1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥር 6 ቀን 2017 የዓለም ዜና

Negash Mohammedማክሰኞ፣ ጥር 6 2017

-የአፋር ክልልን በመታዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከቤት ንብረታቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎች በቂ ዕርዳታ እንዳላገኙ አስታወቁ።በመሬት መንቀጥቀጡ ከተጎዱ አካባቢዎች ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።ተፈናቃዮቹና ርዳታ አቀባዮች እንደሚሉት የምግብ፣የመድሐኒትና የመጠለያ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።----የሶማሊያ የፀጥታ ኃይላት በሐገሪቱ ሰሜናዊ ግዛት ሸምቀዉ ነበር ያሏቸዉን የእስላማዊ መንግስት (IS) ታጣቂዎች መግደላቸዉን አስታወቁ።-የእስራኤልና የሐማስ ተደራዳሪዎች ጋዛን የሚያወድመዉን ጥቃት ለማቆምና ታጋቾችን ለመልቀቅ የሚረዳ ስምምነት ለማድረግ መቃረባቸዉ እየተነገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4p8na

አዋሽ-የመሬት መንቀጥቀጥ ተፈናቃዮች በቂ ርዳታ አያገኙም-የርዳታ ሰራተኞች

 

በአፋር ክልል በተደጋጋሚ የደረሰዉን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሸሽተዉ በተለያዩ አካባቢዎች የሠፈሩ ነዋሪዎች በቂ ድጋፋ አለማግኘታቸዉን ተፈናቃዮችና የርዳታ ሠራተኞች አስታወቁ።በአፋር ክልል አዋሽ-ፈንታሌና ዱለቻ ወረዳዎች በሬክተር መመዘኛ እስከ 5.8 በሚደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለተከታታይ ሳምንታት ተመትተዋል።የመሬት መንቀጥቀጡ ሳቡሬ፣ ዶፈን፣ ቀበና በተባሉ ከተሞችና በርካታ መንደሮች ዉስጥ የሚገኙ ቤቶችና ሕንፃዎችን አፈራርሷል።ቤታቸዉ የፈረሰባቸዉና የመሬት መንቀጥቀጡ የእሳት ገሞራ ፍንዳታ ያስከትላል ወይም በአካባቢዉ የሚገኝ ግድብን ያፈርሳል ብለዉ የሠጉ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች አካባቢያቸዉን ለቀዉ ሸሽተዋል።የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ቢሮ (OCHA በምሕፃሩ) እንዳስታወቀዉ መንግሥት ለአደጋ የተጋለጡ 60ሺሕ ነዋሪዎችን አሽሽቶ የተሻለ ሥፍራ አሥፍሯል።ይሁና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ያነጋገራቸዉ ተፈናቃዮች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና ርዳታ አቀባዮች እንዳሉት በየግላቸዉም ሆነ በመንግሥት ድጋፍ ከየቀያቸዉ የሸሹት ነዋሪዎች በቂ ድጋፍ አላገኙም።

ሞቃዲሾ-የሶማሊያ መንግሥት ጦር የIS ተዋጊዎችን መግደሉን አስታወቀ

የሶማሊያ ሰሜናዊ ግዛት የፑንትላንድ ጦር ኃይል ባሪ አዉራጃ  ሸምቀዉ ነበር ያላቸዉን በርካታ የእስላማዊ መንግስት (IS) ተዋጊዎችን መግደሉን አስታወቀ።የጦሩ አዛዦች እንዳሉት የIS ተዋጊዎች ካል ሚስካት በተባለዉ አካባቢ ሸምቀዉ በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ ነበር።በጦር አዛዦቹ መግለጫ መሠረት ጦራቸዉ ምሽግ ይዘዉ ይዋጉ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎችን ገድሏል።ፈንጂ የተጫኑ 9 ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖችን (ድሮን) መትቶ ጥሏል።ስምንት አካባቢዎችን ተቆጣጥሯልም።የሟቹን ቁጥር ቁጥር ግን አልጠቀሱም።

 

ፖርት ሱዳን-የሱዳን ጦር ዉንጀላዉን አስተባበለ

የሡዳን መከላከያ ጦር በሐገሪቱ ማዕከላዊ ግዛት አል ጀዚራ ዉስጥ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል፣ አቁስሏል፣ አስሯልም የሚለዉን ወቀሳ አስተባበለ።የሱዳን መከላከያ ጦር ሰሞኑን አል ጀዚራ ግዛትን ይቆጣጠር በነበረዉ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፍቶ የግዛቲቱን ርዕሰ ከተማ ዋድ ማዳኒን ተቆጣጥሯል።የሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ ጠበቆች የተባለዉ ስብስብ እንዳስታወቀዉ ጦር ኃይሉ ዋድ ማዳኒን ለመቆጣጠር በከፈተዉ ጥቃት ቢያንስ 13 ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል።ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቀ ሰዎችን አቁስሏል።ድርጅቱ ትናንት ባወጣዉ መግለጫ የመከላከያ ጦሩና ተባባሪዎቹ ሚሊሺዎች ከገደሉና ካቆሰሏቸዉ በተጨማሪ ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን አስረዋል።ጦሩና ሚሊሻዎቹ ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ፣ያቆሰሉና ያሰሩት ከፈጥኖ ደራሽ ጦር ጋር ተባባብራችኋል በሚል ሰበብ ነዉ።የሱዳን መከላከያ ጦር ግን ወቀሳና ዉንጀላዉን አጣጥሎታል።

 

 ካይሮ-እስራኤልና ሐማስ ተኩስ ለማቆም ሊስማሙ ነዉ

የፍልስጤምን ግዛት ጋዛን ሠርጥን ያወደመዉን ድብደባ ለማቆም እስራኤልና ሐማስ የስምምነት ፍንጭ ማሳየታቸዉን ተደራዳሪዎችና ሸምጋዮች አስታወቁ።የአሜሪካዉ ዜና አገልግሎት አሶስየትድ ፕሬስ በድርድሩ የተሳተፉ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበዉ ሐማስ የተኩስ አቁሙን ረቂቅ ሰነድ ተቀብሎታል።የእስራኤል ተደራዳሪዎችም መጨረሻ የተባለዉን ሰነድን ለሐገሪቱ ካቢኔ እንደሚያቀርቡ አስታዉቀዋል።ድርድሩን ከሚመሩት አንዷ የሆነችዉ የቀጠር ባለሥልጣናትም እስራኤልና ሐማስ ስምምነት ለማድረግ «ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ ተቃርበዋል» ማለታቸዉ ተጠቅሷል።

እስራኤልና ምዕራባዉያን መንግስታት በአሸባሪነት የፈረጁት ሐማስ ደቡባዊ አምና መስከረም 29 ደቡባዊ እስራኤልን አጥቅቶ 1200 ሰዎች ገድሏል።ወደ 250 ሰዎች አግቶ ነበር።እስራኤል የሐማስን ጥቃት ለመበቀል ላለፉት 15 ወራት ጋዛ ላይ በከፈተችዉ መጠነ-ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ከ46 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዉያንን ገድላለች።የጋዛ ሰርጥን አብዛኛ አካባቢ አዉድማለች።ተስፋ የተደረገበት የተኩስ አቁም ስምምነት ተቀባይነት ካገኘ በጋዛ ላይ የሚደርሰዉ ድብደባ ይቆማል።እስካሁን እንደታገቱ የሚገኙ የእስራኤልና የሌሎች ሐገራት ዜጎች ይለቀቃሉ።

ሎስ አንጀለስ-የእሳት ቃጠሎዉ እንደቀጠለ ነዉ

የዩናይትድ ስቴትስን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ሎስ አንጀለስን የሚያጋየዉን ሰደድ እሳት ለማጥፋት የሚደረገዉ ጥረት በከባድ ነፋስና በደረቅ ዓየር ምክንያት እየተ,ደናቀፈ መሆኑን የእሳት አደጋ መከላከያ ባለሙያዎች አስታወቁ።8ኛ ቀኑን የያዘዉ ከፍተኛ ቃጠሎ እስከ ዛሬ ድረስ 24 ሰዎች ገድሏል።ከ12 ሺሕ የሚበልጡ ቤቶች፣ሕንፃዎችና ተቋማትን አዉድሟል።ከ170ሺሕ በላይ ሰዎችን አፈናቅሏል።ቃጠሎዉ ከ16 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬትን ሌጣ አስቀርቷል።በተለያዩ አካባቢዎች የሚቀጣጠለዉን እሳት ለማጥፋት ከ8000 በላይ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ከአየርና ከምድር እየታገሉ ነዉ።እሳቱን ለማጥፋት ከሚታገሉት ባለሙያ አንዱ ጃክ ዲን እንደሚሉት የቃጠሎዉ መጠን ከፍተኛ ነዉ ባይባልም ያደረሰዉ ጥፋት ግን አቻየለዉም።

                          

«ጥር ወር ነዉ።በዚሕ ጊዜ ቃጠሎ ባልነበረ ነበር።ቃጠሎዉ በጣም ከፍተኛ የሚባል አይደለም።ያደረሰዉ ጥፋት ግን ሲበዛ ከባድ ነዉ።ከዚሕ ቀደም ካሊፎርኒያ ዉስጥ በተነሱ ቃጠሎዎች ብዙ ቤቶች ወድመዋል።አሁን እዚሕ በትንሽ አካባቢ የማየዉን ያክል ጥፋት ግን አላየሁም።ሌሎቹ እሳቶች በጣም ትላልቅ ናቸዉ፤ ብዙ አካባቢዎችን ያዳርሳሉ።ይኸኛዉ ያደረሰዉ ጥፋት ግን በጣም ብዙ ነዉ።»

ደረቅ ዓየርና በሰዓት እስከ 120 ኪሎ ሜትር የሚገፋዉ ከባድ አዉሎንፋስ የእሳት መከላከሉን ጥረት እያደናቀፈዉ ነዉ።

ሔልሲንኪ-NATO ቦልቲክ ባሕር ላይ ጦር ሊያሰፍር ነዉ

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል ሐገራት ቦልትክ ባሕር ላይ ጦር ኃይል ሊያሰፍሩ ነዉ።ዛሬ ሒልሲኪ-ፊንላንድ የተሰበሰቡት ቦልቲክን የሚያዋስኑ የጦር ተሻራኪዉ ድርጅት አባል ሐገራት ሩሲያ በቦልቲክ ባሕር ዉስጥ የሚያልፉ የሥልክ፣የኤሌክትሪክ፣ የጋስና መስመል መስመሮችና ቧምቧዎችን ትቆርጣለች ወይም ታበላሻለች በማለት ወንጅለዋታል።ተሰብሳቢዎቹ «የፀጥታ ሥጋት» ያሉትን የሩሲያን እርምጃ ለመግታት በቦልቲክ ባሕር ላይ የሚደረግ እንቅስቃሴን የሚቃኙ አዉሮፕላኖች፣መርከቦችና የባሕር ኃይል ሰዉ አልባ አዉሮፕላኖች ለማስፈር ተስማምተዋል።በስብሰባዉ ላይ የተካፈሉት የጀርመን መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ የጀርመን ባሕር ኃይል አዲስ ለሚሰፈረዉ ጦር መርከቦች እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።በሩሲያ ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንደሚወስዱም አስጠንቅቀዋል።

«በድብቅ በሚቀዝፉ የሩሲያ መርከቦች ላይ እስካሁን የተጣለዉን ማዕቀብ ጨምሮ ተጨማሪ እርምጃ መዉሰዳችንን እንቀጥላል።እርምጃዉ ሥጋት በሚያስከትሉ በተወሰኑ መርከቦችና የመርከብ ኩባንዮች ላይ ያነጣጠረም ሊሆን ይችላል።»

የቦልቲክ ባሕርን ከሚያዋስኑ የNATO አባል መንግስታት ዉስጥ ከጀርመን በተጨማሪ ፊንላንድና ስዊድን የጦር መርከብ ለማዋጣት ቃል ገብተዋል።ኢስቶኒያ ከዚሕ ቀደም ባሕሩን የሚቃኝ መርከብ አስፍራለች።8ቱ የቦርልቲክ አካባቢ የNATO አባል ሐገራት ዴንማርክ፣ኢስቶኒያ፣ፊንላንድ፣ጀርመን፣ላቲቪያ፣ሉትዌንያ፣ፖላንድና ስዊድን ናቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።