ጋዛ የጦርነቱ ጀርባ ጥልፍልፍ
ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2006ለሙስሊሞች ቅዱሱ-ታላቁ የፆም-ፀሎት ወር ረመዳን ያበቃበት፤ የታላቅ ፌስታ ዕለት ነዉ ዛሬ። ኢድ-አልፊጥር። ከአስር ቀን በፊት በታላቁ የፀሎት-ሥግደት ዕለት ዓርብ በታላቁ አንዋር መስጊድ በታደሙ የአዲስ አበባ ሙስሊሞች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ሐይሎች የፈፀሙትን ድብደባ፤ እንግልትና እስራትን ያየ የሰማ የአዲስ አባባ ሙስሊሞችን ለዚሕ ታላቅ በዓል «በሰላም አደረሳችሁ» ማለት በርግጥ ከባድ ነዉ። የጋዛ ደግሞ ሲበዛ የከፋ ነዉ። በዓሉ ግን አዲስ አበቦች ቁስላቸዉ የሚጠርጉበት፤ እስረኞቻቸዉንየሚጠይቁበት ጋዛዎችም ሙቶቻቸዉንየሚቀብሩበት ፋታ ሆነ። ጋዛ ተኩስ ቆመ። እስከ መቼ አይታወቅም።
የእሥራኤል ጦር የጋዛ ሠላማዊ ሕዝብን መግደል፤ ማቁሠል፤ ማሰቃየቱን የሚቃወመዉ ሕዝብ ባለፈዉ ሳምንት ከቺካጎ-እስከ ለንደን፤ ከፓሪስ እስከ ኢስታንቡል፤ ከበርሊን እስከ ቴሕራን የሚገኙ አደባባዮችን በሠልፍ አጥልቅልቋቸዉ ሰነበተ።የእሥራኤል ደጋፊዎችም ተሠልፈዋል።ግን ቁጥሩ ከተቃዋሚዎቹን አንፃር ኢምንት የሚባል አይነት ነበር።ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ፤ ሊባኖስ፤ ዱባይ ሌላዉ ቀርቶ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎች ሮኬት በሚወርድባት ቴል አቪቭም የእሥራኤልን መንግሥት በመቃወም-አደባባይ የወጡ ነበሩ።
በ1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እሥራኤል በተመሠረተች ማግሥት የአረብ ሊግ ጋዛ ላይ የመላዉ ፍልስጤማዉያን መንግሥት እንዲመሠረት አዉጆ ነበር።አዋጁ የዛሬዉን የዮርዳኖስ ምዕራባዊ ወንዝ ዳርቻ ግዛትን ትገዛ የነበረችዉ ዮርዳኖስ የጋዛ ሠርጥን እንዳትጠቀልል ከማገድ ባለፍ-መንግሥት የመመሥረት ሙከራ፤ ጅምር፤ ፅናት አላማም አልነበረዉም።አዋጁ ካይሮ ላይ ተረቅቆ ፤ ካይሮ ተነግሮ-እዚያዉ ካይሮ ወረቅት ክምር መሐል ሲቀበር ጥንታዊቱ፤ ሥልታዊቱ፤ ትንሺቱ ሥርጥም በካይሮ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር መገዛቷን ቀጠለች።
በ1967ቱ ጦርነት የእሥራኤል ጦር ጋዛን-ከግብፅ፤ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን-ከዮርዳኖስ፤የጎላን ኮረብታን ከሶሪያ ቀምቶ የደማስቆ፤ካይሮ፤ አማን ገዢዎችን እርስ በርስ ከመሻኮት ገላገላቸዉ።በ1979 የግብፁ ፕሬዝዳንት አንዋር አሳዳት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ከሜናሔም ቤገን ጋር የሠላም ዉል ሲፈራረሙ እስራኤል ከግብፅ የማረከችዉን ሲናይ በረሐን አስመልሰዉ ጋዛን እስራኤል እንደያዘችዉ እንድትቀጥል ፈቀዱ።
ሳዳት ሥምምነቱን በመፈረማቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ በዓመት የሚቆረጥላቸዉን ሁለት ቢሊዮን ዶላር እያሰሉ «የጋዛ ዕጣ ፈንታ አጠቃላዩ» የፍልስጤሞች ጉዳይ ሲወሰን አብሮ ይወሰናል ብለዉ አለፉት-አለፈላቸዉ-ግን የሥምምነቱ መዘዝ ግን ካይሮ አደባባይ ሕይወታቸዉን አሳለፈዉ።ሳዳትን የተኩት ሆስኒ ሙባረክ የእሥራኤል-ወዳጁነት ያሜሪካኖች ጥቅም እንዳይቀርባቸዉ የፍልስጤሞችና ለፍልሴሞች የሚቆረቆረዉ ወገናቸዉም እንደ ሳዳት እንዳያሳልፋቸዉ ለሠላሳ ዘመናት በጥንቃቄ ተጓዙ።
እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የሠሞኑን አይነት ርምጃ በወሰደች ቁጥር ለፍልስጤሞች መቆርቆሩን ከማንም ቀድሞ የሚገልጠዉ የግብፅ ሕዝብ ነበር።የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን መንግሥት ባለፉት ሰወስት ሳምንታት በጋዛ ሕዝብ ላይ የወሰደና የሚወስደዉን ርምጃ የአዉሮጳ፤ አሜሪካ፤ የቱርክ-ፋርስ ሕዝብ አይደለም ቁጥራቸዉ አናሳ ቢሆንም የየሩሳሌሙ ነዋሪ ያይር ሐኮሕንን የመሳሰሉ እስራኤላዉያን ሳይቀሩ ተቃዉመዉታል።
«እንደሚመስለኝ የፍልስጤሞችን ጥያቄ በመዘንጋታችንና በመታበያችን አሁን ዋጋ እየከፈልን ነዉ። በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን መፈናፈኛ አሳጥተን መቆየት እንደማንችልና እንደማያዛልቀን ልንገነዘበዉ ይገባል።»
በሕዝብ ብዛትም፤ በጦር ሐይል ትልቅነትም ከአረቦች ቀዳሚዉን ሥፍራ ከምትይዘዉ፤ ለጋዛ ሕዝብ ከጋዛዎች ቀጥሎ ከማንም በላይ ታሪካዊ፤ ፖለቲካዊ፤ መልከዓ ምድራዊ ሐላፊነት ያለባት የግብፅ ገዢዎች ግን የእስራኤል እርምጃ ሊቃወሙ ቀርቶ ተራዉ ሕዝብ በአደባባይ እንዲቃወም እንኳን አልፈቀዱለትም።
ምክንያት እሥራኤል ላይ ሮኬት የሚያወነጭፈዉ ሐማስ የግብፁ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበር ቅርንጫፍ ወይም ጥብቅ ወዳጅ ነዉ።በግብፅ ሕዝብ የተመረጡትን የሙስሊም ወንድማማቾቹን ፖለቲከኛ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን ያስወገዱት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ የሙስሊም ወድማማች ጠላት ናቸዉ።ሐማስ ድሮም-ዘንድሮም የእሥራኤል ጠላት ነዉ።
አልሲሲና እስራኤል ምን-ምን ምን ናቸዉ? በ1979 ሳዳት፤ ቤገን፤ ካርተር ነበሩ።በ1994 ቢል ክሊንተን-ካርተር ያደረጉትን፤ የዮርዳኖስ ንጉስ ሁሴን ቀዳማዊ-ሳዳት፤የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን-ቤገን ያደረጉትን ደገሙት።በክሊንተን ሸምጋይነት ሁሴይናና ራቢን የሠላም ዉል ሲፈራረሙ እሥራኤል በ1967ቱ ጦርነት ከዮርዳኖስ የቀማችዉን የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን ግዛት «አጠቃላዩ የፍልስጤሞች ጉዳይ መልስ ሲያገኝ ይፈታል» ብለዉ አለፉት።
የጋዛ ሕዝብ ለግብፅ እንደመቅረቡ ሁሉ-የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሕዝብ ለዮርዳኖስ ቅርብ ነዉ።የእሥራኤል ጦር ጋዛን መደብደቡን ዮርዳኖስ አልተቃወመችም።ድብደባዉን በመቃወም አደባባይ የወጣዉ የምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሕዝብን የእሥራኤል ጦር ሲገድል-ሲደበድበዉ የአማን ገዢዎች ትንፍሽ አላሉም።ምክንያት እስራኤል ከእስራኤልም ይልቅ ለአማን ገዢዎች ዙሪያ መለስ ድጋፍ የምትሠጠዉ ዩናይትድ ስቴትስ ትቆጣቸዋለች።የረመላሕን የከንቲባነት ያክል እንኳን ሥልጣን ሳይኖራቸዉ «የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ፕሬዝዳንት» የሚል ሥም የተሸከሙት ማሕሙድ አባስ አምጠዉ አምጠዉ እስራኤል ጋዛን መዉረር ማጥፋቷን መቃወማችዉ አልቀረም።
ፈራ-ተባ እያሉ ያሰሙት ተቃዉሞ የሕዝባቸዉን ቁጣ፤ የእሥራኤሎችን ዱላ ለማብረድም ሆነ የአሜሪካኖችንም ይሁንታ ለማግኘት የተከረዉ አለመኖሩ ነዉ ድቀቱ።በስድስት ቀን ጦርነት ድፍን አረብን የረመረመችዉ እሥራኤልን በየሥስርቻዉ የሚሽሎኮሎኩት፤ የዉጊያ ዕዉቀት፤ ሥልጠና፤ በቂ መሳሪያ የሌላቸዉ የሐማስ ደፈጣ ተዋጊዎች ለሠወስት ሳምንት ያክል መዋጋታቸዉ ከፍልስጤሞች አልፎ በድፍን አረብ ተወዳጅ አድርጓቸዋል።
በ2006 ተድርጎ በነበረዉ ምርጫ አሸንፎ የነበረዉ ሐማስ ዳግም መግነኑ በአዉሮጳ ሕብረት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ጉዳይ አጥኚ ማቲያ ቶላዶ እንደሚሉት አቅመ ቢሱን መሪ ይበልጥ የሚሽመደምድ ነዉ።
«የሕዝብ ድጋፍን በተመለከተ እሳቸዉ (አባስ) በጣም እየተዳከሙ ነዉ።በዚሕ ሳምንት የተሰባሰበዉ የሕዝብ አስተያየት እንደሚያመለክተዉ ከሥልሳ ከመቶ የሚበልጠዉ ሐማስን ሲደግፍ፤ ለአባስ ቡድን ድጋፉን የሰጠዉ ሃያ-ሁለት ከመቶ ብቻ ነዉ።»
አባስ በራሳቸዉ ሕዝብ ጨርሶ ከመንኮታኮት የሚድኑት አንድም ሐማስ ከጠፋ፤ ሁለትም የእሥራኤሎች ልብ ራርቶላቸዉ ማብቂያ የሌለዉን የሠላም ድርድር ከጀመሩ፤ ሠወስትም ከሐማስ ጋር የጀመሩትን ተጣማሪ መንግሥት ካጠናከሩ ብቻ ነዉ።የእሥራኤል ዱላ ሐማስን ማዳካሙ አይቀርም ጨርሶ ሊያጠፋዉ ግን በፍፁም አይችልም።
የኔትንያሁ መንግሥት ቢሆንለት ሁለት ደካማ የፍልስጤም ቡድናት (ሐማስና ፋታሕ) «ሲቦጫጨሩ» ዳር ቆሞ ማየትን እንጂ ፤ብዙዎች እንድሚሉት፤ አባስን ለማዳን ሲል ወደ ድርድር ይገባል ብሎ ማሰብ ጅልነት ነዉ። ከሐማስ ጋር የጀመሩትን ጥምር መንግሥት ማጠናከር ለአባስ የተሻለዉ ምርጫ ነዉ።ግን ቶላዶ እንደሚሉት እስራኤል አትፍፈቅድም ።
«በእሥራኤል በኩል የአመለካከት ለዉጥ ይደረጋል ብዬ አላስብም።የእግረኛዉ ጦር ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት ጀምሮ ከእሥራኤል ጥቃት ዋነኛ አላማዎች አንዱ ተጣማሪዉን መንግሥት ማፍረስ ነዉ።ሥለዚሕ እሥራኤል በቅርብ ጊዜ ዉስጥ በሐማስ የሚደገፍ መንግሥት ትቀበላላች ብዬ አላስብም።ይልቅዬ ዩናይትድ ስቴትስና አዉሮጶች ተጣማሪ መንግሥት መኖሩን ይበልጥ እያመኑበት መምጣታቸዉን አምናለሁ።»
በሁለት ሺሕ ስድስቱ ምርጫ ያሸነፈዉን ሐማስን ከሥልጣን ያስወገደዉ የእሥራኤል ጠመንጃ፤ የአዉሮጳና የአሜሪካኖች ማዕቀብ እና የነአባስ ሻጥር ነበር።
አረብ የሐይማኖት መሪ፤ የሐብት ልዕለ ሐያል ሐገር ካለዉ ሳዑዲ አረቢያን የሚቀድም የለም።የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ መንግሥት በጋዛ ሕዝብ ላይ የሚወስደዉን እርምጃ የፋርስ፤ የቱርክ፤ የፓሪስ፤ የለንደን፤ የበርሊን ሕዝብ ባደባባይ ሲያወግዝ ከሪያድ የተሠማ ነገር የለም።
ማዉገዝ መቃወሙ ቀርቶ የቀጠር፤የቱርክ፤ የአዉሮጳና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ለሠላማዊ መፍትሔ ፍለጋ ሲዳክሩ የሪያድ ነገሥታት ጥምጣማቸዉ የተሸራተተባቸዉን ያክል እንኳን አልተንቀሳቀሱም።ምክንያት የግብፁን አምባገነን ገዢ ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን ለማስወገድ አብይ ሚና የተጫወቱዉ የሙስሊም ወንድማማቾች ማሕበርን ሪያዶች እኛም ጋ ይደገማል በሚል ሥጋት እንደጠላት ነዉ የሚያዩት።
ጄኔራል አል ሲሲ መሐመድ ሙርሲን ከሥልጣን ሲያስወግዱ ቀድመዉ የተደሰቱት፤ ለጄኔራሉ ዶላር ያንቆረቆሩት ሪያዶች ናቸዉ።ሐማስ የሙስሊም ወንድማማቾች ተቀጥላ ወይም ወዳጅ ነዉ።ሳዑዲ አርቢያ የሙስሊም ወድማማቾች ጠላት ናት።ሐማስ የእስራኤል ጠላት ነዉ።በየጠላትሕ ጠላት ስሌት የእስራኤልና የሳዑዲ አርቢያን ግኙነት- እርስዎ እንዴት ይፈርጁታል?
ሊቢያ፤ኢራቅ፤ሶሪያ እርስ በርስ እተጠፋፉ ነዉ።ቱኒዚያ ሕዝባዊ አመፅ ካዳፋት ወዲሕ በሁለት እግሯ ለመቆም ገና እየተዉተረተረች ነዉ።ነግሥታት የሚገዟት ሞሮኮ ከሪያድ፤ከአማንና ኩዌት የተለየች አይደለችም።የመን እንደ ሐገር ብትኖርም የምትተክረዉ የለም።አልጄሪያ እድሜም ጤናም የራቃቸዉን ሽማግሌ መሪዋን እያስታታመች ነዉ።
አረብ እርስ በርሱ እየተጠላለፈ-ይጥመለመላል።ሐያሉ ዓለም አንድም ተደፋፍጧል አለያም እስራእል እራሷን የመከላከል መብቷን «እስኪያቅለሸልሸን» እየነገረን ነዉ።በመሐሉ ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተኩስ አቁሙ ይላል።ማንሰምቶት? በኮሶቮና በአፍቃኒስታን የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቶም ኮኒግስ እንደሚሉት አባላቱ ለየጥቅማቸዉ የሚሻኮቱበት ደካማ ማሕበር ሰሚ አይኖረዉም።
«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ሊያገኝ ይገባል።ድርጅቱ አሁን በጣም ደካማ ነዉ ማለት ይቻላል።አዎ ድርጅቱ ልክ እንደሚያስተናብራቸዉ አባላቱ ደካማ ነዉ።አባላቱ ደግሞ አሜሪካኖች፤ ወይም እስራኤሎች ብቻ አይደሉም።ጀርመን፤ ዮርዳኖስ እና ሌሎቹም በድርጅቱ ዉስጥ ያሉት ሁሉም ናቸዉ።»
ለጋዛ ሕዝብ የተከረዉ የለም።ካለም ተፋላሚዎች አንድም ዳግም እስኪደራጁ፤ ሁለትም አቅም እስኪፈታተሹ፤ ወይም ደክሟቸዉ በገዛ ፍቃዳቸዉ ተኩስ ማቆማቸዉ ነዉ። እስከ ዛሬ ጋዛ ሕፃናት፤ ሴቶች፤ ሽማግሌዎች፤ አካለ ጎዶሎዎች ሳይለዩ ከአንድ ሺሕ ሰላሳ በላይ ነዋሪዎች አልቀዉባትል።ሰወስት ሺሕ ያሕል ቆስለዉባታል።እሥራኤል አርባ ሰዎስት ወታደሮች፤ ሁለት ሠላማዊ ስዎች አንድ የዉጪ እንግዳ ተገድለዉባታል።የዚያን ምድር ራብ፤ ጥም ለማስታገስ፤ የእስከዛሬዉ እስከሬን ደም ይበቃዉ ይሆን?
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ