1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ መስከረም 12 ቀን፣ 2011 ዓ.ም

ሰኞ፣ መስከረም 12 2012

በቡንደስሊጋው ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ መሪነቱን ለላይፕሲሽ አስረክበው እየተከተሉ ነው። የኢትዮጵያ አትሌቶች የፊታችን የሳምንት ፍጻሜ ላይ ለሚከናወኑ ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድሮች ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። ዝግጅታቸውን በተመለከተ አነጋግረናቸዋል። 

https://p.dw.com/p/3Q7Gg
CHAN qualification game in Mekele Äthiopien
ምስል DW/M. Haileselassie

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ እና የሩዋንዳ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች መቀሌ ከተማ ውስጥ ግጥሚያቸውን ሲያከናውኑ የተመልካቹ ስሜት ምን ይመስል ነበር? በስፍራው ከነበረ ወኪላችን ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅን ቀዳሚ እናደርጋለን። የፕሬሚየር ሊጉን ሊቨርፑል በቀዳሚነት እየመራ ነው። በቡንደስሊጋው ባየር ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ ዘንድሮ መሪነቱን ለላይፕሲሽ አስረክበው እየተከተሉ ነው። የኢትዮጵያ አትሌቶች የፊታችን የሳምንት ፍጻሜ ላይ ለሚከናወኑ ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድሮች ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። ዝግጅታቸውን በተመለከተ አነጋግረናቸዋል። 

ለ2020 የቻን አፍሪቃ ዋንጫ እግር ኳስ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታው ትናንት ትግራይ ስታድየም ሩዋንዳን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 ተሸንፏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመቐለ ከተማ ጨዋታውን ሲያካሂድ የትናንቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ነበር፡፡ ጨዋታውን ሀያ ሺህ ገደማ ተመልካች መቐለ በሚገኘው ትግራይ ስታድዮም ተገኝቶ በመከታተል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ሲያበረታታ ነበር፡፡ የመቐለው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ የትናንቱን ጨዋታ ስታዲየም ተገኝቶ ተከታትሏል። የደጋፊዎች ስሜት እና የስታዲየሙ ድባብ ምን ይመስል እንደነበር በመግለጥ ይጀምራል።

CHAN qualification game in Mekele Äthiopien
የሩዋንዳ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንምስል DW/M. Haileselassie

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራህቱ ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ሁሉ እንዳደረጉ በመጥቀስ በመልስ ጨዋታ ውጤቱን ለመቀልበስ እንደሚዘጋጁ ገልፅዋል፡፡

የሩዋንዳው አሰልጣኝ ቪሴንት ሚሻሚ በበኩላቸው፦ «የመልስ ጨዋታ ቢቀረንም የመጀመሪያው ጨዋታ በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል፡፡ ከጥሩ ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው፤ በቴክኒክም፣ በታክቲክም ጥሩ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያን ማሸነፍ ቀላል ነገር አደለም» ብለዋል፡፡የመልሱ ጨዋታ ከ27 ቀናት በኋላ በሩዋንዳ ይካሄዳል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ በአጠቃላይ ጨዋታ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚው የተሻለ የነበረ ቢሆንም፤ ውጤት አልቀናዉም፡፡ በተለይም በጨዋታው የመጀመሪያና የመጨረሻ ዐሥራ አምስት ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተጋጣሚው ሩዋንዳ ላይ ከፍተኛ ብልጫ አሳይቶ ነበር፡፡  በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ስልሳኛ ደቂቃ የሩዋንዳው አጥቂው ኤርነስት ሱጊራ ከቅጣት ምት የተሻማ ኳስ ወደ ግብ በመቀየር ቡድኑን አሸናፊ አድርጓል።

CHAN qualification game in Mekele Äthiopien
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ በመቀሌ ስታዲየምምስል DW/M. Haileselassie

በ17ኛው የአይኤኤኤፍ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ቅዳሜ በሂልተን ሆቴል የአሸኛኘት ስነ-ስርዓት ተደርጎለታል። ካታር በምታስተናግደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ19 ሴት እና በ17 ወንድ አትሌቶች የምትወከል ይሆናል። ከመስከረም 16 - 25 በሚቆየው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ7 የስፖርት አይነቶች በሁለቱም ፆታ ትወዳደራለች። ብሄራዊ ቡድኑ ነገ ወደ ዶሃ ይጓዛል። የአትሌቲክ ፌሬሽን ተቀ/ም/ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራር ቱሉ ቡድኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጣ ውጤት የሚሠምረው በጋራ አንድንነትብ ማጠናከር ሲቻል መኾኑን ተናግራለች።

በዶሃ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ ከኾኑ አትሌቶች መካከል በ5000 ሺ ሜትር የሚሳተፈው ጥላሁን ሃይሌ በቀለ በበኩሉ በውድድሩ የተቻለውን ለማድረግ እንደሚጥር ለዶይቸ ቬለ ተናግሯል።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የፊታችን ዐርብ የሚጀምር ሲሆን ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ የበርሊን ማራቶን ይከተለዋል።

Äthiopische Leichtathleten vor der Weltmeisterschaft in Doha
በ17ኛው የአይኤኤኤፍ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ምስል DW/O. Tadele

ከዚሁ ከአትሌቲክሱ ዜና ሳንወጣ በትናንትናው ዕለት፦ «ኢሬቻ የሰላም ሩጫ» በሚል ርእስ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተከናውኗል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማኅበራዊ ድረ-ገጹ እንደዘገበው፦«በወንዶች ምድብ 1ኛ በሪሁ አረጋዊ ከሱር ኮንስትራክሽን አትሌቲክስ ክለብ፤ 2ኛ ኃይለማርያም ኪሮስ ከትግራይ ክልል፤ 3ኛ ደጀኔ ደበላ ከኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ተከታትለው በመግባት ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡»

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ቸልሲን 2 ለ1 ያሸነፈው ሊቨርፑል የደረጃ ሰንዘረዡን እየመራ ይገናል። ሊቨርፑል የትናንቱን ጨምሮ በዘንድሮ የውድድር ዘመን አንድም ጊዜ አልተሸነፈም።እስካሁን ያደረጋቸውን አምስት ውድድሮች በአጠቃላይ ማሸነፍ ችሏል። በአንጻሩ የባለፈው የውድድር ዘመን ላይ ዋንጫውን የወሰደው ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ አስደንጋጭ በሚባል መልኩ ዋትፎርድ ሲቲን 8 ለ 0 አንኮታኩቷል። ኾኖም እስካሁን አንድ ጨዋታ ተሸንፊ፤ በአንዱ አቻ በመውጣቱ ከሊቨርፑል በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በ13 ነጥብ ይከተላል። ላይስተር ሲቲ 11 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Formel 1 Großer Preis von Singapur | Sebastian Vettel
ምስል Reuters/F. Lim

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ከአይንትራኅት ፍራንክፉርት ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል። በዚህም መሠረት ከመሪው ላይፕሲሽ በሦስት ነጥብ ተበልጦ በ11 ነጥቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ላይፕሲሽ ትናንት ቬርደር ብሬመንን 3 ለo ድል አድርጎ በአምስት ጨዋታዎች ነጥቡን 13 ማድረስ ችሏል። ቅዳሜ ዕለት ኮሎኝን 4 ለ 0 ያሸነፈው ባየር ሙይንሽን 11 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ ላይ ይገኛል።

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ሰባስቲያን ፌትል ትናንት ድል ቀንቶታል። ሌላኛው የፌራሪ አሽከርካሪ ቻርለስ ሌችልርችን አስከትሎ አንደኛ መውጣት ችሏል። የሬድ ቡሉ ማክስ ፈርሽታፓን ሦስተኛ ሲወጣ፤ በተደጋጋሚ ድል ሲንበሸበሽ የቆየው የመeሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን ግን የአራተኛ ደረጃን አግኝቶ አጠናቋል።

ኢራን ከጁዶ ፌዴሬሽን መታገዷ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተነግሯል። ኢራን ከጁዶ ፌዴሬሽን የታገደችው ሳይድ ሞላይ የተባለው ተፋላሚዋ ከእስራኤል ተፎካካሪው ጋር በፍጻሜው ላለመገናኘት በሚል ግማሽ ፍጻሜ ላይ ኾን ብሎ ነጥብ እንዲጥል ተነግሮታል በሚል ነው። ዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን የኢራን ቡድን መሰል የዲሲፕሊን ጥሰቶችን በተደጋጋሚ ፈጽሟል ሲል ከሷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ