ስለምርጫው በጀርመን የኢትዮጵያውያን አስተያየት
ማክሰኞ፣ ሰኔ 15 2013በአገር ውስጥ እና በውጭ ኃይላት ግጭትና ፖለቲካዊ ቀውስ በገጠማት ኢትዮጵያ 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለ ሁከትና የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው በጀርመን ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ገለጹ። የምርጫው አጠቃላይ ሂደትና የመወዳደሪያው ሜዳ ለገዢው መንግሥትም ሆነ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል እንዳልነበረ ለዶይቼ ቨለ (DW) የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ ያም ቢሆን ሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ተጠቅሞ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግስትን ለመምረጥ ያሳየው ትዕግስትና ጨዋነት ምርጫውን ለማደናቀፍ ጥረት ሲያደርጉ ለቆዩ አካላት ትምህርት የሰጠና የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ዓለማቀፍ መስፈርትን ያሟላ ቅቡልነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ በቅድሚያ የሕዝቦችን ደህንነት የመኖር ህጋዊ ዋስትናንና ሰላምን ማረጋገጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለውን አሰራር ማስፈን በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ በሰበብ አስባቡ እስርና ማዋከብን ማቆም እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። በጀርመን እና አውሮጳ የሚገኙ አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ አመራሮችም በትላንቱ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የታዩት የተፎካካሪ ፓርቲ የምርጫ ታዛቢዎችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከል የምርጫ ቁሳቁሶች እጥረትና የሎጂስቲክስ ችግሮች የፊታችን ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም በሀረሪ በሶማሌና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በሚካሄዱ ቀጣይ ምርጫዎች እንዳይደገሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል:: መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት በሰላም እንዲቀበሉም ጥሪ አቅርበዋል።
እንዳልካቸው ፈቃደ
ሸዋዬ ለገሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ