1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ወታደራዊ ሹማምንት ባለፈው ሳምንት መክረዋል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 18 2009

የባህረሰላጤዋ ትንሽ ሀገር ኳታር በኤርትራ እና ጅቡቲ ድንበር ያሰፈረቻቸውን ወታደሮች ከአካባቢው በማስወጣቷ በሁለቱ ሐገራት መካከል የነበረዉ ውጥረት ማገርሸቱ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ የሚከታተሉ ታዛቢዎችም ከጅቡቲ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን አንድምታ መፈተሽ ይዘዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2h8QW
China Djibouti Militärbasis
ምስል picture alliance/AP/Xinhua News Agencyvia/W. Dengfeng

የኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ወታደራዊ ሹማምንት መክረዋል

ጅቡቲ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ ወታደራዊ ቦታነቷን እያስመሰከረች መጥታለች፡፡ የፈረንሳይ ወታደሮች መናኸሪያ የነበረችው ትንሽይቱ የቀይ ባህር ዳርቻ ሀገር የአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስፔን እና ጃፓን ወታደሮችንም  እያስተናገደች ነዉ፡፡ ከአሜሪካ ጋር ለልዕለ ኃይልነት እየተፎካከረች ያለችው ቻይናም በዚያ የጦር ሰፈር መስርታ ወታደሮቿንም በዚህ ወር ወደ አካባቢው አንቀሳቅሳለች፡፡ 

እንዲህ ካለው ጦር ሰፈር የመትከል እሽቅድምድም ሌላ ጅቡቲ ባህረ ሰላጤውን እየናጠው የሚገኘው ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ተጠቂ መሆኗም ይነሳል፡፡ ኳታር ከጎረቤቶቿ የአረብ ባህረ ሰላጤ ሀገራት “ጽንፈኞችን ትረጃለሽ” የሚል ውንጀላ ቀርቦባት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ካቋረጠች በኋላ ከወሰደቻቸው ቀደምት ማስተካከያዎች አንዱ ጅቡቲ ላይ ተጽእኖ አሳርፏል፡፡ማስተካከያው በድንበር ይገባኛል ወደሚወዛገቡት ጅቡቲ እና ኤርትራ የላከቻቸውን የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ከአካባቢው ማስወጣት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ጅቡቲ አወዛጋቢውን የራስ ዱሜራ ተራራ የኤርትራ ወታደሮች ተቆጣጥረውታል ስትል ጅቡቲ ይፋ ክሷን ለአፍሪካ ህብረት አቅርባ ነበር፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የእውነት አፈላላጊ ቡድን ወደ ጅቡቲ የላከ ሲሆን በኤርትራ በኩል ግን እስካሁንም ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሆነ አሳውቋል፡፡ ጅቡቲ ባለፈው ሰኔ መጨረሻ በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ወቅት ህብረቱ የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ድንበሩ እንዲልክ ጥያቄ አቅርባለች፡፡ ይህ የጅቡቲ ጥያቄ በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራትም ተቀባይነት ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡

ይህ ጥያቄ በእንጥልጥል ላይ ባለበት ወቅት ነው እንግዲህ ከሀገሯ ውጭ የመጀመሪያውን የጦር ሰፈር በጅቡቲ የመሰረተችው ቻይና የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ድንበሩ ለመላክ እያጤነች እንደምትገኝ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያሳወቀችው፡፡ የቻይና የአፍሪካ ህብረት አምባሳደር የሆኑት ኩዋንግ ዌይለን ለአሶሴትድ ፕሬስ እንደተናገሩት “ሀገራቸው ጥያቄ ከቀረበላት በጅቡቲ እና ኤርትራ መካከል የተከሰተውን ውዝግብ ለማሸማገል” ሀሳብ አላት፡፡

China Soldaten auf dem Weg nach Militärstation Djibouti
ምስል Reuters/Stringer

አፍሪካ ኮንፊዴይንሻል የተሰኘዉ መፅሔት ምክትል አዘጋጅ አንድሪው ዌየር ይህን የቻይናን ያልተጠበቀ እርምጃ ሀገሪቱ በአካባቢው ካላት ስትራቴጂካዊ ጥቅም አንጻር መመዘን አለበት ይላሉ፡፡ “የቻይና አካሄድ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በቀጠናው ያልነበራትን ላቅ ያለ ሚና ለመወጣት እየተዘጋጀች መሆኑን ያሳያል፡፡ በደቡብ ሱዳን ግጭት እርዳታ ሰጥታለች፡፡ በጅቡቲ አዲስ የጦር ሰፈር ማቋቋሟ የሚያመለክተው ከከዚህ ቀደሙ ከፍ ባለ መጠን በአህጉሪቱ ቁልፍ ጥያቄዎች ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀቷን ነው” ብለዋል አንድሪው፡፡

ቻይና በጅቡቲ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ከሀገሪቱ ጋር እንደምትተባበር ሁሉ ዋነኛ መገልገያ የባህር በሯ በጅቡቲ የሆነው ኢትዮጵያም የሀገሪቱን ጉዳይ እንዲህ በዋዛ የምታልፈው አይመስልም፡፡ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንት መካከል ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የጋራ ስብሰባም የሚያስተላልፈው መልዕክት ከፍ ያለ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አቶ መለስ አለም ግን እንደዚህ አይነት ውይይቶች ከጅቡቲ ጋር በመደበኛነት የሚካሄዱ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በሁለቱ ሀገሮች መሪዎች እና ሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረግ የግንኙነት መርሃ ግብር እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡ የሀገራቱ የጋራ ድንበር ስብሰባም ባለፈው ታህሳስ ወር በጅቡቲ ላይ መካሄዱን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ደረጃም በሁለቱ ሀገሮች የሚደረግ መደበኛ እና ተከታታይ ግንኙነት እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

“እንደሚታወቀው በጅቡቲ እና ኢትዮጵያ መካከል [ያለው] በጣም ጠንካራ የሚባል ግንኙነት ነው፡፡ በሀለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር የተቀመጡ የአሰራር ሂደቶች አሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የእዚህ መደበኛ ግንኙነት የሆነ አካል ነው፡፡ የኢፌዲሪ የመከላከያ እና የጅቡቲ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ ውስጥ ውይይት አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የሀገር መከላከያ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሳሞራ የኑስ እና በጅቡቲ በኩል ደግሞ ጄነራል ዘካርያ የመሩት ቡድን ተወያይቷል፡፡ በቀጣይ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሊኖር የሚችልን ትብብር በተመለከተ ውይይት አድርገዋል፡፡” 

ኢትዮጵያ በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል የተቀሰቀሰውን ውጥረት በቅርበት እየተከታተለችው እንደሆነ መግለጿ አይዘነጋም፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ