1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 4 ቀን 2017 ዓ ም የዓለም ዜና

ልደት አበበ
እሑድ፣ ጥር 4 2017

ለአንድ ዓመት ገደማ ከዘለቀ ውጥረት በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ እና ለማጠናከር ተስማሙ። የሱዳን ጦር ወሳኝ እና ስልታዊ ያለውን የዋድ ማዳኒ ከተማን መልሶ መቆጣጠሩን አስታቀወ። ጀርመን 50 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ድጋፍ ለሶሪያ እንደምትሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በተሳተፉበት ጉባኤ ላይ ዛሬ ተናገሩ። በዩናይትድ ስቴትሷ ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢዋ የተከሰተው ሰደድ እሳት የሟቾች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ብሏል። የንጋፋው ፖለቲከኛና የምጣኔ ሐብት ባለሙያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ስርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈፀመ።

https://p.dw.com/p/4p50R


ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚኖራቸው አስታወቁ

ለአንድ ዓመት ገደማ ከዘለቀ ውጥረት በኋላ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ተስማሙ። ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ እና ለማጠናከር መስማማታቸውን ያስታወቁት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ትናንት ቅዳሜ  ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው።  በዚህም መሠረት ሁለቱም ሀገራት በየመዲናቸው ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ  ተወካይ ይኖራቸዋል። ለቀጠናዊ መረጋጋቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል መተማመን እና መከባበር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያስፈልግም ሁለቱ ሀገራት አጽንኦት ሰጥተዋል። መሪዎቹ ባደረጉት ውይይትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ማጠናከር እና ከጽንፈኛ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በተያያዘ  በጸጥታ ሁኔታ ላይ መስራት የመወያያ ርዕሶቻቸው እንደነበር ተዘግቧል።

 

የሱዳን ጦር  ስልታዊዋን ከተማ በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን አስታወቀ

የሱዳን ጦር  ወሳኝ እና ስልታዊ ያለውን የዋድ ማዳኒ ከተማን መልሶ መቆጣጠሩን አስታቀወ።  ከተማዋ ከአንድ ዓመት በላይ በተፋላዊው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በምህፃሩ RSF እጅ ነበረች። የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ በቴሌግራም ቻናላቸው በድምጽ ባስተላለፉት መልዕክት ሽንፈቱን ማመናቸውን የጀርመን ዜና ምንጭ ዲፒኤ ዘግቧል።  ዳጋሎ ለሁለት ዓመት ገደማ ባካሄዱት ትግላቸው  አንድ ዙር አሁን ቢሸነፉም ጦርነቱን ግን ሙሉ በሙሉ ተሸነፉ ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል። የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን በበኩላቸው ለይፋዊ ጉብኝት ከሚገኙበት ማሊ በመሆን ከሳህል ሀገራት ጋር አብረው መስራት እንደሚሹ ተናግረዋል።

እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሆነ በሱዳን በሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት መካከል በሚካሄደው ጦርነት የተነሳ ከ 12 ሚሊዮን በላይ ሱዳናውያን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ወይም ወደ ጎረቤት ሀገራት  ተሰደዋል።  25 ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝብ ደግሞ ግማሽ ያህሉ በቂ ምግብ አያገኝም።

 

ጀርመን   50 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ለሶሪያ እንደምትሰጥ አስታወቀች

ጀርመን  50 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ድጋፍ ለሶሪያ እንደምትሰጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ  በሳዑዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ በተሳተፉበት ዓለም አቀፍ  ጉባኤ ላይ ዛሬ አስታወቁ። እንደ የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገንዘቡ  ለተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና ለተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤  ለምግብ፣ መጠለያ እና ህክምና ለመሳሰሉ ጉዳዮች እንደሚውል ተናግረዋል። ቤርቦክ በሶርያ እርስ በርስ ጦርነት ወቅት ከባድ ወንጀል የፈፀሙ የበሽር አል አሳድ  አገዛዝ እና አባላት ላይ የተጣለው ማዕቀብም ባለበት እንዲቆይ ጠይቀዋል።  ለአመታት በጦርነት የወደመችውን ሶርያ እንዴት ማገዝ እንደሚቻል ለመምከር ዛሬ በርካታ የአካባቢው እና ምዕራዊ ሀገራት በሳውዲ አረቢያ ዋና ከተማ ሪያድ ተሰብስበዋል። ከሶሪያ ጎረቤት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች - ቱርክ ፣ ኢራቅ ፣ ርዳኖስ እና ሊባኖስ እንዲሁም የግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እና ኩዌት ተወካዮች በውይይቱ ለመሳተፍ ሪያድ መግባታቸው ተዘግቧል።

 

ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢዋ የተከሰተው  ሰደድ እሳት ተጠናክሯል

በዩናይትድ ስቴትሷ ሎስ አንጀለስ ከተማ እና አካባቢዋ የተከሰተው ሰደድ እሳት እንደ ሀገሪቱ አቆጣጠር ቅዳሜ ምሽት ወደ ምስራቅ እና ሰሜናዊ ክፍል በተለይም ደግሞ ብዙ ሰዎች ወደሚኖሩበት ሳን ፈርናንዶ ቫሊ ተጠናክሮ እንደነበር አዣንስ ፍራንስ ዘገበ።  እንደ ሎስ አንጀለስ ባለስልጣናት ገለፃ የሟቾች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ብሏል።  ምሽት ሰአታት ላይ በነበረው ነፋሻማ አየር እና ደረቅ እፅዋት ምክንያት የእሳት አደጋ ሰራተኞች እሳቱ የበለጠ እንዳይሰራጭ ለማድረግ እንዳላስቻላቸው ተዘግቧል።

ቅርብ ጊዜ የወጣ የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ መረጃ እንደሚጠቁመው 12,000 የሚጠጉ ሕንፃዎች፤ ተንቀሳቃሽ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች በእሳት ወድመዋል።  ከባድ ቃጠሎ በገጠማት የፓሲፊክ ፓሊሳዴስ ከ9,500 ሄክታር በላይ መሬት ወድሟል። በአልታዴና አካባቢ በነበረው የእሳት ቃጠሎ ደግሞ ተጨማሪ 5,650 ሄክታር መሬት ጋይቷል።  በካሊፎርኒያ ግዛት በተለይም የብዙ ኢትዮጵያውያን  መኖሪያ በሆነችው ሎስ አንጀለስ ከተማና አቅራቢያዋ ብዙ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ።

 

እውቁ ፖለቲከኛ እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ስርዓተ ቀብራቸው ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተፈፀመ

በ94 ዓመታቸው ባለፈው ሰኞ ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት አቶ ቡልቻ በብሔራዊ ስርዓት የአስከሬን ሽኝታቸው አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የአደዋ መታሠቢያ ሙዚየም ከተከናወነ በኋላ ስርዓተ ቀብራቸው ጳውሎስ-ወ ጴጥሮስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡ አደዋ መታሠቢያ ሙዚየም በተደረገው የሽኝት መርኃግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አቶ ቡልቻን የአገር ባለውለታ እና ለትውልዱ ትልቅ አርዓያ ሆነው በማለፍ ኃላፊነታቸውን በሚገባ የተወጡ ብለዋቸዋል። አቶ ቡልቻ ባለትዳርና የ6 ልጆች አባት ነበሩ፡፡ ከልጆቻቸው አንዱ አቶ ብስራት ቡልቻ በአስክሬን ሽኝት መርሃግብሩ እንደተናገሩት አባታቸው በሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ልብ «በሰናይ ምግባራቸው የሚታወሱ» ናቸው ሲሉ መግለፃቸውን ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።