ሚሼል ፕላቲኒ ከሙስና ጋር በተያያዘ ታሰሩ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 2011የቀድሞው የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ከሙስና ጋር በተያያዘ ዛሬ በፈረንሳይ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋሉ። በጎርጎረሳዊ 2007 ዓም የአዉሮጳን እግርኳስ ማኅበር እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት ፈረንሳዊዉ አንጋፋ የእግር ኳስ ኮከብ ሚሼል ፕላቲኒ የተያዙት በ2022 ዓ.ም ኳታር የዓለም ዋንጫ እንድታስተናግድ ስትመረጥ ሙስና ተፈጽሟል በሚል ጥርጣሬ ነው። የቀድሞው የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ከተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ሁሉ ነፃ ናቸዉ ሲል አንድ ሕጋዊነቱ የተረጋገጠ የፕላቲኒ ማኅበር ወይም ቡድን በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አዉግዞአል። የአዉሮጳ የእግር ኳስ ማኅበርን እስከ ጎርጎረሳዉያኑ 2015 በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት የ 63 ዓመቱ ሚሼል ፕላቲኒ፤ ከቀድሞዉ የፊፋ ኃላፊ ሴፕ ብላተር ሁለት ሚሊዮን ዶላር በመቀበል የሥነ-ምግባር ጥሰቶችን ፈፅመዋል በሚል ለአራት ዓመታት ከእግር ኳስ ታግደዉ እንደነበርም ይታወሳል። አንድ የአሜሪካ ገለልተኛ መርማሪ ይፋ ባደረገዉ መረጃ ኳታር በ 2022 የዓለም እግር ኳስን ለማስተናገድ የምርጫ ድምፅን ገዝታለች። ዛሬ ፈረንሳይ ዉስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ከዚህ የሙስና ወንጀላቸዉ ነጻ ለመባል ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ጥረት ያደርጉ እንደነበር ተዘግቦአል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ