1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሐምሌ 11 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሐምሌ 11 2008

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ሊጀመር 26 ቀናት ይቀሩታል። የማማሟቂያ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ሌስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ብሎም ቸልሲ ከአሸናፊዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል። አርሰናል አልቀናውም። በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ኢትዮጵያዊው ተወዳዳሪ ጽጋቡ ገብረማሪያም ከ100 በላይ ተወዳዳሪዎችን መቅደም ችሏል።

https://p.dw.com/p/1JR3A
Der deutsche Triathlet Jan Frodeno
ምስል picture-alliance/dpa/D. Karmann

ስፖርት፣ ሐምሌ 11 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ አዲስ ክፍለ ጊዜ ሊጀመር 26 ቀናት ብቻ ይቀሩታል። አንዳንድ ቡድኖች አቅማቸውን ለመፈተሽ ወደ ውጪ ሃገራት ተጉዘው ግጥሚያ አድርገዋል። አንዳንዶች ደግሞ እዛው እንግሊዝ ውስጥ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር በመጋጠም አቅማቸውን ፈትሸዋል።

ቸልሲ ወደ ኦስትሪያዋ ቪዬና ከተማ አቅንቶ ቅዳሜ ዕለት ከራፒድ ቪዬና ጋር ባደረገው ጨዋታ 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል። በተመሳሳይ ቀን አርሰናል ብሔራዊ ሊግ ውስጥ ከሚገኘው ቦረሃም ውድ ጋር ተጋጥሞ 3 ለ0 ተሸንፏል። ማንቸስተር ዩናይትድ የሊግ ዋን ተሳታፊው ዊጋን አትሌቲክን ቅዳሜ ዕለት በሜዳው 2 ለባዶ ድል አድርጓል። ዊጋን አትሌቲክ በበነጋታው በሜዳው ባካሄደው ጨዋታ በሊቨርፑልም 2 ለ0 ተቀጥቷል። ፍሊት ውድ ታውንን 5 ለዜሮ ያንኮታኮተው ሊቨርፑል እስካሁን ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችሏል። ማንቸስተር ሲቲ ከነገ በስትያ ጀርመን ውስጥ በአሊያንስ አሬና ስታዲየም ከኃያሉ ባየር ሙይንሽን ጋር ይጋጠማል። ሌስተር ሲቲ ነገ ከኦክስፎርድ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል። ክሪስታል ፓላስ ከአሜሪካው ፊላዴልፊያ ዩኒየን ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል።

የእግር ኳስ ተጨዋቾች ዝውውር

ሊቨርፑል የአውስቡርገሩ የመሀል ተከላካይ ራግናር ክላቫንን በ 4,2 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያስፈርም መቃረቡን ቢቢሲ ዘግቧል። ኢስቶኒያዊው የ30 ዓመት ተከላካይ በቁርጭምጭሚት ጉዳት በአዲሱ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሰለፍ የማይችለውን ፈረንሳዊው ማማዱ ሳኮ ቦታን ይሸፍናል ተብሏል። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ተከላካያቸው ኮሎ ቱሬ ቡድኑን ለቆ በመውጣቱ እና ማርቲን ስክርቴል ለፌኔርባኅ በመሸጡ የተከላካይ ክፍላቸውን ማጠናከር አጥብቀው ይሻሉ። ራግናር ክላቫን በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ለቀያዮቹ የፈረመ አራተኛ ተጨዋች ይኾናል።

የባለፈውን ዙር የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ በአስደናቂ ኹናቴ በእጁ ያስገባው ሌስተር ሲቲ ቡድን አማካዩ ንጎሎ ካንቴን በ30 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ወደ ቸልሲ ሊያዘዋውር መሆኑን አስታወቋል። ቀበሮዎቹ በሚል የሚታወቁት ሌስተር ሲቲዎች እንዲህ በርከት ያለ የዝውውር ክፍያ ሲያገኙ በቡድናቸው ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ሌስተር ሲቲ የፈረንሣዩ አማካይ ተጨዋች ንጎሎ ካንቴን ባለፈው ዓመት ከካኤን ቡድን ያስፈረመው በ6 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነበር። አኹን አራት ዕጥፍ አትርፎበት ለቸልሲ አስረክቦታል። ንጎሎ ካንቴ ሰሞኑን ለቸልሲ ቡድን በመፈረም ሁለተኛው ተጨዋች ኾኗል። ቀደም ሲል ከፈረንሳዩ ማርሴ ቡድን ለቸልሲ የፈረመው ተጨዋች የቤልጂየሙ አጥቂ ሚኪ ባትሹዋይ ነው።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ማሪዮ ጎይትሰ ወደ ቀድሞ ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሊመለስ መሆኑ ተዘግቧል። ሆኖም ማሪዮ ጎይትሰ ከባየር ሙይንሽን ጋር ያደረገው ውል ሊያበቃ ገና አንድ ዓመት ይቀረዋል። የማሪዮ ጎይትሰ ዝውውር ዜና በተሰማበት ወቅት የባየርን ሙይንሽኑ የክንፍ ተጨዋች ሆላንዳዊው አሪየን ሮበን ብሽሽቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት በቡንደስ ሊጋው አዲስ የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ጨዋታዎች እንደማይሰለፍ ተነግሯል። ባየር ሙይንሽን ከሦስት ዓመት በፊት በ37 ሚሊዮን ዶላር ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ያስመጣውን ማሪዮ ጎይትሰን ወደቦሩስያ ዶርትሙንድ ለመመለስ 30,9 ሚሊዮን ዶላር መጠየቁ ተገልጧል። ያኔ የ24 ዓመቱ አማካይ ማሪዮ ጎይትሰ ወደ ባየር ሙይንሽን የተዘዋወረበት ክፍያ በጀርመን የቡንደስ ሊጋ ታሪክ ትልቁ ክፍያ ነበር።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ማሪዮ ጎይትሰ
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ማሪዮ ጎይትሰምስል Getty Images/M. Hangst
የአውስቡርገሩ የመሀል ተከላካይ ራግናር ክላቫን
የአውስቡርገሩ የመሀል ተከላካይ ራግናር ክላቫንምስል Imago/MIS

አትሌቲክስ

ትውልደ ኢትዮጵያዊት ስዊድናዊቷ አትሌት አበባ አረጋዊ አበረታች ንጥረ ነገር ተጠቅማለች በሚል የተጣለባት እገዳ መነሳቱ ቅዳሜ ዕለት ቢነገርም በሪዮ ኦሎምፒክ እንደማትሳተፍ የስዊድን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። አትሌት አበባ በዓለም አቀፉ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ተከታታይ ተቋም በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (WADA) የተከለከለውን ሜልዶኒየም የተሰኘውን ንጥረ ነገር ተጠቅማለች በሚል ነበር ከውድድር ታግዳ የቆየችው። አትሌት አበባ በስዊድን የኦሎምፒክ ቡድን የመታቀፍ ተስፋ አለኝ ስትል መናገሯን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል። የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ተከትሎ የስዊድን ጋዜጦች እና ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ምን አሉ? የስዊድኑ ወኪላችን ቴድሮስ ምሕረቱን በስልክ አነጋግሬዋለሁ። በፌዴሬሽኑ ውሳኔ በርካታ አትሌቶች መደመማቸውን ገልጧል።

ዓለም አቀፉ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ተቋም ሩስያን በተመለከተ በካናዳዊው ፕሮፌሰር ማክላረን በኩል ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። ሩስያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 ዓመት የሶቺ ኦሎምፒክ ወቅት አትሌቶቿ የተከለከሉ አበረታች ንጥረ ነገሮችን ሲጠቀሙ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል በሚል ምርመራ እየተደረገባት ቆይቷል። በዛሬው መግለጫ የሞስኮ ቤተ-ሙከራዎች የተጠርጣሪ አትሌቶች የምርመራ ውጤቶችን አዛብቷል ተብሏል። ኾኖም ግን ለዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የመፍትኄ ሐሳቦችን አላቀረበም።

አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ በላውዛኔ፤ ስዊዘርላንድ ቤተ-ሙከራ ውስጥ
አበረታች ንጥረ ነገር ምርመራ በላውዛኔ፤ ስዊዘርላንድ ቤተ-ሙከራ ውስጥምስል picture-alliance/AP Photo/F. Coffrini

የሩስያ ኦሎምፒክ ኃላፊ አሌክሳንደር ዙኮብ ዋዳ ለዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴ አንዳችም የመፍትኄ ሐሳብ ባለማቅረቡ ደስተኛ ነን ብለዋል። ዓለም አቀፉ የጂምናስቲክ ፌዴሬሽን በበኩሉ ቀደም ሲል የሩስያ ጂምናስቲክ ስፖርተኞች በኦሎምፒክ እንዲሳተፉ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብሏል። የበርካታ ሃገራት ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ተቋማት ግን ሩስያ ሙሉ ለሙሉ ከሪዮ ኦሎምፒክ እንድትታገት ሲወተውቱ ነበር። የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባኅ ዛሬ ይፋ የተደረገው የዋዳ ሰነድ ለስፖርቱ እጅግ አስደንጋጭ እና ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት ነው ሲሉ ኮንነዋል። ፕሬዚዳንቱ ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ኮሚቴው ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ አንዳችም እንደማያመነታ ተናግረዋል። ሪዮ ኦሎምፒክ ሊጀመር 18 ቀናት ይቀሩታል።

በትሪያትሎን ሽቅድምድም ያን ፍሮዴኖ አዲስ ክብር ወሰን አስመዘገበ። የ34 ዓመቱ ጀርመናዊ አትሌት ክብር ወሰኑን የሰበረው ትናንት ኑረንበርግ ከተማ ውስጥ በተደረገው ውድድር ነው። በውድድሩም፦ 3,86 ኪሎ ሜትር በመዋኘት፣ 180 ኪሎ ሜትር ቢስክሌት በመንዳት ከዚያም 42,195ኪሎ ሜትር ማራቶን በመሮጥ በጥቅሉ ውድድሮቹን በ7:41:33 በመጨረስ አዲስ ክብር ወሰን ተመዝግቦለታል።

Der deutsche Triathlet Jan Frodeno Weltrekord
ምስል picture-alliance/GES-Sportfoto

«በርግጥም ደስ የሚል ስሜት ነው ምንም ጥርጥር የለውም። ዝም ብሎ ከመከተል አንዳች ነገር አቅደህ ማሳካቱ የበለጠ የተሻለ ነው። ግን በመሀከል መሰናክል ገጥሞኛል። እናም ትንሽ ሰአት ዘግይቶብኛል። መቼም የት ጋር እንደምትቆም አታውቀውም። ያም በመሆኑ ያለምንም ግብ ዝም ብዬ በመሮጥ ሩጫዬን ላጣጥምም እችል ነበር።»

በውድድሩ ወቅት ያን ፍሮዴኖ ሁለት ጊዜ አስደንጋጭ ነገር ገጥሞታል። የመጀመሪያው 120 ኪሎ ሜትር ላይ ተሰናክሎ ወድቋል። በእርግጥ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ሩጫ ሊጀምር ሲል ደግሞ ሳይታሰብ በአጠገቡ አንድ መኪና ውልብ ብሎ አልፏል። አትሌቱ በጥንቃቄ በመመልከቱ ሊደርስበት ከነበረው አደጋ ተርፏል። እናም አሁን እጅግ የዛለ ሰውነቴን ለማሳረፍ ለጥ ማለት ነው የሚበጀኝ ብሏል።

በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም 15ኛ ዙር ውድድር አጠቃላይ ውጤት ኢትዮጵያዊው ብስክሌተኛ ጽጋቡ ገብረማርያም ግርማይ 83ኛ ደረጃን ሲይዝ፤ የኤርትራ ተፎካካሪዎቹ ዳንኤል ተክሃይማኖት እና ናትናኤል ብርሐኔ 90ኛ እና 118ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ