የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ የጉዞ ሰነድ ያልነበራቸው እና በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ታግተው የነበሩ 26 ኢትዮጵያዉያንን ማስለቀቁን አስታወቀ።
ነጻ የወጡት ኢትዮጵያዉያኑ በጆሃንስበርግ ከተማ ዳርቻ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ እርቃናቸውን ታጉረው ነበር።
የደቡብ አፍሪቃ ፖሊስ የቅድመ ወንጀል መከላከል ክፍል እንዳለው ፖሊስ ታጋቾች ወደነበሩበት ህንጻ በደረሰበት ወቅት ታግተው ከነበሩ ሰዎች በተጨማሪ 30 ያህል ሰዎች መስኮት ሰብረው ሳያመልጡ አልቀረም።
ፖሊስ ታጋቾችን ለማስለቀቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ያልተለመደ እንቅስቃሴ መመልከታቸውን ተከትሎ ጥቆማ ከሰጡ በኋላ እርምጃ መውሰዱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።
ታጋቾቹ ለምን ያህል ጊዜ ታግተው እንደነበሩ አልተገለጸም ። ነገር ግን ነጻ ከወጡት ታጋች ኢትዮጵያዉያን መካከል የጤና መታወክ የገጠማቸው አስራ አንዱ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
ከዚህ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ፖሊስ ሶስት ኢትዮጵያዉያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
ባለፈው የነሐሴ ወር 2016 በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 80 ያህል ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ማስለቀቁን የጠቀሰው የሀገሪቱ ፖሊስ በወቅቱ ታጋቾቹ ያለ በቂ ምግብ እና ዉሃ ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ታጉረው እንደነበር አስታውሷል።
ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ ስራ እና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንደሚጓዙ ዘገባው አስታውሷል።
ኢትዮጵያ ከስድስት አስርት ዓመታት ገደማ በኋላ እንደገና ያቋቋመችው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በይፋ ሥራ ጀመረ።
ገበያውን ሥራ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ እና የፋይናንስ ሥርዓት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት በገበያው 25 በመቶ ድርሻ ሲኖረው፤ የተቀረው 75 በመቶ በኢትዮጵያ ባለወረቶች እና የውጪ ኢንቨስተሮች የተያዘ ነው። የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ 48 ኢንቨስተሮች ያሉት ሲሆን 1.5 ቢሊዮን ብር ወይም 26 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ሰብስቧል። የኢትዮጵያ 16 የግል የንግድ ባንኮች፣ 12 የኢንሹራንስ ድርጅቶች እና ሌሎች 17 የሀገር ውስጥ ተቋማዊ ባለሐብቶች ድርሻ ገዝተዋል። ከውጪ ኢንቨስተሮች መካከል የናይጄሪያው ኤክስቼንጅ ግሩፕ እና በምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ገበያዎች የሚሰራው የኮሜሳ (COMESA) የንግድ እና የልማት ባንክ ይገኙበታል።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ በ11 ቀበሌዎች ላይ በተሰበሰበ ከ150 በላይ የሰብል ክምር ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን አርሶ አደሮች እና የአካባቢ ባለስልጣናት ተናገሩ።
በአደጋው ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት እህል ሲወድም ከ770 በላይ አርሶ አደሮችን ለችግር አጋልጧል።
በወረዳዉ 03 ቀበሌ ቀጭኔ ጎጥ ኗሪ የሆኑት ቄስ ተፈራ አናወጥ ትናንት ከሰዓት በኃላ ምክንያቱ ያልታወቀ እሳት ተነስቶ አዉድማ ላይ የነበረ 4 ክምር እህል እንዳቃጠለባቸው ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
በወረዳው ካለፈው ታህሳስ 5 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በተከታታይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የእህል ክምር መውደሙን ያመለከቱት የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙልየ የመኖሪያ ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው አርሶ አደሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው በእሳት አደጋ የእህል ክምር እና መኖሪያቸው የተቃጠለባቸውን ሰዎች ለመደገፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሃላፊው ጠቁመዋል።
በተያዘው አዲሱ የጎርጎርሳዉያን ዓመት ሱዳን ውስጥ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 3.2 ሚሊዮን ገደማ ሕጻናት ለአስከፊ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ እንደሚችሉ በመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ዩኒሴፍ አስጠነቀቀ።
ዩኒሴፍ እንዳለው በዓመቱ 772,000 ህጻናት እጅግ አስከፊ ለሆነ የምግብ እጥረት ሊጋለጡ ይችላሉ ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድጋፍ ባለፈው ወር ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በሱዳን አምስት አካባቢዎች ረሃብ ተከስቷል። እንደ ጥናቱ በዚህ አመት እስከ ግንቦት ወር ድረስ ወደ አምስት ተጨማሪ የምዕራብ ሱዳን ዳርፉር አካባቢዎች ሊስፋፋ ይችላል።
በተጨማሪም ሌሎች 17 የምዕራብ እና ማዕከላዊ የሱዳን አካባቢዎችም በተመሳሳይ ለረሃብ የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቱን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ይህንኑ ተከትሎም "አፋጣኝ፣ ያልተቋረጠ እና ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ አቅርቦት ምላሽን ካልተሰጠ ፣ በአካባቢዎቹ የምግብ እጥረት ሊጨምር ይችላል" ሲሉ በዩኒሴፍ የሱዳን ተወካይ እና የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ኢቫ ሂንድ አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው የጥቅምት ወር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች " ረሃብን እንደጦር ስልት ይከተላሉ " ሲል ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።
ናይጄሪያ በቀድሞ የነዳጅ ሚንስትሯ ተመዝብሮ ከሀገር የሸሸ ከ52 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማስመለስ ከአሜሪካ ጋር ተስማማች።
በስምምነቱ መሰረት የቀድሞው የነዳጅ ሚንስትር ዳያዛኒ አሊሰን እና አጋሮቻቸው ንብረቶች የተገኘ ከ52 ሚዮን ዶላር በላይ የሆኑ ሃብቶች ለናይጄሪያ መንግስት ተመላሽ እንደሚሆኑ የናይጄሪያ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ተመላሽ የሚሆነው የ50 ሚሊዮን ዶላር የዓለም ባንክ በሚመራው ፕሮጀክት የገጠር ኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ስራ እንደሚውል የፍትህ ሚንስትሩ ላጢፍ ፋግቤሚ ተናግረዋል። ፕሬጀክቱ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይሎችን ለማስፋፋት ያለመ ነውም ተብሏል።
ቀሪውን የ2.88 ሚሊዮን ዶላር ናይጄሪያ በመላው አፍሪካ ሽብርተኝነትን የመከላከል አቅም ለማሳደግ ለዓለማቀፉ የፍትህ ተቋም እንድትሰጥ ከስምምነት መደረሱን ሚንስትሩን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ናይጄሪያ በከፍተኛ ደረጃ ሙስና ከተንሰራፋባቸው እና በነዳጅ ዘይት ከበለጸጉ የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሽ ናት።
እስራኤል ዛሬ የመን ውስጥ በሁቲ አማጽያን ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።
እስራኤል በዛሬው የአየር ጥቃቷ በአማጽያኑ ይዞታ ስር ያሉ የኃይል ማመምጫ እና ወደቦች ዒላማ መደረጋቸውን ገልጻለች። ጥቃቱ የሁቲ አማጽያን ለሰነዘሩት የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶች አጸፋ መሆኑን የጠቆመው የእስራኤል መከላከያ መግለጫ የአማጽያኑን አዛዦች እንደሚያድንም ዝቷል።
በጥቃቱ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በምዕራባዊ የባህር ዳርቻ እና በማዕከላዊ የየመን ክፍሎች በተመረጡ ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውንም መግለጫው አመልክቷል። በሆዳይዳ እና ራስ ኢሳ ወደቦች የሚገኙ ወታደራዊ ይዞታዎች ዒላማ ከመደረጋቸው በተጨማሪ የሂዛዝ የኃይል ማመንጫ ጣቢያም እንዲሁ የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ ከአየር ጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ "ሁቲዎች ሃገራቸው ላይ ለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ቅጣታቸውን ያገኛሉ " ፤ ብለዋል።
የዛሬውን ጥቃት በተመለከተ ሁቲዎች ያሉት ነገር ስለመኖሩ በዘገባው አልተጠቀሰም።
የየመን መዲናን የተቆጣጠሩት ሁቲዎች በጋዛ በእስራኤል እና ሃማስ መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሃማስን በመወገን በእስራኤል ላይ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃት ሲሰነዝር ቆይቷል።
ታምራት ዲንሳ