1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

2018 የፕረስ ነፃነት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17 2010

እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ የያኔዉ የሶቭየት ሕብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን ጋዜጠኞችን «ፀረ-ሕዝብ» ብለዋቸዉ ነበር -ይላሉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት -የአፍሪቃ ተጠሪ አርናዉድ ፍሮዠር። በስልሳ ሰባተኛ ዓመቱ አምና ዶናልድ ትራምፕ ደገሙት «የሕዝብ ጠላት» ብለዉ።

https://p.dw.com/p/2wfBd
Symbolbild Pressefreiheit
ምስል picture-alliance/dpa/I. Langsdon

Press index - MP3-Stereo

ፖለቲከኞች፤ የሐገራት መሪዎች እና አምባገነን መንግሥታት በጋዜጠኞች  እና በመገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚንፀባርቁት ጥላቻ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለአደጋ ማጋለጡን ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት፤ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች አስታወቀ። ድርጅቱ አራተኛ ወሩን በያዘዉ በጎርጎርያዉያኑ 2018 የፕረስ ነፃነትን ይዞታ ባጠናበት ዘገባዉ እንደሚለዉ በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ዘዴዎች ላይ ያለዉ ጥላቻ እየተጠናከረ ነዉ። ጥላቸዉ የሚሰነዘረዉ ከአምባገነን መሪዎች ብቻ ሳይሆን የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዝደንት ከመሳሰሉት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጡ መሪዎች ጭምር ነዉ።
ርዕሠ መንበሩን ፓሪስ-ፈረንሳይ ያደረገዉ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች (RSF ይሉታል በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) እንደዘገበዉ፤ ጋዜጠኛ እና መገናኛ ዘዴዎችን እንደ አጥፊ ማንጓጠጥ፤ እንደተቀናቃኝ ማበሻቀጥ፤ ከሥራ ማገድ፤ እንደታጣቂ ጠላት በአሸባሪነት መወንጀል፤ ማሰር እና ማሰቃየት ለዓለም እንግዳ አይደለም።ዘንድሮ ብሷል።
በዘንድሮዉ የፕሬስ ነፃነት መዘርዝር ከ180 ሐገራት-180ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዉ ሰሜን ኮሪያ፤ ከሰሜን ኮሪያ ባንድ ደረጃ ተሽላ 179ኛ ላይ ያለችዉ ኤርትራ፤   176ኛነቱን የያዘችዉ ቻይናም ሆነች፤ 150ኛዋ ኢትዮጵያ፤ ጋዜጠኞች ያልታደኑ፤ ያልተሰሩ፤ ያልተወነጀሉበት፤ መገናኛ ዘዴዎች ያልተዘጉበት የቅርብ ዓመት ታሪክ የላቸዉም።

አምና የዶናልድ ትራምፕዋ ዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጠኞችን ከሚያስፈራሩ፤ ከሚሳደቡ እና ከሚያበሻቅጡት ጎራ መቀየጧ ነዉ የኋሊቱ ጉዞ። እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1950ዎቹ የያኔዉ የሶቭየት ሕብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን ጋዜጠኞችን «ፀረ-ሕዝብ» ብለዋቸዉ ነበር -ይላሉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት -የአፍሪቃ ተጠሪ አርናዉድ ፍሮዠር። በስልሳ ሰባተኛ ዓመቱ አምና ዶናልድ ትራምፕ ደገሙት «የሕዝብ ጠላት» ብለዉ።
                                  
«ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ መገናኛ ዘዴዎችን በማበሻቀጥ የታወቁ ናቸዉ። ጋዜጠኞችን የህዝብ ጠላት ብለዋል። ይሕ አገላለፅ ጆሴፍ ስታሊን ከ67 ዓመት በፊት የተጠቀሙበት ነበር።»
ከሆሊዉድ ፊልሟ እስከ ጂንስ ሱሪዋ፤ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓትዋ እስከ ከኮካ ኮላ መጠጥዋ የአሜሪካን ምርት የሚያፈቅረዉ እና አሜሪካን ለመከተል የሚሽቀዳደመዉ ዓለም ትራምፕን አብነ- አርአያዉ የማያደርግበት ምክንያት የለም። ከአዉሮጳ የቼክ ሪፐብሊክ፤ ከእስያ የፊሊፒንስ ፕሬዝደንቶች ለየጋዜጠኞቻቸዉ ትራምፕን ተከትለዉ ትራምፕን መስለዉ ጋዜጠኞቻቸዉን ያስፈራሩ ገቡ።
«አዉሮጳ እምብርት ላይ ለምሳሌ የቼክ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት የሚሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የሚከታተሉ ጋዜጠኞችን በአርቴፊሻል ክላሺንኮቭ አስፈራርተዋል። ከእስያ የፊሊፕንሱ ፕሬዝደንት ከመገደል ያመለጣችሁት ጋዜጠኛ ሥለሆናችዉ አይደለም ብለዉ ዛቱ።»

Türkei Protest
ምስል Getty Images/AFP/A. Altan

የትራምፕ ጥላቻ እና ማስፈራሪያ ድሮም ነፃ መገናኛ ዘዴዎች እና ጋዜጠኞችን ለማጥፋት ለማይተኙት ለአፍሪቃ ገዢዎች «ወትሮም ልክ ነበርን» ለማለት ጥሩ ማረጋገጪያ ነዉ የሆነዉ። እርግጥ ነዉ ጋምቢያ፤ ዚምባቡዌ እና አንጎላ ዉስጥ የሥርዓት ወይም የመሪዎች ለዉጥ በመደረጉ የፕሬስ ነፃነትም በመጠኑ መሻሻል አሳይቷል። ኢትዮጵያም መሪ ተለዉጧል። ብዙ ጋዜጠኞችም ተፈትተዋል። አምና ከነበራት ደረጃ ግን አልተሻሻለም። ከዓለም 150ኛ። ለምን? ፍሮዠር መልስ አላቸዉ። «ደረጃ የሚሰጠዉ ሐገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ነዉ። የ2001ዱ የፀረ-ሽብር ሕግ አሁንም ጋዜጠኞችን ያለፍርድ ለተወሰነ ጊዜ ለማሰር እያገለገለ ነዉ። ሐገሪቱ አሁንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ናት። ጋዜጠኞች በ2017 ሥራቸዉን ሲሰሩ ታስረዋል ወይም ታግተዋል።» 
ያም ሆኖ ከኬንያ በስተቀር ከሁሉም የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት የተሻለ ደረጃ ላይ ያለችዉ ኢትዮጵያ ናት። ጅቡቲ 173ኛ ደረጃ ይዛለች። ሱዳን 174ኛ። የጠና መንግሥት የሌላት ሶማሊያ ከጅቡቲም ከሱዳንም ትሻላላች። 168ኛ ናት። ግብፅ ከጅቡቲም፤ ከሱዳንም፤ ከሶማሊያም ትሻላለች። 161ኛ ናት። የኤርትራ ከአፍሪቃ ከማንም አይገጥምም።
                             
«ኤርትራ ከሰሐራ-በስተደቡብ ካሉ ሐገራት ብዙ ጋዜጠኞች የታሰሩባት ሐገር ናት።  11 ጋዜጠኞች አሁንም እንደታሰሩ መሆናቸዉን እናዉቃለን። በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ጋዜጠኞቹ ሥላሉበት ሁኔታ ምንም የሰማነዉ ነገር የለም። በሕይወት ሥለመኖራቸዉም የምናዉቀዉ ነገር የለም። ሥለዚሕ የኤርትራ (ጉዳይ) በጣም አሳሳቢ ነዉ።»
የፕሬስ ነፃነትን በማክበር የስካንድኒቪያ ሐገራትን የተፎካከረ የለም። ኖርዌይ ዘንድሮም እንዳምናዉ የአንደኝነቱን ደረጃ እንደያዘች ነዉ። ስዊድን ሁለተኛ ናት።ከተቀረዉ አዉሮጳ ኔዘርላንድስ ሽቅብ ወጥታ፤ ፊንላንድን ወደ አራተኛነት ገፍትራ የሰወስተኝነቱን ሥፍራ ተቆናጥጣለች። ጀርመን 11ኛ ናት። ዩናይትድ ስቴትስ አምና ከነበራት የ43ኛነት ደረጃ አሽቆልቁላ 45ኛ ሆነለች። -ዕድሜ ለትራምፕ።

Sudan Pressefreiheit Symbolbild
ምስል Getty Images/AFP/A. Shazly
Türkei - Friedensdemonstration in Solidarität mit Cumhuriyet
ምስል Reuters/M. Sezer

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ