ፈንድቃ ኮሮና በሸበበዉ በጀርመኑ የጃዝ መድረክ
ዓርብ፣ ግንቦት 20 2013መቀመጫዉን አዲስ አበባ ያደረገዉ የባህል ቡድን ዓለም በኮሮና እንቅስቃሴዋ ከተገደበ ከሁለት ዓመት ግድም በኋላ ወደ ጀርመን መጥቶ በዓለም አቀፉ የጃዝ ፊስቲቫል ላይ ድንቅ ዝግጅቱን አሳየ። ዘንድሮ 50ኛ ዓመቱን ያከበረዉ የጀርመኑ ዓለም አቀፍ የጃዝ መድረክ ሞርዝ የጃዝ ፊስቲቫል የተለያዩ ባህላዊ እና ዘመናዊ የሙዚቃ መሳርያ ጥበበኞች ተሳትፈዉበታል። ፈንድቃ በኢትዮጵያ ባህላዊ መሳርያ እና በዉዝዋዜ ድንቅ ትዕይንትን አሳይቶአል። በዓለማችን የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭትን ለመግታት የዝዉዉር እገዳዉ ከጠበቀ ወዲህ፤ የዓለም የኪነ-ጥበብ መድረክ ተዳክሞ ቆይቶአል። ከባለፈዉ ሁለት ሳምንት ወዲህ እዚህ በጀርመን የተለያዩ የኪነ-ጥበብ መድረኮች ሙዚየሞች በሮቻቸዉን በመጠኑም ቢሆን እየከፈቱ ነዉ። በጀርመን በየዓመቱ ለሦስት ቀናት የሚካሄደዉ ታዋቂዉ የጃዝ ፊስቲቫል ሞርዝ ፊስቲቫል ዘንድሮ በሃምሳኛ ዓመቱ በርካታ ተመልካቹቹን ወደ መድረኩ ባይጋብዝም፤ ከተለያዩ የዓለም ሃገራት የተለያዩ የኪነ-ጥበበኞችን ጋብዞ የኮሮና ምርመራን እያካሄደ በኢንተርኔት አማካኝነት ዝግጅቱን ለዓለም አስተላልፎአል። ለዚሁ ዝግጅት በተመልካችነት እቦታዉ ላይ የታደሙት ከ 50 ሰዎች አይበልጡም። ከኢትዮጵያ የተጋበዘዉ የፈንድቃ ባህላዊ ቡድን ስድስት አባላትን የያዘ ነበር።
የዶቼ ቬለ ራድዮ ጣብያ በሚገኝበት በኖርዝ ራይን ዌስት ፋልያ ግዛት ዉስጥ በምትገኘዉ ሞርዝ ከተማ ጃዝ ድግስ ላይ፤ በየዓመቱ የዓለም የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾች የሚሰባሰቡባት መድረክ ነዉ። ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሞርዝ የተጓዘዉ የፈንድቃ የባህል መድረክ ዋና ስራ ስኪያጅ መላኩ በላይ በፈንድቃ የባህል ቡድን የባህላዊ ሙዚቃ ጨዋታ ያሳየዉ ባህላዊ ዉዝዋዜ እድምተኛዉን አስደምሞት ነበር። የፈንድቃ የባህል ቡድን በኮሮና ተኅዋሲ መሰራጨት ምክንያት የዝዉዉር ሕግ ጠብቆ ባለበት በአሁኑ ወቅት ወደ ጀርመን ሊመጣ የቻለዉ በቅድምያ ቡድኑ ከኮሮና ነጻ መሆኑን ተመርምሮ በሌላ በኩል አዲስ አበባ በሚገኘዉ የጀርመን ኤንባሲ እና የኖርዝ ራይን ዌስት ፋልያ ግዛት ባለስልጣን ቢሮ ከፍተኛ ጥረት መሆኑ ተመልክቶአል።
የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት የእንቅስቃሴ ገደቡን ባይገታዉ ኖሮ የፈንድቃ ቡድን መሪ 23 ችበበኞችን ይዞ በሞርዝ ከተማ ላይ በተካሄደዉ 50 ኛ ዓመት የጃዝ መድረክ ላይ ይገኝ እንደነበር ተናግሮአል። ከዚህ ሌላ የጋሞ የባህል ሙዚቃ ተጫዋቾች በምናለሽ ተራ ብረት የሚቀጠቅጡ ሰዎችን ይዞ አዲስ ያለዉን ትዕይንት ሊያሳይ እንደነበር አቶ መላኩ በላይ ተናግሮአል።
የፈንድቃ ባህላዊ ቡድን መስራች አቶ መላኩ በላይ ያሆ ያሆ ና በለዉ ና በለዉ፤ ሲል ያዜመዉ እና አንድነት ፍቅርን ሰላምን የሚገልፅ ዜማ በመሆኑ በጀርመን ተወዶለታል። የጋዜጠኞችንም ቀልብ የሳበ እና የተዘገበለት ርዕስም ነዉ። መላኩ በእንጊሊዘኛ በሰጠዉ ቃለ ምልልስም ስለ ኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ መሰንቆ፤ ክራር በተለይ ስለ አዝማሪ ጥንታዊነት በማኅበረሰቡ ያለን እፀፅ ነቃሽ መሆኑን አስረድቶአል።
የኮሮና ተኅዋሲ ስጋት በአለበት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄን በማድረግ ወደ ጀርመን የተጓዘዉ ፈንድቃ ባህላዊ ቡድን በአንጋፋዉ የጃዝ ፊስቲቫል ላይ እንዲሳተፍ ተደርጎአል፤ ያለዉ አቶ መላኩ በላይ በኢትዮጵያ በኮሮና የተሰበረዉ የጥበብ መድረክ መንግሥት ሊደግፈዉ እንደሚገባ ሳይገልፅ አላለፈም። ጥበብ ለኅብረተሰብ እድገት መሰረት ነዉ፤ የአለም ሃገራት ጥበብ እንድትለመልም ድጋፍ ያደርጋሉ ፤ ለምሳሌ ኮሮና ተኅዋሲ ባስከተለዉ የዝዉዉር ገደብ ምክንያት ጎረቤት ኬንያ እንኳ ለጥበብ መድረክዋ በሚሊዮን የሚቆጠር ድጋፍ አድርጋለች ያለዉ አቶ መላኩ በላይ፤ በኢትዮጵያ በጥበቡ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሞያዎች አብዛኞቹ ሞያቸዉን እንዲለቁ ሆነዋል ሲል ተናግሮአል።
«በኮሮና ምክንያት ዓለም ጨልሞ ተጋግቶ ነበር፤ በአሁኑ ጉዞአችን ለፈንድቃም ሆነ ለሌሎች የባህል እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ጉዞ ነዉ። ተስፋ ስጪ ስል፤ ለህዝቡም ለኪነ-ጥበቡም ለቱሪዝሙም በአጠቃላይ ለዓለም እንቅስቃሴ ሁሉ ማለቴ ነዉ። ዓለም እንዲህ ጭልም ብሎ በነበረበት ወቅት ይህ በጀርመን የተካሄደዉ የጃዝ ፊስቲቫል በግንባር ቀደምትነት ጥበበኞችን በማሰባሰቡ እኛም በዚህ መድረክ ላይ መገኘታችን ትልቅ ምልከታ እና ተስፋ ሰጭም ነዉ፤ በዚህም እጅግ ተደስተናል። በዚህ ሂደት የተማርነዉ ነገር ቢኖር እንደዚህ በዓለም ላይ ጨለማ የሆነ ነገር ሲከሰት፤ ሁሌ ከጥበብ ጋር ሁሌ ከእምነት ጋር ያለ ሰዉ ተስፋ አይቆርጥም፤ ተስፋ መቁረጥን ራሱ ገድለን ነዉ እየሰራን ያለነዉ፤ ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አስቆርጠነዋል። ሁሉ ነገር ያልፋል፤ ለሚያልፍ ቀን ፤ ባልሆነ ጭንቀት ዉስጥ መግባት አያስፈልግም ። መበርታት ለሌላዉ ማሰብ ነዉ።»
የኢትዮጵያ ባህል አምባሳደርና የውዝዋዜ አርቲስት መላኩ በላይ እና የኪነ-ጥበብ ቡድኑ በጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ.ም በተለያዩ የአዉሮጳ ሃገራት በተካሄዱ ፌስቲቫሎች፤ የሙዚቃ ዝግጅቶችና ዎርክሾፕ ተሳትፈዋል፡፡ የባህል ሙዚቃ ቡድኑ ዝግጅቶቹን ካቀረበባቸው አገራት መካከል ፈረንሳይ፤ ፤ ቤልጅዬም፤ ሆላንድ፤ ሃንጋሪና ጣሊያን ይገኙበታል፡፡ መላኩ እና የባህል ሙዚቃ ቡድኑ ፈንዲቃ የኢትዮጵያ ባህል አምባሳደሮች ሆነው በየፌስቲቫሎቹ ላይ ከትልልልቅ የሙዚቃ ቡድኖች እና ሙዚቀኞች ጋር በመስራት ከፍተኛ ትኩረት መሳባቸው አሁንም በተለያዩ የባህል መድረኮች ለመጋበዝ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነዉ። በጋዜጦች ላይም የባህል ርዕሰ አንቅቀፅ ሆነዉ በፎቶ በተደገፈ ስለ ፈንድቃ መፃፉ ቀጥሎአል። 2015 ዓ.ም ፈንድቃዎች በአውሮጳ በነበራቸው የአንድ ወር ቆይታ ከሰሩባቸው ግዙፍ ፌስቲቫሎች መካከል የአምስተርዳሙ ቢምሂውስ ፌስቲቫል፤ የሃንጋሪ ቱፍካን ፌስቲቫል፤ የቤልጅዬሙ ዱወር ፌስቲቫል፤ የቦርዴሪጅ ፌስቲቫል፤ የቪሌጅ ፌስቲቫል፤ የቫልኮሀፍ ፌስቲቫል፤ የቶታአል ፌስቲቫል ይጠቀሳሉ። የፈንድቃ ቡድን በጀርመን በሞርዝ የጃዝ ፊስቲቫል ላይ ዝግጅቱን ካሳየ በኋላ ወደ ሆላንድ ተጉዞ ሌላ የቀረፃ መረሃ-ግብርም ነበረዉ። በጀርመኑ ዓለም አአፍ የጃዝ ፊስቲቫል ላይ ለመካፈል እና በሆላንድ ቀረፃን ለማካሄድ ወደ አዉሮጳ የመጣዉ የኢትዮጵያዉ ባህላዊ ቡድን ፈንድቃ በጀርመን ባህላዊ የጃዝ ድግሱን አሳይቶ ሆላንድ የትርኢት ቀረፃን አድርጎ ከአምስt ቀናት አዉሮጳ ቆይታ በኃላ ወደ ዋና መቀመጫዉ መዲና አዲስ አበባ ተመልሶአል።
በኮሮና ተኅዋሲ የተጎዳዉ የኢትዮጵያ የጥበብ መድረክ እገዛ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል እንላለን። የፈንድቃ የባህል ቡድን አባላትን እና ዋና ተጠሪዉን አቶ መላኩ በላይ ለሰጠን ቃለ ምልልስ እናመሰግናለን። ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ