1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሆንግ ኮንግ ተቃዉሞ፣ምክንያቱና የምክንያቱ ምክንያት

ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2011

ከሰኔ ጀምሮ እስከ ዛሬ የዘለቀዉ የዘንድሮዉ ተቃዉሞ መነሻ የወይዘሮ ኬሪ ላም አስተዳደር በወንጀል የሚጠረጠሩ የግዛቲቱ ተወላጆችን ለቤጂንግ አሳልፎ የሚያሰጥ ደንብ ማርቀቁ ነዉ።ይሁንና መሰረታዊዉ ምክንያት ከ2014 ምናልባትም ከ1997 ጀምሮ የተጠራቀመዉ ብሶት በመሆኑ ረቂቁ ከተሻረ በኋላም ተቃዉሞዉ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/3Ottn
Proteste in Hongkong
ምስል picture alliance/AP/V. Yu

የሁለት ወር ተቃዉሞ፣የብዙዎች ሽኩቻ ግዛት ሆንግ ኮንግ

የቤጂንግ ኮሚንስቶችን፣የሆንግ ኮንግ ተከታዮቻቸዉን አስተዳደር በመቃወም በ2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ተሰልፈዉ የነበሩ ወጣቶችን ፖሊስ ሲበትን ሰልፈኞቹ «እንመለሳል» ብለዉ ነበር።ባመቱ አምስት የሆንግ ኮንግ መፅሐፍት ሺያጮች ታፍነዉ ዋናዋ ቻይና ዉስጥ መታሰራቸዉ ተስማ።ዘንድሮ የሆንግ ኮንግ መሪዎች በወንጀል የሚጠረጠሩ የግዛቲቱ ተወላጆችን ለቤጂንግ አሳልፎ የሚሰጥ ደንብ አረቀቁ።በጦር ኃይል ጉልበት ተመስርታ፣ በቅኝ ገዢዎች ታምቃ፣ 150 ዓመት በተቃዉሞ ኖራ፣ በእልሕ የበለፀገችዉ ግዛት አዲስ ትዉልድ እንደዛተዉ ለተቃዉሞ ታደመ።ሰኔ።2019።የተቃዉሞዉ መነሻ፣የግዛቲቱ ዳራ ማጣቀሻ፣ የኮሚንኒስት ካፒታሊስቶቹ ፍትጊያ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

 የሆንግ ኮንግን አስተዳደር በዉጤቱም የቻይናን ኮሚንስታዊ አገዛዝ የሚቃወሙት የግዛቲቱ ወጣቶች የእኛን ታላቅ አብዮታዊ መሪ የማኦ ዜዶንግን አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና አስተምሕሮ  ምናልባት ከተጣመመ ትርጓሜዉ ባለፍ አይተዉት፤ ኖረዉበት፣ በቅጡ አስተንትነዉትም ማወቃቸዉ በርግጥ አጠራጣሪ ነዉ።

የሚቃወሟቸዉ የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪዎች «ነዉጠኛ ተቃዋሚዎች» እያሉ ሲያጣጥሏቸዉ ግን፣ እኛ እዉቅ ኮሚንስታዊ መሪ የዛሬ 85 ዓመት ግድም ብለዉት እንደነበረዉ «እኛ ብዙሐን አብዮተኞች ነን» አሉ።ዘንድሮ። ማኦ በ1934 በፃፉት መጣጥፍ «አብዮታዊ ጦርነት፣ የሰፈዉ ሕዝብ ጦርነት ነዉ» ብለዉ ነበር ይላሉ የሚያዉቁ።ሆንግ ኮንጎች አንበበዉት ይሆን ወይስ አጋጣሚ? ሆነም አልሆነ ተቃዉሟቸዉ  «የሰፊዉ ሕዝብ» ባይባል እንኳ ሚሊዮኖችን ማሰለፉ እርግጥ ነዉ።

Hongkong PK Carrie Lam
ምስል Getty Images/AFP/L. Suwanrumpha

ማኦ በ1963 ለጓድ KUO MO-JO መልስ ባሉት ግጥማቸዉ «በዚች ትንሽ ዓለም፣ ጥቂት ዝንቦች ከግንብ ጋር ይላተማሉ» ብለዉ ነበር።የቤጂንግ ተከታዮቻቸዉ የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚዎችን ብዛት ለማሳነስ ዘንድሮ ተጠቀሙበት።የሆንግ ኮንግ አስተዳደር ዋና ፀኃፊ ደግሞ ዛሬ የታላቁን አብታዊ መሪ ቅኔን ተቃዋሚዎችን ለማስጠንቀቅ፣ ሕዝብን በተቃዋሚዎቹ ላይ ለማሳመፅ አዋሉት።

«እነዚሕ ጥቂት ነዉጠኛ አመፀኞች ሁከታቸዉን እያባባሱት ነዉ።ሕግ እየጣሱ ነዉ፣ የሆንግ ኮንግን ሰላም፣ ሥርዓትና የሕዝቡን ኑሮ ክፉኛ እያወኩ ነዉ።ለሕዝብ ደሕንነት ደንታ የላቸዉም።ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እራሱን ከሁከቱ ማራቅና የነዉጠኞቹ የጭካኔ ርምጃን ማዉገዝ አለበት።መንግስት ሁከቱን ለማስቆም አበክሮ ይጥራል።»

ሆንግ ኮንግ

ከዓለም ትላልቅ የገንዘብ ማዕከላት አንዷ ናት።የዓለም ቱጃሮች ሸጠዉ፣ለዉጠዉ፣ ገዝተዉ፣ቆምረዉ፣ዘርፈዉ አጭበርብረዉ የሚያተርፉባት ለቀቅ፣ዘና፣ ፈታ ማለት ሲያሰኛቸዉ ደግሞ የሚደላቀቁ፣የሚምነሸነሹ፣ የሚቀብጡባት ትንሽ ግዛት ናት።ሸቀጦች ወደ ዉጪ በመላክ ከዓለም አስረኛ፣ ሸቀጦች በማስገባት ደግሞ ዘጠነኛ ናት።

ለተቃዉሞ አደባባይ የወጣና የሚወጣዉ ዓይደለም፣አጠቃላዩ ሰባት ሚሊዮን ሕዝቧ ቢያምፅ እንኳ 1.386 ቢሊዮን ከሚገመተዉ የቻይና ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር በርግጥም ማኦ እንደተቀኙት ከግንቡ ጋር እንደሚላተሙት «ጥቂት ዝንቦች» ኢምንት ነዉ።

China Hong Kong Chinese Enterprises Association
ምስል picture-alliance/Xinhua News Agency/L. Hanxin

ይሁንና አምና አዲስ አበባ ላይ እንዳስተዋልነዉ የ27 ዓመቱን የሕወሐት-ኢሕአዲግን አገዛዝ ለማስወገድ መቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ለተቃዉሞ መሰለፍ አላስፈለዉም።ከቱኒስ እስከ ካርቱም፣ ከካይሮ እስከ ቲቢሊሲ የማንይደፈሩ የሚመስሉ ገዢዎችን ከየመንበራቸዉ አሽንቀንጥሮ ለመጣል የሕዝብ ዓላማና ፍላጎትን ያነገቡ ወጣቶች እንጂ መላዉ ሕዝብ አደባባይ መሰለፍ አላስፈለገዉም።

የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚ ሰልፈኞችም ጥያቄ-አላማችን የሕዝብ ነዉ ባዮች ናቸዉ።ከተቃዉሞ ሰልፈኞቹ መሪዎች አንዷ ባለፈዉ አርብ እንዳለችዉ ደግሞ መንግስት ጥያቄዉን ከመመለስ ይልቅ ከዚሕ ቀደም የተጠመበትን ስልት አሁንም ገቢር ለማድረግ እየተዉተረተረ ነዉ።«ዋጋ ቢስ» ትለዋለች-እሷ።

«የሆንግ ኮንግ መንግሥት ተቃዉሞ ሰልፈኞችን ለመበትን ከዓምስት ዓመት በፊት የተጠቀመበትን ሥልት ዛሬም እየተጠቀመበት ነዉ።እነዚያ ስልቶች ግን ዛሬ ዋጋ የላቸዉም።መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ፣ (የቻይና) የሕባዊዉ ነፃ አዉጪ ጦርን ይሰፍራል በማለት  ሕዝቡን እያስፈራራ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ ተማሪዎችን በመደዳ እንደሚያጠቃ (እየዛተም) ነዉ።»

የዛሬ አምስት ዓመት።2014 ነዉ።ያኔ፣ ቻይና በሆንግ ኮንግ አስተዳደር በቀጥታ ጣልቃ እየገባች ነዉ በማለት ድርጊቱን በመቃወም የተደረገዉ ሰልፍ፣ የሰልፈኞችን ጥያቄ አድበስብሶ ነበር የተበተነዉ።ሰልፈኞቹ ሰፍረዉበት ከነበረዉ የመጨረሻ አደባባይ ፖሊስ ሲበትናቸዉ «እንመለሳለን» በማለት የዛቱትም ጥያቄያቸዉ መልስ ባለማግኘቱ ነበር።

Hongkong Protestkundgebung vor dem Chater Garden
ምስል picture-alliance/AP Photo/K. Cheung

የቻይና መንግስት ሆንግ ኮንግን ከብሪታንያ ቅኝ ገዚዎች በ1997 ሲረከብ በወጣዉ መሠረታዊ ሕግ (ሕገ-መንግስት) መሠረት ግዛቲቱ የቻይና ግማደ-ግዛት ግን በራስዋ ሕግ አዉጪና ሕግ አስፈፃሚ የምትተዳደር ራስ-ገዝ አስተዳደር ናት።

ይሁንና የግዛቲቱን ዋና አስተዳዳሪ ወይም አገረ-ገዢን የሚመርጠዉ ለቤጂንግ ይወግናል የሚባለዉ 1200 አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ ነዉ።በ2014 ቻይና አዲስ ማሻሻያ ማዉጣትዋ ለከፋዉ ተቃዉሞ ምክንያት፣ ለዘንድሮዉም እርሾ ሆኗል።የ2014  ሕግ እንደሚለዉ ለቤጂንግ አስተዳደር ቅርበት አለዉ የሚባለዉ ኮሚቴ ለመሪነት የሚወዳደሩ ዕቹዎችን ዝርዝር ለሕዝብ ያሳዉቃል።ሕዝቡ ከቀረቡለት ዕቹዎች መሐል ብቻ አስተዳዳሪዉን ይመርጣል።

ሕጉ «አሳፋሪ ዴሞክራሲ» የሚል ዉግዘትና ተቃዉሞ ከገጠመዉ በኋላ የግዛቲቱ ምክር ቤት ዉድቅ አድርጎታል።ምክር ቤቱ ከሚያስተናብራቸዉ ከ70ዎቹ የእንደራሴዎች እንኳ የተወሰኑት በቤጂንግ ትዕዛዝ ምክር ቤት የሚገቡ እንጂ በሕዝብ የተመረጡ ዓይደሉም።

ከሰኔ ጀምሮ እስከ ዛሬ የዘለቀዉ የዘንድሮዉ ተቃዉሞ መነሻ የወይዘሮ ኬሪ ላም አስተዳደር በወንጀል የሚጠረጠሩ የግዛቲቱ ተወላጆችን ለቤጂንግ አሳልፎ የሚያሰጥ ደንብ ማርቀቁ ነዉ።ይሁንና መሰረታዊዉ ምክንያት ከ2014 ምናልባትም ከ1997 ጀምሮ የተጠራቀመዉ ብሶት በመሆኑ ረቂቁ ከተሻረ በኋላም ተቃዉሞዉ ቀጥሏል።

በርዕዮተ ዓለም፣ በግዛትም፣ በገበያ ሽሚያም፣ የዓለምን ሐብት በመቀራመትም፣ በቆየ ቂም ቁርሾ ሰበብ ከቤጂንጎች ጋር የሚሻኮቱት፣ ከቶኪዮ-እስከ ዋሽግተን፣ ከለንደን እስከ ፓሪስ፣ ከሶል እስከ ብራስልስ ያሉ መንግስታት ተቃዉሞ ሰልፉን ቤጂንግን ለማሳጣት እንደጥሩ አጋጣሚ ማየታቸዉ አልቀረም።

የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ብሪታንያን ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት ለማስወጣት እንዲመቻቸዉ በሕዝብ የተመረጠዉን የሐገሪቱን ምክር ቤት (ፓርማ)ን ማዘጋታቸዉን በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የብሪታንያ ሕዝብ ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉሞታል።የብራስልስ-ዋሽግተን መሪዎች በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት ስለመዘጋቱ የሚሉት ካለ፣ ሲሉ እንሰማለን።

Hongkong Gewalt bei Protesten
ምስል Reuters/T. Siu

የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚዎችን በመደገፍ ቤጂንግን ለማዉገዝ ግን ቀዳሚዎቹ የቀድሞዋ የግዛቲቱ ቅኝ ገዢ ብሪታንያ ፖለቲከኞች ነበሩ።የቡድን ሰባት ሐገራት መሪዎች ቀጠሉ፤ የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬድሪካ ሞጎሕሮኒ አርብ አሰለሱ።

«በርግጥ፣ ሆንግ ኮንግ ዉስጥ በተለይ ባለፉት ሰዓታት ዉስጥ የሚወሰደዉ እርምጃ በጣም አሳሳቢ ነዉ። የሆንግ ኮንግ ባለስልጣናት የመሰብሰብ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመደራጀትና በሠላም የመሰለፍ መብትን እንዲያከብሩ እንጠብቃለን። እንደ አዉሮጳ ሕብረትና ከአባል መንግስታት ጋር በመቀናጀትም ሁኔታዉን በቅርብ መከታተላችንን እንቀጥላለን።»

ሆንግ ኮንግ ለተቃዉሞ ሰልፍ እንግዳ አይደለችም።

በ1841 የመጀመሪያዉ የኦፕየም ጦርነት በተባለዉ ዉጊያ ብሪታንያ ቂዊንግ ከተባለዉ የቻይና ሥርወ-መንግስት አገዛዝ ትንሺቱን የባሕር ዳርቻ ግዛት ማረከች።በ1898 ሌላዉን አካባቢ ለ99ኝ ዓመት ከቻይና ተኮናተረች።ከ1920ዎቹ ጀምሮ የግዛቲቱ ሕዝብ የብሪታንያን እና ላጭር ጊዜ የቆየዉን የጃፓንን አገዛዝ ሲቃወም-ሲያድም ዓመታት አስቆጥሯል።በተለይ በ1922፤ በ1925፣ በ1950፣ በ1967 እና እስከ 1997ት የተደረገዉን ሰልፍና አድማ የመሩት ኮሚንስቶች ነበሩ።

ከ1997 እስካሁን የቀጠለዉ ሰልፍ አስተባባሪዎች ደግሞ ስልጣናቸዉን የተቀሙ የካፒታሊስቱን ዴሞክራሲ የሚያቀነቅኑ፣ ቻይና እንደምትለዉ ደግሞ በካፒታሊስቶች የሚደገፉ ናቸዉ።የቻይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል ቀባይ ጌንግ ሹዋንግ ባለፈዉ ሳምንት ለቡድን 7 አባል ሐገራት መሪዎች መግለጫ በሰጡት አፀፋም   የቡድኑ አባላት «አመፁን ከጀርባ የሚገፉ»  ብለዋቸዋል።

«የቡድን ሰባት መሪዎች የሆንግ ኮንግን ጉዳይ በተመለከተ፣ (አመፁን) ከጀርባ  እንደሚገፋ (ኃይል) ባወጡት አፍራሽ መግለጫ ጨርሶ አልረካንም።አጥብቀን እንቃወመዋለንም።የሆንግ ኮንግ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የቻይና የዉስጥ ጉዳይ መሆኑን ደጋግመን ገልፀናል።ማንኛዉም የዉጪ መንግስት፣ድርጅት ወይም ግለሰብ ጣልቃ የመግባት መብት የለዉም።»

Hongkong Victoria Park Demonstration und Proteste
ምስል AFP/I. Lawrence

ተቃዉሞ፣ዉዝግቡ ቀጥሏል።ወይዘሮ ካሪ ላምም ስልጣናቸዉን የማስረከብ አዝማሚያ አላሳዩም።የትንሺቱ፣ ኮሚንስቶችን በማሳጣት የእልሕ-መርሕ የከበረችዉ የንግድ ማዕከል ምጣኔ ሐብትም እየተሽመደመደ ነዉ።ባለፉት ሁለት ወራት ፖሊስና ተቃዋሚ ሰልፈኞች፣ ተቃዋሚና ደጋፊዎች ያልተጋጩበት ሳምንት የለም።እስካሁን ግን አንድም ሕይወት አልጠፋም።ከእንግዲሕ?ነጋሽ መሐመድ ነኝ ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ