1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሐምሌ 30 ቀን፣ 2010 ዓ.ም

ሰኞ፣ ሐምሌ 30 2010

የሚዘጋጀው በዓመት አንዴ ነው፤ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ የማይረሳ እንከን ግን አያጣውም የኢትዮጵያዊያን በአውሮፓ የባሕል እና ስፓርት ፌስቲቫል። የዘንድሮው ፌስቲቫል በቅሬታ ነው የተጠናቀቀው። የአውሮጳውን ፌዴሬሽን እና የሽቱትጋርት አዘጋጆችን በውድድሩ ወቅት እንዲሁም ታቅደው በተሰናከሉት የምሽት የሙዚቃ ድግሶች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።

https://p.dw.com/p/32i7B
Frankfurt ESCFE Festival
ምስል DW/S. Mantegaftot Sileshi

ሳምንታዊ የስፖርት ጥንቅር

የሚዘጋጀው በዓመት አንዴ ነው፤ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ የማይረሳ እንከን ግን አያጣውም የኢትዮጵያዊያን በአውሮፓ የባሕል እና ስፓርት ፌስቲቫል። የዘንድሮው 16ኛው ፌስቲቫል በርካቶችን ከመላው ዓለም በተለይም ከአውሮጳ ቢያስባስብም ያሰናበተው ግን በቅሬታ ነው። የአውሮጳውን ፌዴሬሽን እና የሽቱትጋርት አዘጋጆችን በውድድሩ ወቅት እና ታቅደው በተሰናከሉት የምሽት የሙዚቃ ድግሶች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።  ተጨማሪ ዘገባዎችን አካተናል፤

ከሐምሌ 25 እስከ  ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም  ድረስ ለአራት ቀናት በተኪያሄደው 16ኛው የኢትዮጵያዊያን በአውሮፓ የባሕል እና ስፓርት ፌስቲቫል በርካቶች ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የቅሬታቸው ምክንያት ደግሞ አዘጋጆቹ በሦስት ተከታታይ ቀናት ታዋቂ ሙዚቀኞችን እናስመጣለን ብለው አላስመጡም፤ ሜዳ ላይም በዚያ ብርቱ ሙቀት ማቀዝቀዣ ውስጥ ያልገቡ ምግቦች ቀርበውልናል፤ የመጠጥጥ አቅርቦትም በበቂ አልነበረም የሚሉ ናቸው። አቶ ተድላ ምዑዝ  እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2008 እስከ 2016 የሽቱትጋርት ቡድን መሪ የነበሩ እና በአሁኑ ወቅት የበዓሉ ዋና አዘጋጅ ናቸው። በአጭሩ የዘንድሮ ዝግጅት ለእርሶ ስኬታማ ነበር ወይንስ ስኬታማ ያልሆነ ስል ጥያቄዬን አቀረብኩላቸው። አንዳንድ እንከኖች ከመፈጠራቸው ውጪ «ስኬታማ ነው» ብለዋል። በሜዳው ላይ ስለነበረው የምግብ እና መጠጥ አቅርቦት እንከን፤ እንዲሁም ስለተሰናከሉት የምሽት ድግሶች መልስ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያዊያን በአውሮፓ የባሕል እና ስፓርት ፌዴሬሽን ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ አበበ በበኩላቸው የዘንድሮው ዝግጅት የተሳካ ነገር ምንም የለውም ብለዋል።

በዘንድሮው ውድድር ኢትዮ ለንደን በፍፁም ቅጣት ምት ኢትዮ ሆላንድ 1 ለ 0 አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል ጥሩ በመጫወት ዋንጫውን ሊወስድ ይችላል ተብሎ ተገምቶ የነበረው ኢትዮ ኮሎኝ በሦስተኛነት አጠናቋል።

FIFA Fußball-WM 2018 in Russland | Deutschland vs. Südkorea
ምስል Reuters/M. Dalder

በሳምንቱ መጨረሻ ናይጀሪያ በተጠናቀቀው የአፍሪቃ አዋቂ አትሌቶች ውድድር ኬንያ 11 የወርቅ ጨምሮ በ19 ሜዳሊያ አንደኛ ደረጃ አግኝታለች።   ደቡብ አፍሪቃ 30 ሜዳሊያ ብታገኝም ወርቁ 9 በመኾኑ 2ኛ ኾናለች። አዘጋጇ ናይጀሪያ ተመሳሳይ 9 ወርቅ ብታገኝም ከደቡብ አፍሪቃ በ7 ያነሰ 6 የብር ሜዳሊያ በማሸነፏ በሦስተኛነት አጠናቃለች።  2 የወርቅ  እና 3 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው ኢትዮጵያ  2 ወርቅ፣ 6 ብር እና 4 የነሀስ ሜዳሊያ ከሰበሰበችው ሞሮኮ በመከተል በአምስተኛነት አጠናቃለች።

በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ጀማል ይመር፤ በሴቶች የኋልዬ በለጠው በ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር ወርቅ አስገኝተዋል። የብር ሜዳሊያውን ያስገኙት በ10 ሺህ ሜeትር አንዳምላክ በልሁ፤ በ5 ሺህ ሜeትር ጌታነህ ሞላ እንዲሁም በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሠንበሬ ተፈሪ ናቸው።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ማሪዮ ጎሜዝ ከ11 ዓመት አገልግሎት በኋላ ኳስ መጫወት ማቆሙን በይፋ ገልጧል።  የ33 ዓመቱ ማሪዮ ጎሜዝ በብሔራዊ ቡድን የጨዋታ ዘመኑ  32 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። ማሪዮ ጎሜዝ ዘንድሮ ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን በመውጣት ከሜሱት ኦዚል ቀጥሎ ሁለተኛው ተጨዋች ነው።  ሌላኛው የብሔራዊ ቡድኑ ተሰላፊ ቶኒ ክሮስ በጀርመን የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር እና ኪከር በተሰኘው የእግር ኳስ መጽሄት  የጀርመን ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተሰይሟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ