1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 1 2014

https://p.dw.com/p/4B1vN
2. Fußball Bundesliga FC Schalke 04 - St.Pauli | Jubel Fans über Aufstieg
ምስል Laci Perenyi/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በባርሴሎና ማራቶን ትናንት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አረንጓዴውን ጎርፍ ደግመውታል። በወንድም በሴትም ዘርፍ በስፔኑ ፉክክር ኢትዮጵያ ልቃ ታይታለች። ከሻምፒዮንስ ሊግ የተሰናበተው ማንቸስተር ሲቲ የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን በእጁ የማስገባት እድሉን ከፍ አድርጓል። ሊቨርፑል ነጥብ በመጣሉ ማንቸስተር ሲቲ እስካልተሸነፈ ድረስ ዋንጫ የማግኘት እድሉ መንምኗል።  ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ የፔፕ ጓርዲዮላ ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ይጥላል ማለት ዘበት ነው ብለዋል። ሽንፈት ሲኖር ግን ሁኔታውን ለቅሶ ቤት አታስመስሉት ሲሉም በጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።  በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የ7 ጊዜያት ባለድሉ ሌዊስ ሐሚልተን ድል ርቆታል። በቡንደስሊጋው ወሳኝ ቦታዎችን ለመያዝ የሚደረገው የመጨረሻ ፉክክር ተጠናክሯል። 

አትሌቲክስ

Symbolbild Startlinie Startschuss
ምስል picture-alliance/Rolf Kosecki

ስፔን ውስጥ በተከናወነው የባርሴሎና የ2022 የማራቶን ሩጫ ሽቅድምድም ላይ ትናንት ኢትዮጵያውያት እና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ዘርፍ እጅግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በሴቶች የሩጫ ፉክክር ከ1ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ በኢትዮጵያውያት ሲያዝ፤ በወንዶቹም ቢሆን ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃውን ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ጠቅልለው ወስደውታል።

በወንዶች አትሌት ይሁንልኝ አዳነ የቦታውን ክብረወሰን ሰብሮ አንደኛ የወጣው 2 ሰአት ከ05 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ በመሮጥ ነው።  አትሌት ሀብሩ ረዳኸኝ 2ኛ (2:05:58)እንዲሁም ከበደ ዋሚ 3ኛ (2:06:03)ወጥተዋል።

መሠረት ገብሬ የቦታውን ክብረወሰን በመስበር ርቀቱን ያጠናቀቀችው 2 ሰአት ከ23 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመሮጥ ነው። አያንቱ ቁመላ 2ኛ (2:25:00)፣ ዘነቡ ፍቃዱ ሦስተኛ (2:25:11)ወጥተዋል። አትሌት ዘርፌ ልመንህ እና አትሌት ታደለች የ4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘዋል። 7ኛ ደረጃም በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጎዴ ጫላ ነው የተያዘው።   

ፕሬሚየር ሊግ

Jürgen Klopp und Pep Guardiola
ምስል Michael Regan/Getty Images

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ 3 ዙር ጨዋታዎች ብቻ ይቀሩታል። እስካሁን በተደረጉ 35 ግጥሚያዎች ትናንት ተጋጣሚው ኒውካስትልን 5 ለ0 ያደባየው ማንቸስተር ሲቲ በአስተማማኝ ሁኔታ በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው። በአንጻሩ በአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ሲከተል የነበረው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በቶትንሀም ጉድ ሆኗል። ደጋፊዎቹን እና ተጨዋቾቹን በሐዘን ድባብ እንዲዋጡ ባደረገው ግጥሚያ ሊቨርፑል ለአንድ ሰአት ግድም ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ ከቶትንሀም ጋር አንድ እኩል ነው የተለያየው። ለቶትንሀም በ56ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሆይንግ ሚን ሶን ነው። 74ኛው ደቂቃ ላይ ሉዊስ ዲያዝ ሊቨርፑልን ከሽንፈት የታደገችውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። ለአንድ ቀንም ቢሆን የፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥን ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል በነጋታው እሁድ ግን የማንቸስተር ድል መርዶ ነው የሆነበት። ለማንቸስተር ሲቲ ራሒም ስተርሊንግ የመጀመሪያዋን በ19ኛው ደቂቃ እንዲሁም የማሳረጊያዋ አምስተኛዋን ግብ በ93ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።  አይመሪክ ላፖርት በ38ኛው፣ ሮዲሪጎ በ61፣ እንዲሁም በጋብሪየል ጄሱስ 63ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ፊል ፎደን በ90ኛው ደቂቃ ላይ ግቦችን በተከታታይ አስቆጥረው ኒውካስልን ጉድ አድርገዋል።  

Jürgen Klopp und Pep Guardiola
ምስል Paul Ellis/AFP/Getty Images

ቸልሲ እና አርሰናልም ሦስት ጨዋታዎች እየቀራቸው በ67 እና 66 ነጥብ የሦስተኛ እና አራተኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ይዘዋል። አርሰናል ትናንት ሊድስን 2 ለ1 በማሸነፉ እና ቶትንሀም ከሊቨርፑል ጋር ነጥብ በመጋራቱ የ4ኛ ደረጃውን አጽንቷል። ቶትንሀም እና ማንቸስተር ዩናይትድ 62 እና 58 ነጥብ ይዘው በ5ኛ እና 6ኛ ደረጃ የአውሮጳ ሊግ የምድብ ግጥሚያ ደረጃ ላይ ሰፍረዋል። በእርግጥ አንድ ተስተካካይ እየቀረው 55 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስትሀም ዩናይትድ በቀጣይ ግጥሚያው ካሸነፈ ማንቸስተር ዩናይትድን ከአውሮጳ ሊግ ምድብ ተሳታፊነት ሊያስወጣው ይችላል። ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ ብዙም ልምድ በሌለው ብራይተን ቅዳሜ ዕለት እንዲያ 4 ለ0 መንኮታኮቱ ደጋፊዎቹን አስከፍቷል። ሊድስ፣ ዋትፎርድ እና ኖርዊች ለመሰናበት ከ18ኛ እስከ 20ኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል። በእርግጥ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው በርንሌይ እንደ ሊድስ 34 ነጥብ ኖሮት በግብ ክፍያ ብቻ መብለጡ ወደ ወራጅ ቀጠና የመግባት ስጋት አጥልቶበታል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቀርቶት 16ኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው ኤቨርተንም ነጥቡ 35 በመሆኑ ከወራጅ ቀጠናው በአስተማማኝ ሁኔታ ለመራቅ ቀጣይ አራት ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ይኖርበታል።  

ቡንደስ ሊጋ

በቡንደስሊጋ የሴቶች እግር ኳስ የዋንጫ ፉክክር ቮልፍስቡርግ ቡድን ተጋጣሚው ካርል ሳይስ ዬና ቡድንን እንደማይሆን አድርጎ አሸንፎታል። ትናንት አቤ ስፖርትፊልድ ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው የዋንጫ ግጥሚያ ዬናን ያሸነፈው 10 ለ1 በሆነ እጅግ ሰፊ የግብ ልዩነት ነው። ለዬና ቡድን ብቸኛዋን አንድ ግብ ዩሊያ አርኖልድ 79ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥራለች። 5 ነጥብ ብቻ ይዞ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ከሚወርደው ዬና ቡድን ጋር ትናንት የተደረገው ግጥሚያ ለደንቡ ያህል ነው እንጂ ቮልፍስቡርግ ዋንጫውን መብላቱን ቀደም ብሎ አረጋግጦ ነበር። የትናንቱ ግን የዘንድሮ የቡንደስሊጋ ድሉ ይፋዊ ተደርጎለታል። ባለፈው ዓመት ዋንጫውን የወሰደው ባየርን ሙይንሽን ዘንድሮ ለጥቂት በ4 ነጥብ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። የዘንድሮው ባለድል ቮልፍስቡርግ 56 ነጥብ ይዞ ነው ያጠናቀቀው።

Frauen Fußball Bundesliga | FC Carl Zeiss Jena - VfL Wolfsburg
ምስል Christian Modla/dpa/picture alliance

በወንዶች የቡንደስ ሊጋ ፉክክር በአንጻሩ ቮልፍስቡርግ 41 ነጥብ ይዞ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት ባደረገው ግጥሚያም ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ የመግባት ከፍተኛ እድል የነበረው ኮሎኝን 1 ለ0 በማሸነፍ ዕድሉን አደብዝዞበታል። የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ 52 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ለአውሮጳ ሊግ ለማለፍ ዕድሉን ያሰፋው ዑኒዮን ቤርሊን በ54 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ነው። 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፍራይቡርግ ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ የመግባት ዕድል አለው። ነጥቡም 55 ነው። ቡንደስሊጋው ሊጠናቀቅ አንድ ዙር ግጥሚያዎች ስለሚቀሩ ኮሎኝ ከሽቱትጋርት ጋር የሚያደርገውን ቀጣይ ጨዋታውን ካሸነፈ ለአውሮጳ ሊግም ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያም የማለፍ ዕድል አለው። ግን ደግሞ የዑኒዮን ቤርሊን እና ፍራይቡርግ ግጥሚያዎችን የመጨረሻ ውጤት ማየት አለበት። ዑኒዮን ቤርሊን ከቦሁም፤ ፍራይቡርግ ከባየርን ሌቨርኩሰን ጋር ቅዳሜ ይጫወታሉ።

አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፊዩርት 27 እና 18 ነጥብ ይዘው ዘንድሮ ከሚሰናበቱት ውስጥ ይገኛሉ። 30 ነጥብ ያለው ሽቱትጋርት በቡንደስሊጋው በቀጣይ የውድድር ዘመን ለመቆየት ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ከሚመጣው ቡድን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ አድርጎ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በሁለተኛው ዲቪዚዮን ሻልከ በ62 ነጥብ መሪ ሲሆን፤ ብሬመን በ60 ነጥብ፤ እንዲሁም ሐምቡርግ እና ዳርምሽታድት በ57 ነጥብ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ሰፍረዋል። በጠበበ የነጥብ ልዩነትም ቢሆን በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ ቡንደስሊጋው ማለፉን ያረጋገጠው ሻልከ ብቻ ነው።  ሳንክት ፓውሊን 3 ለ2 አሸንፎ ወደ ቡንደስሊጋው ማለፉን ባረጋገጠበት ዕለትም ወደ 2000 የሚጠጉ የሻልከ ደጋፊዎች ወደ ጨዋታ ሜዳው ተምመው በመግባታቸው በተፈጠረ መገፋፋት በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ሌሎቹ ሦስት ቡድኖች ማለትም ብሬመን፣ ሐምቡርግ እና ዳርምሽታድት ሁለተኛ ሆነው በቀጥታ ለማለፍ የሞት ሽረት ግጥሚያ ይጠብቃቸዋል። ነጥባቸው እጅግ ተቀራራቢ ስለሆነ ፉክክሩ ጠንካራ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከሦስቱ ቡድኖች አንደኛው የሦስተኛ ደረጃ ይዞ   ከቡንደስሊጋው 16ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሽቱትጋርት ጋር በደርሶ መልስ የመጋጠም የመጨረሻ ዕድልም አለው። ሁሉም የሁለተኛ ዲቪዚዮን ግጥሚያዎች የሚከናወኑት እሁድ እለት ነው።

Fussball 2. Bundesliga | 08.05.2022 | FC Erzgebirge Aue - SV Werder Bremen
ምስል jan Huebner/IMAGO

በቡንደስሊጋው ቅዳሜ ከላይፕትሲሽ ጋር የሚጋጠመው አርሜኒያ ቢሌፌልድ የማሸነፍ እድሉ እጅግ የመነመነ ነው። ባልታሰበ ሁኔታ ቢያሸንፍ እና ነጥቡን ከሽቱትጋርት እኩል ቢያደርግ እና ሽቱትጋርት በኮሎኝ ቢሸነፍ እንኳን ከመውረድ አይተርፍም። ምክንያቱም አርሜኒያ ቢሌፌልድ 26 የግብ እዳ አለበትና። ሽቱትጋርት የግብ እዳው 19 ነው። 57 ነጥብ ይዞ በ4ኛ ደረጃ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታውን እንዳያጣ ስጋት የገባው ላይፕትሲሽን አርሜኒያ ቢሌፌልድ በ8 የግብ ልዩነት ያሸንፋል ማለትም ዘበት ነው።

ይልቁንስ 30 ነጥብ ይዞ ቅዳሜ ከኮሎኝ ጋር የሚጋጠመው ሽቱትጋርት ካሸነፈ እና ሔርታ ቤርሊን በቦሩስያ ዶርትሙንድ ከተሸነፈ ከገባበት ጉድ በመውጣት በቡንደስሊጋው ለመቆየት ይችላል። በምትኩ ሔርታ ቤርሊን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ቡድን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ለማድረግ ይገደዳል ማለት ነው። ያም በመሆኑ ጨዋታዎቹ እጅግ አጓጊ ናቸው። 66 ነጥብ ይዞ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለክብሩ ሲል ላለመሸነፍ ይጫወት እንጂ ማሸነፉ የሚፈይድለት ነገር የለም።

Formel 1 Miami Grand Prix | Start
ምስል BRIAN SNYDER/REUTERS

የዘንድሮ የቡንደስሊጋ ዋንጫን መውሰዱን ያረጋገጠው ባየርን ሙይንሽን ነጥቡ 76 ነው። የቡንደስሊጋው የመጨረሻ ግጥሚያውን ቅዳሜ ዕለት ከቮልፍስቡርግ ጋር ሲያከናውን ነጥቡን 79 ሊያደርስ ይችላል እንጂ የሚቀየር ነገር የለም። የአውሮጳ ሻምፒዮንስ የምድብ ማጣሪያ ውስጥ መሳተፍ የሚችለው ፍራይቡርግ ባለበት ለመቆየትም አለያም የላይፕትሲሽን ቦታ ለመውሰድ እና የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን የግድ ቀሪውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ፎርሙላ አንድ

በሚያሚ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽስታፐን ድል ተቀዳጅቷል። በመሪነቱም እየገሰገሰ ነው። የመርሴዲሱ ሌዊስ ሐሚልተን ዘንድሮ ድል ርቆት በ7ኛ ደረጃ ላይ እየዋዠቀ ነው። በትናንቱ ሽቅድምድም የፌራሪ አሽከርካሪው ሻርል ሌክሌር የሁለተኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ ሌላኛው የቡድን አጋሩ ካርሎስ ሳይንስ የሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ