ካስታወቁና ለኤርትራም የሰላም እጃቸዉን ከዘረጉ በኋላ ነዉ። የሁለቱ ሃገራት የድንበር ውዝግብ መፈታቱ ለሕዝቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሰላምም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተነግሮአል። ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሕመድ ኢትዮጵያና ኤርትራ ካካሄዱት የ2 ዓመቱ ጦርነቱ በኋላ«ሞት አልባ ጦርነት» ውስጥ ነበሩ ፤ «ሰላምም ጦርነትም የሌለበት» መባሉን እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።
በዓለም ሁሉ ይስፈንልን ሰላም
አንጋፋዉ ድምፃዊ መሃሙድ አሕመድ በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ለኤርትራዉያኑ ልዑካን በተካሄደዉ የእራት ግብዣ ላይ« ሠላም» ን አዜሞአል። በአንድ ላይ በሙዚቃዉ እጅ ለእጅ አያይዞ «በዓለም ሁሉ ይስፈንልን ሰላም» ሲል በጋራ አዚሞአል። ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በበኩላቸዉ፤ «የናፈቀን አስመራ መጥተን ወንድሞቻችንን ማቀፍ፤ መሳም ነው» ሲሉ ተናግረዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ «ከዚያ በመለስ ያሉ ጥያቄዎች ለእኛ በጣም ትናንሽ ናቸው። በፍቅር ከተግባባን ድንበር የምናሰምረው ሳይሆን የማያስፈልገን ሊሆን ይችላል» ብለዋል። አንድ የኤርትራ መንግሥት የመልዕክተኞች ቡድን ኢትዮጵያን በይፋ ሲጎበኝት ከ1990 ወዲሕ የዛሬዉ የመጀመሪያዉ ነዉ።
የኤርትራ ሕዝብም ከአጎራባቹ ጋር ሠላምን ይፈልጋል
አስመራ ውስጥ በተካሄደ የሰማዕታት መታሰቢያ የ72 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባሰሙት ንግግር፤ በኢትዮጵያ በጎ ምልክቶች በመኖራቸው ወቅታዊውን ሁኔታ ለመመርመር የኤርትራ ልዑካንን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ ያሳወቁት ኢትዮጵያ የድንበር ግጭትን ለማስቆም የተፈረመውን የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር መወሰኗን ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ካስታወቁ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነበር። ፕሬዚደንት ኢሳያስ «ለሁለቱ ሀገራት እና ህዝቦች መደጋገፍ የጋራ ጥቅም እና ብልጽግና የታገልንለት ለሁለት ትውልዶች መስዋዕትነት የከፈልንበት ቅዱስ ዓላማ ነው፤ ከእንግዲህ በንቃት የምንሳተፍበት ጉዳይ ነው» ብለዋል።
ሞት አልባ ጦርነት
ኢትዮጵያና ኤርትራ ከ1990 እስከ አልጀርሱ ስምምነት ለ 2 ዓመት ባደረጉት ጦርነት በመቶ ሺህዎች ሞተዋል። ስምምነቱ ውጊያውን ቢያስቆምም ዘላቂ ሰላም ለማውረድ የፈየደዉ ነገር የለም። ኢትዮጵያ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ለመቀበል የወሰነችው ሀያ ዓመት ያስቆጠረውን ፍጥጫና አለመተማመን ለማስወገድ ነው። የፖለቲካ ተንታኞች በመጀመርያ በሁለቱ ሃገራ መካከል መተማመን መጎልበት እንደሚኖርበት ይናገራሉ። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት በጎርጎረሳዊዉ 2000 ላይ በተፈረመዉ የአልጀርስ ስምምነትና የድንበር አካላዩ ኮሚሽን ዉሳኔ ላይ ከታዛቢዎቹ መካከል አንዱ በመሆኑ በሁለቱ ሃገራት ትስስር መጎልበት ላይ ጉልህ ሚናን መጫወት እንዳለበት ይናገራሉ።
የኢትዮጵያን እና የኤርትራን መቀራረብ የተለያዩ መንግሥታትና የፖለቲካ ተንታኞች በጎ ጅማሮ ታሪካዊ ሲሉ አወድሰዋል። ለሁለት አስርተ ዓመታት ተቋርጦ የነበረዉ የኤርትራና የኢትዮጵያ ይፋዊና ዲፕሎማስያዊ ግንኙነት አንድ ርምጃ ከፍ ብሎ በመታየቱ መደሰታቸውን በጀርመን የጀርመን-አፍሪቃ ድርጅት ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡሺ አይድ ገልጸዋል። እንዲያም ቢሆን ይህ አወንታዊ ክስተት ሊሆን የቻለዉ በአዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀና እና ደፋር ርምጃ ብሎም የኤርትራዉ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ ወገን የቀረበላቸዉን የሰላም ጥያቄ በአዎንታ በመቀበላቸዉ ነዉ፤ ብለዋል።