1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስያ መሠረተ ልማት መዋዕለ ነዋይ ባንክ እና ኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ መጋቢት 14 2009

የእስያ መሠረተ ልማት መዋዕለ ነዋይ ባንክ በእንግሊዝኛዉ ምሕጻር AIIB 13 አዲስ አባላትን መቀበሉን በዛሬው ዕለት ይፋ አደረገ። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2017 መባቻ ሥራ የጀመረዉ ይኽ ባንክ ለአባልነት ያቀረቡትን ማመልከቻ ተቀብሎ አባል ካደረጋቸዉ ሃገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።

https://p.dw.com/p/2ZqmX
China AIIB Entwicklungsbank Jin Liqun
ምስል picture alliance/dpa/W. Hong

AIIB (CMA) - MP3-Stereo

 

ዋና ጽሕፈት ቤቱን በቤጂንግ ቻይና ያደረገዉ እና የዓለም ባንክ ተገዳዳሪ መሆኑ የሚነገርለት ዘርፈ ብዙዉ አበዳሪ የእስያ የመሠረተ ልማት መዋዕለ ነዋይ ባንክ ሥራዉን የጀመረዉ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መባቻ ነዉ።  አንድ መቶ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መነሻ ካፒታል ባለዉ በዚህ ባንክ በርካታ የአዉሮጳ ሃገራትን ባለድርሻ ናቸዉ። ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴትስ ርምጃቸዉን አጥብቃ ብትቃወምም። ዛሬ ደግሞ የባንኩ አባል ለመሆን ማመልከቻ ካቀረቡት መካከል 13 ሃገራትን መቀበሉን አስታዉቋል። ከእነዚህ መካከልም ኢትዮጵያ፤ ካናዳ፤ ሆንግ ኮንግ፣ ቬንዝዌላ፤ አፍጋኒስታን፤ አየርላንድ፤ ሀንጋሪ፤ ቤልጅየም፤ ፔሩ፤ እንዲሁም ሱዳን ይገኙበታል። የባንኩ ፕሬዝደንት ዢን ሊኩዊን፤ የእስያ የመሠረተ ልማት መዋዕለ ንዋይ ባንክ አባል ለመሆን የሚያመለክቱ ሃገራት ቁጥር መበራከት፤ ባንኩን በዓለም አቀፍ ተቋምነት ለመመሥረት ያደረጉትን ፈጣን እድገት እንደሚያመላክት ነዉ የተናገሩት። በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ AIIB ከመላዉ የዓለም ክፍሎች አባላትን ማሰባሰብ መቻሉም በጣም እንደሚያኮራቸዉ ያመለከቱት ፕሬዝደንቱ በቀጣይም የባንኩ የቦርድ ገዢዎች ሌሎች ማመልከቻዎችንም እመረመሩ እንደሚያጸድቁ ጠቁመዋል። ዛሬ ማመልከቻቸዉ ተቀባይነት ማግኘቱ የተገለጠዉ 13ቱ አዳዲስ አባል ሃገራት የባንኩ አባልነታቸዉ የጸድቀዉ ግን የመጀመሪያ ክፍያቸዉን ወደ ባንኩ ሲያስገቡ፤ በተጨማሪም አስፈላጊዉን የሰነድ ሂደት ሲያጠናቅቁ እንደሚሆን ተገልጿል። ባንኩ 13  ሃገራትን በአዲስ አባልነት መቀበሉም ያሉትን የአባል ሃገራት ብዛት 70 ያደርሰዋል ተብሏል።  የባለ ድርሻ አባላቱ ቁጥር መበራከት ደግሞ የባንኩን የማበደር አቅም እንደሚያጠናክረዉ ነዉ የሚነገረዉ። የዚህ ባንክ መቋቋምና አባል መሆኗ ለኢትዮጵያ መንግሥት አማራጭ አጋር ማግኘት ያስችለዋል ይላሉ፤ የቀድሞዉ የምክር ቤት አባል እና የኤኮኖሚ ባለሙያ አቶ ግርማ ሠይፉ።

China AIIB Entwicklungsbank Jin Liqun
የAIIB ፕሬዝደንት ዢን ሊኩዊምስል picture alliance/dpa/W. Hong

የእስያ የመሠረተ ልማት መዋዕለ ንዋይ ባንክ ባለፈዉ ዓመት ሰኔ ወር ለአራት ሃገራት የሚሆን ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብድር አጽድቋል። ብድሩም በፓኪስታን፣ ኢንዶኔዢያ፣ ታጃኪስታን እና ብንግላዴሽ ዉስጥ ለሚተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተሰጥቷል። ቀደም ሲል እነዚህ ፕሮጀክቶች በእስያ የልማት ባንክ እና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የተጀመሩ ነበሩ። የባንኩ መጠናከር የሚያሳስባቸዉ ብድር ለመስጠት የሚያወጣዉ መሥፈርት ዝቅተኛ እንደሚሆን፤ እንደ ዓለም ባንክ እና መሰል ለልማት እንቅስቃሴዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያቀርቡ ተቋማት ያስቀመጧቸዉን ዘላቂ የማህበራዊ፣ አካባቢያዊ እና ኤኮሚያዊ መርሆዎችን ከግምት የማያስገባ ይሆናል የሚል ትችት እየሰነዘሩ ነዉ። አቶ ግርማ ግን እነዓለም ባንክ የሚባለዉን መስፈርትና መርሆ ችላ ካሉት እንደቆዩ  ያስረዳሉ።

China AIIB Entwicklungsbank Eröffnungszeremonie
የእስያ መሠረተ ልማት መዋዕለ ነዋይ ባንክ ምሥረታ ጉባኤ እኤአ ጥር 2016ምስል picture alliance/ZUMA Press/L. Weibing

ይህም ሆኖ አቶ ግርማ በዓለም ላይ አንድ ብቻ ግዙፍ አበዳሪ የገንዘብ ተቋም ከሚኖር እንደዚህ ዓይነቱ ተጨማሪ አማራጭ ባንክ መኖሩ ከጉዳቱ ጥቅሙ ከፍ እንደሚል ነዉ ያመለከቱት። የዓለም ባንክ ተቀናቃኝ ተደርጎ ከወዲሁ የታየዉ የእስያዉ የመሠረተ ልማት መዋዕለ ነዋይ ባንክ አብዛኞቹን ሃገራት አጓጉቱ እየሳበ መሆኑ ቢነገርም፤ በአንደኛ እና በሦስተኛ ደረጃ የዓለም ትልቁ ኤኮኖሚ ባለቤቶች የሆኑት ዩናይትድ ስቴትስ እና ጃፓን እስካሁን የዚህ ባንክ አባል መሆን አልፈለጉም።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ