ሰኞ፣ መስከረም 22 2010
የኤርትራ መንግስት አቋም የአልጄርሱ ስምምነት ይከበር የሚል ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ስምምነቱ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት መጀመርያ ዉይይት መካሄድ አለበት ይላል። የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በሐገሪቱ ለተከሰተዉ የፖለቲካ አለመረጋጋት የኤርትራ መንግስት እጅ አለበት ሲል ይወቅሳል። የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ የሶማሊያውን ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብን ትረዳለች በሚል ክስ ታህሳስ 14 ቀን 2002 ዓ/ም ማዕቀብ እንደጣለባት ይታወሳል።
የኤርትራዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኦስማን ሞሃመድ ሳሌህ መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ/ም ለ72ኛዉ የተባባሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር የተጣለዉ ማዕቀብ «ፍትሀዊና ተገቢ» ስላልሆነ ይነሳ ሲሉ ጠይቀዋል። ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ መንግስት የአገራቸዉ ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ ወደ ፊት እንዳይራመድ እንቅፋት ሆኗል ሲሉም ከሰዋል: «በኤርትራ፣ ብሎም በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ፣ የተጋረጠው ሌላው እንቅፋት ላለፉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያ የኤርትራን ሉዓለዊ ግዛት መዉረሯ ነዉ። ኤርትራም የፀጥታ ምክር-ቤት ፣የዓለም አቀፍ ህግንና የተለያዩ የተባበሩት መንግስት ዉሳኔዎችን ጥሰት እንዲያስቆም ጥሪ ታቀርጋለች።»
በቅርቡ «Understanding Eritrea» የሚል መፃፍ ያሳተሙትና በለንዶን ዩቨርስቲ «የጋራ ብልጽግና ማህበር ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ማርቲን ፕላዉት የሚንስትሩ ንግግር ትክክል ነዉ ይላሉ። ይሁን እንጅ በኤርትራም በኩልም ችግሮች እንዳሉም አንስተዋል: «ኢትዮጵያ ባድሜ አከባቢ ያሉ የተወሰኑ የኤርትራ መሬቶችን እንደያዘች ነው። ኤርትራም በስምምነቱ ለኢትዮጵያ የተሰጡትን አንድ አንድ ቦታዎች እንደያዘች ነው። ሁለቱም አገሮች ተመሳሳይ ፖሊስዎች አላቸዉ፤በማንኛዉንም መንግድ አንዱ ሌላዉን ለማሳጣት መሞከር ነዉ።»
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለዉ የድንበር ግጭት ከጦርነት ይልቅ በዉይይት ሊፈታ እንደሚችል ፕላዉት ለዶይቼ ቬሌ ይናገራሉ። ለመፍትሄውም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አስተወጽኦ ቢኖራቸዉም መሪዎቹን አንድ ላይ ለማምጣት መሞከር አንዱና ዋነኛ መፍትሄ ነዉ ይላሉ። ግን መሪዎቹ እስካሁን ተገናኝተው ችግሩን መፍታት ለምን ተሳናቸዉ? ፕላውት መልስ አላቸው: «ሁለቱንም አገራት ለሚመሩ ፓርቲዎች ይህን ማድረግ በጣም ከባድ ነዉ። ወደፊት ለመራመድ የሚፈልግ ማንኛዉም አመራር ወደ ውይይት የሚወስድ ገላጋይ ሀሳብ ላይ ቢደርስ በሁለቱም በኩል ለቆሙለት ብሔራዊ ዓላማ እንደ ድክመት እንደ ክህደት ነው የሚቆጠረው። ፕሬዝዳንት እሳያስ አፈወርቂ በሁለቱም አገራት በኩል ያለዉ ዉጥረት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፣ ምክንያቱም ስልጣን ላይ ለመቆየት ሰበብ ይሆንላቸዋል። በኢትዮጵያ በኩልም የትኛዉም ሙከራ ቢያደርግ ከስልጣኑ ይባረራል።»
በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ መንግስትም በኩል የበለጠ መረጃ ለማግኘት ያደርገነዉ ሙከራ አልተሳካም።
መርጋ ዮናስ
ነጋሽ መሃመድ