1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 14 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 14 2015

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአውሮጳ ምድር የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደምቀው ታይተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ግስጋሴውን ቀጥሏል። መሪው አርሰናል ትናንት ነጥብ መጣሉ ማንቸስተር ሲቲ በነጥብ እጅግ እንዲቀርበው ዕድል ፈጥሮለታል። ለካታር የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ የሴኔጋሎቹ «የቴራንጋ አናብስት» ብርታት ከወዲሁ ስጋት ፈጥሯል።

https://p.dw.com/p/4IcR5
Katar Fifa World Cup 2022 Symbol
ካታር፦ ፊፋ የዓለም ዋንጫ ምልክት ከበስተጀርባግዙፍ ሕንጻዎች በምሽት ዕየታየምስል Nikku/XinHua/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአውሮጳ ምድር የሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደምቀው ታይተዋል። በስፔን፤ በአየርላንድ እና በስሎቬኒያ አትሌቶቻችን እንደተለመደው ድል ተቀዳጅተዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ግስጋሴውን ቀጥሏል። መሪው አርሰናል ትናንት ነጥብ መጣሉ ማንቸስተር ሲቲ በነጥብ እጅግ እንዲቀርበው ዕድል ፈጥሮለታል። ባለፈው ሳምንት ጠንካራ ቡድንን ያሸነፈው ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት ወራጅ ቀጣና ውስጥ በሚገኝ ቡድን መሸነፉ ደጋፊዎቹን አስደንግጧል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የመሪው ዑኒዮን ቤርሊን የትናንት ሽንፈት ከባየር ሙይንሽን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጎታል። ለካታር የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ የሴኔጋሎቹ «የቴራንጋ አናብስት» ብርታት ከወዲሁ ስጋት ፈጥሯል።

አትሌቲክስ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የተለያዩ የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያየ መስክ ድል ተቀዳጅተዋል። አየርላንድ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ አቀበት በበዛበት እና በውድድሩ ዋዜማ ምሽት በጣለው ብርቱ ዝናብ በጨቀየ ሳራማ ሜዳ በተደረገው ፉክክር ኢትዮጵያውያኑን የሚበግራቸው አልተገኘም። ከ500 በላይ አትሌቶች ተሳታፊ በሆኑበት የአየርላንድ የ8 እና የ6 ኪሎ ሜትር አገር አቋራጭ ውድድሮች በወንዶችም በሴቶችም ዘርፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንደኛ ወጥተዋል። 

በወንዶች የ8 ኪሎ ሜትር ሩጫ ፉክክር፦ ጊዜአለው አያና የ1ኛ ደረጃን ያገኘው 0:25:24 በመሮጥ ነው። ጊዜአለው በቅርቡ በተከናወነው የካርዲፍ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች አትሌቶች የዓለም ግማሽ ማራቶን ፉክክር ላይ የብር ሜዳሊያ ማስገኘት የቻለ ነው።

Symbolbild Leichtathletik Laufen
የተለያዩ ሯጮች እግር በቅርበት መወዳደሪያ መም ላይ ይታያሉምስል picture-alliance/dpa/B. Thissen

ኮሎምቢያ በተከናወነው እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች አትሌቶች የ5000 ሜትር የሩጫ ፉክክር ለኢትዮጵያ ወርቅ ያስገኘችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መዲና ኢሳም በአየርላንዱ ውድድር አሸናፊ ሆናለች። መዲና በ«ሮቢ ሪያ ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ» የ6 ኪሎ ሜትር የሩጫ ፉክክር 0:21:07 በመሮጥ ነው አንደኛ የወጣችው። በኮሎምቢያው ፉክክር መዲናን ተከትላ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መልክናት ውዱ ደግሞ ለጥቂት ተቀድማ የ2ኛ ደረጃን አግኝታለች። በአየርላንድ የስፖርት መገናኛ አውታሮች ታሸንፋለች ተብላ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው የብሪታንያዋ ሯጭ ኢዚ ፍሪ ከኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች 41 ሰከንድ በኋላ በመግባት የሦስኛ ደረጃን አግኝታለች።

በሌሎች የአትሌቲክስ የሩጫ ፉክክሮች፦ ትናንት በተካኼደው የስፔን 16ኛው የቫለንሺያ የግማሽ ማራቶን ውድድር ዮሚፍ ቀጀልቻ በ0:58:32 ሰከንድ 2ኛ ደረጃን አግኝቷል። ታደሰ ወርቁ ከዮሚፍ በ15 ሰከንዶች ተበልጦ አራተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል። በዚሁ ውድድር 0:58:09 በመሮጥ የአንደኛ ደረጃ ያገኘው ኬንያዊው ሯጭ ኪቢዎት ካንዲዬ ነው። ሌላኛው ኬንያዊ አትሌት ዳንኤል ማታይኮ ታደሰን በ7 ሰከንዶች ብቻ በልጦ የሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ዮሚፍ ቀጄልቻ በቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን ከሦስት ዓመት በፊት አሸናፊ ነበር።

ትናንት በተከናወነው የስሎቬኒያ የልዩብልያና ማራቶን ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት አዲሃና ገብረ ፃዲቅ 2:06:09 በመሮጥ 1ኛ ደረጃን ይዞ አሸንፏል። ኤርትራዊው ሯጭ ሄኖክ ተስፋዬ 2:07:12 ሮጦ በማጠናቀቅ የ2ኛ ደረጃን ይዟል።ኢትዮጵያዊው አትሌት አብደላ ጎዳና 2:08:55 በመሮጥ 4ኛ ደረጃን አግኝቷል። የሦስተኛውን ደረጃ ኬንያዊው ሌዮናርድ ላንጋት ይዟል። በሴቶች ተመሳሳይ የሩጫ ፉክክር ደግሞ፦ 2:21:09 የሮጠችው ሥራነሽ ይርጋ የ1ኛ ደረጃን አግኝታለች። 2ኛ ደረጃን በማግኘት ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ስንታየሁ ለውጠኝ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 2:22:38 ነው። አትሌት ሸጋ ማረጉ ኬንያዊቷ ጃኔት ሩጉሩን ተከትላ የ4ኛ ደረጃን አግኝታለች።

እግር ኳስ

BdTD | England
በርካታ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደጋፊዎች ተሰባስበው፥ በመሀል የመንገድ መብራት ላይም ሰዎች ተንጠላጥለው ምስል Oli Scarff/AFP/Getty Images

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አጓጊ እንደሆነ ቀጥሏል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በነበሩ ግጥሚያዎች፦ መሪው አርሰናል ትናንት ወደ ሳውዝሐምፕተን አቅንቶ ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል ተለያይቷል። በአስተማማኝ አቋም ላይ የሚገኘው ዋነኛ ተፎካካሪው ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ብራይተንን 3 ለ1 ድል አድርጓል። አርሰናል ትናንት ነጥብ መጣሉ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን ነጥብ ወደ ሁለት ብቻ አውርዶታል። 26 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ሲቲ በዚህ አያያዙ ዘንድሮም የፕሬሚየር ሊጉ ዋንጫን የሚያነሳ ይመስላል። 23 ነጥብ ይዘው የሊጉ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቶትንሀሞች ትናንት በሜዳቸው ባደረጉት ግጥሚያ በኒውካስል ዩናይትድ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግደዋል። ኒውካስል ነጥቡን 21 አድርሶ ከስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ተፈናጥሯል። አራተኛ ደረጃ የነበረው ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር አንድ እኩል በመለያየቱ በ21 ነጥቡ ወደ አምስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። በእርግጥ ኒውካስል እና ቶትንሀም እንዲሁም ፉልሀም 12 ጨዋታዎችን ካደረጉ ቡድኖች ውስጥ ይመደባሉ። በደረጃ ሰንጠረዡ ከላይ እንደሚገኙት አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ 11 ጨዋታዎችን ያደረገው ማንቸስተር ዩናይትድ 20 ነጥብ ይዞ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

የቀድሞ የሊቨርፑል ተጨዋች የነበረው አሰልጣኝ ሽቴፋን ጄራርድን ያሰናበቱት አስቶን ቪላዎች በጊዜያዊ አሰልጣኛቸው አሮን ዳንክስ መሪነት ብሬንትፎርድን ትናንት 4 ለ0 ድል አድርገዋል። ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ የመጨረሻዎቹ ረድፍ በሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት የ1 ለ0 አስደንጋጭ ሽንፈት ገጥሞታል። የኖቲንግሀም ፎረስት ተጨዋቾች በሜዳቸው ባደረጉት የሞት ሽረት ትግል የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድሉ ሊቨርፑልን አሸንፈው ቢቦርቁም በ9 ነጥብ ተወስነው፤ በደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ግርጌ 20ኛ ላይ ይገኛሉ። ሊቨርፑል የነበረበትን የ7ኛ ደረጃ ለፉልሃም አስረክቦ ወደ 8ኛ ደረጃ ተንሸራቷል።  ሊቨርፑል አሁን ባለበት ሁኔታ በዘንድሮ ውድድር ቢያንስ የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን እንኳን በሚያሰጋ አቋም ላይ ይገኛል።

ትናንት በነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ፉልሀም ሊድስ ዩናይትድን 3 ለ2 አሸንፏል። ዎልቨርሀምተን በላይስተር ሲቲ የ4 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል።  ኤቨርተን ክሪስታል ፓላስን 3 ለ0 አሸንፏል። ዛሬ ማታ ዌስትሀም ዩናይትድ ከቦርመስ ጋር ይጋጠማል። 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦርመስ ዛሬ ማታ ካሸነፈ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ ከሊቨርፑል ጋር በነጥብ በመስተካከል የ9ኛ ደረጃ ቦታውን ከብራይተን ይረከባል።  ድሉ 17ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ዌስትሀም ዩናይትድ ከሆነ ደግሞ ዌስትሀም ወደ ላይ ተወርውሮ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብሬንትፎርድ ቦታን ይረከባል። ሁለቱም ቡድኖች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ቢገኙም ዛሬ ማታ የሚያገኙት ድል ግን እንዲህ ወሳኝ ነው።

Fußball - Premier League - Liverpool vs Burnley
የሊቨርፑል አንፊልድ ስታዲየም፥ የሊቨርፑል እና በርንሌይ ጨዋታ በተደረገበት ወቅት ፎታ ከማኅደርምስል imago images/Colorsport

በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ቦሁምን 2 ለ1 ያሸነፈው ዑኒዮን ቤርሊን በ23 ነጥብ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት ሆፈንሀይምን 2 ለ0 በማሸነፉ 22 ነጥብ ይዞ      በሰንጠረዡ 2ኛ ደረጃን ይዟል። ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን አስተናግዶ የ2 ለ0 ድል የቀናው ፍራይቡርግ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፤ ነጥቡም 21 ነው። 14ኛው ደቂቃ ላይ ፍሪድል ኳስ ይዞ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት መለያ ክልል ለማለፍ የሞከረው የፍራይቡርጉ አጥቂ ሚካኤል ግሬጎሪችን ጠልፎ በመጣሉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከሜዳው ውጪ ባደረው ግጥሚያ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ1 አሸንፏል። 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሽቱትጋርትን 5 ለ0 አንኮታኩቶ ነጥቡን ወደ 19 ከፍ አድርጓል። ሽቱትጋርት፤ ቦሁም እና ሻልከ ከ16ኛ እስከ 18ኛ የመጨረሻ ደረጃ ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ተደርድረዋል።

የዓለም ዋንጫ መዳረሻ

ካታር ውስጥ የሚከናወነው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ሊጀመር 27 ቀናት ብቻ ቀርተውታል። አፍሪቃን ወክለው በዓለም መድረክ ከሚሰለፉ ቡድኖች መካከል ሴኔጋል ዘንድሮ ጠንካራው ቡድን እንደሆነ ይነገርለታል። የባየር ሙይንሽን አጥቂ ሳዲዮ ማኔን እና ሌሎች ምርጥ ተጨዋቾችን የሚያሰልፈው የሴኔጋል ቡድን ምናልባትም ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ ዕድል አላቸው ከተባለላቸው ጥቂት ቡድኖች መካከል ይገኛል። ሴኔጋል የቀኝ ወሳኝ ተከላካዩዋ ቦና ሳርን በጉዳት የተነሳ ዘንድሮ በዓለም ዋንጫ ማሰለፍ ባትችልም እንደ ትልቅ ችግር ግን የምታየው አይደለም።

ካታር፦ ፊፋ የዓለም ዋንጫ ምልክት ከበስተጀርባግዙፍ ሕንጻዎች ከፊት ጎብኚዎች ዕየታዩ
ካታር፦ ፊፋ የዓለም ዋንጫ ምልክት ከበስተጀርባግዙፍ ሕንጻዎች ከፊት ጎብኚዎች ዕየታዩምስል Karim Jafar/AFP/Getty Images

የቀድሞ የሊቨርፑል ወሳኝ አጥቂ ከነበረው ሳዲዮ ማኔ በተጨማሪ ሴኔጋል በአውሮጳ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች የሚሰለፉ ታዋቂ ተጨዋቾችን ታሰልፋለች። እንደ ሳዲዮ ማኔ ሁሉ የቸልሲዎቹ ግብ ጠባቂው ኤዱዋርድ ሜንዲ እና ተከላካዩ ካሊዱ ኩሊባሊም ወሳኝ ተጨዋቾች ናቸው። አማካዮቹ ኢድሪስ ጉዬ እና ቼኩህ ኩያቴ እንዲሁም አጥቂው ኢስማይላ ሳራ «የቴራንጋ አናብስት» በሚል የሚታወቀው የሴኔጋል እግር ኳስ ቡድንን በካታር ምድር እጅግ አስፈሪ አድርገውታል።

ሳዲዮ ማኔ በፍጹም ቅጣት መለያ ሴኔጋልን ለአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊነት ከማብቃቱ በፊት የቴራንጋ አናብስቱ ሻምፒዮን መሆን ያልቻሉ ግን ምርጦች በሚል ስያሜ ተወስነው ነበር። የቴራንጋ አናብስቱ ባለፈው ዓመት ጥር ወር መገባደጃ ላይ ግብጽን በፍጹም ቅጣት ምት መለያ አሸንፈው የአፍሪቃ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳታቸው አይዘነጋም።

ለዐሥርተ ዓመታት ጫፍ እየደረሱ ጫፉን መንካት ተስኗቸው የቆዩት ሴኔጋሎች ዘንድሮ የስኬት ግስጋሴያቸውን በካታሩ የዓለም ዋንጫም እንደሚያስቀጥሉ የብዙዎች እምነት ነው። አሰልጣኝ አሊዮ ሲሴም ወደ ካታር የሚያቀኑት ደረታቸውን ገልብጠው ነው።

ሴኔጋል የመክፈቻ ጨዋታዋን የምታከናውነው ከኔዘርላንድስ ጋር ነው። በምድብ ሀ ከሚገኙት አስተናጋጇ ካታር እና ኤኳዶር ጋርም ትፋለማለች። ቱኒዝያ፣ ሞሮኮ ጋና እና ካሜሩንም ሊጀመር ከአንድ ወር በታች በቀረው የካታር የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ አፍሪቃን ይወክላሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ