1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥር 2 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ጥር 2 2014

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እሁድ ጥር 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ካሜሩን ውስጥ ከኬፕ ቬርዴ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያ አብዛኛውን ሰአት በ10 ተጨዋቾች ተጋጥሞ አንድ ለዜሮ ተሸንፏል። በጀርመን ቡንደስሊጋ በርካታ ተጨዋቾቹን በኮቪድ-19 የተነሳ ማሰለፍ ያልቻለው ባየርን ሙይንሽን ሽንፈት ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/45M2k
Fußball Africa Cup of Nations | Äthiopien v Kap Verde
ምስል Kenzo Tribouillard/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እሁድ ጥር 1 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ካሜሩን ውስጥ ከኬፕ ቬርዴ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያው አብዛኛውን ሰአት በ10 ተጨዋቾች ተጋጥሞ አንድ ለዜሮ ተሸንፏል። ቡድኑ በ8ኛው ደቂቃ አካባቢ በተከላካዮች በተሠራ ጥፋት የቀይ ካርድ ሠለባ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ከኬፕ ቬርዴ በኩል ይደርስበት የነበረውን ጫና ሲከላከል ቆይቷል። ስለጨዋታው አጠቃላይ ኹኔታ እና ስለቀጣይ ግጥሚያ ማብራሪያ የሚሰጠን የስፖርት ጋዜጠኛ አነጋግረናል። በጀርመን ቡንደስሊጋ በርካታ ተጨዋቾቹን በኮቪድ-19 የተነሳ ማሰለፍ ያልቻለው ባየርን ሙይንሽን ሽንፈት ገጥሞታል። በአንጻሩ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሲመራ ቆይቶ የማታ ማታ ለድል በቅቷል። በሳምንቱ መጨረሻ የተከናወነው የእንግሊዝ የኤፍ ኤ ካፕ ጨዋታ ቀጥሎ ዛሬ ማታ ማንቸስተር ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም አስቶን ቪላን ይገጥማል። 

እግር ኳስ
በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚከናወነው 33ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳታፊ የኾነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ትናንት ከኬፕ ቬርዴ ጋር ባደረገው የመጀመሪያ ግጥሚያው አንድ ለዜሮ ተሸንፏል። የሶከር ኢትዮጵያ የስፖርት ድረ-ገጽ አዘጋጅ ሚካኤል ለገሰ ቡድናችን ገና ከመነሻው ቀይ ካርድ ማግኘቱ እጅግ እንደጎዳው ገልጧል። ቡድኑ ከ80 ደቂቃ በላይ በ10 ተጨዋቾች ብቻ ተወስኖ ለመጫወትም ተገዷል። ስለቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ለመናገር በትናንቱ ኹኔታ አስቸጋሪ መሆኑን ሚካኤል ጠቁሟል። 

የአፍሪቃ ዋንጫ የምድቡ የመጀመሪያ ግጥሚያውን እሁድ ጥር አንድ ቀን ከኬቬርዴ ቡድን ጋር ያካኼደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ በመቀጠል ሐሙስ ጥር አምስት ቀን ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር ይፋለማል። ሦስተኛ ጨዋታውን ሰኞ ጥር 9 የሚያከናውነውም ትናንት አዘጋጇ ካሜሩንን ካስጨነቀው የምድቡ ሌላኛው ብርቱ ቡድን ቡርኪናፋሶ ጋር ነው። ያውንዴ ከተማው ውስጥ ሲመራ የነበረው ካሜሩን 40ኛው እና የመጀመሪያው መደበኛ አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመረው 3ኛ ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምቶች ባገኘው ዕድሎች ትናንት ቡርኪናፋሶን 2 ለ1 አሸንፏል። የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ዛሬ እና ነገ ቀጥለው እስከ ረቡዕ ይከናወኑ እና ሐሙስ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያዎች ይቀጥላሉ።
ቡንደስሊጋ 
በሳምንቱ መጨረሻ በተከናወኑ የጀርመን ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች ፍራንክፉርት የማታ ማታ ድሉን በቦሩስያ ዶርትሙንድ ተነጥቋል። መሪው ባየርን ሙይንሽን በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ሽንፈት ገጥሞታል። 9 ተጨዋቾቹን በኮቪድ-19 ማሰለፍ ያልቻለው ባየርን ሙይንሽን ቅዳሜ ዕለት በሜዳው አሊያንስ አሬና በበ‍ሩስያ ሞይንሽንግላድባህ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። ለቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ እጀግ ወሳኝ በሆነው ድል ባየርን ሙይንሽን ታዳጊ ተጨዋቾችን ለማሰለፍ ቢገደድም ሽንፈቱን ግን አስተናግዷል። ላባየር ሙይንሽን 9 ወሳኝ ተጨዋቾች በኮቪድ ምክንያት ካለመሰለፋቸው በተጨማሪ ቺፖ-ሞቲንግ እና ዛር ለአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ በቡድናቸው ውስጥ አልተገኙም። 

Fußball Africa Cup of Nations | Kamerun v Burkina Faso
ምስል Kenzo Tribouillard/AFP
Fußball Africa Cup of Nations | Äthiopien v Kap Verde
ምስል Kenzo Tribouillard/AFP

ቀዳሚውን ግብ በ18ኛው ደቂቃ ላይ በሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ያስቆጠረው ባየርን ሙይንሽን በመሪነት የቆየው ለ9 ደቂቃ ያህል ብቻ ነበር። በ27ኛው ደቂቃ ላይ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባህ አቻ የምታደርገውን ኳስ በጀርመን በሔራዊ ቡድን አማካዩ ፍሎሪያን ኖየሀውስ ከመረብ አሳርፏል። አፈታም ሳይቆይ 31ኛው ደቂቃ ላይ የኦስትሪያ ብሔራዊ ቡደን ተከላካዩ ሽቴፋን ላይነር የማሸነፊያዋን ግብ አስቆጥሯል። በሌሎች ግጥሚያዎች ትናንት ቮልፍስቡርግ በቦሁም 1 ለ0 ተሸንፏል። የቦን ከተማ ተጎራባቹ ኮሎኝ ሔርታ ቤርሊንን 3 ለ 1 ድል አድርጓል። በቅዳሜ ግጥሚያዎች፦ ፍራይቡርግ ከአርሜኒያ ቢሌፌልድ፤ እንዲሁም ባየር ሌቨርኩሰን ከዑኒዬን ቤርሊን ጋር ሁለት እኩል ተለያይተዋል። ሽቱትጋርት እና በደረጃው መጨረሻ ላይ የሚገኘው ግሮይተር ፊዩርትስ ያለምንም ግብ አቻ ወጥተዋል። ሆፈንሃይም አውግስቡርግን 3 ለ1፤ ላይፕትሲሽ ማይንትስን 4 ለ1 እንዲሁም ዶርትሙንድ ፍራንክፉርትን 3 ለ2 አሸንፈዋል። በዚህም መሠረት የቡንደስሊጋውን ደረጃ ባየርን ሙይንሽን በ43 ነጥብ ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ37 ነጥብ ይከተላል። ሆፈንሃይም 31፤ ፍራይቡርግ 30 ነጥብ ይዘው ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። አርሜኒያ ቢሌፌልድ እና ግሮይተር ፊዩርትስ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 17ና እና 18ኛ ላይ ይገኛሉ።

Fußball Bundesliga Eintracht Frankfurt v Borussia Dortmund
ምስል KAI PFAFFENBACH/REUTERS

የኤፍኤ ካፕ ግጥሚያ
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ግጥሚያዎች በሳምንቱ መጨረሻ ሲከናወኑ ቆይቷል። ዛሬ ማታም ማንቸስተር ዩናይትድ ከአስቶን ቪላ ጋር ይጋጠማል። ትናንት ሊቨርፑል ሽሬውስበሪ  ታውንን 4 ለ1 ሲያንኮታኩት፤ ሀሮጌት በሉቶን ታውን የ4 ለ0 ብርቱ ሽንፈት ገጥሞታል። አርሰናል በኖቲንግሃም ፎረስት 1 ለ0 ተሸንፏል። ቶትንሃም ሆትስፐር ሞርካምብልን 3 ለ1 ድል አድርጓል። 

የሜዳ ቴኒስ
የዓለማችንዕውቁ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች በአውስትራሊያ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች ከአውስትራሊያ ሊባረር እንደሚችል ተገለጠ። ያለኮቪድ ክትባት ሜልቦርን የሚገኘው የ34 ዓመቱ ሠርቢያዊ ቪዛው ሊሰረዝበት እንደሚችል ተገልጧል። «ምንም እንኳን ያ ሁሉ ቢከሰትም እዚሁ መቆየት እና የአውስትራሊያ ግጥሚያን ለመወዳደር ሙከራ ማድረግ እፈልጋለሁ» ሲል በትዊተር ጽሑፉ ዐሳውቋል። የአውስትራሊያ የሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ የሚቀጥለው ሳምንት ይጀምራል። 

Tennisspieler Novak Djokovic
ምስል WILLIAM WEST/AFP

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ