1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጥር 23 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ ጥር 23 2014

እጅግ ከፍተኛ የማሸነፍ እልህ በታየበት የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ግብፅ ሞሮኮን እንዲሁም ሴኔጋል ኤኳቶሪያል ጊኒን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል። ኮሮና ክትባት ጉዳይ የኤርትራ ብርቱ የብስክሌት ጋላቢዎችን ከርዋንዳው የዘንድሮ ፉክክር ውጪ አድርጓቸዋል። 

https://p.dw.com/p/46KXG
AFCON Viertelfinale Senegal - Äquatorialguinea Kamerun
ምስል Shaun Roy/empics/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

እጅግ ከፍተኛ የማሸነፍ እልህ በታየበት የአፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ግብፅ ሞሮኮን እንዲሁም ሴኔጋል ኤኳቶሪያል ጊኒን አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ወደ ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ዙር ለማለፍ የፊታችን ዐርብ በሜዳው ወሳኝ ግጥሚያ ይጠብቀዋል። ስፔናዊው የሜዳ ቴኒስ ዕውቅ ተጨዋች ትናንት ለ21ኛ ጊዜ በማሸነፍ ክብረወሰን ሰብሯል። ዋነኛ ተፎካካሪው ሠርቢያዊው ተጨዋች በኮሮና ክትባት ውዝግብ በውድድሩ እንዲሳተፍ አልተፈቀደለትም። ይኸው የኮሮና ክትባት ጉዳይ የኤርትራ ብርቱ የብስክሌት ጋላቢዎችን ከርዋንዳው የዘንድሮ ፉክክር ውጪ አድርጓቸዋል። 

አትሌቲክስ
በቅድሚያም አትሌቲክስ። በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች በተከናወኑ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።  ጀርመን ካርልስሩኸ ከተማ ውስጥ ዐርብ ዕለት በተከናወነው የ3000 ሜትር የሩጫ ፉክክር የ5 ሺህ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ በሪሁ አረጋዊ ለጥቂት ክብረወሰን ሳይሰብር ቀርቷል። በሪሁ የ3 ሺህ ሜትር ሩጫ ፉክክሩን አንደኛ ኾኖ ያጠናቀቀው 7:26,20 በመሮጥ ነው። ይህም የዓለማችን ምርጡ ሰአት ተብሎ ተመዝግቦለታል። የ20 ዓመቱ አትሌት ክብረወሰን ሳይሰብር የቀረው በ1,3 ሰከንድ ብቻ መኾኑ እጅግ ያስቆጫል። ቡዳፔስት ከተማ ውስጥ በኬኒያዊው ዳኒኤል ኮመን የተያዘው የ3 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ሳይሰበር 24 ዓመታትን አስቆጥሯል።    

Südkorea Daegu - Leichtathletik WM 2011
ምስል picture-alliance/sampics/S. Matzke

በካርልስ ሩኸ በሴቶች የ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት አመርቂ ድል አስመዝግበዋል። በዚህም አክሱማዊት እምባዬ 4:02.12 በመሮጥ 1ኛ በውጣት አሸንፋለች። ሂሩት መሸሻ በ4:02.14 2ኛ፤ እንዲሁም ፍሬወይኑ ኃይሉ በ4:02.66 የ3ኛ ደረጃን ይዘዋል። በተመሳሳይ ርቀት ያለፈው ዓመት አሸናፊ የነበረችው ጀርመናዊቷ ሯጭ ካታሪና ትሮስት በፈጣኑ የዘንድሮ ፉክክር የ7ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 

ከዚህ በተጨማሪ፦ ስፔን ውስጥ በተከናወነው የሴቪያ የግማሽ ማራቶን ፉክክር በወንዶች አትሌት ገብሬ እርቅይሁን በ1:00:26 3ኛ ወጥቷል። እዛው ስፔን በተከናወነ የጌታፌ የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ደግሞ በሴቶች ቤተልሔም አፈንጉስ በ1:08:22 1ኛ ወጥታለች። የሀገሯ ልጅ ብርቱካን ወርቅነህ በ1:09:11 ተከትላት በመግባት 2ኛ ደረጃን አግኝታለች። በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር ሀብታሙ ብርሌው በ1:02:16 2ኛ፤ አትሌት ስንታየሁ ድንቄሳ ደግሞ በ1:02:37 የ3ኛ ደረጃን አግኝተዋል። ጣሊያን ሣን ቪቶሬ ኦሎና ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው ቺንኲዌ ሙሉኒ በተሰኘው 90ኛው አገር አቋራጭ ዓለም አቀፍ ውድድር፤ኢትዮጵያዊው አትሌት ንብረት መላክ 28:33 በመሮጥ ዳግም አንደኛነቱን አስመስክሯል። ንብረት ባለፈው ዓመትም እዚህ ውድድር ላይ አንደኛ በመውጣት አሸንፎ ነበር። ንብረት ታዳሚያኑን ባስደመመ መልኩ በስተመጨረሻ ላይ ተስፈንጥሮ ባሸነፈበት የዘንድሮው ፉክክር ኬኒያዊው አትሌት ኬቪን ሌቪ ሁለተኛ ወጥቷል። የዛሬ ሁለት ዓመት ሣን ቪቶሬ ኦሎና ውስጥ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ታደሰ ወርቁ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። የገባበት ሰአትም 28:36 ነው። አትሌት ቢቂላ ታደሰ በ28:36 4ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። 

እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለዓለም ዋንጫ የማጣሪያ የ4ኛ ዙር ሁለተኛ ጨዋታውን የፊታችን ዐርብ ያከናውናል።  ቡድኑ ዛንዚባር አማን ስታዲየም ውስጥ ባከናወነው የመጀመሪያ ግጥሚያ የተሸነፈው በጠበበ የግብ ልዩነት 1 ለ0 ነው።  ሁለተኛ ጨዋታውን ጥር 27 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የሚያካኺደው በሜዳው አበበ ቢቂላ ስታዲየም  ነው።  ከታንዛኒያ መልስ ከአንድ ቀን ረፍት በኋላ ወደ ልምምድ የገባው የኢትዮጵያ ቡድን በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምዱን አጠናክሮ መስራቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል።
በኮስታሪካ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የ2022 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቡድን የተሸነፈው በታንዛኒያ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ቡድን በዐርቡ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ ታንዛኒያን ካሸነፈ ወደ መጨረሻው እና አምስተኛ ዙር የጥሎ ማለፍ ውድድር ይገባል። በመጨረሻው ዙር የሚሳተፉ ቡድኖች አራት ብቻ ሲሆኑ፤ከአራቱ ሁለቱ ለዓለም ዋንጫ ያልፋሉ። 

FBL-AFR-AFCON-2021-2022-MLI-MTN
ምስል AFP via Getty Images
Adidas Leichtathletik
ምስል picture alliance/dpa/B. Thissen

ካሜሩን ውስጥ የሚከናወነው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር ግማሽ ፍጻሜ አላፊዎች ተለይተዋል። ትናንት በድንቅ ፉክክር ኤኳቶሪያል ጊኒን 3 ለ1 የረታችው ሴኔጋል ኢትዮጵያ ከነበረችበት ምድብ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው ቡርኪናፋሶን ከነገ በስትያ ትገጥማለች። ኢትዮጵያ በነበረችበት ምድብ ተፎካካሪ የነበረችው ሌላኛዋ ጠንካራ ቡድን ካሜሩን ትናንት ሞሮኮን 2 ለ1 ካሸነፈችው ግብጽ ጋር የፊታችን ሐሙስ ከምሽቱ አራት ሰአት ላይ ለግማሽ ፍጻሜው ትገጥማለች።  እሁድ ከሰአት በኋላ ለሦስተኛ ደረጃ፤ ምሽት አራት ሰአት ላይ ደግሞ ለዋንጫ የፍጻሜ ግጥሚያ ይኖራል። 

ወደ ግማሽ ፍጻሜው ካለፉ ቡድኖች መካከል በተለይ አዘጋጇ ካሜሩን እና ግብጽ የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። ካሜሩንም ኾነች ግብጽ አብዛኞቹ ተጨዋቾቻው በአውሮጳ ታላላቅ ቡድኖች ውስጥ የሚጫወቱ ዝነኞች ናቸው። ካሜሩን እና ግብጽ ላለፉት ዐርባ ዓመታት ግድም በአፍሪቃ ዋንጫ እና ለወዳጅነት ለ28 ጊዜያት ተገናኝተዋል። ግብጽ 15 ጊዜያት አሸንፋለች። ካሜሩን በአንጻሩ ግብጽን ያሸነፈው ለ6 ጊዜያት ነው። ቀሪውን አቻ ነው የወጡት። 

ሁለቱ ሃገራት ባለፉት 38 ዓመታት ያደረጓቸውን 10 የአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያዎችን ብንመለከት ደግሞ፦ ግብጽ ስድስት ጊዜ ስታሸንፍ፤ ካሜሩን ግብጽን አራት ጊዜ አሸንፋለች። በአራት ዐሥርተ ዓመታት ግድም ሁለቱ ቡድኖች በአፍሪቃ ዋንጫ ለሦስት ጊዜያት ለፍጻሜ ተገኛንተዋል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1986 ያለምን ግብ ተለያይተው በመለያ ምት ግብፅ 5 ለ4 አሸንፋለች።  በ2008ም ግብጽ 1 ለ0 አሸንፋ ዋንጫውን ወስዳለች። በ2017 ግን ካሜሩን በፍጻሜው ግብጽን 2 ለ1 ድል አድርጋ ዋንጫውን አንስታለች። ዘንድሮ ለፍጻሜው ማን ይደርስ ይሆን? ዋንጫውስ ወደ የትኛው ከተማ ያቀና ይሆን? እስከ እሁድ መጠበቅ ነው። በፊፋ የወቅቱ የእግር ኳስ ደረጃ ግብጽ ከቀድሞው ደረጃዋ በአንድ ዝቅ ብላ 45ኛ ላይ ትገኛለች። ካሜሩን በአንጻሩ በነበረበት ደረጃው 50ኛ ላይ ይገኛል። በነገራችን ላይ ለግማሽ ፍጻሜው ከደረሱት አራት ቡድኖች መካከል ሴኔጋል በፊፋ ከዓለም 20ኛ ደረጃን ከአፍሪቃ የአንደኛ ደረጃን ይዛለች። በፊፋ 28ኛ የኾነችው ሞሮኮ ከአፍሪቃ ሁለተኛ ናት፤ በሩብ ፍጻሜ ግን ዘንድሮ ተሰናብታለች። 

AFCON Viertelfinale Ägypten vs Marokko
ምስል KENZO TRIBOUILLARD/AFP/Getty Images

የአውሮጳ እግር ኳስ ቡድኖች የተጨዋቾች ዝውውር መዝጊያ
በአውሮጳ ታላላቅ የእግር ኳስ ሊጎች የተጨዋቾች ዝውውር ዛሬ በመዝጊያው ያበቃል። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፣ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ፤ የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪኣን የመሳሰሉ ሊጎች የመዝጊያው ቀን ዛሬ ከማክተሙ በፊት ተጨዋቾችን ለማስመጣት እየተረባረቡ ነው። አርሰናል ሠርቢያዊው አጥቂ ዱሳን ቭላሆቪችን ወደ ኤሚሬትስ ስታዲየም ለማስመጣት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ሆኖም የ22 ዓመቱ አጥቂ በስተመጨረሻ ለጣሊያኑ ጁቬንቱስ ቱሪን ወስኗል። የቀድሞው የፍሎሬንትስ አጥቂ በሴሪ ኣው ቆይታው እስካሁን 21 ግቦችን አስቆጥሯል። በዱሳን ያልተሳካለት አርሰናል ከአትሌቲኮ ማድሪድ በውሰት ጁቬንቱስ ቱሪን የሚገኘው የ29 ዓመቱ አጥቂ አልቫሮ ሞራታን ለማስመጣት ላይ ታች ሲል ከርሟል።

BdTD | UK, Londen - Premier League - Arsenal v Crystal Palace
ምስል Hannah Mckay/REUTERS

የ32 ዓመቱ የቀድሞው የአርሰናል አምበል ጋቦናዊው አጥቂ ፒዬር-ኤመሪክ አውባሜያንግ በውሰት ወደ ባርሴሎና የሚያቀና ከኾነ በልዋጩ አልቫሮ ሞራታ ወደ አርሰናል ሊመጣ ይችላል ተብሏል። ከአርሰናል በተጨማሪ ግን ቶትንሀም ሆትስፐር እና ኒውካስትል ዩናይትድም ከአልቫሮ ሞራታ ጋር እየተነጋገሩ እንደነበር ታውቋል።  የስፔኑ የስፖርት ጋዜጣ «ሙንዶ ዴፖርቲቮ» ዛሬ እንደዘገበው ከኾነ፦ አርሰናል አውባሜያንግን ለባርሴሎና በውሰት ለመስጠት ተስማምቷል። በልዋጩም ባርሴሎና የቀድሞው የዶርትሙንድ አጥቂ ኦስማኔ ዴምቤሌን ወደ አርሰናል መላክ ይኖርበታል። ፒዬር-ኤመሪክ አውባሜያንግ እና ኦስማኔ ዴምቤሌ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ቡድን አንድ ላይ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። 

የግራ ተከላካይ መስመር እና የመሀል አጥቂ እጅግ የሚያስፈልገው ባርሴሎና ምናልባትም ኦስማኔ ዴምቤሌን በ20 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ፓሪስ ሳንጃርሞ ለመላክ አስቧል ሲሉም ስፖርት እና ሌሎች ጋዜጦችም ዘግበዋል። በተጨዋቾች ልዋጭ ሊዘዋወር ይችላል የሚለውም ጎልቶ ወጥቷል። ባርሴሎና በልዋጩ ከፓሪስ ሳን ጃርሞ ተጨዋቾች ከ28 ዓመቶቹ ኹዋን ቤርናት፣ ዩሊያን ድራክስለር እና ማውሮ ኢካርዲ እንዲሁም ከ33 ዓመቱ አንገል ዲ ማሪያ ሁለቱን ማስመጣት ይሻል። «ኤኤስ» የተሰኘው የስፖርት ጋዜጣም፦ ባርሴሎና ኹዋን ቤርናት እና አንገል ዲ ማሪያን እንደሚፈልግ ዘግቧል። አንዱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እስከ ዛሬ እኩለ-ሌሊት ድረስ ብቻ ነው የቀረው ጊዜ።  

FIFA 2018 WM Qualifikation Frankreich - Niederlande Kylian Mbappe
ምስል picture-alliance/abaca/C. Liewig

ፓሪስ ሳንጃርሞ የኬሊያን እምባፔ የዝውውር ጉዳይንም እልባት ሊሰጠው ይገባል። ፓሪስ ሳን ጃርሞ እምባፔን ከሞናኮ ለማስመጣት 145 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎ ነበር። አሁን ግን ውሉ ስላለቀ ያለ ክፍያ ነው ወደ ሌላ ቡድን የሚዛወረው። ኬሊያን እምባፔ ላይ ዐይኖቻቸው ካሳረፉ ታዋቂ የአውሮጳ ቡድኖች መካከል ቀዳሚው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ነው። «ቢልድ» የተሰኘው እና ከፍተኛ ተነባቢነት ያለው የጀርመኑ ታብሎይድ ጋዜጣ ዛሬ እንደዘገበው ከኾነ ሪያል ማድሪዶች በቀጣዩ የበጋ ወራት የፓሪስ ሳንጃርሞው ኮከብ አጥቂን በዝውውር ለማስመጣት ሁሉን ነገር ጨርሰዋል። ሆኖም እስከ ቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ የሚደረጉ ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ድረስ ግን መጠበቅ ይኖርባቸዋ።  ፓሪስ ሳንጃርሞ የካቲት 8 እና የካቲት 29 ከራሱ ከሪያል ማድሪድ ጋር ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታል።  

ከሁለቱ ለሩብ ፍጻሜ የሚደረጉ ጨዋታዎች በኋላም ኬሊያን እምባፔ ወደ ስፔን ዋና ከተማ አቅንቶ በዓመት የ50 ሚሊዮን ዩሮ ተከፋይ እንደሚሆን ነው የተነገረው። በዚህም የዓለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ጥቂት ተጨዋቾች ተርታ ይገባል። 23 ዓመቱ ነው።

ብስክሌት
የኤርትራ ብስክሌት ጋላቢዎች ቡድን የኮቪድ-19 መከላከያ አልተከተበም በሚል በሚቀጥለው ወር በርዋንዳ ከሚካሔድ ውድድር መውጣቱን አዘጋጆቹ ዐስታወቁ። ከአፍሪቃ የብስክሌት ጋላቢዎች ጠንካራ ተፎካካሪዎችን በአኅጉሩም ኾነ በዓለም አቀፍ ውድድሮች በማሳተፍ የሚታወቀው የኤርትራ ቡድን እዛው ርዋንዳ ውስጥ የዛሬ ሁለት ዓመት እጅግ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ይታወቃል። በያኔው ውድድር፦ የኤርትራ ቡድን ምርጥ የአፍሪቃ ብስክሌት ጋላቢ ቡድን፣ ምርጥ ወጣት ብስክሌት ጋላቢ እንዲሁም ምርጥ ብስክሌት ጋሊቢ ዘርፎች አሸናፊ ነበር። ከአጠቃላይ ውድድር ደግሞ ጣሊያን ውስጥ ከተመዘገበው እና በምኅጻሩ (DRA) በሚል ከሚታወቀው ቡድን ቀጥሎ ሁለተኛ በመውጣት ማጠናቀቁ ይታወሳል። ባለፈው ዓመትም አዘጋጇ ርዋንዳን በልጦ በ7ኛነት አጠናቋል። በዘንድሮው የርዋንዳ የብስክሌት ውድድር አምስት የኤርትራ ጋላቢዎች ይጠበቁ ነበር።

Das Radrennen Tour du Rwanda
ምስል DW/A.O'Donnell

የሜዳ ቴኒስ የአውስትራሊያ ፍጻሜ
ስፔናዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ራፋኤል ናዳል 21ኛ የሜዳ ቴኒስ አጠቃላይ ውድድሩን አውስትራሊያ ሜልቦርን ውስጥ በማሸነፍ ክብረወሰን ሰበረ። ትናንት የ35 ዓመቱ ራፋኤል ናዳል አሸናፊ የኾነው ሠርቢያዊው የ34 ዓመቱ ዋነኛ ተቀናቃኙ በሌለበት ፉክክር ነው። ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ኮሮና ሳይከተብ አውስትራሊያ በመግባቱ በተፈጠረ ውዝግብ ውድድሩ ሳይጀምር ከሀገሪቱ እንዲወጣ መደረጉ ይታወሳል። እንዲያም ሆኖ ግን ኖቫክ ጄኮቪች እስካሁን በተደረጉ አጠቃላይ ውድድሮች በ11015 ከፍተኛ ነጥብ ይመራል። ትናንት በራፋኤል ናዳል የተሸነፈው ሩስያዊው የቴኒስ ተጨዋች ዳኒል ሜድቬዴቭ በ1110 ነጥብ ተበልጦ የሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጀርመናዊው አሌክዛንደር ትስቬሬቭ በ7780 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ራፋኤል ናዳል በ6875 ነጥብ ደረጃው አምስተኛ ነው። ራፋኤል ናዳል ትናንት በዳኒል ሜድቬዴቭ በሁለት ዙር ጨዋታዎች እየተመራ ቆይቶ ነበር በኋላ ላይ ለድል የበቃው። ውጤቱም 2-6፤ 6-7 (5/7) በሩስያዊው መሪነት ከዚያም 6-4፤ 6-4፤ 7-5 በራፋኤል አሸናፊነት ነው የተጠናቀቀው። 

Australian Open Tennis Gewinner Rafael Nadal
ምስል William West/AFP

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ