1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶናልድ ያማሞቶ የአፍሪቃ ቀንድ ጉብኝት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 16 2010

የዩኤስ አሜሪካ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዶናልድ ያማሞቶ  በኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳምንት ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ያማሞቶ ይህን የሶስት የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ጉብኝታቸውን ትናንት በኤርትራ በመጀመር ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተዋል።

https://p.dw.com/p/2wa5E
Karte Ethiopia und Eritrea ENG

«ኤርትራ እና ኢትዮጵያን የማቀራረብ ዓላማ ሊኖረው ይችል ይሆናል»

የዩኤስ አሜሪካ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዶናልድ ያማሞቶ ከትናንት ጀምረው በኤርትራ በጀመሩት የሶስት ቀናት ጉብኝታቸው በአስመራ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለቱ ሀገሮቻቸው የጋራ ጉዳዮች እና ትብብር ፣ እንዲሁም፣ በቀጣናው ጉዳይ ላይ ከፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር አቶ የማነ ገብረመሥቀል በግል የትዊተር ገጻቸው ያስነበቡት ጽሁፍ ያመለክታል።  ያማሞቶ ከሀገራቸው ኤምባሲ ሰራተኞች እና በዚያ ካሉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር እንደሚገናኙም የአሜሪካውያኑ ውጭ ጉዳይ ሚንስtር አስታውቋል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ አንድ ከፍተኛ የዩኤስ አሜሪካ ባለስልጣን ኤርትራን ሲጎበኝ ያማሞቶ የመጀመሪያው ሲሆኑ ይህ የጉብኝት አንዳንድ ጉዳዮችን እንዲንቀሳቀሱ ወይም ትኩረት እንዲያገኙ ሊያበረታታ እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዩሱፍ ያሲን ግምታቸውን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። 

USA Washington - Donald Yamamoto (L)
ምስል picture-alliance/dpa/J. Lo Scalzo


አሜሪካዊው የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ያማሞቶ መፍትሔ ላላገኘው የሁለቱ ሀገራት የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ለማስገኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ካሁን ቀደም መግለጻቸው ሲታወስ ምናልባት ያሁኑ ጉብኝታቸው ኤርትራ እና ኢትዮጵያን የማቀራረብ ዓላማ ሊኖረው ይችል ይሆናል የሚል ግምት ይሰማል። ይሁንና፣ እንደ ፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲን አስተያየት፣ ያማሞቶ በአፍሪቃ ቀንድ አሁን የጀመሩት ጉብኝት ይህን ዓላማ የማሳካት እቅድ መያዙ በርግጥ ባይታወቅም፣ የድንበሩ ውዝግብ የሚያበቃበትን መንገድ ለማፈላላግ ያስችል ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራ መረጃን ያላገናዘበ የተሳሰተ ውሳኔ አድርጋ የምትመለከተው ኤርትራ የሶማልያን ዓማፂ ቡድን  አሸባብን ትረዳለች በሚል የተመድ ም/ቤት የሶማልያ እና ኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን በጎርጎሪዮሳዊው 2009 ዓም የጣለባት ማዕቀብ ጉዳይ በጉብኝቱ ሊነሳ የሚችልበት አበረታቺ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል አቶ ዩሱፍ ይገምታሉ።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ