ሕንድ እና ፓኪስታንን እንደገና ያቃቃረው የካሽሚር ቀውስ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 7 2011ሕንድ በምታስተዳድረዉ የካሽሚር ግዛት የጣለችው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ሲይዝ የግዛቲቱ ነዋሪዎች ለዕለት ከዕለት ኑሯቸው የሚያሿቸው ሸቀጦች እጥረት ገጥሟቸዋል። አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው በየዕለቱ ሕንድ ላይ ያነጣጠሩ ተቃውሞዎች ይደረጋሉ፤ ወጣቶች ድንጋይ ይወረውራሉ፤ ጎማ ያቃጥላሉ። የካሽሚር ዋና ከተማ በሆነችው የሸሪነገር ሰማይ ሰው አልባ የስለላ አውሮፕላኖች እና ወታደራዊ ሔሊኮፕተሮች በየቀኑ ያንዣብባሉ።
የሕንድ መንግሥት የግዛቲቱን የመደበኛ ስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ዘግቷል። ጋዜጠኞችም እንዳሻቸው መንቀሳቀስ አይችሉም። የካሽሚር ታይምስ ጋዜጣ አርታኢ አኑራድሐ ባኻሲን በግዛቲቱ ጋዜጠኞች እንዳይንቀሳቀሱ የተጣለው ዕገዳ እንዲነሳ ለፍርድ ቤት ያቀረበችው አቤቱታ ውድቅ ሆኗል። በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ የተጠየቀው የሕንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ባስተላለፈው ውሳኔ በጉዳዩ ስሱነት ሳቢያ መንግሥት የፈለገውን ገደብ መጣል ይችላል የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጣጠኛው አንቀፅ 370
የሕንድ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በአብላጫ ድምፅ የሻረው የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 370 ሕንድ፣ ፓኪስታን እና ቻይና ከ70 አመታት በላይ ለተወዛገቡበት የጃሙ እና ካሽሚር ግዛት ልዩ አስተዳደራዊ ሥልጣን ይሰጥ ነበር። ከመከላከያ፣ የውጭ ግንኙነት፣ ፋይናንስ እና ኮምዩንኬሽን ውጪ ግዛቲቱ የራሷን ሕግጋት የማውጣት ሥልጣን በዚሁ አንቀጽ ተሰጥቷት ነበር። የሕንድ ምክር ቤት ከአራቱ ጉዳዮች ውጪ የሚያወጣቸው ሕግጋት በጃሙ እና ካሽሚር ገቢራዊ እንዲሆኑ የግዛቲቱን መንግሥት ይሁንታ ማግኘት ነበረበት።
የሕንድ መንግሥት ውሳኔ የከፋ ቁጣ እና ተቃውሞ የገጠመው መጀመሪያ ከዚያው ከካሽሚር ነዋሪዎች ነው። ከትናንት በስቲያ የኢድ አል-አድሐ በዓል በካሽሚር ተወላጆች ዘንድ ሲከበር ቁጣ እና በሕንድ ውሳኔ ያነጣጠረ ተቃውሞ ተጭኖት ነበር። ቃዚ መሐመድ ዋጂድ አሁን በሕንድ መዳፍ ሥር በሚገኘው የካሽሚር ግዛት ቢወለዱም ኑሯቸው አዛድ ካሽሚር ተብሎ በሚጠራው የፓኪስታን ግዛት ነው። ቃዚ መሐመድ ዋጂድ «እዚህ የተሰበሰብንው ኢድን ለማክበር አይደለም። በኃይል በሕንድ መዳፍ ሥር ለወደቁት ዜጎች አጋርነታችንን ለመግለጽ ነው። በሸሪነገር [በሕንድ ቁጥጥር ሥር የምትገኘው የካሽሚር ግዛት ዋና ከተማ] ሰማይ የካሽሚር እና የፓኪስታን ሰንደቅ ዓላማዎች ጎን ለጎን እስኪውለበለቡ ድረስ ሕንድ የቱንም ያክል ብታፍነን የካሽሚር ሰዎች ዝም አንልም» ሲሉ ዝተዋል።
በሕንድ ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ጃሙ እና ካሽሚር ተብሎ የሚታወቀው ግዛት በሁለት አስተዳደሮች ይዋቀራል። ይኸ ለረዥም ዓመታት በካሽሚር ጉዳይ የከረረ አቋም አላቸው ለሚባሉት የሒንዱ ብሔርተኞች የሚያስደስት ሆኗል። ካሽሚር ተወልደው ኒው ደልሒ የሚኖሩት ኡታል ካውል ለዘመናት ጠብቄዋለሁ ያሉትን ውሳኔ የሕንድ መንግሥት ሲያሳልፍ ደስታቸውን የገለጹት ከእምባቸው እየታገሉ ነበር። ኡታል ካውል «የማይታመን ነው። እውነቱን የሚናገሩ የማይሸፋፍኑ ፖለቲከኞች ይመጣሉ ብለን አላሰብንም። ይኸን ውሳኔ የሚያስተላልፍ የሕንድ መንግሥት አልጠበቅንም። ይኸ ከ1947/1948 ዓ.ም. በኋላ እጅግ ትልቅ ውሳኔ ነው። አሁን አንድ ሕዝብ ነን» ሲሉ ይናገራሉ።
የሕንድና ፓኪስታን አዲስ ውጥረት
የፓኪስታን መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከሕንድ ጋር የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዝቅ ማድረጉን አስታውቋል። ፓኪስታን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባ የጠየቀች ሲሆን ጉዳዩን ወደ ጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እንደምትወስድም አስታውቃለች። የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ሻሕ መሐመድ ቁረይሽ «አንደራደርም ብለዋል፤ ሶስተኛ ወገን ባለበት ውይይት እንዲደረግም ፈቃደኛ አይደሉም። ከሁለትዮሽ ግንኙነትም እያፈገፈጉ ነው። ይኸ በእንዲህ እንዳለ ነው የይገባኛው ውዝግብ ያለበትን የጃሙ እና ካሽሚርን ሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደር የቀየሩት። ውዝግቡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር የሚያውቀው ነው። ምን ማድረግ ነበረብን? ፓኪስታን የቀራት ብቸኛው ምክንያታዊ መፍትሔ ጉዳዩን ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በማቅረብ መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነት እንዳለባቸው መናገር ነው። ጉዳዩ ከዚህ ቀደም የሚያውቁት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሰላም እና ደሕንነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው» ሲሉ መንግሥታቸው የተከተለውን መንገድ አስረድተዋል።
በአሜሪካው ዉድሮው ዊልሰን ማዕከል የእስያ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ሚካኤል ኩግልማን ሕንድ በካሽሚር የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ እና አለመረጋጋት ለምን ያክል ጊዜ እና እንዴት ተቆጣጥራ ትቆያለች የሚለው ጉዳይ ፈታኝ መሆኑን ተናግረዋል። ተንታኙ እንደሚሉት ከፓኪስታን በኩል ለጉዳዩ የሚሰጠው ምላሽ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቁትን ጎረቤታሞች ለሌላ ስጋት ይዳርጋል።
ተንታኙ "ሕንድ ለካሽሚር ልዩ አስተዳደራዊ ሥልጣን የሚሰጠውን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 370ን መሰረዟን ፓኪስታን አትደግፍም። ምክንያቱን ፓኪስታን በካሽሚር ግዛት የሚገኘው የጃሙ አካባቢ ላይ ለረዥም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ ስታቀርብ ቆይታለች። ጥያቄው አሁን ፓኪስታን ምን ታደርጋለች የሚለው ነው። በካሽሚር ችግር ለመፍጠር የጦር ኃይሏን ትጠቀማለች? ወይስ በሕንድ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና ለማሳደር እንደ መሳሪያ ትገለገልበታለች? ይኸ ወደ ፊት የሚታይ ነው። ሕንድስ በካሽሚር የሚታየውን አለመረጋጋት እንዴት ትቆጣጠረዋለች? ከፓኪስታን በኩል የሚመጣውንስ ምላሽ እንዴት ትቋቋማለች?" ሲሉ ይጠይቃሉ።
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ዋንግ ይ በዛሬው ዕለት ከሕንዱ አቻቸው ሱብራሕማንያም ጃይሻንካር ጋር ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ መምከራቸውን ሸንዋ ዘግቧል። እንደ ሽንዋ ዘገባ ከሆነ ሕንድ «በቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አዎንታዊ ሚና ይኖራታል» የሚል ተስፋ ቻይና እንዳላት ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባለፈው ሳምንት በቃል አቀባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ሕንድም ሆነች ፓኪስታን ጉዳዩን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት «የጃሙ እና ካሽሚር እጣ-ፈንታ በሰላማዊ መንገድ ሊወሰን ይገባል» የሚል አቋም እንዳለው የገለጹት ዋና ጸሐፊው ሕንድ ከጣለችው የሰዓት ዕላፊ በኋላ በግዛቲቱ የሚኖረው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።
የሕንዱ ጠቅላይ ምኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ግን የመንግሥታቸውን ውሳኔ የነቀፉትን ሁሉ ተችተው የካሽሚር ጣጣ የአገራቸው የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል። ሞዲ በመንግሥታቸው ውሳኔ መሰረት ከጃሙ እና ካሽሚር ግዛት የተወሰኑ አካባቢዎች የመምረጥ ዕድል ማግኘታቸው ተጭኖባቸው የነበረውን ኢ-ፍትኃዊነት የመሻሩ ምልክት አድርገው አቅርበውታል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ