የግንቦት 9 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 9 2013አሊሰን ቤከር ሊቨርፑልን በመጨረሻዎቹ ሰከንዶች ከጭንቀት ታድጓል። የሻምፒዮንስ ሊግ የመነመነ ተስፋውንም አለምልሟል። በሴልታቪጎ የ2 ለ 1 ሽንፈት የገጠመው ባርሴሎና ከዋንጫ ውድድሩ ወጥቷል። በሴቶች ቡድኑ ግን ባርሴሎና ቸልሲን ትናንት 4 ለ0 ድል አድርጎ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ወስዷል። ቸልሲ በወንዶች ፉክክር የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን አስቀድሞ ያነሳው ማንቸስተር ሲቲን ከ12 ቀናት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ይገጥማል። በላሊጋው አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ ዋንጫውን ለማንሳት ተፋጠዋል። በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫ ባለድል የሆነው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቡንደስሊጋውም ቀንቶታል። ከቮልፍስቡርግ ጋር ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ በቀጣይ የውድድር ዘመን ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል።
በአውሮጳ ሊጠናቀቁ ስለተቃረቡት የሊግ ውድድሮች ከማንሳታችን በፊት የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የዘንድሮ ውድድር ክብረ ወሰን ስለተሰበረበት ጉዳይ አጠር አድርገን እናውሳችሁ። በብሔራዊ ቡድኑ የፊት መስመር አጥቂ የኾነው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ተጫዋች አቡበከር ናስር በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ የውድድር ዘመን በርካታ ጎል በማስቆጠር ክብረወሰን መስበር ችሏል። አቡበከር እስካሁን 27 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ይገኛል።
ከዚህ ቀደም በአንድ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግብ በማስቆጠር ክብረወሰን ይዞ የቆየው ጌታነህ ከበደ ነበር። በ2009 ዓ.ም ጌታነህ በአንድ የጨዋታ ዘመን 25 ግቦችን አስቆጥሮ ነበር። በዘንድሮው የውድድር ዘመን አቡበከር ከጌታነህ በ2 ግቦች መብለጥ ችሏል። እሱን በመከተል የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በ19 ግቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጌታነህ ከበደ በ12 ከመረብ ያረፉ ኳሶቹ ሦስተኛ ግብ አግቢ መሆን ችሏል። አሁን ወደ ዓለም አቀፍ የስፖርት ዘገባዎችን ነው የምንሻገረው።
ፕሬሚየር ሊግ
ሊጠናቀቅ ሁለት ዙር ግጥሚያዎች በቀሩት የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሦስት ቡድኖች ከወዲሁ መሰናበታቸውን አረጋግጠዋል። ከተሰናባቾቹ ቡድኖች መካከል በተለይ 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዌስት ብሮሚች ትናንት የሊቨርፑል ደጋፊዎችን ልብ ቀጥ አድርጎ 90 ደቂቃ መድረስ ችሎ ነበር። የትናንቱን ጨምሮ ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎችን አሸንፎ 9 ነጥብ ቢይዝ እንኳን ዌስት ብሮሚች ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከመሰናበት አይተርፍም። ከወራጅ ቀጣናው ውጪ 17ኛ ደረጃ ዘርዝ ላይ የሚገኘው ብራይተን ያለው 38 ነጥብ ነው። 26 ነጥብ ያለው ዌስት ብሮሚች ትናንት ሊቨርፑልን የባከነው ደቂቃ ሊገባደድ ሰከንዶች እስኪቀሩት ድረስ በአንድ እኩል አስጨንቆት ቆይቷል።
ለሊቨርፑል የትናንቱ ግጥሚያ እጅግ ወሳኝ ነበር። በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን በመሪነት ቆይቶ ወደ በኋላ ላይ በተከታታይ ነጥብ የጣለው ሊቨርፑል በቀጣይ የውድድር ዘመን በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የትናንቱን ግጥሚያ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበት ነበር። እናም በተደጋጋሚ ጊዜያት በደካማ አቋሙ ቡድኑን ነጥብ ያስጣለው ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር በ95ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት በጭንቅላት በመግጨት ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑ ታድጓል። የራሱንም ተደጋጋሚ ድክመት በወሳኝ ግብ ማካካስ ችሏል።
በሊቨርፑል የ129 ዓመት ታሪክም የባላጋራ ቡድን ላይ ግብ አስቆጣሪ ግብ ጠባቂ በመሆንም አዲስ ታሪክ ሠርቷል። ከአንድ ምዕተ ዓመት ከሩብ በላይ አንድ የሊቨርፑል ግብ ጠባቂ ግብ አስቆጥሮ ዐያውቅም። አሊሰን ቤከር የትናንቱን ግብ በቅርቡ በአደጋ ለተለዩት አባቱ መታሰቢያ አውሏል። የአሊሰን ቤከር አባት የ57 ዓመቱ ሆዜ አውጎስጢኖስ ቤከር ባለፈው የካቲት ወር ብራዚል ላቭራስ ዶ ሱል ውስጥ በሚገኘው የረፍት ጊዜ ማሳለፊያ መኖሪያ አቅራቢያ በጎርፍ ተወስደው ነበር በሞት የተለዩት።
የትናንቱ የአሊሰን ቤከር ግብ ሊቨርፑል ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍም ዳግም ዕድሉን በእጁ እንዲጨብጥ አስችሏል። ሊቨርፑል ቀጣይ ሁለት ውድድሮቹን ካሸነፈ 69 ነጥብ ይዞ ፕሬሚየር ሊጉን በማጠናቀቅ በቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል።
64 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ እና በ66 ነጥቡ የ3ኛ ደረጃውን የተቆጣጠረው ላይስተር ሲቲ ነገ የሚያደርጉት ግጥሚያ ነገሮችን የሚወስን ይሆናል። ሁለቱ አቻ ከወጡ ቸልሲ ቀጣዩን ውድድር ቢያሸንፍ እንኳን በ68 ነጥብ ነው የሚወሰነው። ላይስተር ሲቲ ነገ አቻ ወጥቶ የመጨረሻ ግጥሚያውን ካሸነፈ በ70 ነጥቡ ከሊቨርፑል ጋር ተያይዞ የሻምፒዮንስ ሊግ አላፊ ይሆናል። ላይስተር ሲቲ ካሸነፈ ግን 69 ነጥብ ስለሚኖረው ሁለቱን ጨዋታዎቹን ሊቨርፑል ካሸነፈ ተያይዘው ያልፋሉ።
የነገውን ጨዋታ ቸልሲ ካሸነፈ ግን ላይስተር ሲቲ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ አይቀርም። ምክንያቱም የመጨረሻ ጨዋታውን ቢያሸንፍ የሚኖረው 69 ነጥብ ብቻ ይሆናል። ያ ደግሞ ከሊቨርፑል ጋር እኩል ነጥብ እና እኩል የግብ ክፍያ ይኖራቸዋል። የሚለዩትም ሲያሸንፉ በሚያስቆጥሯቸው የግብ ብዛቶች ይሆናል ማለት ነው።
ሊቨርፑል ከነገ በስትያ ከበርንሌይ ጋር ሲጋጠም የመጨረሻ ጨዋታው እሁድ እለት ከክሪስታል ፓላስ ጋር ነው። በርንሌይ 15ኛ ደረጃ፤ ክሪስታል ፓላስ ደግሞ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱም ቡድኖች በሊቨርፑል ቢሸነፉም ቢያሸንፉም የሚቀየርባቸው ነገር የለም። በአንጻሩ ላይስተር ሲቲ በስተመጨረሻ የሚገጥመው ቶትንሀም ሆትስፐር የአውሮጳ ሊግ ቦታውን ላለመነጠቅ የሚደርገው የሞት ሽረት ግጥሚያ ነው። ቸልሲ በስተመጨረሻ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላን ይገጥማል።
ከወዲሁ መውረዳቸውን ያረጋገጡት ሦስት ቡድኖች ከታች ወደላይ ሼፊልድ ዩናይትድ 20ኛ፣ ዌስት ብሮሚች 19ኛ እንዲሁም ፉልሃም 18ኛ ናቸው። ማንቸስተር ዩናይትድ ከሲቲ በ13 ነጥብ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ 70 ነጥብ አለው። ላይስተር ሲቲ፣ ቸልሲ እና ሊቨርፑል ከሦስተኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ተደርድረዋል። ነገ እና ረቡዕ የሚደረጉ ወሳኝ ጨዋታዎችም ኹኔታዎችን በሙሉ የሚቀያይሩ ይሆናሉ።
ቡንደስሊጋ
አንድ ዙር ጨዋታ ብቻ በቀረው የጀርመን ቡንደስሊጋም ዋንጫውን አስቀድሞ መውሰዱን ያረጋገጠው ባየርን ሙይንሽን በ75 ነጥብ ይመራል። በጀርመን እግር ኳስ ማኅበር የዋንጫ ግጥሚያ በቦሪስያ ዶርትሙንድ የ4 ለ1 ብርቱ ሽንፈት የገጠመው ላይፕትሲሽ 65 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዋንጫውን የነጠቀው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 61 ነጥብ ይዞ ይከተለዋል። ቅዳሜ ዕለት ማይንትስን 3 ለ1 ድል ያደረገው ዶርትሙንድ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ቮልፍስቡርግ ጋር በነጥብ ተስተካክሎ ለሻምፒዮንስ ሊግ ማለፉን አረጋግጧል።
ቦሩስያ ዶርትሙንድን ከወደቀበት አፈር ያነሱት ወጣቱ አሰልጣኝ ኢዲን ቴርዚች በቀጣዩ የውድድር ዘመን ምክትል አሰልጣኝ ኾነው ይቀጥላሉ መባሉ እጅግ አነጋግሯል። የማርኮ ሮይስ ወደ ቀድሞ ብቃቱ መመለስ፣ የኧርሊንግ ኦላንድ ተከላካዮችን እያስጨነቀ የግብ ቀበኛ መሆን፣ የጄደን ሳንቾ ብቃት እና ፍጥነት እንዲሁም ዘንድሮ ጫማውን የሚሰቅለው የ35 ዓመቱ ሉቃስ ፒስቼክ አስደናቂ እንቅስቃሴዎች ዶርትሙንድን ለሻምፒዮንስ ሊግ አብቅቷል። በተጨማሪም ስድስት ግጥሚያዎችን በተከታታይ በማሸነፍ ቡድኑን ለድል ያበቁት አሰልጣኝ ኢዲን ቴርዚች ድርሻም የጎላ ነው። ማርኮ ሮይስ ማይንትስን ካሸነፉ በኋላ ስለ ቡድኑ ቀጣዩን ብሏል።
«ሁሉም ጥሩ አቋም ላይ ስለነበሩ፤ ግብ ስላስቆጠርን፤ እንደ ቡድን በጋራ የቻልነውን ስላደረግን ለድል በቅተናል። ለረዥም ጊዜ ራሳችን እንድንወቅስ ያስገደደን እና የተነጋገርንበትን ጉዳይ ባለፉት ሣምንታት ውስጥ ወደ ተግባር ቀይረናል። ቡድኑ በጥሩ አቋም ላይ እንዳለ ያሳያል።»
ወጣቱ አሰልጣኝ በተደጋጋሚ ሲሸነፍ የነበረ ቡድናቸውን ከተሰናባቹ አሰልጣኝ ሉቺያን ፋቭሬ ሲረከቡ እንኳን ሻምፒዮንስ ሊግ የቡንደስሊጋ ይዘቱም አጠያያቂ ነበር። ሉቺያን ፋቭሬ ሲሰናበቱ ግን ቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ማርኮ ሮስን ከቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ ለማምጣት አስቀድሞ ወስኗል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ግላድባኅ 7 ነጥብ አጥቷል። የዶርትሙንድ ምክትል አሰልጣኝ የነበሩት ኢዲን ቴርዚች በድል ላይ ድል ተጎናጽፈዋል። እናስ እንዲህ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ አሰልጣኝ ከሌላ ቡድን በሚመጣ አሰልጣኝ ስር ሆነው ይቀጥላሉ? ዐይታወቅም። የቡድኑ አመራር ግን ከወጣቱ አሰልጣኝ ጋር በምሥጢር የተነጋገሩት ነገር እንዳለ ተጠቅሷል። ምን እንደሆነ በሒደት የሚታይ ነው።
ላሊጋ
ባርሴሎና የትናንት ሽንፈቱ የአትሌቲኮ ድል ተደምሮ በላሊጋው ዋንጫ የማንሳት ዕድሉን አምክኗል። ቀዳሚዋን ግብ ለባርሴሎና በ28ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሌዮኔል ሜሲ ነበር። ሆኖም ሴልታቪጎዎች አቻ የምታደርጋቸውን ለማስቆጠር ከ10 ደቂቃ በላይም አልፈጀባቸውም። በ38ኛው ደቂቃ እና የማሸነፊያዋን ግብ መደበኛ የጨዋታ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በሚና ሎሬንትሶ አስቆጥረው ለድል በቅተዋል። ክሌሞ ሌንግሌ በ83ኛው ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ሁለት ቢጫ ካርድ በማየቱ ምክንያትም በሚቀጥለው ሳምንት ከአይበር ጋር በሚኖረው የመጨረሻ ግጥሚያም መሰለፍ አይችልም። በዚህም የላሊጋ የዘንድሮ ተሰላፊነቱን በቀይ ካርድ አጠናቋል።
በ37ኛው ዙር ግጥሚያ አትሌቲኮ ማድሪድ 83 እንዲሁም ሪያል ማድሪድ 81 ነጥብ ይዘው የመጨረሻ ግጥሚያቸውን ይጠብቃሉ። ሪያል ማድሪድ ዋንጫውን ለማንሳት ቀጣዩን ከቪላሪያል ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። የመጨረሻ ግጥሚያውን እሁድ ዕለት ከቫላዶሊድ ጋር የሚያደርገው አትሌቲኮ ማድሪድ ካሸነፈ የላሊጋውን ዋንጫ በእጁ ያስገባል። አቻ ቢወጣም ሪያል ማድሪድ በአራት ግብ ልዩነት ካላሸነፈ በስተቀር ዋንጫውን መውሰዱ አይቀርም። የአትሌቲኮ ማድሪድ እና የሪያል ማድሪድ ተጋጣሚዎች 7ኛ እና 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ከሚገኘው አይበር አንድ ከፍ ብሎ የሚገኘው ቫላዶሊድ ከመሪው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያደርገው ግጥሚያ ከወራጅ ቃጣናው ውስጥ ለመውጣት የሞት ሽረት ነው።
ሊዮኔል ሜሲ ከባርሴሎና ጋር የገባው ውል ዘንድሮ ይጠናቀቃል። እናም ከቡድኑ ጋር ለመቀጠል ውሉን ያራዝም እንደሆነም የሚታይ ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ