1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰኔ 20 ቀን፣ 2008 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሰኔ 20 2008

የጀርመን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግ በቡድኑ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ እየጎላ ነው። ትናንት ለጀርመን የመጀመሪያዋን ግብ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ ካሳረፈ በኋላ በደስታ ተውጦ የከነፈው ወደ አሰልጣኙ ሳይሆን ወደ ቡድኑ ወጌሻዎች ነበር። ቡድኑ ውስጥ ውዝግብ ይኖር ይኾን?

https://p.dw.com/p/1JEcc
UEFA EURO 2016 - Achtelfinale | Ungarn vs. Belgien | 0:1 Tor durch Alderweireld
ምስል Reuters/S. Perez

ስፖርት ሰኔ 20፣ 2008 ዓም

በደቡብ አሜሪካው አህጉራዊ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፍፃሜ ዕለት ፍጹም ቅጣት ምት የሳተው አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሴ ለብሔራዊ ቡድኑ ከእንግዲህ እንደማይሰለፍ መግለጡ ብዙዎችን አስደምሟል። በደርባኑ የአፍሪቃ አትሌቲክስ ፉክክር ኬንያውያን እንደ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ባይኮንም ድል ቀንቷቸዋል። ኢትዮጵያውያትም ከሜዳሊያዎቹ ተቋዳሽ ኾነዋል።

ለአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ትናንት ሦስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ጀርመን ስሎቫኪያን በሰፋ የግብ ልዩነት 3 ለ0 አሸንፋታለች። የጀርመን ቡድን ከዚህ ቀደም የነበረበትን ድክመት አስተካክሎ በተቀናጀ መልኩ ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረጉ ለድል በቅቷል። የጀርመኑ ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግ ከስሎቫኪያ ግብ በስተግራ በኩል ከማዕዘን የተላከችው ኳስ ተጨናግፋ እግሩ ስር ስትደርስ አንዳችም አላመነታም። ኳሷ አየር ላይ ተንሳፋ እንደመጣች በቀጥታ አክርሮ በመምታት የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር ገና ስምነተኛው ደቂቃ ነበር። ጄሮም ቦዋቴንግ ለራሱም የመጀመሪያ የሆነችውን ግብ ፈጣን በሆነ መልኩ በማስቆጠሩ እጅግ መደሰቱን ገልጧል።

«ኳሱን አክርሬ ነው የመታሁት፤ ከመረብ በማረፉም ደስተኛ ነኝ። በውድድሩ ኧረ እንደው አንተ መቼ ነው ግብ የምታገባው ተብዬ በተደጋጋሚ ስጠየቅ እል የነበረው፦ ራሴን ለውድድሩ አዘጋጅቻለሁ ነበር። እናም የዕድል ነገር ሆኖ ተሳክቶልኛል። በተለይ ግን ዛሬ በጣም ጥሩ ለተጫወተው ቡድናችን ደስ ብሎኛል። »

ግብ በማስቆጠሩ እጅግ ተደስቶ እየዘለለ ወደ ተቀያሪ ወንበር አቅጣጫ የሮጠው ጄሮም ቦዋቴንግ አሰልጣኙ ዮኣሂም ሎይቭን አልፎ ምክትል አሰልጣኙን እና የቡድኑ ሐኪሞችን በማቀፍ ደስታውን ገልጧል። በአቅራቢያው የነበሩት ዋና አሰልጣኝ ችላ ማለቱ በቡድኑ ውስጥ ቅራኔ ይኖር ይኾን እንዴ የሚል ጥያቄ አጭሯል። በእርግጥም ባለፉት ጨዋታዎች በቡድኑ የማጥቃት ስልት ተበሳጭቶ የነበረው ተከላካይ ጄሮም ቦዋቴንግ ቅሬታውን ገልጦ ነበር።

አንዳንዶች በጀርመን ቡድን ውስጥ መከፋፈል ሳይፈጠር አልቀረም ሲሉ ጥርጣሬኃቸውን ገልጠው ነበር። ሆኖም ተከላካዩ ሲጠየቅ ወደ ቡድኑ ሐኪሞች ሄጄ ደስታዬን የገለጥኩት እግሬ ላይ የደረሰውን ጉዳት በፍጥነት አክመው ለዚህ ስላበቁኝ ነው ሲል ማስተባበያ ሰጥቷል። አሰልጣኙ ዮኣሂም ሎይቭ በበኩላቸው ቡድናቸው የተሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጉ ለድል መብቃታቸውን ገልጠዋል።

«ዛሬ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም የምንፈልገውን በሚገባ ተግባራዊ አድርገናል። ባላጋራችንን ገና ከመጀመሪያው አንስቶ መፈናፈኛ ማሳጣት፤ አንዳችም ሳንዘናጋ፤ ለቅጽበት እንኳን ፋታ ሳንሰጥ ተጋጣሚያችን ከፍቶ እንዲጫወት ማድረግ ነበር ፍላጎታችን። ከዚያ አንፃር ቡድናችን ጥሩ ነው ያደረገው። በመከላከሉ በኩልም ጥሩ ዘልቀንበታል። ወደፊት ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ የጨዋታ ቅንጅት አሳይተናል። ያም በመሆኑ ድሉ ይገባናል።»

በ12ኛው ደቂቃ ላይ ለጀርመን የሁለተኛ ግብ ዕድል ተፈጥሮ ነበር። ማሪዮ ጎሜዝ በመጠለፉ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሜሱት ኦዚል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በስተቀኝ በኩል ዝቅ አድርጎ የመታትን ኳስ የስሎቫኪያው ግብ ጠባቂ ማቱስ ኮዛቺክ ተወርውሮ በሁለት እጆቹ አጨናግፎ ግብ ከመሆን አግዷታል። የመጀመሪያው አጋማሽ መደበኛ ሰአት ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ስሎቫኪያዎች ጥሩ የግብ ዕድል አጋጥሟቸው ነበር። ሆኖም የዓለማችን ኮከብ ግብ ጠባቂ ጀርመናዊው ማኑዌል ኖየር ኳሷን በቡጢ ደልቆ ከግቡ ማዕዘን ውጪ ልኳታል። ለጀርመን ሁለተኛዋን ግብ ያስቆጠረው ማሪዮ ጎሜዝ ቡድናቸው በርካታ ግብ መሆን የሚችሉ ዕድሎች አጋጥመውት እንደነበር ተናግሯል።

ፓሪስ አይፍል ማማ አጠገብ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ተሰብስበው ኳስ ሲመለከቱ
ፓሪስ አይፍል ማማ አጠገብ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ተሰብስበው ኳስ ሲመለከቱምስል DW/H. Tiruneh
የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በፓሪስ ከተማ፤ ፈረንሳይ
የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በፓሪስ ከተማ፤ ፈረንሳይምስል H. Tiruneh
ፓሪስ፤ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ተሰብስበው ኳስ ሲመለከቱ
ፓሪስ፤ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ተሰብስበው ኳስ ሲመለከቱምስል H. Tiruneh

«ዛሬ በድንቅ ኹኔታ ነው የተጫወትነው። ስሎቫኪያውያን ሲመስለኝ አንድ የግብ ዕድል ሳያገኙ አልቀሩም። እኛ ግን በርካታ ግቦችን ማስቆጠር እንችል ነበር። ሁሉም ነገር የሚያዝናና ነበር፤ የጨዋታው ፍሰት፣ ፈታ ማለቱ፣ የማጥቃቱ ስልት፤ ወደፊት እንዲያ መቀጠል መቻል አለበት። »

ለማሪዮ ጎሜዝ ሁለተኛዋ ኳስ ግብ እንድትሆን ጨርሶ ያቀበለው 11 ቁጥሩ ዩሊያን ድራክስለር ሦስተኛዋን ግብ ራሱ አስቆጥሯል።

የትናንቱ የአየርላንድ እና የፈረንሳይ ግጥሚያም ድንቅ የሚባል ነበር። አየርላንዶች ባገኙት ፍጹም ቅጣት ምት ቀዳሚውን ቢያስቆጥሩም፤ አስተናጋጇ ሀገር ፈረንሳይ ድንቅ በሆነ አጨዋወት እና ብልጫ በማሸነፍ ወደቀጣዩ ዙር ማለፍ ችላለች። የፓሪሷ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህ ፓሪስ የሚገኙ የተለያዩ ሃገራት የስፖርት ደጋፊዎችን አነጋግራ ነበር።

ትናንት ቤልጂየም ሀንጋሪን በሰፋ የግብ ልዩነት እና ብልጫ ባለው አጨዋወት 4 ለ0 አሸንፋ ወደቀጣዩ ዙር አልፋለች። ሰሜን አየርላንድን አንድ ለባዶ ረትታ ካለፈችው ዌልስ ጋር በሩብ ፍፃሜው ትፋለማለች። ቤልጂየም እሁድ እለት በግልም በቡድንም ያሳየው ጥንካሬ በዚሁ ከቀጠለ እንደ ጀርመን ቡድን ያሰጋል።

የትናንትናውን የእግር ኳስ ፍልሚያ በተመለከተ የአውሮጳ የተለያዩ ታዋቂ ጋዜጦችእንደሚከተለው ዘግበውታል። የጣሊያኑ የስፖርት ጋዜጣ « Gazzetta dello Sport» አሁን ጀርመን አስጊ ኾናለች። ጣልያን እና ስፔን የሞት ሽረት ያደርጋሉ ሲል ዘግቧል። ለስሎቫኪያ መሪር ሐዘን ለጀርመን ወደፊት ርምጃ ሲልም አክሏል። የስፖርት መልእክተኛው በጣሊያንኛ «Corriere dello Sport» የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ «ጀርመን ስታመር፤ ስሎቫኪያ ድባቅ ተመታለች» ብሏል። በስጳኝ ቋንቋ የሚታተመው ሀገሪቱ የተሰኘው «El País»: ጋዜጣ «ጀርመን ደምቃለች። የዓለም ባለድሏ በተመስጋኙ ማሪዮ ጎሜዝ ደካማዋን ተቀናቃን ቀጥታለች። እናም ስሎቫኪያ ያለ ረዳት ተሰናብታለች» ሲል አትቷል።

በዛሬው እለት ጣልያን ከስፔን የሚያደርጉት ጨዋታ እየተከናወነ ሲሆን እንግሊዝ ከአይስላንድ ጋር ይጋጠማሉ። በዛሬው ጨዋታ ከእንግሊዝ እና ከአይስላንድ አሸናፊ የሆነው ቡድን ከአዘጋጇ ሀገር ፈረንሳይ ጋር ይጋጠማል። እናም ሐይማኖት ያነጋገረችው ፈረንሳዊው ደጋፊ ዴቪድ ምኞቱ ተሳክቶለት እንግሊዝ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፋ ከፈረንሳይ ጋር ትገጥም ይኾን? አብረን የምናየው ይሆናል።

በፍፁም ቅጣት ምት መለያው ተራው ደረሰና ኳሷን ለጋ፤ እናም ከግቡ ማዕዘኑ ወዲያ ወደ ዓየር አጎናት። በዚሁ ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን መፋታቱን ይፋ አድርጓል፤ ሊዮኔል ሜሲ። 29ኛ ዓመቱን በያዘ በሁለተኛ ቀኑ ባደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ያልቀናው ሊዮኔል ሜሲ ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ውድድሮች ውጪ እንደሚሆን አስታውቋል።

አርጀንቲና በኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ውድድር በፍጹም ቅጣት ምት መለያ እሁድ በቺሊ 4 ለ2 ተረታለች። በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ሊዮኔል ሜሲ እና የአርጀንቲና ቡድኑ ሦስት ወሳኝ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ሁለት የኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ውድድሮች እና እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2014 የተከናወነው የዓለም ዋንጫ። በወቅቱ ጀርመን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ሰአት በ113ኛው ደቂቃ ላይ ማሪዮ ጎትስ በመጨረሻ ሰአት ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ነበር አርጀንቲናን 1 ለ0 ቀጥታ ዋንጫውን የወሰደችው።

ጣሊያኖች ስፔኖች ላይ ግብ ባስቆጠሩበት ቅጽበት
ጣሊያኖች ስፔኖች ላይ ግብ ባስቆጠሩበት ቅጽበትምስል Reuters/C. Hartmann
የስፔን ደጋፊ ከጣሊያን ጋር የሚኪያሄደውን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሲከታተል
የስፔን ደጋፊ ከጣሊያን ጋር የሚኪያሄደውን የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሲከታተልምስል picture-alliance/AP Photo/F. Augstein

የአምስት ጊዜያት የፊፋ የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋች፤ በሻምፒዮንስ ሊግ የአራት ጊዜያት ኮከብ ተጨዋች እንዲሁም በስፔን ላሊጋ ከባርሴሎና ጋር ለስምንት ጊዜያት የድል ዘውዱን መድፋት ተሳክቶለታል ሊዮኔል ሜሲ። ከአርጀንቲና ቡድን ጋር ሆኖ ግን አንድም ጊዜ ዋንጫ ሊያገኝ አለመቻሉ ከባድ መሆኑን ገልጧል። «በመልበሻ ክፍል ውስጥ ሆኜ የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ አከተመለት ስል አሰብኩ፤ የኔን ግን አይደለም» ሲልም ተናግሯል።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1993 ወዲህ የናፈቁትን ዋንጫ እንደ ኳስ ንጉሣቸው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ወደ ሃገራቸው ያመጣልናል ሲሉ ይመኙ የነበሩ የአርጀንቲና የኳስ አፍቃሪያን ሕልምን ሊዮኔል ሜሲ በትናንትናው መግለጫው እንደ ጉም በትኖታል። በ1993 አርጀንቲና በጋብሪዬል ባቲስቱታ ሁለት ግቦች ሜክሲኮን ድል አድርጋ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ግጥሚያን ካሸነፈች ወዲህ ውጤቱ ርቋት ቆይቷል።

በደቡብ አፍሪቃ ደርባን ከተማ በተከናወነው የአፍሪቃ አትሌቲክስ የሩጫ ፉክክር በ20 ኪሎ ሜትር ውድድር ኬንያዊቷ ግሬስ ዋንጂሩ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የኋልዬ በለው ሁለተኛ በመውጣት ነሐስ አጥልቃለች። በ3000 ሜትር የመሰናክል ሩጫ ደግሞ ኬንያውያን አንደኛ እና ሁለተኛ በመውጣት የወርቅ እና ነሀስ ሜዳሊያ ሲያጠልቁ፤ ኢትዮጵያዊቷ ወይንሸት አንሳ በሦተኛናነት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

በአጠቃላይ ውድድሩ አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ 16 የወርቅ፣ ዘጠን የነሐስ እንዲሁም ስምንት የብር በድምሩ 33 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ወጥታለች። ኬንያ በ24 ሜዳሊያ በሁለተኛነት እንዲሁም ናይጄሪያ 16 ሜዳሊያ በማግኘት በሦስተኛነት አጠናቀዋል። የአፍሪቃ ድንቅ አትሌቶች ስብስብ ያካተቱት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለሪዮ የኦሎምፒክ ውድድር ዝግጅት በሚል በብዛት በውድድሩ አለመሳተፋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የሪዮ ኦሎምፒክ ሊጀመር 39 ቀናት ከስድስት ሰአት ይቀረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ውድድር ፍጹም ቅጣት ምት ስቶ
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በኮፓ አሜሪካ የፍፃሜ ውድድር ፍጹም ቅጣት ምት ስቶምስል Reuters/Adam Hunger-USA TODAY Sports

ነጋሽ መሐመድ