1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካቲት 6 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ የካቲት 6 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዱባይ ማራቶን ዳግም እጅግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በወንዶች 12ኛ ደረጃውን ብቻ ጣልቃ በማስገባት ከ1ኛ እስከ 13ኛ እንዲሁም በሴቶች ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃውን ተቆጣጥረውታል። በሆንግ ኮንግ የማራቶን ሩጫም ድሉ የኢትዮጵያውያን ሆኗል። የእግር ኳስና ሌሎች መረጃዎችም ተካተዋል።

https://p.dw.com/p/4NQPR
USA NFL Football | Philadelphia Eagles - Kansas City Chiefs
ምስል Matt Slocum/AP Photo/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በዱባይ ማራቶን ዳግም እጅግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በወንዶች 12ኛ ደረጃውን ብቻ ጣልቃ በማስገባት ከ1ኛ እስከ 13ኛ እንዲሁም በሴቶች ከ1ኛ እስከ 10ኛ ደረጃውን ተቆጣጥረውታል። በሆንግ ኮንግ የማራቶን ሩጫም ድሉ የኢትዮጵያውያን ሆኗል። በርካቶች ሲጠብቁት የነበረው የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ሊግ (NFL) ፍፋሜ ውድድርንም ቃኝተናል።  የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሻ ውጤቶችን በመጠኑ ዳሰናል።

አትሌቲክስ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተለያዩ ሃገራት በተደረጉ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅግ ደማቅ ውጤት አስመዝግበዋል። በዱባይ ማራቶን በወንዶችም በሴቶችም ሙሉ ለሙሉ ድሉ ለኢትዮጵያ ሆኗል። በወንዶች ውድድር ከአንደኛ እስከ 13ኛ ደረጃ ድረስ አንድ አትሌት ጣልቃ ከመግባቱ ውጪሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያኑ ተይዟል። በዚህ የዱባይ ማራቶን የመጀመሪያው በሆነው ፉክክር አትሌት አብዲሳ ቶላ 2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ በመሮጥ 1ኛ ወጥቷል። ከ9 እና ከ16 ሰከንዶች በኋላ ደሬሳ ገለቴ እና ሐይማኖት ዐለው ተከታትለው በመግባት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
አትሌቶች በስታዲየም መሮጫ መም ላይ ሲሮጡ እግሮቻቸው ይታያልምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

በሴቶች ተመሳሳይ የማራቶን ፉክክርም ኢትዮጵያውያቱ ከ1ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ተቆጣጥረውታል። አትሌት ደራ ዲዳ ያሚ በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ነው። ታዋቂዋ ሩቲ አጋ በሀገሯ ልጅ ደራ በ13 ሰከንዶች ተበልጣ የሁለተኛ ደረጃውን ይዛለች። ሥራነሽ ይርጋ ከደራ 48 ሰከንድ በኋላ በመግባት የሦስተኛውን ደረጃ ይዛለች።

የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥግናው ታደሰ የኢትዮጵያ አትሌቶች ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የዱባይ ማራቶንን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የቻሉበትን ምሥጢር ያጋራናል።

በዱባዩ ማራቶን የተገኙ ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች ለአትሌቶቹ ብርቱ ድጋፍ ከማሳየትም ባሻገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የተጀመረውን የተቀናጀ ወከባ በመቃወም ድምፃቸውን ሲያስተጋቡ ተሰምተዋል።

ከዱባዩ ማራቶን ባሻገር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት የሆንግ ኮንግ ማራቶንንም በበላይነት ተቆጣጥረው አሸንፈዋል። በዚሁ 25ኛው የሆንግ ኮንግ ማራቶን በሴቶች ውድድር ፋንቱ ኢቲቻ በአንደኛነት ለማሸነፍ የፈጀባት 2:27:50 ነው። ስንቄ ደሴ 2:34:46 በመሮጥ 2ኛ ስትወጣ፤ ጋዲሴ ነጋሣ 2:48:05 ሮጣ የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች። በወንዶች ፉክክር ደግሞ አትሌት ልመንህ ጌታቸው 2:11:25 በመሮጥ 2ኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ ገዛ ሠንበታ ሦስተኛ ሆኖ አጠናቋል። የገባበትም 2:11:59 ሰከንድ ነው። በዚህ ውድድር በአንደኛነት ያጠናቀቀው ኬንያዊው አትሌት ፊሊሞን ኪፕቱ ኪፕቹምባ 2:10:47 ሮጦ በመግባት አንደኛ ወጥቷል።

Frankreich Paris Sportler aus Äthiopien beim Paris Diamond league
ምስል ከክምችት፦ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ፓሪስ ከተማ በዲያመንድ ሊግ ሲወዳደሩምስል DW/Haimanot Tiruneh

የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ውል መፍረስ

ሲጠናቀቅ 60 ሺህ ታዳሚያንን ያስተናግዳል ተብሎለት የነበረው የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታን ለማከናወን ተስማምቶ የነበረው የቻይናው የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ በዋጋ ማስተካከያ አለመስማማት ውሉ መፍረሱ ተዘግቧል። እንደ ሪፖርተር ዘገባ ከሆነ፦ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት «ከቻይናው ካምፓኒ ጋር ድርድር ላይ እያለን ሦስት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ብረት ተሰርቋል» ብለዋል። የፕረጀክቱ ንድፍ ከ11 ዓመት በፊት ይፋ ሲደረግ የሚያስፈልገው 2,4 ቢሊዮን ብር ተብሎ ነበር። ግንባታው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2016 ተጀምሮ በ2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎም ነበር። የግንባታ ሒደቱ በተባለበት ጊዜ ሳይጠናቀቅ በተለያዩ ምክንያቶች ሲንከባለል ቆይቶም አሁን 17 ቢሊዮን ብር መጠየቁን የሪፖርተር ዘገባ ይጠቁማል። 

ሱፐር ቦውል

በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ሊግ (NFL)ፍፋሜ ባለድልን ለመለየት በሚደረገው እና እጅግ ተወዳጅ በሆነው የሱፐር ቦውል የትናንት ግጥሚያ ካንሳስ ሲቲ አሸንፏል። ከሦስት ዓመት በፊትም በፍጻሜው አሸናፊ የነበረው ካንሳስ ሲቲ ፊላዴልፊያ ኤግልስን ትናንት የረታው 38 ለ35 በሆነ ውጤት ነው። ብርቱ ፍክክር የሚታይበት የሱፐር ቦውል ውድድር ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቴሌቪዥን ሥርጭት ከፍተኛ ተከታታይ ያለው ስፖርት ነው። ምንም እንኳን እኩለ ሌሊት ቢሆንም የፍጻሜ ግጥሚያውን ጀርመን ውስጥም ከ1, 77 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ተከታትለውታል።

Super Bowl LVII - Philadelphia Eagles - Kansas City Chiefs
በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ሊግ (NFL) ፍፋሜ ምስል Ashley Landis/AP/dpa

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው አርሰናል በሳምንቱ መጨረሻ ነጥብ ሲጥል ማንቸስተር ሲቲ በግስጋሴ ተጠግቶታል። ትናንት ማንቸስተር ሲቲ አስቶን ቪላን 3 ለ1 ድል በማድረግ ነጥቡን 48 አድርሷል። አርሰናል በበኩሉ ቅዳሜ ዕለት ከብሬንትፎርድ ጋር አንድ እኩል በመለያየቱ ከማንቸስተር ሲቲ የሚበልጠው በሦስት ነጥብ ብቻ ነው። በሽንፈት እና ነጥብ በመጣል አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘው አርሰናል የፊታችን ረቡዕ የሚገጥመው ማንቸስተር ሲቲን ነው። በዚህ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲ ካሸነፈ ከአርሰናል ጋር በነጥብ ይስተካከላል። ሆኖም በርካታ የግብ ክፍያ ስላለው ግን ማንቸስተር ሲቲ የመሪነቱን ቦታ ከአርሰናል ይረከባል ማለት ነው። ትናንት ሊድስ ዩናይትድን 2 ለ0 ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድም በ46 ነጥብ የሦስተኛ ደረጃን ይዞ መሪዎቹን እጅግ ተጠግቷል። 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ከኤቨርተን ጋር ይጋጠማል። ይህ ውድድር ከወራጅ ቀጣናው ከ18ኛ ደረጃ ለመውጣት ለኤቨርተን ወሳኝ ሲሆን፤ በ29 ነጥብ ለተወሰነው ሊቨርፑል ግን ለጊዜው ብዙም የሚፈይደው ነገር የለም።

Bundesliga I FSV Mainz 05 - FC Augsburg
የቡንደስሊጋ ጨዋታ በከፊል፦ የማይንትስ እና አውግስቡርግ ቡድን ተጨዋቾችምስል Jan Huebner/IMAGO

በጀርመን ቡንደስሊጋ እጅግ በጠበበ የነጥብ ልዩነት አሁንም መሪው ባየርን ሙይንሽን፤ ዑኒዮን ቤርሊን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ እንደተከታተሉ ናቸው። ቅዳሜ ዕለት ቦሁምን 3 ለ0 ድል ያደረገው ባየርን ሙይንሽን 43 ነጥብ ሰብስቦ በቡንደስሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ አንደኛነት ሰፍሯል። በተመሳሳይ ቀን ላይፕትሲሽን 2 ለ 1 ድል ያደረገው ዑኒዮን ቤርሊን በ42 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃውን ይዟል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከትናንት በስትያ ቬርደር ብሬመንን 2 ለ0 አሸንፏል። 40 ነጥብ ይዞም ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሔርታ ቤርሊን ሽቱትጋርት እና ሻልከ ከ16ኛ እስከ 18ኛ የመጨረሻ ወራጅ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ