የጥቅምት 22 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥቅምት 22 2014የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር ትናንትና እና ከትናንት በስትያ ድል ቀንቶታል። በሁለቱ ቀናት ውድድር ብሔራዊ ቡድኑ 12 ግቦችን ሲያስቆጥር አንድም ግብ አልተቆጠረበትም።16 የሻምፒዮንስ ሊግ ቀጣይ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይከናወናሉ። አራት የጀርመን ቡድኖች ተጋጣሚዎች ናቸው። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ላይም ዳሰሳ አድርገናል።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሃገራት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች እግር ኳስ ውድድር የኤርትራ ቡድንን ዛሬ ኡጋንዳ ንጄሩ ስታዲየም ውስጥ 5 ለ0 አሸነፈ። በዛሬው ውድድርም ረድኤት አስረሣኸኝ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር እንደተለመደው ግብ አዳኝነቷን አስመስክራለች። ቀሪዎቹን ሦስት ኳሶች ከመረብ ያሳረፉት፦ ቱሪስት ለማ፤ መሳይ ተመስገን እና ብዙዓየሁ ታደሰ ናቸው።
ከትናንት በስትያ በነበረው ግጥሚያም የኢትዮጵያ ቡድን የጅቡቲ ቡድንን 7 ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት ነው ያሸነፈው። በቅዳሜው ግጥሚያ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረድኤት አስረሣኸኝ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርታለች። ቱሪስት ለማ ሁለት፤ እፀገነት ግርማ እና ቤተልሔም በቀለ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ግብ አስቆጥረዋል። ረድኤት አስረሣኸኝ ሔትሪክ በመሥራቷ የኳስ ተሸላሚ ሆናለች። በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ጥቅምት 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የጀመረው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ ሀገራት ውድድር ጥቅምት 30 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት በ2022 ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ውድድሩን ባለፈው ማክሰኞ ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ከውድድሩ የወጣው ለጥቂት ነበር። ዩጋንዳ ውስጥ 2 ለ0 የተረቱት ሉሲዎቹ አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ በተመሳሳይ ውጤት 2 ለ0 ድል ማድረግ ተሳክቶላቸው ነበር። ሆኖም በፍጹም ቅጣት ምት የዩጋንዳ ቡድን 2 ለ1 ሲያሸንፍ የኢትዮጵያ ቡድን ሁለት ኳሶች በተመሳሳይ አቅጣጫ የግቡ የቀኝ ማእዘንን መትተው ተጨናግፈዋል። ወደፊት በዋናው ቡድንም ሆነ በታዳጊዎቹ ቡድን ውስጥ የፍጹም ቅጣት ምት ስልጠና በልዩ መልክ ይበልጥ ሊሰጥ ይገባል።
ሻምፒዮንስ ሊግ
ነገ እና ከነገ በስትያ ለሻምፒዮንስ ሊግ 16 የመልስ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። ነገ እና ረቡዕ አራት የጀርመን ቡድኖች ይጋጠማሉ። ነገ ማታ ለሦስት ሩብ ጉዳይ ላይ ቮልፍስቡርግ በሜዳው ፎልክስቫገን አሬና ስታዲየም የአውስትሪያው ዛልትስቡርግ ቡድንን ይፋለማል። ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ ሲል ደግሞ ባየርን ሙይንሽን የፖርቹጋሉ ቤኔፊካን በሜዳው አሊያንትስ አሬና ስታዲየም ውስጥ ያስተናግዳል። ለባለፈው ግጥሚያ ፖርቹጋል ያቀናው ባየርን ሙይንሽን ከሜዳው ውጪ 4 ለ0 አሸንፏል።
ከነገ ወዲያ ደግሞ በተመሳሳይ ከምሽቱ አምስት ሰአት ላይ ላይፕትሲሽ የፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞን ሬድ ቡል አሬና ላይፕትሲሽ ስታዲየም ውስጥ ይገጥማል። ባለፈው ጨዋታ ላይፕትሲሽ 3 ለ2 ሽንፈት ገጥሞታል። አምስተርዳም አሬና ስታዲየም ውስጥ ባለፈው ግጥሚያ በሆላንዱ አያክስ 4 ለ0 የተረታው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ደግሞ ለመልሱ ጨዋታ ሲግናል ኤዱና ፓርክ ስታዲየም ውስጥ ቀጥሮታል። አትሌቲኮ ማድሪድን በሜዳው 3 ለ 2 ያሸነፈው ሊቨርፑል ከነገ በስትያ አንፊልድ ላይ ይገጥመዋል።
ማልሞ ከቸልሲ፤ ዲናሞ ኪዬቭ ከባርሴሎና፤ አታላንታ ከማንቸስተር ዩናይትድ፤ ቪላሪያል ከያንግ ቦይስ፤ ሴቪያ ከሊል እንዲሁም ጁቬንቱስ ከዜኒት ሴንት ፔተተርስቡርግ የሚጋጠሙት በነገው ዕለት ምሽት ነው። ረቡዕ ዕለት በሚኖሬት ጨዋታዎች፦ ኤሲ ሚላን ከፖርቶ፤ ሪያል ማድሪድ ከሻካታር ዶኔትስክ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከክሉብ ብሩዥ፤ ስፖርቲንግ ከቤሺክታስ እንዲሁም ሸሪፍ ከኢንተር ሚላን ጋር ተቀጣጥረዋል።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ሊድስ ዩናይትድ ኖርዊች ሲቲን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ዌስትሀም ዩናይትድ አስቶን ቪላን 4 ለ 1ረትቶ ነጥቡን 20 አድርሷል። ተመሳሳይ ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ የሚበለጠው በግብ ክፍያ ብቻ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በክሪስታል ፓላስ 2 ለ0 መሸነፉ በቀዳሚዎቹ ተርታ የነበረውን ግስጋሴ ለጊዜው ገትቶበታል። ቅዳሜ ዕለት በሰፋ የግብ ልዩነት 3 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ የደረጃ ሰንጠረዡን በ25 ነጥብ እየመራ ነው። ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ብራይተንን ገጥሞ ሁለት እኩል ተለያይቷል። በእለቱ ሊቨርፑል እንደ ሌላው ጊዜ የማሸነፍ ወኔ ዐልታየበትም። ከተከላካይ እስከ አማካይ ፍዘት ይስተዋልበት ነበር። በቅዳሜ ዕለት ጨዋታአቻ በመውጣቱ አጠቃላይ ነጥቡን 22 ከፍ ማድረግ አልቻለም። ከመሪው ቸልሲም በ3 ነጥብ ይበለጣል።
በርንሌይ፤ ኒውካስትል ዩናይትድ እና ኖርዊች ሲቲ ከ18ኛ እስከ መጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በሰፊ የግብ ልዩነቶች በተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠመው ማንቸስተር ዩናይትድ ባልተጠበቀ መልኩ ቶትንሀም ሆትስፐር ላይ ብርታቱን ዐሳይቷል። የ3 ለ0 ድል በመጎናጸፍም ነጥቡን 17 እንደ አድርሶ አምስተኛ ደረጃን ተቆናጧል። ከስሩ በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ የሚበለጠው እና ቅዳሜ ዕለት ላይስተር ሲቲን 2 ለ0 ድል ያደረገው አርሰናል ይገኛል። ድሉ ለአሰልጣኝነት ኦሌ ጉናር ሶልስካየር ትልቅ እፎይታ ቢመስልም በዕለቱ በጉዳት ምክንያት አላሰለፍኩትም ያሉት ፈረንሳዊ አጥቂ አንቶኒ ማርሻል ጉዳይ ለሌ ጣጣ አምጥቶባቸዋል። የአንቶቶኒ ማርሻል ባለቤት ሜላኒ በኢንስታግራም አድራሻዋ ባለቤቷ ምንም ጉዳት የሌለበት እና ለጨዋታ ዝግጁ የነበረ መሆኑን መናገሯ አሰልጣኙ ዋሽተዋል የሚል ቅሬታ አስነስቷል። እንዲያም ሆኖ ቅዳሜ ዕለት ከአራት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ያሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ከቡድናቸው ጋር አሉ። ለተቀናቃኝ ቡድኑ ቶትንሀም ሆትስፐር አሰልጣኝ ግን የቅዳሜ ዕለቱ ግጥሚያ የመሰናበቻ ጨዋታ ነበር።
የቶትንሀም ሆትስፐር አጣብቂኝ
ከአራት ወራት በላይ መቆየት ያልቻሉት የቶትንሀም ሆትስፐር አሰልጣኝ ኑኖ ኤስፒሪቶ በማንቸስተር ዩናይትድ በደረሰባቸው ሽንፈት ከቡድኑ መሰናበታቸው ዛሬ ተሰምቷል። ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከዎልቭስ ቡድን የአራት ዓመታት የስኬት ቆይታ በኋላ ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር የ2 ዓመታት ውል ፈርመው ነበር። አሰልጣኝ ኑኖ ቡድናቸው በገዛ ሜዳው በማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት 3 ለ0 መሸነፉ ለመባረራቸው ምክንያት እንደሆነ ተገልጧል። ቡድኑ ቅዳሜ ሲሸነፍ ከሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች አምስተኛ ጊዜው ነበር።
በቅዳሜው ጨዋታ፦ ሉቃስ ሙራን በሽቴቨን ቤርግዊጂን በቀየሩበት ወቅት ደጋፊዎች ስታዲየም ውስጥ የተቃውሞ ድምፃቸውን አስተጋብተው ነበር። «የምትሠራውን ዐታውቅም» ሲሉም አሰልጣኙን በጩኸት ተቃውመዋል። የለንደኑ ቡድን ቶትንሀም ሆትስፐር ዛሬ ይፋ ባደረገው መግለጫው፦ «አሰልጣኝ ኑኖ ኤስፒሪቶ እና ረዳቶቻቸው ኢያን ካትሮ፤ ሩይ ባርቦሳ እንዲሁም አንቶኒዮ ዲያስ መሰናበታቸው ቡድኑ ማሳወቅ ይችላል» ሲል ይነበባል።
ኑኖን የቶትንሀም ሆትስፐር የቀድሞው አሰልጣኝ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ አለያም የቀድሞው የቸልሲ አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ሊተኳቸው ይችሉ ይሆናልም እየተባለ ነው። የ52 ዓመቱ አንቶኒዮ ኮንቴ የሚያሰለጥኑት ኢንተር ሚላን ባለፈው የጨዋታ ዘመን የጣሊያን ሴ ሪ ኣ ዋንጫ አሸናፊ ነው። በአሁኑ ወቅትም ሚላን በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ትናንት በሴሪኣው ግጥሚያ ዑዲኒዜን 2 ለ0 አሸንፏል። አሰልጣኝ ኑኖ ኤስፒሪቶ የቶትንሀም ሆትስፐር አሰልጣንኝ የነበሩት እና በውጤት ማሽቆልቆል የተሰናበቱት አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪኞን ከተኩ ገና መንፈቅም አልሞላቸው ነበር። «ኑኖ ስርዓት ያላቸው ሰው ናቸው፤ ምንጊዜም እዚህ እንኳን ደህና መጡ የሚባሉ ናቸው» ያሉት የቶትንሀም ሆትስፐር የአስተዳደር ኃላፊ ፋቢዮ ፓራቲቺ፤ የቀድሞውን አሰልጣኝ አመስግነዋል። «እሳቸውን እና የአሰልጣኝ ክፍል አባላቶቻቸውን ወደፊት መልካም እንዲገጥማቸው እንመኛለን» ሲሉም በቶትንሀም ሆትስፐር ይፋዊ ድረ-ገጽ ላይ ጽፈዋል።
ቶትንሀም ሆትስፐር እስከአሁን ባደረጋቸው ዐሥር የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎቹ አምስቱን ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት ገጥሞታል።አሁን ባለው ነጥቡ ከአውሮጳ ሻምፒዮንስም ሆነ ከአውሮጳ ሊግ ውድድር ውጪ ነው። ቶትንሀም ሆትስፐር በደረጃ ሠንጠረዡ 15 ነጥብ ይዞ ስምንተኛ ላይ ይገኛል።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ተጋጣሚዎቹን በሰፋ ልዩነት ማሸነፉን ተያይዞታል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ተጋጣሚው ዑኒዬን ቤርሊንን በገዛ ሜዳው 5 ለ2 አሸንፏል። ቀዳሚዋን ግብ ጨዋታው በተጀመረ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ግብ አዳኙ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ነው። 23ኛ ደቂቃ ላይም ይኸው ፖላንዳዊ ግብ አዳኝ ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሯል። ሦስተኛዋ የባየርን ሙይንሽን ግብ የተቆጠረችው 35ኛው ደቂቃ ላይ በጀርመናዊው አማካይ ሌሮይ ሳኔ ነው። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት በ43ኛው ደቂቃ ላይ የዑኒዬን ቤርሊኑ ጀርመናዊ ተከላካይ ኒኮ ግሪትሰልማን ቡድኑ በዜሮ ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራት ያዳነውን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል።
ከእረፍት መልስ 61ኛው ደቂቃ ላይ ግብ የተጠሙት ባየር ሙይንሽኖች አጥቅተው በፈረንሳዊው አማካይ ኪንግስሌይ ኮማን 4ኛ ግባቸውን ከመረብ አሳርፈዋል። 65ኛው ደቂቃ ላይ ዑኒዬን ቤርሊን በኖርዌያዊው ተከላካይ ጁሊያን ራዬርሰን በኩል 2ኛ ግብ አስቆጥረዋል። ለባየር ሙይንሽን የማሳረጊያዋን አምስተና ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ ያሳረፈው ቶማስ ሙይለር ነው።
ባየርን ሙይንሽን እስካሁን ባደረጋቸው ዐሥር ጨዋታዎች ስምንት ጊዜ አሸንፎ አንድ ጊዜ በመሸነፍ እና አቻ በመውጣት ነጥቡን 25 አድርሷል። በደረጃ ሠንጠረዡ ላይም በመሪነት ተቀምጧል። ተፎካካሪው ቦሩስያ ዶርትሙንድም ተጋጣሚዎቹን በመርታት ባየርን ሙይንሽንን በ24 ነጥብ እግር በእግር እየተከተለው ነው። ከትናንት በስትያ ዶርትሙንድ ከ66 ሺህ በላይ ታዳሚዎች በተገኙበት በሜዳው ኤዱና ፓርክ ከኮሎኝ ጋር ባደረገው ግጥሚያ በቤልጂጋዊው አጥቂ ቶርጋን ሐዛርድ እና ሽቴፈን ቲገስ ሁለት ግቦች ኮሎኝን በባዶ አሰናብቶታል። ዶርትሙንድ የቅዳሜውን ጨዋታ ያሸነፈው የኖርዌዩ ግብ አዳኝ ኧርሊንግ ኦላንድ በሌለበት ነው።
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በተደረጉ የቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች፦ ትናንት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቦኹምን 2 ለ1 አሸንፏል። ሽቱትጋርት በአውግስቡርግ የ4 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። በቅዳሜ ዕለት ግጥሚያዎች ደግሞ፦ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቮልፍስቡርግ ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ0 በመርታት ነጥቡን እንደምንም 16 አድርሷል። በዕለቱ ማይንትስ አርሜኒያ ቢሌፌልድን 2 ለ1 ማሸነፍ ችሏል። ግሮይተር ፍዩርት እንደለመደው ሽንፈት ገጥሞት 3 ለ1 ተረትቷል። በዚህም መሠረት፦ በደረጃ ሰንጠረዡ 1 ነጥብ ብቻ ይዞ የመጨረሻ ግርጌ 18ኛ ላይ ይገኛል። ከበላዩ ዝቅተኛ ነጥብ ያላቸው አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና አውግስቡርግ ተደርድረዋል፤ አምስት እና ዘጠኝ ነጥብ ብቻ አላቸው።
ባለፈው የውድድር ዘመን ለአውሮጳ ሊግ ማለፍ የቻሉት አይንትራኅት ፍራንክፉርት፤ ቮልፍስቡርግ እና ላይፕትሲሽ ዘንድሮ በመንገታገት ላይ ናቸው። ላይፕትሲሽ ወደ አውሮጳ ሊግ ለመግባት የሚያስችለውን ደረጃ ማግኘት ተስኖት በ15 ነጥቡ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቅዳሜ ዕለት ከፍራንክፉርት ጋር ባደረገው ግጥሚያ አንድ እኩል አቻ ነው የተለያየው። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በ9 ነጥብ ብቻ 15ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ