የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ሐምሌ 18 2008
ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሩስያን በተመለከተ ትናንት ያስተላለፈው ውሳኔ ብዙዎችን አስደምሟል። የሩስያ መንግሥት አትሌቶቹ አበረታች ንጥረ ነገሮችን እንዲጠቀሙ ሁኔታዎችን ሲያመቻች በመክረሙ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ከሪዮ ኦሎምፒክ ሊታገድ ይችላል ተብሎ ነበር። ያ ግን አልሆነም። የቱር ደ ፍሯንስ ብስክሌት ሽቅድምድም በብሪታንያዊው ክሪስ ፍሮም ድል ተጠናቋል። በሜዳ ቴኒስ የሞንትሪያል ውድድር ሴሬና ዊሊያምስ ለሦስት ጊዜያት ያሸነፈችበት ውድድር ላይ አትካፈልም። የአውስትራሊያ የኦሎምፒክ ቡድን ወደ ሪዮ የኦሎምፒክ መንደር እንደማይገባ አስታወቋል። በፖላንዱ ዓለም አቀፍ የታዳጊዎች አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮፕያ የሦስተኛ ደረጃን አገኘች። በሪዮ ኦሎምፒክ የስደተኞች ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሳተፍ ነው። ከዓሥሩ የቡድኑ አባላት መካከል ኢትዮጵያዊ ይገኝበታል።
ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሩስያ ሙሉ ለሙሉ ከሪዮ ኦሎምፒክ ትታገድ የሚለውን ሐሳብ ውድቅ አድርጓል። ሐሳቡ የቀረበው በዓለም አቀፉ ጸረ አበረታች ንጥረ ነገር ተከታታይ ተቋም በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (WADA) ነበር። እያንዳንዱ አትሌት በውድድሩ ላይ መሳተፍ አለያም አለመሳተፉን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኖች በተናጠል ሊወስኑ ይችላሉ ብሏል። ሩስያ ለረዥም ዓመታት በተለይ በ2014 የሶቺ ኦሎምፒክ ወቅት አትሌቶቿ አበረታች ንጥረ ነገር እንዲጠቀሙ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል መባሉ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ሊሰረዝ ይችላል የሚል ግምት አስነስቶ ነበር። ብዙአየሁ ዋጋው የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበርን (IAAF)ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ መገናኛ አውታሮች ዘጋቢ ነው። በሩስያ ጉዳይ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማቱ ወዲህ እና ወዲያ የማለታቸውን ምክንያት እንዲህ ያብራራል።
ወደ ሪዮ የሚያቀናው የሩስያ ኦሎምፒክ ቡድን በአበረታች ንጥረ ነገር ቅጣት የተነሳ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 13 ሰዎች ብቻ እንደሚኖሩት ሮይተርስ ዛሬ ዘግቧል። ይህን የተናገሩት የሩስያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊ አሌክሳንደር ዙኮቭ መሆናቸውን አር ስፖርት የዜና ምንጭ ዘግቧል ሲል ሮይተርስ አክሎ ጠቅሷል።
በፖላንድ ቢድጎቺች ከተማ ለ6 ቀናት የተከናወነው የታዳጊዎች የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ትናንት ተጠናቋል። ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች በሚሳተፉበት ውድድር ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 2 የብር እና 4 የነሀስ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ኬንያን ተከትላ ሦስተኛ ወጥታለች። ኬንያ 5 የወርቅ፣ 2 የብር እና 2 የነሀስ በአጠቃላይ 11 ሜዳሊያዎች አግኝታለች። 11 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሀስ በአጠቃላይ 21 ሜዳሊያዎች ሰብስባ ዩናይትድ ስቴትስ አንደኛ ወጥታለች።
የእግር ኳስ ተጨዋቾች የዝውውር ዜና
አርሰናል በ75 ሚሊዮን ፓውንድ ውል የሌስተር ሲቲው የክንፍ ተጨዋች ሪያድ ማህሬዝን እና የሊዮኑ አጥቂ አሌክሳንደር ላካዜቴን ወደ ኤሚሬት ስታዲየም ሊያስመጣ መሆኑን ሰንደይ ሚረር የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። ስዋንሲ ሲቲ ደግሞ የ27 ዓመቱ ዊልፍሬድ ቦኒን ከማንቸስተር ሲቲ ሊያስፈርም እየተነጋገረ መሆኑን ሰንዴይ ኤክስፕረስ የተሰኘው ጋዜጣ አትቷል። የአይቮሪኮስቱ አጥቂን ኤቨርተንም ዐይኑን ጥሎበታል።
የ23 ዓመቱ የኤቨርተን አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ እንደ እሱ አባባል «ያልተጠናቀቀ ጉዳዩን» ለማጠናቀቅ ወደ ቸልሲ ሊመለስ መሆኑን ሰን ኦን ሰንደይ ጋዜጣ ዘግቧል። ቸልሲ በቅርቡ ያስፈረመው ንጎሎ ካንቴ በሚቀጥለው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሚለብሰው ሰባት ቁጥር መለያ ሰጥቶታል። የማርሴዩ የክንፍ ተጨዋች ጌኦርጌስ ኬቪን ንኮዱ ለቶትንሀም ለመፈረም ጫፍ ላይ መድረሱን ኢንዲፔንደት ዘግቧል። ዋይኔ ሮኑ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ አምበል ሆኖ እንደሚቆይ የእንግሊዙ አዲሱ አሰልጣኝ ሳም አላርዲስ ተናግረዋል። ሊቨርፑል ለአውሮጳ ሊግ ከስፔኑ ሴቪያ ጋር በተጫወተበት ወቅት ደጋፊዎቹ ርችቶችን እየተኮሱ በመበጥበጣቸው 13,400 ፓውንድ መቀጣቱ ተገልጧል። የደጋፊዎች ብጥብጡ የተከሰተው ከሁለት ወራት በፊት የስዊዘርላንድ ባዝል ከተማ ውስጥ ነበር።
ብስክሌት
ብሪታንያዊው ክሪስ ፍሮም በቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም 21ኛ እና የመጨረሻ ዙር ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆነ። ክሪስ ዘንድሮ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን ለሦስተኛ ጊዜ ነው። ይኽም በብሪታንያ የብስክሌት አሽከርካሪዎች ታሪክ የመጀመሪያው ስፖርተኛ አድርጎታል።
አሜሪካዊው ላንስ አርምስትሮንግ ውጤቶቹን በመነጠቁ ክሪስ ፍሮም ከስፔናዊው ሚጉዌል ኢንዱራይን ቀጥሎ ውጤቱን በማስጠበቅ ሁለተኛ ነው። ለ7 ተከታታይ ጊዜያት አሸናፊ የነበረው አሜሪካዊው ላንስ አርምስትሮንግ አጠቃላይ ውጤቶቹ የተሰረዙበት አበረታች ንጥረ ነገር መጠቀሙን በማመኑ ነበር።
ስፔናዊው ሚጉዌል ኢንዱራይንእንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1991 አንስቶ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም አሸናፊ ጠንካራ ተወዳዳሪ ነው። የዘንድሮውን ጨምሮ ለሦስት ዓመታት ባለድል የሆነው የብሪታንያው ክሪስ ፍሮሜሚጉዌል ላይ ለመድረስ እየገሰገሰ ነው። ምናልባት ጥንካሬው በዚሁ ከቀጠለ እና በተከታታይ ካሸነፈ በ34 ዓመቱ ስፔናዊውን በመብለጥ ክብርወሰኑን ይሰብር ይሆናል።
ለ21 የተለያዩ ቀናት በተከናወነው የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም አጠቃላይ ውጤት ኢትዮጵያዊው ጽጋቡ ገብረማርያም ከ174 ተወዳዳሪዎች የ92ኛ ደረጃን አግኝቷል። ጽጋቡ ለመጀመሪያ ጊዜ በቱር ደ ፍሯንስ ያስመዘገበው ውጤት እጅግ የሚበረታታ ነው። የኤርትራው ናትናኤል ብርሃኔ 125ኛ ደረጃን ሲያገኝ፤ ሌላኛው የኤርትራ ተወዳዳሪ ዳንኤል ተክለ ሃይማኖት 85ኛ በመውጣት ጠንካራ ብስክሌተኛነቱን አስመስክሯል።
የሜዳ ቴኒስ
አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ ሞንትሪያል ካናዳ ውስጥ በሚቀጥለው ሣምንት በሚደረገው የዓለም ቴኒስ ማኅበር ግጥሚያ እንደማትካፈል አሳወቀች። ሴሬና ከውድድሩ የወጣችው ትከሻዋ ላይ በደረሰባት ጉዳት መሆኑን የውድድሩ አዘጋጆች ገልጠዋል። የዓለም ቴኒስ ማኅበር ውድድሮችን ለሦስት ጊዜያት አሸናፊ ከሆነችው ሴሬና ዊሊያምስ ባሻገር በወንዶች ውድድርም ዋነኛ ተፎካካሪዎች ከውድድሩ መውጣታቸው ምናልባትም ከሁለት ሳምንት በታች ለቀረው የሪዮ ኦሎምፒክ ጊዜ ወስደው ለማረፍ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
የመኪና ሽቅድምድም
በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ብሪታንያዊው ልዊስ ሐሚልተን በተመሳሳይ መርሴዲስ ተሽከርካሪ የቡድኑ ተፎካካሪ ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግን በ6 ነጥብ እየመራ ይገኛል። በእሁዱ የሐንጋሪ ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ሐሚልተን 1ሰአት ከ40 ደቂቃ ከ30.115 ሰከንድ በማጠናቀቅ መሪነቱን አስጠብቋል። በዚህም መሠረት ሌዊስ ሐሚልተን 192 ነጥቦችን እስካሁን ሰብስቧል። ኒኮ ርዝበርግ በ186 ነጥቦች ይከተላል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው አውስትራሊያዊው ዳንኤል ሪካርዶ 115 ነጥቦች አሉት። በፌራሪ ተሽከርካሪው የሚወዳደረው የፊንላንዱ አሽከርካሪ ኪም ሬይከነን በ114 ነጥቡ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የስደተኞች ቡድን በኦሎምፒክ ይሳተፋል። በስደተኞች ቡድን ከታቀፉት 10 አትሌቶች መካከል የ36 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ማራቶን ሯጭ ዮናስ ኪዳኔ ይገኝበታል። ዮናስ ካለፉት አምስት ዓመታት አንስቶ ነዋሪነቱን በአውሮጳ ሉግዘምበርግ አድርጓል። ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ ጀርመን ውስጥ ያደረገውን ውድድርም 2 ሰአት ከ17 ደቂቃ በማጠናቀቅ ብርቱ ተፎካካሪ መሆኑን አሳይቷል።
የአውስትራሊያ የኦሎምፒክ ቡድን የብራዚሏ ሪዮ የኦሎምፒክ መንደር የጥራት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም በሚል አትሌቶቹ መንደሩ ውስጥ እንደማይቆዪ አስታወቀ። ፍሳሽ በአግባቡ የማያስተላልፉ መጸዳጃ ቤቶች እና የሚያንጠባጥቡ ቧንቧዎች መገኘታቸው አውስትራሊያ ወደ ኦሎምፒክ መንደሩ ላለመሄድ ምክንያት እንደሆናት አስታውቃለች።
ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፍጻሜ እና የደረጃ ውድድሮች የፊታችን ቅዳሜ እንደሚከናወኑ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በኢሜል በላከው መልእክት ገልጧል። የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ደግሞ ሐሙስ ይከናወናሉ።
የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቮልፍጋንግ ኒርስባኅ ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለአንድ ዓመት ታገዱ። ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማሕበራት ፌዴሬሽን በእንግሊዝኛ ምኅፃሩ (FIFA) ቮልፍጋንግ ኒርስባኅን ያገዳቸው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2006 ዓመት ሀገራቸው ጀርመን የዓለም ዋንጫን እንድታሰናዳ ሙስና ፈጽመዋል በሚል ነው።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አርያም ተክሌ